Saturday, 23 January 2016 14:05

እራስህን/ሽን እንኳን ደስ ያለህ/ሽ ማለት ልመድ/ጂ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

•    ከወሊድ በሁዋላ በሚፈጠር የአእምሮ ጭንቀት ወይንም ድብርት እናቶች እራሳቸውንና የወለዱትን ልጅ በተለያየ መንገድ ሊጎዱ ይችላሉ።
•    ልጅ ከተወለደ በሁዋላ የሚፈጠር የአእምሮ ጭንቀት ወንዶችንም ሊይዝ ይችላል።
•    ማንኛውም ሰው የድብርት መንፈስ ከተጫጫነው ተስፋ ያጣ መስሎ ሊሰማው ይችላል።
ሰዎች ሁልጊዜ አንድ አይነት ስሜት አይኖራቸውም። አንዳንድ ጊዜ ቀለል ያለና ጥሩ ስሜት የሚሰማቸው ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የመጫጫን የድብርት ስሜት ይሰማቸዋል። ታድያ ድብርት ሲሰማ መፍትሔውን በጊዜው ካልፈለጉ ሰፋ ያለ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ ወላድ ሴቶች ልጃቸውን ወልደውና ታቅፈው ከቤታቸው ከደረሱ በሁዋላ ለራሳቸውም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ድብርት ይሰማቸዋል። ከወሊድ በሁዋላ በጥቂት ወራት ውስጥ አንዳንድ እናቶች ላይ የሚፈጠር የመንፈስ ጭንቀት ቀላል የማይባል ሕመም ነው። እናቶች እርግዝናው በራሱ ጊዜ ሲወርድና ሕይወት የሌለው ልጅ ወይንም የተለያየ የአካል ጉድለት ያለበትን ልጅ ሲገላገሉ የአእምሮ ጭንቀት ሊከሰት እንደሚችል ጥናቶች ያስረዳሉ። ከወሊድ በሁዋላ ለሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት የሚዳረጉት ሴቶች ከ5-25  የሚደርሱ ሲሆን ወንዶችም የልጅ አባት ሲሆኑ ከ1.2-25.5 የሚሆኑት ለችግሩ ይዳረጋሉ።
Postpartum Depression በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የአእምሮ ጭንቀት ሴቶች በወለዱ ከአራት ሳምንት ጀምሮ ሊከሰት የሚችል ሲሆን ማብቂያው ከተወሰኑ ወራት እስከ አንድ አመት ሊደርስ ይችላል። ምናልባትም በትክክል የህክምና እርዳታ ካላገኘ ለከፋ ሁኔታ ሊጋብዝ ይችላል። ልጅ መውለድ ተፈጥሮአዊ የሆነና እናትየውንም ሆነ አባትየውን የሚያስደስት መሆኑ የታመነበት ነው። እናቶች በእርግዝናቸው ወቅት ስለወደፊቱ ሁኔታ ማለትም በምን ሁኔታ ልጅ እወልድ ይሆን? እንዴትስ አሳድገዋለሁ የሚሉት እና ሌሎችም ተያያዥ የሆኑ ነገሮች የሚያስጨንቋቸው ሲሆን ልጃቸውን በሰላም ሲገላገሉ ግን የሚጠበቀው ደስተኛ እንዲሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን ስሜታቸው በተቃራኒው መንገድ ይሄድና ልጃቸውን ከወለዱ በሁዋላ ሊያሳዩ የሚገባቸውን የደስታ ስሜት ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥማል። ብዙዎቹ እናቶች ልጃቸውን ከወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስሜታቸው መረበሽ፣ የሚያዩትና የሚሆነው ነገር አለመገናኛት፣ ስለራሳቸው፣ ስለቤታቸው፣ ስለቤተሰባቸው የሚያስቡት ሁኔታና እውነታው አልገናኝ ስለሚላቸው የሀዘን ስሜት በውስጣቸው ይፈጠርና ስሜታቸው ይረበሻል። እናቶች ከእርግዝናው ጋራ በተያያዘ የሆርሞኖች፣ የንጥረ ነገሮች እና የተለያዩ ነገሮች ለውጦች ስለሚኖሩ እነዚህ ለውጦች ከአስተሳሰብ ወይንም ከአእምሮ ጋር ስለሚገናኙ በድንገት በሚቋረጥበት ጊዜ የአእምሮ መረበሽንና መጨነቅን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን ነገር ግን ይህ ስሜት ቀላልና በብዙዎች ዘንድ የሚታይ ሕክምናን የማይፈልግ እና በጥቂት ጊዜያት በራሱ የሚወገድ ነው።
        ዶ/ር አታላይ አለም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ።        
የድብርት መንፈስ ከተጫጫነህ ተስፋ ያጣህ መስሎ ሊሰማህ ይችላል። በእርግጥ የባለሙያ እርዳታ ማስፈለጉ አይቀርም። ነገር ግን ስሜቱ ያደረበት ሰው በራሱ ጊዜ ነገሩን ቀለል አድርጎ እራሱን መርዳት ይችላል።
የምትወደውን እና ላንተ ጥሩ የሆነውን ሰው አትራቀው። ምናልባትም ጥሩ ጉዋደኛህብ የቅርብ ሰው ልታደርገው ይገባል። ከዚህ ሰው ጋር ስትጫወት አንዳንድ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ስታደርግ ለሌላ ሰውም ጠቃሚ እንደሆንክና ከራስህ ወጪ ለሌሎችም ሰዎች እንደምታስፈልግ ስትረዳ በውስጥህ ያለው የጭንቀት ወይንም የድብርት ስሜት ሊጠፋ ወይንም ሊቀንስ ይችላል።
ጤናማ አመጋገብ ድብርትን ለመቀነስ ከሚረዱ መካከል ናቸው። ፍራፍሬዎችን፣ ቅጠላ ቅጠሎችን እና አትክልቶችን መመገብ ጤናማ አመጋገብ ስለሆነ አካልንና የአእምሮ አስተሳሰብን ያሳድጋል። ጤናማ ያደርጋል።
ኦሜጋ 3-ፋቲ አሲድስ እና ቫይታሚን ቢ12/ ያላቸውን ምግቦች መመገብ በማይችሉ ሰዎች ላይ ይህ የድብርት መንፈስ አይሎ ይታያል። ለምሳሌ የአሳ ምግቦቸን ቱናን ጨምሮ እንደ ኦቾሎኒ አኩሪ አተር እና ጥቁር አረንጉዋዴ መልክ ያላቸው ቅጠላ ቅጠሎችን የተጠቀሱትን ማእድናት ለማግኘት ይጠቅማሉ። ስጋ ወይም አሳ የማይበሉ ሰዎችም ከጥራጥሬዎችና የወተት ተዋጸኦዎች ቫይታሚን ቢ12/ን ማግኘት ይችላሉ።
ካፊን ያለባቸውን መጠጦች ማብዛት ጎጂ ነው። የካፊን መጠጥ በበዛ ቁጥር ሰውነትን መረበሽ ወይንም ነርቨስ ያደርጋል። የካፊን መጠጦችን መቀነስ ሰውነት እንዲያርፍና እንቅልፍ እንዲያገኝ ስለሚረዳም የመደበር ወይንም የመረበሽን አጋጣሚ ይቀንሳል።
የሚሰማህን ሕመም ችላ ሳትል ተቆጣጠረው ወይንም በሕክምና እርምጃ ውሰድ። ይህ ስሜት ሲከማች ስሜትን ወደ ድብርት ሊለውጠው ይችላል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ድብርትን ለማባረር ይረዳል። ይህ ማለት ግን ከምትችለው በላይ መሮጥ ሳይሆን በእርጋታ እርምጃን መራመድ ነው። ቀናትን ሳያቋርጡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እርምጃዎን በራስዎ አቅም እያሻሻሉ ከተንቀሳቀሱ የምሽት መኝታዎ በጥሩ እንቅልፍ የተሞላ ይሆናል። ድብርት የሚባል ነገርም ከአካባቢዎ አይደርስም። ብስክሌት መጋለብ፣ አትክልት ውስጥ መስራት፣ ኒስ መጫወት፣ ዋና መዋኘት ከመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች የሚስማማዎትን መምረጥ ይጠቅምዎታል። ከሰዎች ጋር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እስፖርቱን ለማዘውተርም ይሁን ለጉዋደኝነቱ ስለሚጠቅም ጥሩ ጎን አለው።
ከአየር ጸባይና መምሸት መንጋት ጋር ያለውን የአእምሮ ንቃትና ጭንቀት ወይንም መደበር መፈተሸ ይገባል። በጭለማና በክረምት ወቅት ምናልባት የበለጠ የሚደበሩበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል በቂ ብርሀን እና ሞቅ ያለ የአየር ጸባይ እንዲኖር የቻሉትን ያድርጉ።
የፈጠራ ችሎታዎን ወደተግባር ለመቀየር ጥረት ያድርጉ። ለምሳሌ ቀለም መቀባት፣ ፎቶግራፍ ማንሳት፣ ሙዚቃ፣ ጽሁፍ መጻፍ ...የትኛውን ማድረግ ይሻሉ? ድብርትዎን ለመቀነስ በሚያስደስትዎ ስራ ላይ ይጠመዱ። በሰሩት ስራ ለመሸለም ወይንም ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን በስራ መጠመድዎ የሚያስገኝልዎትን የድብርት መጥፋት ምክንያት በማድረግ ነው።
አእምሮህን ለማዝናናት አትቦዝን። ጭንቀትና መረበሽ የድብርት ስሜትን ለመፍጠር ቅርብ ናቸው። አእምሮን ማዝናት የተረጋጋና ልትቆጣጠረው በምትችለው መንገድ ማስተዋል እና ማድረግን ያተርፍልሀል። ረዘም ላለ ሰአትና ሙቀቱ በሚስማማ ውሀ ሙዚቃ እያዳመጡ ገላን የመታጠብ ፕሮግራም መያዝ አእምሮን ከሚያዝናኑባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ንጹህ አየር እየወሰዱ ጉዞ ማድረግ የመሳሰሉትም ይመከራሉ።
በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ የድብርት ስሜትን ለመላቀቅ ይረዳል። ወይንም ውይይቶችን፣ ስብሰባዎችን መሳተፍ ቤተእምነቶች ጋ መገኘት ከአዳዲስ ሰዎች ጋር መገናኘት የመሳሰሉት ሁሉ ጠቀሜታ አላቸው።
በሕይወት ዘመንህ ያገኘሃቸውን ጉዋደኞችህንና ቤተሰቦችህን በቅርብ አግኛቸው። ሊረዱህ ወይንም ሊጠይቁህ የሚችሉ ሰዎችን ካራቅሀቸው ሊረዱህ አይችሉም። ካቀረብካቸው ግን ይጠቅሙሀል። ከጉዋደኛ ወይንም ከቤተሰብ ጋር መገናኘት የስኒ ቡና መጋራት የመሳሰለው የሚሰጥህ ደስታ ድብርት በአቅራቢያህ እንዳይደርስ ይረዳል።
ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ለጤና ጠቃሚ ነው። አንዳንዶች በድብርት ምክንያት ረዥም ሰአት ይተኛሉ። ሌሎች ደግሞ ጭርሱንም መተኛት አይችሉም። ስለዚህ የመኝታ ሰአትን መጠበቅ እና ድብርት እንዳይከሰት ለማድረግ የተሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ያስችላል።
አልኮሆልና ሱስ አስያዥ እጾችን ማስወገድ ሌላው የሚመከር ነገር ነው። ምክንያቱም ከድብርት መንፈስ ለመላቀቅ የሚያስችል ወይንም ለመላቀቅ ረዥም ጊዜን ሊፈጅ የሚያስችል ነው። ድብርትን ለመላቀቅ እንዲያስችል ከተወሰደው መድሀኒትም ጋር ሊጋጭ ይችላል። ከሚጠቀሙዋቸው እጾችና መጠጥ መላቀቅ ካልቻሉ ግን የህክምና እርዳታ ያስፈልጋል።
ከላይ የተዘረዘሩት ጠቃሚ ምክሮች የራስን አቋም ለማስተካከል የሚረዱ ቢሆኑም ከሐኪምዎ መራቅ ግን አይመከርም።
•    ድብርት ደስታን ያርቃል።
•    ተስፋቢስ እንደሆኑ እንዲሰማ ያደርጋል።
•    አቅምን ያሳጣል። እንቅልፍ ይከለክላል።
•    ችግርን መቋቋም አያስችልም።
•    አንዳንዴም በራስ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስሜትን ሊፈጥር ይችላል።
ስለዚህ ምንጊዜም ከሐኪም መራቅ አይገባም።
በማጠቃለያው ባለሙያዎች የሚሰጡት ምክር የሚከተለው ነው።
    ምንጊዜም ጥሩ ስራ እንደሰራህና እንደተሳካልህ ስትገነዘብ እራስህን እንኩዋን ደስ ያለህ በለው። በአንጻሩ ደግሞ ስህተት እንደሰራህ ስታውቅ ካለምንም ማወላወል እመን። እራስህንም...አ.አ.ይ ተሳስተሀል እዚህ ጋ ልታርም ይገባሀል ስትል ለቀጣዩ ስኬት ተዘጋጅ።
ስለዚህ ምንጊዜም የሰራነውን ስራ ማድነቅና ስህተትም ቢኖር ምንም አይደለም... ይስተካከላል ብሎ በጸጋ መቀበልን መልመድ አእምሮን ለማዳበር በድብርት እንዳይያዝ ለማድረግም ይረዳል።


Read 4637 times