Saturday, 06 February 2016 10:57

ጦማርያኑ ለተጠየቀባቸው ይግባኝ ምላሽ ሰጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   በአቃቤ ህግ ይግባኝ የተጠየቀባቸው የዞን 9 ጦማሪያን፣ በቀረበባቸው አቤቱታ ላይ ትናንት ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቀደም ሲል አቃቤ ህግ፣ ለከፍተኛው ፍ/ቤት በተከሳሾቹ ላይ ያቀረባቸው ማስረጃዎች በአግባቡ ታይተው አልተመዘኑልኝም በሚል የጠቅላይ ፍ/ቤቱ እንደገና እንዲመለከትለት አቤቱታውን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በአቃቤ ህግ አቤቱታ ላይ ጦማሪያኑ ምላሽ እንዲሰጡ ፍ/ቤቱ ለትናንት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በቀጠሮው መሰረትም ጦማሪያኑ በጠበቃቸው አማካይነት ትላንት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቃቤ ህግ፤ በከፍተኛው ፍ/ቤት ክሱን እንዲያሻሽል በተደጋጋሚ እድል እንደተሰጠው ያስታወሱት ተከሳሾች፤ ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግላቸው  ጠይቀዋል፡፡
የጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ጠበቃ ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ጦማሪው በስር ፍ/ቤት በወንጀል ክስ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ጦማሪው በሁለት ቦታ ክስ ሊቀርብበት አይገባም ብሏል፡፡
ፍ/ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 20 ቀጠሮ ይዟል፡፡
ቀደም ሲል ከፍተኛው ፍ/ቤት በነፃ ያሠናበታቸውና አቃቤ ህግ ይግባኝ የጠየቀባቸው የዞን 9 ጦማሪያን ሶሊያና ሽመልስ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀና ማህሌት ፋንታሁን ሲሆኑ በፍቃዱ ሃይሉ የሽብር ክሱ ወደ ወንጀል ክስ ዞሮ እንዲከራከር መወሰኑ ይታወሳል፡፡

Read 3300 times