Saturday, 16 January 2016 10:21

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፌደሬሽኑ የስፖርት ሚዲያዎች ተሽለዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  በወርቅ ኳስ እና ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ መንሱር አብዱልቀኒ
              በሴቶች ኮከብ ተጨዋችና ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ይስሐቅ በላይ
    በ2015 የፊፋ የወርቅ ኳስ እና የዓመቱ ከኮቦች ምርጫ ላይ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች ባሉት የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና አምበሎች ምርጫ በፌደሬሽኑ ድክመት ሳትሳተፍ ብትቀርም ሁለት የስፖርት ሚዲያዎች በንቁ ተሳትፏቸው አርዓያ እንደሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ሁለቱ የስፖርት ሚዲያው አባላት የኢትዮ-ስፖርት ጋዜጣ ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነውና የብስራት ስፖርት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ እና የሀትሪክ ጋዜጣና መጽሔት እንዲሁም የፕላኔት ስፖርት ሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ የሆነው ይስሐቅ በላይ ናቸው፡፡ በሁለቱም የወንድ እና የሴት ብሄራዊ ቡድኖች ያሉት ዋና አሰልጣኞች እና አምበሎች በምን ምክንያት ድምፅ እንዳልሰጡ ግልፅ አይደለም። ባለፉት 5 ዓመታት ይህን እድል ባለመጠቀም 4 ጊዜ አጋጥሟል፡፡ የፌደሬሽኑ የግንኙነት ደካማነት ነው፡፡
በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና አምበሎች ደረጃ በፌደሬሽኑ ጥረት ተሳትፎ ማረግ የተቻለው በ2011 እና በ2012 እኤአ ላይ ብቻ ነበር፡፡ በ2010፤ በ2013፤ በ2014 እና በ2015 እኤአ በተካሄዱት ምርጫዎች ግን የፌደሬሽኑ ውክልና ያላቸው አሰልጣኞችእና አምበሎች አልተሳተፉም። በድምፅ አሰጣጡ የፊፋ አባል አገራን ወክለው ድምፅ የሚሰጡት ሁሉም ባለሙያዎች ድምፃቸው 33 በመቶ ዋጋ  ነበረው፡፡ በወርቅ ኳስ፤ ኮከብ ተጨዋች እና ኮከብ አሰልጣኞች ምርጫ ላይ ጋዜጠኛው የሚሰጠው ድምፅ  ከ1-3 በሚሰጠው ደረጃ ለ1ኛ/ 5 ነጥብ ፤ ለ2ኛ/ 3 ነጥብ እንዲሁም ለ3ኛ/ 1 ነጥብ ስለሚታሰብ ተሳትፎው ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
በወርቅ ኳስ፤ ኮከብ ተጨዋች እና ኮከብ አሰልጣኞች ምርጫ ላይ የተሳተፉት ሁለቱ የስፖርት ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን ውክልና ማቀጠላቸው የሚደነቅ ሲሆን በአንፃሩ ፌዴሬሽኑ በምርጫው ላይ ያሳየው የአሠራር ግድፈትና ንዝላልነት የሚወቀስ እና ወደፊት መደገም የሌለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምርጫው ያልተሳተፈው በዓለምአቀፍ ግንኙነት ያለው አሠራር እጅግ ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ባለፉት 3 ዓመታት በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ የቢጫ ካርድ ጥፋትና የሴቶች ብሔራዊ ቡድን  ከውድድር መሰረዝ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ በፊፋ የወርቅ ኳስ ምርጫ ላይ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እና ዋና አምበሉ አለመሳተፋቸው ወይም በጊዜው ድምጽ የመስጠት ርምጃ ባለመወሰዱ በመዘንጋት ወይም በአሰራር ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ግን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከዓለምአቀፍ ካርታ የሚያሳጣ አስተዳደራዊ እንቅፋት ነው፡፡ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምርጫውን አከናውኛለሁ ብለው በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ቢናገሩም፤ ፊፋ ይፋ ባደረገው የስም ዝርዝር የሉበትም፡፡ የብሄራዊ ቡድን አምበል በበኩሉ ስዩም ተስፋዬ ቋሚ ሃላፊነት ስለሌለው ወይንም ፎርሙን እንዲሞላ ስላልተሰጠው ከነጭራሹ እንዳልተሳተፈም ተገልጿል፡፡
በፊፋ የወርቅ ኳስ  ምርጫ ላይ መሳተፍ ካሉት ጥቅሞች መካከል ዋንኛው ዓለም አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር ነው የሚለው መንሱር አብዱልቀኒ፤ ከዓለም የእግር ኳስ ማህበረሰብ ጋር ለመቀራረብና ተቀባይነትን ለማስፋት የሚያስችል እድል መሆኑንም ሲያስገነዝብ  የሚዲያ ሥራችን ተቀባይነትና ተሰሚነት የምናሳድግበት፡ የሰጠነው ድምጽ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገጽ በፍራንስ ፉትቦል መጽሔትና ድረገፆች ሥማችንና የወከልነው አገራችን ተጠቅሶ ስለሚታተም ዓለም አቀፍ ግንኙነት መዳበር የምንለው በእነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች ነው ሲል አብራርቷል፡፡
የፊፋ የወርቅ ኳስ በዓለም እግር ኳስ ትልቁ የሽልማት ሂደት በመሆኑ  ኢትዮጵያ በፍፁም መራቅ የለባትም፤ አይኖርባትምም በማለትም የፌደሬሽኑ ግድየለሽነት ተገቢ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡  በጋዜጠኝነቴ በወርቅ ኳስ እና ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫው ላይ ስሳተፍ የዘንድሮው በተከታታይ ለአምስተኛ ጊዜ ነው ያለው መንሱር አብዱልቀኒ፤ በተለይ ከፈረንሳዩ የእግር ኳስ መጽሔት ፍራንስ ፉትቦል ዋና አዘጋጆችና ሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በየጊዜው በምንፈጥረው ግንኙነት መልካም ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው ሲል ይናገራል፡፡ ፍራንስ ፉትቦል መጽሔት በወርቅ ኳስ ምርጫው የኢትዮጵያን ሚዲያ በመወከል የሚሞላውን ፎርም በሚስጥራዊ ኮድ በሚከፈት የኢሜል አድራሻችን ከላከልን በኋላ፤ በየጊዜው በስልክና በኢሜል መልዕክቶች ግንኙነት በማድረግ ምላሻችንን እንድንሰጥ ይጠይቃል፤ ስለሆነም በአግባቡ ምርጫችንን በማከናወን ተሳትፏችን ቀጥሏል በ2015 እኤአ የወርቅ ኳስ እና የኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ላይ መንሱር አብዱልቀኒ  ለሜሲ፤ ኔይማርና ሮናልዶ በተከታታይ ደረጃ ድምፅ ሲሰጥ በኮከብ አሰልጣኝ ምርጫ ደግመ ለኤነሪኬ፤ ለጋርዲዮላ እና ለሳምፖሊ ተከታታይ ደረጃ በመስጠት ተሳትፏል፡፡       በወርቅ ኳስ አሸናፊዎች ምርጫ ላይ ከፊፋ 209 አባል አገራት መካከል 165 የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች፤ 162 የብሄራዊ ቡድን አምበል የሆኑ ተጨዋቾች እንዲሁም 171 የሚዲያ ሰዎች ድምፅ ሰጥተው ነበር፡፡ ሊዮኔል ሜሲ የወርቅ ኳሱን ለአምስተኛ ግዜ ለማሸነፍ የቻለው 41.33 በመቶ የድምፅ ድርሻ በማስመዝገብ ሲሆን ክርስትያኖ ሮናልዶ በ27.76 በመቶ እንዲሁም ኔይማ በ7.86 በመቶ የድምፅ ድርሻቸው ተከታታይ ደረጃዎቹን ወስደዋል፡፡ በሌላ በኩል ሊውስ ኢነርኬ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ የተመረጠው 31.08 በመቶ የድምፅ ድርሻ በማግኘት ሲሆን በባየር ሙኒክ የሚገኘው ፔፕ ጋርዲዮላ በ22.97 በመቶ እንዲሁም የቺሊ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጆርጌ ሳምፖሊ በ9.47 በመቶ የድምፅ ድርሻቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2011 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለአራት ዓመታት በፊፋ የሴት ኮከብ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ምርጫ ላይ ሳያቋርጥ የተሳተፈው የስፖርት ጋዜጠኛ ይስሐቅ በላይ ነው፡፡   ይስሃቅ እንደሚናገረው በምርጫ ላይ ድምፅ በመስጠት የሚያደርገው ተሳትፎ  ከዓለም አቀፉ ተቋም  የሙያ እና የውጭ ውድድሮችን የመዘገብ እድሎችን እየፈጠረለት በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ  በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች ላይ ግብዣ እያደረገልኝ ጠቃሚ ተመክሮዎችን እያገኘሁ ቆይቻለሁ የሚለው ይስሐቅ፤ በወንዶቹም በሴቶችም ዓለም ዋንጫዎች ለመገኘት መብቃቴ የሚያኮራኝ ነው ይላል። ባለፉት 4 አመታት እንኳን በሴቶች እግር ኳስ የተካሄዱ ሁለት  የዓለም ዋንጫዎችን በስፍራቸው በመገኘት መዘገቡን የጠቀሰው ይስሐቅ፤ በ2011 እ.ኤ.አ  በጀርመን እንዲሁም በ2015 እ.ኤ.አ ላይ በካናዳ በተካሄዱት የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ላይ እንደነበሩ ያታሳል፡፡ በሴት ኮከብ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ምርጫ ላይም እንድሳተፍ አለምአቀፉ ተቋም በስልክና በኢሜል መልዕክቶች በቀጥታ ከእኔ ጋር በሚፈጥረው ግንኙነት በተደጋጋሚ ያሳውቀኛል የሚለው ይስሐቅ፤ በሴቶች እግር ኳስ ላይ ያለኝን ልምድ በመጠቀም ምርጫውን አከናውኜ ጊዜውን ጠብቄ እልካለሁ ብሏል፡፡  ዘንድሮ በሴት ኮከብ ተጨዋችእና ኮከብ አሰልጣኝ ምርጫዬ በሰጠሁት ድምፅ አሸናፊዎቹን በመገመት  መቶ በመቶ እንደተሳካለት ሲያመልክት የአሜሪካዎቹ ተጫዋች እና አሰልጣኝ የኮከብ ሽልማቶችን መውሰዳቸው እንዳስደሰተው በመግለፅ ጭምር ነው፡፡ የሴቶች እግር ኳስ በዓለምአቀፍ ደረጃ እድገት እያሳየ መሆኑን ካለኝ ልምድ በመነሳት እመሰክራለሁ ያለው ይስሐቅ፤ ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ለሁለቱም ፆታዎች እኩል ትኩረት እንደሚሰጥ ለማገንዘብ ከሞከረ በኋላ ባለፈው ዓመት የታደመበት የካናዳው የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ታላቅ እንደነበር የሚያመለክቱ አሃዞችን ጠቃቅሷል። በካናዳው የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ  24 ቡድኖች መሳታፋቸው በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑን ጠቅሶ፤ ዓለም ዋንጫን ከ750 ሚሊዮን በላይ ተመልካች በቲቪ እንደተከታተለው፤ በኢንተርኔት ማህበረሰብ ገፆች ለመጀመርያ ጊዜ ሽፋን ያገኘ መሆኑን በማስታወስ በዓለም ዙርያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በሚያዘወትሩት እግር ኳስ ላይ አስተዋፅኦ ስላበረከትኩ ደስተኛ ነኝ ብሏል፤ ይስሃቅ በላይ፡፡
በአጠቃላይ ከወርቅ ኳሱ ባሻገር የአሜሪካ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጂል ኤሊስ የዓመቱ ኮከብ ሴት አሰልጣኝ የአሜሪካዋ አማካይ ካርሊ ልሎይድ የዓመቱ ኮከብ ሴት ተጨዋች ሆነው በመመረጥ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በዓመቱ ምርጥ ጎል የፑሽካሽ ሽልማን ያሸነፈው የብራዚሉ ጎያንሳ ክለብ ተጨዋች የሆነው ዌንዲል ሊራ ነው፡፡ ለዚህ ምርጫ በፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፆች እና በዩቲውብ 1.6 ሚሊዮን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ዌንዴል ሊራ ከተሰበሰበው ድምፅ 46.7 በመቶ ድርሻ በማግኘት የፑሽካሽ ሽልማት ሲቀበል ሜሲ በ33.3 እንዲሁም አሌሳንድሮ ፍሎሬንዚ በ7.1 በመቶ የድምፅ ድርሻቸው ተከታታይ ደረጃዎችን ወስደዋል፡፡
የፊፋ ስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ በዓለም ዙርያ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ድርጅቶች እና ተቋማት በጋራ የተሸለመ ሲሆን  በ2015 የዓመቱ ምርጥ ቡድን ምርጫ የዓለም ፕሮፌሽና ተጨዋቾች ማህበር አባል የሆኑ 26478 ተጨዋቾች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ እና የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ክለቦች በብዛት ሲወከሉ፤ የፈረንሳዩ ሊግ  እና የጣሊያኑ ሴሪኤም አንድ አንድ ተጨዋች ማካተት ችለዋል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በአንድም ተጨዋች ሳይወከል ቀርቷል፡፡
ግብ ጠባቂ
ማኑዌል ኑዌር— ባየር ሙኒክ ፤ ጀርመን
ተከላካዮች
ዳኒ አልቬስ— ባርሴሎና ፤ብራዚል
ማርሴሎ — ሪያል ማድሪድ፤ ብራዚል
ሰርጂዮ ራሞስ— ሪያልማድሪድ ፤ስፔን
ቲያጎ ሲልቫ— ፒኤስጂ፤ ብራዚል
አማካዮች
አንድሬስ ኢንዬስታ —ባርሴሎና፤ ስፔን
ሉካ ሞድሪች— ሪያል ማድሪድ፤ ክሮሽያ
ፖል ፖግባ— ጁቬንትስ፤ ፈረንሳይ
አጥቂዎች
ክርስትያኖ ሮናልዶ— ሪያል ማሪድ ፖርቱጋል
ሊዮኔል ሜሲ— ባርሴሎና አርጀንቲና
ኒዬማር —ባርሴሎና ብራዚል
የብሔራዊ ቡድን አምበሎችና ዋና አሰልጣኞች በሰጡት ድምጽ ለአገራቸው ዜጋ፣ ለሚሰሩበት ወይም ሰርተው ለሚያውቁበት ክለብ፤ ለቡድን አጋራቸው አድልተው ድምፅ መስጠታቸው ይስተዋላል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ የ2017 ማጣሪያ እና በቻን 2016 ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉ ቡድኖችም ሙሉ ለሙሉ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በወርቅ ኳሱ የሰጧቸውድምፆች ናቸው፡፡
በወርቅ ኳስ
ከቻን 2016 የምድብ 2 ቡድኖች አምበሎች
ስቴፈን ምብያ- ካሜሮን - ያያ ቱሬ፣ ኢብራሞቪችና ማኑዌል ኑዌር
ካርዶስ ዳራክ -አንጐላ - ሜሲ፣ ሮናልዶና ኔይማር
ሙሉም የሱፍ -ዲ. ሪፖብሊክ ኮንጐ -ሜሲ፣ ሮናልዶና ያያ ቱሬ
በአፍሪካ ዋንጫ 2017 ማጣሪያ የምድብ3 አምበሎች
ሜጃኒ ብራል -አልጀሪያ -  ሜሲ፣ ሮናልዶና ኔይማር
ማኑ ያኒክ -ሲሸልስ  - ሜሲ፣ ሮናልዶና ኔይማር
በቻን 2016 የምድብ 2 አሰልጣኞች
ፍሌሞን ሮሜው - አንጐላ - ሮናልዶ፣ ሜሲና ሃዘርድ
ቤሊንጋ ቤሊንጋ-  ካሜሮን - ሮናልዶ፣ ሜሲና ቶማስ ሙለር
ኢቤንጐ ፍሉረንት- ደ.አ ኮንጐ - ሜሲ፣ ሮናልዶና ያያ ቱሬ
በአፍሪካ ዋንጫ 2017 ማጣሪያ አሰልጣኞች
ክርስቲየን ጉርኩፍ - አልጀሪያ - ሜሲ፣ ኔይማርና ቶማስ ሙለር
ዓልዬ ሞሰስ - ሌሶቶ - ሜሲ፣ ኔይማርና ሮናልዶ
ጆን ሊውስ -ሲሸልስ - ሜሲ፣ ሮናልዶና ኔይማር

Read 2187 times