Saturday, 30 January 2016 12:33

በቻን ማግስት…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)


              የኢትዮጵያን እግር ኳስ አንድ ደረጃ ከፍ አድርጌዋለሁ - ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ
              የውጤት ታሪካቸው ግን ቡድኑ መውረዱን ያመለክታሉ
                             
      በሩዋንዳ የሚካሄደው 4ኛው ቻን ዛሬ ወደ ጥሎ ማለፍ ይሸጋገራል፡፡ ከምድብ 1 ሩዋንዳና ኮትዲቯር፤ ከምድብ 2 ካሜሮንና ዲ . ሪ ኮንጎ ፤ ከምድብ 3 ቱኒዚያ እና ጊኒ እንዲሁም ከምድብ 4 ዛምቢያ እና ማሊ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ጋቦን፣ አንጎላ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄርያ፣ ኒጀር፣ ኡጋንዳ እና ዚምባበቡዌ ከምድብ የተሰናበቱት  ናቸው፡፡  ዋልያዎቹ ከምድባቸው የመጨረሻውን ደረጃ ይዘው በተሰናበቱ ማግስት   ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ   ለቡድኑ ውጤት ማጣት በፌደሬሽኑ ላይ ቅሬታቸውን እንደገለፁ የዘገበው ሶካ አፍሪካ ሲሆን በቂ ዝግጅት አላደረግንም ማለታቸውን አውስቷል፡፡ በሌላ በኩል ፌደሬሽኑ በዋና አሰልጣኙ የ10 ወራት ቆይታ ሙሉ ለሙሉ ግምገማ ማድረግ እንዳለበት የስፖርት ቤተሰቡ እየጠየቀ ሲሆን አሰልጣኙ በቀጣይ የሚጠብቋቸውን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች በብቃት ስለመወጣታቸው ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሰጡት ተከታይ መግለጫቸው የኢትዮጵያን እግር ኳስ አንድ ደረጃ ከፍ በማድረጌ ከሃላፊነቴ የምለቅበት ሁኔታ የለም ብለዋል። በቻን ተሳትፏቸው በተቃራኒ ቡድኖች  የአካለ ብቃት ብልጫ ስለነበረ መብለጣቸውን የገለፁት አሰልጣኙ፤ ወጣት ተጨዋቾችና  ከረጅም ዓመት በፊት ኢንተርናሽናል  ልምድ የነበራቸውን ተጨዋቾች እንዲጫወቱ እድል መስጠቴ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ካሉ በኋላ  ከ20 በላይ ጨዋታ አድርገን  አንድ ቀይ ካርድ ብቻ ማየታችን ትልቅ ነገር  ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
በብሄራዊ  ቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር ላይ ዋና አሰልጣኙ ሲናገሩ ‹‹ጎል የማግባት ችግር የሀገሪቱ ችግር ነው፡፡ ያሉን አጥቂዎች የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ እኛም ጎል የማግባቱን ችግር ሙሉ ለሙሉ በአጥቂዎቻችን ላይ አልጣልንም፡፡ ከአጥቂ ጀርባ የሚሰለፉትን ተጨዋቾች በተለይ የመሀል መስመር ተጨዋቾቻችን ከመሀል እየተነሱ ጎሎችን እንዲያስቆጥሩ አድርገናል፡፡ ለዛም ነው በመጨረሻው ጨዋታ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካያችን ስዩም ጎሉን ያስቆጠረው፡፡ ሌላው ጎል ማስቆጠር የተቸገረንበት ምክንያት የተጋጣሚያችን የተከላካይ ክፍል ጠንካራ መሆን እንደ ዋንኛ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡›› ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ለአዲስ አበባ መግለጫ የሰጡት ዋና አሰልጣኙ በኃላፊነታቸው ዙሪያ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ውጤት አምጥቻለው፡፡ የተሻለ ውጤት እስካመጣሁ ድረስ ከሃላፊነት አለቅም፡፡ ከዚህም በፊት የምለቀው ካለፈው የተሻለ ነገር ካላመጣው እንደሆነ ተናግሬያለሁ፡፡ ፌደሬሽኑ ያስቀመጠልኝ ግብ ለቻን ቡድኑን እንዳሳልፍ ነበር፡፡ እኔም ፌደሬሽኑ ያለኝን አድርጌያለው፡፡ ነገር ግን ቻን ላይ ባስመዘገብነው ውጤት አልረካውም። ከዚህ የተሻለ ነገር ብናመጣ ከዚህ የበለጠ እደሰት ነበር፡፡ በውድድሩ ያሉኝን ተጨዋቾች ለማሳየት ጥሬያለው ደግሞም ተጠቅሜበታለው፡፡” በማለትም በሃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በ2018 እና በ2020 እኤአ የሚካሄዱትን ሁለት የቻን ሻምፒዮናዎች አከታትላ እንድታስተናግድ መጠየቁን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እየገለፁ ቢሆንም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በጉዳዩ ላይ መግለጫ አልሰጠም፡፡
በሩብ ፍፃሜው የጨዋታ ድልድል መሰረት ሩዋንዳ ከዲሪ ኮንጎ፤ ዛምቢያ ከጊኒ፤ ቱኒዚያ ከማሊ እንዲሁም ካሜሮን ከኮትዲቯር ይጫወታሉ፡፡  በሻምፒዮናው ከሩብ ፍፃሜው በፊት በተደረጉት 24 ጨዋታዎች 62 ጎሎች ከመረብ ሲዋሃዱ ሻምፒዮናው በአማካይ በአንድ ጨዋታ 2.58 ጎሎች የሚመዘገቡበት ሆኖ አዲስ ታሪክ ተብላል፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር የናይጄርያው ቺሶም ሲካትራና የቱኒዚያው አህመድ አካቺ በእኩል 4 ጎሎች ተያይዘዋል፡፡
ኮትዲቯር በ2009 እኤአ ባዘጋጀችው  1ኛው ቻን  በአጠቃላይ 30 ጎሎች የተቆጠሩበትና በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1.88 ጎሎች የተመዘገቡበት ሲሆን ዲ ሪ ኮንጎ ዋንጫውን ስትወስድ ጋና እና ዛምቢያ በ2ኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎች  ጨርሰዋል፡፡ በ2011 እኤአ ሱዳን አዘጋጅታው በነበረው 2ኛው ቻን በአጠቃላይ 59 ጎሎች የተቆጠሩበትና በአንድ ጨዋታ በአማካይ 1.84 ጎሎች ሲመዘገቡ ቱኒዚያ ሻምፒዮን ሆና አንጎላ እና ሱዳን በ2ኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎች  ጨርሰዋል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ 3ኛውን ቻን ስታስተናግድ በአጠቃላይ 73 ጎሎች የተቆጠሩበትና በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.28 ጎሎች ሲመዘገቡ  ሊቢያ ዋንጫውን ስትወስድ ጋና እና ናይጄርያ በ2ኛ እና ሶስተኛ ደረጃዎች  ጨርሰዋል፡፡
ዋና አሰልጣኙና ፌደሬሽኑ …
ዋና አሰልጣኙ ከቻን  ማግስት ለሶካ አፍሪካ በሰጡት አስተያየት ‹‹ በመጀመርያ ደረጃ ተጨዋቾቼ ለሰሩት ሁሉ አድናቆቴን መግለፅ እፈልጋለሁ። ከ52 አገራት መካከል ማጣርያውን አልፈው ምርጥ 16 ቡድኖች ተርታ መግባታቸው ይደነቃል፡፡ ብዙዎቹ ተጨዋቾች በኢንተርናሽናል ደረጃ ሲጫወቱ የመጀመርያቸው በመሆኑ ጥሩ ሰርተዋል ብዬ ነው የምረዳው፡፡ አንዳንዴ ተጨዋቾችን በየጊዜው መኮነን የለብንም፡፡ ለአህጉራዊ ውድድሮች በቂ ዝግጅት ያስፈልግ ነበር፡፡ በፌደሬሽኑ በኩልም  ተጨዋቾቹ ዝም ብለው ሜዳ ገብተው እንዲያሸንፉ መጠበቅ የለበትም፤ የበኩላቸውን እርዳታ ማድረግ ነበረባቸው፡፡  ከቻን  ቡድኖች አንዳንዶቹ ከወር በላይ ተዘጋጅተዋል፤ በቂ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎችንም አድርገዋል፡፡  የእኛ ዝግጅት 9 ቀናትና 1 የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ብቻ ነበር፡፡ ›› በማለት በምሬት ተናግረዋል፡፡ በቻን  ተሳትፎ ከቡድናቸው ጋር በርካታ ልምዶች መቅሰማቸውን የተናገሩት አሰልጣኙ በመጋቢት ወር ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ግጥሚያዎች የሚያግዝ እንደሆነ ገልፀው ፤ ቡድናቸው ለአፍሪካ ዋንጫ እና ሌሎች ውድድሮች ማጣርያዎችን በማለፍ የመሳተፍ አቅም እንዳለውም አሳስበዋል፡፡ ‹‹ጥሩ ቡድን አለን፤ አቋማችን ሳይዋዥቅ መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ከቻን ያገኘነው አንድ ትልቅ ትምህርት በሻምፒዮንሺፕ የመጀመርያ ጨዋታን በጥሩ ውጤት ለመጀመር መጣር እንዳለብን ነው፡፡  በዲ.ሪ ኮንጎው ጨዋታ ቢያንስ 1 ነጥብ ብናገኝ ኖሮ የተሻለ ይሆን ነበር›› ሲሉም የ52 ዓመቱ ዮሃንስ ሳህሌ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዋልያዎቹ በተከታታይ በሁለት ቻን መሳተፋቸው ማረጋገጣቸው አንዱ በጎ ተመክሮ ሲሆን ማጣርያውን አልፈው በ4ኛው ቻን የተሳተፉበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ውጤት ነው። ዋልያዎቹ  በ2014 እኤአ ላይ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 3ኛው ቻን በሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ከምድብ ሲሰናበቱ በ3 ጨዋታዎች አንድም ግብ አላስቆጠሩም ነበር፡፡ በ4 የግብ እዳና ያለምንም ነጥብ የምድባቸውን የመጨረሻ ደረጃ ይዘው  ሽልማታቸው 100ሺ ዶላር ነበር፡፡ በ4ኛው ቻን  ላይ ዋና አሰልጣኙ ካለፈው የቻን ተሳትፎ አንፃር አዳዲስ ታሪኮች በተሳትፏቸው እንደሚያስመዘግቡ ቢጠበቅ ይቻላል፡፡ አሰልጣኙም ሩብ ፍፃሜ ለመግባት እንደሚፈልጉ እና የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን እንደሚቀይሩ ገልፀው ነበር፡፡   በምድብ 2 ባደረጓቸው ጨዋታዎች ግን የተጠበቀውን ያህል ውጤት ሳያስመዘግቡ ቀርተዋል፡፡   በምድባቸው የመጨረሻ ጨዋታ የገጠማቸው ሽንፈት ሳቢያ ካለፈው 3ኛው ቻን አንፃር ሁለት አዳዲስ ታሪኮች የሚያስመዘግቡበት እድላቸውም ተበላሽቶባቸዋል፡፡ ከአንጎላ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሽንፈት ባይገጥማቸው ኖሮ በምድባቸው 3ኛ ደረጃ ይዘው ለመጨረስ እና 125ሺ ዶላር የመሸለም  እድሎች ነበራቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን  የመጀመርያውን የቻን 1 ነጥብ ማስመዝገባቸውና 1 የቻን ጎል ለመጀመርያ ጊዜ ማስቆጠራቸው ግን አዳዲስ ታሪኮች ሆኖ ይመዘገብላቸዋል፡፡ ምድባቸውን በ1 ነጥብ እና በአራት የግብ እዳ በአራተኛ ደረጃ ስላጠናቀቁም  100ሺ ዶላር ያገኛሉ፡፡
የቅጥር ውሉ መጨረሻ
ከ4ኛው ቻን በኋላ በዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የስራ ዘመን  በፉትቦል ዳታቤዝ ድረገፅ የቀረቡ አሃዛዊ ስሌቶች የቡድኑን ውጤት አልባነት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ባለፈው 1 ዓወት  ብሄራዊ ቡድኑ በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በ5 አሸንፎ በ6 አቻ በመውጣት በሰባት ተሸንፏል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ   16 ጨዋታዎች  አድርገው  የተሳካላቸው 36 በመቶ  ነው፡፡
ዋና አሰልጣኙ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመርጠው ስራቸውን ከጀመሩ 10 ወራት ተቆጥረዋል፡፡   የቅጥር ውሉ መጨረሻ እ.ኤ.አ. በ2017 ጋቦን በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ዋሊያዎቹ ከተደለደሉበት ምድብ 10 ከስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ውስጥ ወደ ዋናው ውድደድር ለማለፍ የሚያስላቸውን ነጥብ በማግኘት የ31ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊነታቸውን በማረጋጋጥ ላይ ይመሰረታል፡፡ ውሉ በቻን 2016 እና በሴካፋ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ውድድሮችም አመርቂ ውጤት የሚጠብቅ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እ.ኤ.አ በ2017  ጋቦን በምታስተናገደው 31ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ ተካፋይ ለመሆን ከቻለ የአሰልጣኝ ዮሐንስ የስራ ዘመን  ይቆያል ተብሎ መገለፁ አይዘነጋም፡፡
 የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዋልያዎቹን የሴካፋ እና የቻን ውጤት አለመሳካት ከግምት ውስጥ ያስገባ ግምገማ አለማድረጉ የሚያሳስብ ሲሆን፤ በ2017 እኤአ ጋቦን ለምታስተናግደው 31ኛው  የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሳተፉ መጠበቁ የሚያስተማምን አይደለም። ምድባቸውን በመሪነት አጠናቅቀው ማለፋቸው  የእቅዱ መነሻ ቢሆንም ተግባራዊነቱ አጠያያቂ የሚሆን ነው። ፌደሬሽኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ከአልጄርያ የሚገጥመውን ከባድ ፉክክር ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረበት፡፡ ዋልያዎቹ  በምርጥ ሁለተኛ ደረጃ ለማለፍ  ለሚችሉበት ሁኔታ  በምድብ ማጣርያው የቀሯቸውን 4 ጨዋታዎች በሜዳቸው ሆነ ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ከሌሶቶ እና ከሲሸልስ ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ ከ2 ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በኋላ አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ ዋልያዎቹ በ4 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ እየተከተሉ ናቸው፡፡ ለማለፍ ሰፊ እድል ያላት አልጄርያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ከአልጄርያ ጋር ከሜዳው ውጭና በሜዳው፤ ከሌሶቶ ጋር ከሜዳው ውጭ እንዲሁም ከሲሸልስ ጋር በሜዳው ይጫወታል፡፡ የምድቡን መሪነት በማግኘት በአፍሪካ ዋንጫው ቀጥታ ተሳትፎ ለማሳካት ዋልያዎቹ በተለይ በአራቱ ጨዋታዎች መሸነፍ የለባቸውም፡፡ በተለይ ከአልጄርያ ጋር በሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ነጥብ መውሰድ ከቻሉ ተስፋ ይኖራቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄርያ አቻው ጋር በታሪክ በ6 ጨዋታዎች ተገናኝቷል። 1 ድል፤ 2 አቻ ሶስት ሽንፈትም አስተናግዷል፡፡ ምድቡን በመሪነት መጨረስ ካልሆነለት ቡድኑ  ማለፍ የሚችለው በምርጥ ሁለተኛነት ከጨረሰ ነው፡፡ ከ14 ምድቦች በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ ሁለት አገራት እድል ይኖራቸዋል፡፡ በምድብ ማጣርያው የሁለት ዙር ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ በሚቻልበት እድል ኢትዮጰያ በሶስተኛ ደረጃ ተመሳሳይ ውጤት ካላቸው የምድብ 4 ዛምቢያ እና የምድብ 12 ዚምባቡዌ ጋር አሰልፏታል፡፡ በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ በምድብ 6 የምተገኘው ሞሮኮ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ እንዲሁም በምድብ 7 የምትገኘው ናይጄርያ በ4 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ይገኛሉ፡፡
2 የቻን መስተንግዶዎች
አህጉራዊ የስፖርት መድረክ ማዘጋጀት በጥቅሉ ከፍተኛ ገፅታ ግንባታ እና ትኩረት የሚያስገኝ ቢሆንም በማርኬቲንግ እንቅስቃሴዎች ትርፋማ መሆን  ወሳኝ ነው፡፡ በርግጥ የቻን ውድድር ለአገር በቀል ተጨዋቾች በሚፈጥረው ከፍተኛ የውድድር መድረክ እንደ ኢትዮጵያ አገራት ተጨማሪ ጠቀሜታዎችንም ሊያገኙበት ይችላሉ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለቻን ውድድር ብዙ ስፖንሰሮች ባለማግኘቱ ትርፋማ ሊሆንበት አልቻለም፡፡
ኬንያ በ2018 እኤአ ላይ 5ኛውን ቻን እንድታዘጋጅ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የወሰነው በ2014 እኤአ ቢሆንም የአገሬው ስፖርት ሚዲያዎች ይህ የመስተንግዶ እድል እንደማይሳካ እየገለፁ ናቸው፡፡ ሶካ አፍሪካ ከሰሞኑ የ5ኛው ቻን መስተንግዶ ከኬንያ ተነጥቆ ለኢትዮጰያ ሊሰጥ እንደሚችል በሚገልፅ ዘገባው፤ ኬንያ ቀጣዩን ሻምፒዮና ለማዘጋጀት የሚያስችል ምንም አይነት አቅም እና ዝግጁነት ስለማይኖራት  የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ስጋት መግባቱን አትቷል፡፡ በተለይ የኬንያ ስታድዬሞች እስከ 2018 እኤአ ድረስ ብቁ ሆነው ቻንን ለማካሄድ  የማይሆን ነው በሚል አረጋግጧል፡፡ ኬንያ በመላው አገሪቱ ካሏት 10 ስታድዬሞች በተለይ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኙት የናይሪቢ ከተማ ብሄራዊ፤ የናያዮ ፤ የኪሳራኒ የሞይ ማእከል አራት ስታድዬሞች አህጉራዊ ሻምፒዮናውን የማስተናገድ ብቃት ቢኖራቸውም አስፈላጊዎቹ መሰረተልማቶች የተጓደሉ መሆናቸው ካፍን ጥርጣሬ ፈጥሮበታል፡፡ የኬንያ መንግስት በካፍ ስጋት ላይ ትኩረት የሰጠ መግለጫ ካልሰጠ በቀር ውሳኔው ሊፀና እንደሚችል እየተነገረ ነው። ኬንያ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ የሚያስፈልጋት እስከ 500 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግም ለማግኘት እንደምትቸገር ዘገባዎች ጠቅሰዋል፡፡  ስለዚህም በ2020 እኤአ ላይ 6ኛውን ቻን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ኢትዮጵያ የኬንያውን 5ኛው ቻን መስተንግዶ ተረክባ እንድታስተናግድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ፍላጎቱን በይፋ አመልክቷል፡፡ በ2020 እኤአ ላይ እንድታስተናግድ የተመረጠችውን 6ኛውን ቻንም ሌላ ምትክ አዘጋጅ ከመፈለግ እንድታስተተናግደው ሃሳብ መኖሩም እየተገለፀ ነው፡፡  በአገሪቱ የተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙት እና ከ30 እስከ 50ሺ ተመልካች የማስተናገድ ብቃት ያላቸው ስታድዬሞች በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ሙሉ ለሙሉ በተሟላ ብቃት አገልግሎት ሊሰጡ መቻላቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን የማረከው ሲሆን በቅርቡ የተስተናገደው የሴካፋ ሻምፒዮና ስኬትም እገዛ ፈጥሯል፡፡ የሴካፋ ምክር ቤትም በኢትዮጵያ መስተንግዶ መተማመመኑን እያስገነዘበ ነው፡፡

Read 2271 times