Saturday, 23 January 2016 14:01

በ4ኛው ቻን የዋልያዎቹ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ቀጥሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

•    ዋልያዎቹ ከምድብ የማለፍ እድላቸውን በመጨረሻ ጨዋታቸው ይወስናሉ
•    ከዋልያዎቹ በቻን የመጀመርያውን ጎል ማን እንደሚያገባ እየተጠበቀ ነው?
•    በአሰልጣኙ ቆይታ፤ በስልጠና ፍልስፍና እና በተለያዩ አስተዳደራዊ ሁኔታዎችችግሮች አሉ፡፡
•    የማልያቸው መዘበራረቅም እልባት ማግኘት ይኖርበታል፡፡
በ4ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ /ቻን/ ላይ የሚሳተፉት ዋልያዎቹ ሐሙስ ምሽት ላይ በምድብ ሁለት ባደረጉት የሁለተኛ ዙር ጨዋታቸው  በሻምፒዮንሺፑ የተሳትፎ ታሪካቸው የመጀመርያውን 1 ነጥብ ያስመዘገቡ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር እንዳዳገታቸው ነው፡፡   
በዋልያዎቹ ሁለተኛው የቻን ተሳትፎ ከሰኞው 6ኛው ጨዋታ በፊት በተደረጉ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልተቻለም፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ላይ በ3ኛው ቻን  በሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ዋልያዎቹ ከምድባቸው ሲሰናበቱ በ3 ጨዋታ አንድም ግብ ሳያስቆጥሩ ነበር፡፡  ዘንድሮ በ4ኛው ቻን የዮሃንስ ዋልያዎች ይህን ታሪክ እንደሚቀይሩና ከምድባቸው አልፈው ሩብ ፍጻሜውን እንደሚቀላቀሉ እየተጠበቁ ነበር፡፡ በምድባቸው ከዲ.ሪ ኮንጎ እና ከካሜሮን ጋር ባደረጉአቸው  ሁለት ጨዋታዎች በ0ለ0 ውጤት አንድ ነጥብ  ከማስመዘገባቸው ባሻገር ከሁለት የማይበልጥ የረባ የግብ ሙከራ እንኳን አለማድረጋቸው የሚያሳስብ ነው፡፡
ከምድብ 2 ዲ.ሪ ኮንጐ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ሩብ ፍፃሜ በመግባት የመጀመሪያዋ ስትሆን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን 3ለ0 ካሸነፈች በኋላ  በሁለተኛው ጨዋታዋ አንጐላን 4ለ2 በማሸነፍ ያረጋገጠችው ነው፡፡ በአንፃሩ አንጎላ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በመሸነፏ ከቻን በመሰናበት የመጀመርያው ሆናለች፡፡ በምድብ 2 በ6 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ የምትመራው ዲ.ሪ ኮንጐ ናት፡፡ ካሜሮን በ4 ነጥብና በላይ ግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ኢትዮጵያ በ1 ነጥብ በ3 የግብ ዕዳ 3ኛ ደረጃ፣ አንጐላ ያለምንም ነጥብ በ3 የግብ ዕዳ 4ኛ ናቸው፡፡
የምድቡ የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች ሰኞ በአማሃሮ ስታድዬም ሲደረጉ ዲ.ሪ ኮንጐ ከካሜሮን እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአንጐላ ይገናኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሩብ ፍፃሜ ሊገባ የሚችለው አንጐላና በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ ፤ ካሜሮን በዲ.ሪ ኮንጐ ከተሸነፈች ነው፡፡
በ4ኛው ቻን በምድብ 1 ከምትገኘው አዘጋጇ ሩዋንዳ ባሻገር ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት ያገኙት ዲ.ሪ ኮንጐ ከምድብ 2፣ ከምድብ 3 ናይጀሪያና ቱኒዚያ እንዲሁም ከምድብ 4 በምድብ 1 የምትገኘው አይቬሪኮስት በሁለተኛ ደረጃ የዋንጫ ግምቱ ተሰጥቷታል፡፡ ከምድብ 2 ባሻገር አዘጋጇ ሩዋንዳ ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የቻን ሻምፒዮንሺፕ   ምድቡን እየመራች ወደ ሩብ ፍፃሜ መግባቷን ማረጋገጧ የውድድሩን ድምቀት ተስፋ ፈጥሮበታል፡፡  ከትናንቱ የምድብ 3 የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች በፊት በ4ኛው ቻን ላይ በ12 ጨዋታዎች 2 ጐሎች ሲቆጠሩ ይህም በአማካይ በአንድ ጨዋታ 2.42 ጐሎች የሚመዘገቡበት ሻምፒዮንሺፕ አድርጎታል፡፡
በዋልያዎቹ የቻን ተሳትፎ በርካታ አበይት የመነጋገርያ አጀንዳዎች ተፈጥረዋል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ስኬት የሚያግዙ ሁኔታዎች አለመተግበራቸው የቡድኑን ተፎካካሪነት በሞት ሽረት ትንቅንቆች የተሞላ አድርጎታል፡፡  ዋልያዎቹ ወደ ቻን ከመግባታቸው በፊት በቂ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጋቸው፤ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የቡድኑን የተሳትፎ ደረጃ ከምድብ ጨዋታዎች እንደማያልፍ  በመወሰን የአውሮፕላን ትኬት መቁረጡ፤ ዋና አሰልጣኙ በዝግጅታቸው ወቅት ግብ ለማስቆጠር እንደሰሩና ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት ማቀዳቸውን ገልፀው ስላልተሳካላቸው፤ ከካሜሮን ጋር ከተደረገው ጨዋታ በፊት የቡድን መሪው ዋልያዎቹ እንዲያሸንፉ ፀሎት ይደረግ ማለታቸው ዋና ዋናዎቹ አበይት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ የውጤት ማነሳሻ የቦነስ ክፍያ ባለመኖሩም ውጤት እንደጠፋ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዋልያዎቹ በቻን ሲሳተፉ በቀን በነፍስ ወከፍ ከሚታሰብላቸው 100 ዶላር ቦነስ ባሻገር በጥቅሉ ከሚሰጥ የማበረታቻ ክፍያ በየጨዋታው የውጤት ቦነስ አለመደረጉ ተገቢ አልነበረም፡፡ እንደ ናይጄርያ አይነት ቡድኖች በየጨዋታው ሲያሸንፉ እስከ 2ሺ ዶላር የሚታሰብ ሲሆን በኢትዮጵያ ደረጃ ቢያንስ እስከ 300 ዶላር አለመጠራቱ ወደፊት መቀየር ያለበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑ ካለበት የግብ ማስቆጠር ችግርና በተፎካካሪያቸው ከሚወሰድባቸው ብልጫ  አንፃር በአሰልጣኙ የስራቆይታ፤ በስልጠና ፍልስፍና ሞቅ ያሉ አጀንዳዎች ተቆስቁሰዋል፡፡ በተለይ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ውጤት ማምጣት ስላዳገታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ፤ በፌደሬሽኑ አሰራር ለብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ የሚሆነው የቴክኒክ አማካሪ አለመኖሩ፤ የቀድሞው ስኬታማ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድኑን እንዲረከቡ የሚጠይቅ መብዛቱ እንዲሁም ታዋቂው የገነነ መኩርያ ‹‹ጂኬ››  የስልጠና ፍልስፍና እንዲሞከር ከፍተኛ ጫና ከስፖርት አፍቃሪው በአዲስ መልክ ጉትጎታ እየተደረገ መሆኑ ናቸው፡፡
ከ4ኛው ቻን በተያያዘ ሌላው የሚነሳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሊያገኝ የሚችለው የአህጉራዊ ውድድር መስተንግዶ ተመክሮ ይሆናል፡፡ በ2020 እ.ኤ.አ ስድስተኛውን ቻን ለማዘጋጀት እድሉን ያገኘው ፌዴሬሽኑ  ከሩዋንዳ ብዙ የሚማራቸው ነገሮች ይኖሩታል፡፡ ምናልባትም ሰሞኑን በወጡ ዘገባዎች እንደተገለፀው በ2018 እ.ኤ.አ ኬንያ ታዘጋጀዋለች ተብሎ የነበረው አምስተኛው ቻንም ለኢትዮጵያ ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል መባሉ በከፍተኛ ደረጃ ሊያነቃ የሚገባ ነው፡፡
ከሩዋንዳ መስተንግዶ መገንዘብ እንደሚቻለው አንድ የቻን አዘጋጅ አገር እስከ 25 ሚ. ዶላር በጀት መያዝ ይኖርበታል፡፡ በብሄራዊ ደረጃ እስከ 200 አባላት ያሉትና በተለያዩ ኮሚቴዎች ተደራጅቶ የሚሰራ ጊዜያዊ  ምክር ቤት ያስፈልጋል፡፡ ሦስት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ማዘጋጀት ሲጠበቅ ስታዲየሞቹም በመሰረተ ልማት አቅማቸው የተሟሉ መሆን አለባቸው፡፡ የሚዲያ ማዕከሎች፣ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ መቀመጫ ቢሮዎች፣ የህክምና መስጫ ተቋማት፤ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥባቸው አዳራሾች፣ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና ሚዲያው ከጨዋታ በኋላ በቀጥታ የሚገናኙባቸው ኮሪደሮች በየስታድዬሞቹ መገኘታቸውም ወሳኝ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከሴካፋ መስተንግዶ እና በ4ኛው ቻን እንደታየውም የየስታድዬሞቹ የፓውዛ መብራት ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከስታዲየሞቹ ባሻገር የቻን አዘጋጅ የ16 ተሳታፊ አገራትን እስከ 500 የሚደርሱ ልዑካን የሚያሳርፍባቸው ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎችም በብዛት በዋና ከተማ ብቻ ሳይሆን በክልልም ያስፈልጋሉ፡፡    
በመጨረሻም ከ4ኛ ቻን ጋር በተያያዘ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ጉዳይ ነው፡፡ ከካሜሮን ጋር በተደረገው ጨዋታ ዋልያዎቹ ለብሰው የነበሩት ሙሉ ቢጫ ማልያ  በለጠፈው ስም ምክንያት አጨቃጫቂ ነበር፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን ደንብ የተጣረሰ ነው በሚል በማሊያው ላይ ያለው ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ በነጭ እንዲሰረዝ ተደርጎ ነበር፡፡ ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ በአውስትራሊያ የሚገኝ የትጥቅ አምራች ኩባንያ በAMS አማካኝነት ለቡድኑ አዲስ የማሊያ ዲዛይን እንደቀረበ ነው፡፡ የዋሊያዎቹ ቁልፍ ተጨዋች ጋቶች ፓኖም ለብሶት በሶሻል ሚዲያዎች ሊያስተዋውቀው ሞክሯል፡፡ ሶካአፍሪካ እንደዘገበው ይኸ ማልያ ማቲው ዎልፍ በተባለ ሰው የቀረበ ዲዛይን ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሊያው ከስፖርት ቤተሰቡ ተቀባይነት እንደማያገኝ በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ዋናው ምክንያት ደግሞ አረንጓዴና ቢጫ የለበትም የሚል ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስልጣኑን ከተረከበ ወዲህ በማሊያው ላይ ምንም አይነት ቋሚ ውሳኔ ያሳለፈ አይመስልም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከሜዳ ውጪና በሜዳ ላይ ቡድኑ የሚያደርገው ማሊያ የተዘበራረቀ ሆኖ ተስተውሏል፡፡  አንዳንድ ጊዜ ታዋቂውን ባለሸንተረር ማሊያ ሌላ ጊዜ ሙሉ ቢጫ አንዳንዴ ደግሞ አረንጓዴ ማሊያ እያደረገ የአገርን ክብር እያዘበራረቀ ነው፡፡ ይባስ ብሎ በቻን ውድድር ላይ በብሄራዊ ቡድኑ ማሊያ ላይ የተወሰነው ሁኔታ የፌዴሬሽኑን ትኩረት አለመስጠት ያመለክታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ2014 እ.ኤ.አ የተመሰረተው የአውስትራሊያ ኩባንያ ያቀረበው የአዲስ ማሊያ ፕሮፖዛል ሙሉ ቡኒ ቀለም የበዛበትና ባህላዊ ሁኔታዎች የሚንፀባረቁበት ነው፡፡ ማሊያው ቢጫና አረንጓዴ ቀለሞችን ደንቡ እንደሚያስገድደው የሌሉበት መሆኑ የሚያሳስብ ነው፡፡  በኤኤምኤስ የቀረበው የማሊያ ዲዛይን ተቀባይነት አገኘም፤ አላገኘም በብሔራዊ ቡድኑ ማሊያ ቋሚነት፤ ልዩ መለያና ቀለም ዘላቂ ውሳኔዎች እንደሚያስፈልጉ አስተያየቶች እየተሰጡ ናቸው፡፡ የአውስትራሊያው ኩባንያ ኤኤምኤስ ለደቡብ ሱዳን፣ ለሩዋንዳና ለሴራሊዮን ባለፉት ሁለት ዓመታት የብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ማሊያ በማቅረብ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከቻን ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ማሊያ አሰርቶ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ከሁለት እና ከሦስት አመታት በፊት በአፍሪካ ዋንጫና በቻን ውድድር ታዋቂ የሆነው ባለሸንተረሩ ማሊያ ከዋሊያዎቹ ባሻገር በስፖርት ቤተሰቡ ያገኘው ተቀባይነት ከግምት ውስጥ ገብቶ ለቡድኑ ቋሚ ማልያ መወሰን አለበት፡፡ ባለሸንተረሩ ማሊያ ከሦስት ዓመት በፊት ከዋሊያዎቹ ስኬት ጋር በተያያዘ በቀን እስከ 250 በነጠላ ይቸበቸብ የነበረ ሲሆን ዋጋቸውም እንደየጥራት ደረጃው ከ50-200 ብር ይሸጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የተለያዩ አስመጪና ላኪ ኩባንያዎችም ከቻይና እስከ 10,000 ማሊያዎችን በማስመጣት እየነገዱ ነበር፡፡ ምናልባትም ይህ ሁኔታ ከዋልያዎቹ ስኬት ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ራሱ በ75 ብር ከ15,000 ማልያዎችን ለገበያ በማቅረብ የተጠቀመበት ሁኔታም አይዘነጋም፡፡ በአጠቃላይ ከቻን መልስ የብሔራዊ ቡድኑ ማልያ ጉዳይ እልባት ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡

Read 2150 times