Saturday, 30 January 2016 11:50

እንኳንስ ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው

Written by 
Rate this item
(27 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አባት ክፉኛ ይታመምና የአልጋ ቁራኛ ይሆናል፡፡ ባለቤቱ ቀደም ብሎ ህይወቷ አልፏል፡፡ ያለው አንድ ልጅ ብቻ ነው፡፡ የሚያስታምመውም እሱ ነው፡፡
በሰፈሩ በየምሽቱ የሚመላለስና በረት የሚያጠቃ አንድ ነባር ጅብ አለ፡፡ ሰው ሁሉ ይሄንን ጅብ ለመግደል ብርቱ ጥረት ያደርጋል፡፡ ሆኖም ሊገድለው የሞከረ ሰው ሁሉ በውጤቱ የሚናገረው አንድ ቃል ብቻ ነው፡፡
“እህ አያ እገሌ ያን ጅብ እንዴት አደረግኸው?” ይላል መንደሬው፡፡
አዳኙም፣
“አዬ! አድፍጬ አድፍጬ አመለጠኝ ባክህ!”
እንዲህ እንዲህ እየተባለ ያ ጅብ ግን በየማታው ከየበረቱ አንድ አንድ አህያና አንዳንድ ጊደር እየመነተፈ ጉልበቱ እየጠነከረ መጣ፡፡
ታማሚው አባትና ልጅም የዚሁ ጅብ ሰለባ እየሆኑ፣ ብዙ ከብት ከበረታቸው ተበልቶባቸዋል፡፡
አንድ ቀን አባትዬው ልጁን ጠርቶ፤
“ልጄ ሆይ”
“አቤት አባባ”
“የዚህን የጅብ ነገር አንድ መላ መምታት አለብን”
“ምን ዓይነት መላ አባዬ?”
“ወጥመድ ሰርተን እንይዘዋለን”
“ምን አይነት ወጥመድ?”
“ሄደህ ከመንደር ሙዳ ስጋ ገዝተህ ትመጣለህ”
“እሺ፤ ከዛስ?”
“ያንን ሙዳ ሥጋ በጠመንጃችን አፈ - ሙዝ ላይ ታስረዋለህ”
“እሺ፤ ከዛስ”
“ሙዳውን ያሰርክበትን ገመድ ጫፍ ጠመንጃው ቃታ ላይ ታስረዋለህ”
“ከዛስ?”
“በቃ ያንን ወስደህ በረታችን ፊት ለፊት ታስቀምጥለታለህ፡፡ አጅሬ ሥጋውን አገኘሁ ብሎ ሲጎትት ቃታውን ይስበዋል፡፡ ጥይቱ ባፉ ይገባና ድብን ያደርገዋል”
“እሺ አባዬ ዛሬ ማታ ያልከኝን አደርጋለሁ፤ ይሄ ከተሳካኮ የመንደሩ ህዝብ ነው የሚገላገለው፡፡ ለእኛም ጥሩ ስም ያተርፍልናል፡፡”
ልጅ በቃሉ መሰረት ሥጋውን ገዝቶ፣ ጠመንጃው ላይ አስሮ በረቱ ደጃፍ ላይ አስቀምጦ ይጠባበቅ ጀመር፡፡
ከሰዓታት በኋላ ልጁ ወደ አባቱ ሲሮጥ ይመጣል፡፡
“አባዬ አባዬ፤ ጉድ ሆነናል”
“ምነው? ምን ተፈጠረ” አለ አባት በድንጋጤ፡፡
“አባዬ፤ ጅቡ ጠመንጃውን በሰደፉ በኩል ነክሶ ሥጋውን ከነጠመንጃው ይዞት ሄደ፡፡”
አባትየውም፤
“ወይ ጉድ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!”
*          *          *
እንዲህ ያለ የሠለጠነ ጅብ አያድርስ ነው፡፡ ዛሬ በሀገራችን አያሌ የሰለጠነ ጅብ አለ፡፡ የሰለጠነ ጅብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን የጅቦች ማሰልጠኛ ያለ ይመስል በርካታ ጅቦች መኖራቸው የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ እጅግ የከፋው ነገር ደግሞ የጅቦች የተጠላለፈ መረብ፣ በሜዳ ስሙ “ኔትዎርክ” የሚባል መኖሩ ነው፡፡ ጅብ ለማጥመድ የሚሞክሩት ጥቂት ናቸው፡፡ ስለሆነም በመረቡ ተጠልፈው ራሳቸው ይያዛሉ፡፡ የሙስናን ነገር ለመፍታት እጅግ አዳጋች ያደረገው ይሄ ነው፡፡ ከላይ ነገሩን ይከላከላሉ፣ እርምጃ ይወስዳሉ የተባሉት አካላት ጉዳዩ ውስጥ ካሉበት ነገሩ ሁሉ የግብር ይውጣ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ “ስለገብስ አታውራ፡፡ ፈረሱ እንዳይሰማ” ሆኗል ችግሩ፡፡ የምናጠምደው ወጥመድ ሁሉ ጠመንጃ የሚያስነጥቀን ከሆነ ገንዘቡ፣ ሀብቱ፣ መሬቱ ወዴት እንደሚሄድ ያለጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ ፈረንጆች who guards the guards ይላሉ፡፡ ተቆጣጣሪዎቹን ማን ይቆጣጠራቸዋል፤ ጠባቂዎቹንስ ማን ሃይ ይላቸዋል፡፡ እንደማለት ነው፡፡ የቢሮክራሲው፣ የሥራ አስፈፃሚውና የነጋዴው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዛሬ “ቢዝነስ” የሚባለው ቃል የተራው ዜጋ፣ የተራው ሟች (average mortal) ቋንቋ ሆኗል፡፡ የካፒታሊዝምን ሥርዓት መቀበል፤ “ነፃ ገበያ”፣ “የግል  ሀብት”፣ “የዲሞክራሲ ሥርዓት”፣ “የኢንዱስትሪ መስፋፋት”… እንደምንለው ቃለ-ተውኔት የቀለለ አይደለም፡፡
የካፒታሊዝምን ሥርዓት መቀበል “መሳም ወደሽ ጢም ጠልተሽ” ማሰኘቱ አይቀሬ ነው፡፡ የባህል ወረራው ታላቅ አደጋ ነው፡፡ In God we trust (በእግዚአብሔር እናምናለን) ከሚለው ዶላሩ ላይ ከተፃፈው መራሄ-ቃል ጀምረን (እንዲህ እያልሽ ውቴልሽን ሽጪ ይላሉ ወሎዎች) እስከ ታላላቅ የንግድ መቆጣጠሪያ ኮርፖሬት ኃይሎች ድረስ የተዘረጋ መረብ እንዳለ ማስተዋል አለብን፡፡ በዚህ መረብ ውስጥ የማይጠመደው ጅብ አለ፡፡ በምንም መልኩ ሰው ገለህም ቢሆን፤ ገንዘብ ያዝ የሚለው መርህ አለ፡፡ ከጋሪ እስከ መርከብ ነግደህ አትርፍ (እያጎ እንደሚለው “ገንዝብ ሰብስብ በተቻለ”) የሚለው አለ፡፡ ጉዳዩ ግን የአስርቱ ቃላት ግልባጭ ስብከት፣ ነው፡፡ ማለትም “ሥረቅ”፣ አመንዝር”፣ “የጓደኛህን ሚስት ተመኝ”፣ “ጎረቤትህን እንደራስህ አድርገህ ጥላ” ወዘተ ማለት ነው፡፡ የመንታፊዎች፣ የወሮበሎች፣ የመንገድ ላይ ጉልቤዎች፣ የታጣቂ ሰራቂዎች፣ የቁጭ በሉዎች፣ የምሁራዊ ሌቦች፣ የልማታዊ ቀማኞች፣ የአዛኝ - ቅቤ - አንጓች ዘራፊዎች፣ የረቂቅ አገር - ቦርቧሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ጨረታ በዝባዦች፣ የባንክና የኢንሹራንስ መዝባሪዎች ወዘተ መፈልፈያ ነው ካፒታሊዝም፡፡ ታዲያ እነዚህ ፍልፍሎች እንደቃላት መጠሪያቸው የረከሱ አይደሉም፡፡ የክርስትና ስምም፣ የማዕረግ ጥምም፣ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያገኘ ስምም፣ የቢዝነስ ስምም፤ ያላቸው  የተከበሩ  ሥራዎች ናቸው። እንደኛ የተደላደለ ኢኮኖሚ በሌላቸው አገሮች ላይ እንግዲህ በእንቅርት ላይ ጆሮ  ደግፍ፣ በቡሃ ላይ ቆረቆር ማለት ነው፤ ካፒታሊዝም፡፡ ገንዘብና ገንዘብ እንጂ ሌላ ነገር  አታስቡ፡፡ እነሆ አምላካችሁ እሱና እሱ ብቻ ነው! ይላል መጽሐፈ - ንዋይ! ዕውቀት ባልበለፀገበት፣ ሃይማኖት በገንዘብ እየተሸረሸረ ባለበት፣ ባህልና ቅርስ ካንገት በላይ እየታሰበ ባለበት፣ አገም ጠቀም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የሚያኮራ በሚመስልበት፣ የሚከበሩ በዓላት ሁሉ  የኛም እየመሰሉ በሚታዩበት፣ መሰረታዊ የሚባሉት ቤት፣ ውሃ፣ መብራት እንኳ በቅጡ በማይገኝበት አገር የካፒታሊዝም አባዜ ሲጨመርበት “እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው” የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን!   

Read 9866 times