Saturday, 16 January 2016 10:31

አዶለሰንት የኅብረተሰብ ክፍሎች የተዘነጉ ናቸው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

         የሕፃናት ሐኪሞች ማህበር፤ “Adolescent Health in Ethiopia” በሚል መሪ ቃል 17ኛ ጠቅላላ ዓመታዊ ጉባኤውን በአዶለሰንት ሥነ ተዋልዶ፣ ማኅበራዊ ሕይወትና ጤና … ላይ በማተኮር ሰሞኑን አካሄደ፡፡
ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ የሕፃናት ሐኪሞች ማኅበር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ቦጋለ ወርቁ፤ ባደረጉት ንግግር፤ “አዶለሰንት፣ ፈረንጆች No Man Territory እንደሚሉት የሕፃናት ሐኪሞች ይህ የእኔ ድንበር አይደለም፣ የማህፀን ሐኪሞችም ይህ የእኔ ድርሻ አይደለም በማለት፣ በመኻል የተረሳ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፤ በዚህ ክፍል ላይ ትኩረት የሚያደርግ ጉባኤ ነው ብለዋል፡፡
የተዘነጋ የኅብረተሰብ ክፍል ስለሆነ በችግሮቻቸው ላይ የተደረገ ጥናት አለ ለማለት አያደፋፍርም ያሉት ፕሮፌሰር ቦጋለ፤ የሥነ ተዋልዶ፣ የአልኮል ሱሰኝነት፣ አደጋ ማብዛት፣ የአዕምሮ ጭንቀት፣ … ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰው፣ አሁን መንግሥት ለእነዚህ ክፍሎች ትኩረት ለመስጠት ፖሊሲ እንደተቀረፀላቸው ተናግረዋል፡፡
ጉባኤው በሁለት ቀን ውሎው ከሚነጋገርባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሌላው፣ ለረጅም ጊዜ አጀንዳቸው ሆኖ የቆየው አሁንም አጀንዳ እንደሆነ የሚቀጥለው የጨቅላ ሕፃናት  ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሕብረተሰቡ፣ ጨቅላ ህፃን ሲሞት “ጠፋ” ከማለት በስተቀር አያዝንም፤ ለመቃብራቸውም ትከረት አይሰጥም ብለዋል። አሁን ግን ይህ ጉዳይ ተገልብጦ ያለ ቀናቸው የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ሁሉ ማደግና ለአገራቸው ጠቃሚ፣ መመኪያና ኩራት መሆን እንደሚችሉ እውቅና አግኝቶ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕፃናት ሐኪሞች ማኅበር፤ በጨቅላ ሕፃናት ላይ ብዙ ጥናት ማካሄዱን የጠቀሱት የማኅበሩ ዳይሬክተር፤ 5 ዓመት ሳይሞላቸው ከሚሞቱ በርካታ ሕፃናት 40 ከመቶ ጨቅላ ሕፃናት ናቸው፡፡ ለምን ይሞታሉ ቢባል? ከቀን በፊት ስለሚወለዱ፣ ብርድ ያለመቋቋም፣ ኢንፌክሽን፣ … (በጀርም መመረዝ) ዋናዎች ናቸው፡፡ ከቀናቸው በፊት የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት፤ ጡት መጥባት ስለማይችሉ ረሃብም ሊገላቸው ይችላል። ችግሮቹ በጥናት ስለተረደሰባቸው መፍትሄ ተፈልጎ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ፕሮፌሰር ቦጋለ ወርቁ አስረድተዋል፡፡ 

Read 3505 times