Saturday, 06 February 2016 11:05

‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ …’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(18 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እነኚህ ‘አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው’ …ብለው የሚለጥፉ ትምህርት ቤቶች አሁንም አሉ ወይስ…እንዴት ነው ነገሩ!
የምር ግን… አለ አይደል… እንግሊዝኛም ሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ማወቅ አሪፍ ነው፡፡ በኢንተርኔት ዘመን ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ማወቁም ሆነ መሞከሩ አሪፍ ነው፡፡ (የቻይኖቹን ‘ማንዳሪን’ ነው ምናምን የሚሉትን ጨምሮ ማለት ይቻላል…ቂ…ቂ…ቂ…) ግን ‘የፈረንጅ አፍ’ ማወቅና…አለ አይደል…‘የቅኝ ተገዥነት እርግማን’ ማዶ ለማዶ ናቸው፡፡ ‘የፈረንጅ አፍ’ ማወቅ ሌላ፣ ፈረንጅ ሲያዩ ጠብ እርግፍ ማለት፣ “እንደ ኮብል ስቶን ልነጠፍልህ ወይ…” ምናምን አይነት መሽቆጥቆጥ፣ ሠላሳ ሁለት ጥርስን ወደ ሀምሳ ስድስት ማብዛት…ሌላ!
የምር ግን… “እንግዳ ተቀባዮች ነን…” ምናምን የምንለው ነገር አለ አይደል! አዎ…“የመሸብኝ የእግዚአብሔር መንገደኛ አሳድሩኝ…” ያለ የማይታወቅ፣ የዳር አገር ሰው ምግብና መኝታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን እግሩ ታጥቦ “በሰላም ያሳድርህ…” የሚባልበት ዘመን ነበር፡፡ “አሳድሩኝ…”  ተብሎ ከበር ላይ… “ማደሪያህን ፈልግ…” ብሎ ማባረር ይቅርታ የሌለው ኃጢአት አይነት ነገር ነበር።
ዘንድሮ…ያ ሁሉ በአብዛኛው ጠፍቷል፡፡
እግረ መንገዴን… ያልተሰነጠቀች ሳህን፡ ያልተሸረፈች ስኒ ምናምን “እሱ ለእንግዳ ነው…” በሚባልበት ህብረተሰብ ውስጥ ነው የኖርነው፡፡ ቤታችን የሆነ ያልተሟላ ነገር ካለ… የምንለውጠው ወይም የምናሻሽለው…“ይሄ ነገር ደስ አላለኝም…” በሚል የራሳችንን ስሜት መሠረት አድርገን ሳይሆን…አለ አይደል… “ሰው ቢመጣ ምን ይላል!” በሚል ነው፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ የምናከብረው እንግዳ…አለ አይደል…‘የአገር ልጅ ዘው፣ ዘው’ ሳይሆን…ፈረንጅ ሆኗል፡፡ ‘የፈረንጅ’ የሆነ ነገር ሁሉ የእኛ ለማድረግ፣ ‘ፈረንጅ’ ለመሆን፣ ‘ፈረንጅ’ን ደስ ለማሰኘት መከራችንን እያየን ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንዳንድ መሥሪያ ቤቶችንና፣ ህንጻዎችን ነገሬ ብላችሁልኛል…እኛ፣ እኛ ‘የአገር ተወላጆቹ’ (ኪሳችን ዶላርና ፓውንድ ሳይሆን ብሪቱ ብቻ የምትገኘውን…ያውም ከተገኘች!) ስንገባ ኪሳችን በመጸዳጃ ወረቀት እንኳን አበጥ ካለ ‘ተበጥረን’ እንፈተሻለን፡፡ እሺ ይሁን…በዚህ በሉሲፈር ዘመን ጠንቅቅ ማለቱ አሪፍ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር ግን ምን መሰላችሁ…በዛው በር ‘ፈረንጅ’ በትከሻ የሚነገብ ሮኬት መክተት የሚችል ሩብ ኩንታል የሚሆን ቦርሳ አንጠልጠሎ ሲገባ እጅ ተነስቶለት ዝንቡ ‘እሽ’ ሳትባል ያልፋል፡፡ እናማ… “ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ…” ብለን በምንኮራባት አገር… ‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ’ እየሰፈረብን ይመስላል፡፡
የአገሩ ምግብ ቤት ሁሉ መጠሪያውን የአውሮፓ አገራትን ከተሞች እያደረገ ነው፡፡ (ስሙኝማ…የአውሮፓ ህብረት አባል አለመሆናችን አይቆጫችሁም! ቂ…ቂ…ቂ…)
ደግሞላችሁ… ኦፊሴላዊ ቋንቋ ሁሉ ‘የፈረንጅ አፍ’ እየተቀላቀለበት “እውን አቻ የአገር ቋንቋ ጠፍቶ ነው!” ያሰኛችኋል፡፡ ልክ ነዋ…በፊት እኮ “አት ሊስት…” ምናምን የምትል ሁሉም የሚያውቃት የምትመስል ‘የፈረንጅ አፍ’ ነበረች፡፡ የምር ግን… ‘ትራንስፎርሜሽን’ የሚለውን ትርጉም ስንቱ ያውቀዋል? ‘ክለስተር፣’ ‘ዳይሬክቶሬት’’…ምናምን የሚሉ ‘የፈረንጅ’ ቃሎችን ስንቱ ያውቃቸዋል?
እናማ… “ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ…” ብለን በምንኮራባት አገር… ‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ’ እየሰፈረብን ይመስላል፡፡
ስሙኝማ…እዚህ ቸርችል መጀመሪያው የትራፊክ መብራት ላይ ቀይ የመንገደኛ መብራት ሲበራ እንዳንሻገር ቀኑን ሙሉ ስትናገር የምትውል አለች፡፡ አሁን ደግሞ ለገሀር ጫፍ ያለው ትራፊክ መብራት ላይም እየሰማነው ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር አሪፍ ነው፡፡ እግረኞች ለመኪኖች ‘ትከሻችንን እያሳየን’ “አጠገቤ ድርሽ ትልና…” በሚል አይነት እየተግተለተልን መንገድ ውስጥ በምንገባበት ዘመን እንዲሀ አይነት ማሳሰቢያዎች አሪፍ ናቸው፡፡ ትራፊክ መብራቶች ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ቢኖሩ አሪፍ ነው፡፡
ኮሚኩ ነገር ግን ምን መሰላችሁ…የማሳሰቢያው ሁለተኛ ቋንቋ ሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ ሳይሆን ‘የፈረንጅ አፍ’ መሆኑ ነው፡፡ ‘የፈረንጅ አፍ!’
እናላችሁ… “ኢት ኢዝ ኤ ፔዴስትርያን ሬድ ላይት፣ ዶንት ፓስ’  እናባላለን፡፡ ታዲያላችሁ… እንደ እግረኛነታችን ፈረንጅ ቆሞ ሲያዳምጥ አይተን አናውቅም፣ ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን በዛ ቦታ ቀኑን ሙሉ አምስት መቶ የአገር ልጅ አልፎ እንደሁ አምስት ፈረንጅ ላያልፍ ይችላል፡፡ ከአምስት መቶው የአገር ልጅ ሁለት መቶው አማርኛ ላያውቅ ይችላል። እና ስንት ሊነገርባቸው የሚገቡ የአገር ቋንቋዎች እያሉ ‘የፈረንጅ አፍ!’…ነው ወይስ ‘መልካም ገጽታ ግንባታ’ መሆኑ ነው!
ደግሞ…ዓለም አቀፍ ጨረታም ወጥቶ ይሁን በሆነ መንገድ ራሷ ‘የፈረንጅ አፏ’ ዓረፍተ ነገር ሙሉ ‘ጤንነት’ ይመርመርልንማ!
እናማ… “ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ…” ብለን በምንኮራባት አገር… ‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ’ እየሰፈረብን ይመስላል፡፡
እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አለቆች በጽሁፍ መልእክት በ ‹ፈረንጅ አፍ› የሚልኩትን  “እንኳን አደረሳችሁ...” ወይ “እንኳን ደስ አላችሁ…” ትመለከቱና…አለ አይደል…ለምን የአለቆችን ‘የፈረንጅ አፍ’ የሚያሳምር ‘ኮንስልታንት’ እንደማይቀጥሩ ግራ ይገባችኋል፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… “ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ…” ብለን በምንኮራባት አገር… ‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ’ እየሰፈረብን ይመስላል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ሌኒን ‘ፈረንጅ’ አይደለም እንዴ! ልክ ነዋ…በሌሎቹ ፈረንጆች ስም የተሰየሙ አደባባዮች፡ መንገዶች ምናምን… ምንም ሳይባሉ የእሱ ሀውልት መፍረሱ ‘ፌይር’ አይደለማ! ከፈረንጅ ፈረንጅ ቢለዩ ምናምን ተብሎ እንዳይተረትብና! ቂ…ቂ…ቂ…
ፑሽኪን በስሙ አሪፍ አደባባይ አለው፡፡ ገና ለገና “የእኛ ደም አለበት…” ተብሎ ከስንት መቶ ዓመታት በፊት ለነበረው ፑሽኪን ሀውልት ስናቆም የእሱን ስንት እጥፍ የሚገባቸው የራሳችን የስነ ጥበብ ሰዎች የሉም ማለት ነው!
እኔ የምለው…የእሱ ሰውዬ ዘር ማንዘሮች ከእኛ ጋር ስላላቸው ‘ዝምድና’ የማይጠየቁልንሳ!
ስሙኝማ…ኦባማ ቸርችል ወረድ ብሎ በስማቸው ካፌ አለቻቸው፣ ሳኒ አባቻም ወደ አጠና ተራ አካባቢ የሜካኒክ ቤት …ምናምን ነበራቸው! ዕድለኛ ማለት እሳቸውን!    ቸርችል ምን የሚያክል ሰፊ መንገድ በስማቸው አላቸው፡፡ እነ ዌዘረል፣ ካኒነግሀም፣ ኮልሰን ምናምን የተባሉት ‘ፈረንጆች’ በስማቸው መንገድ ምናምን አላቸው፡፡ እንግሊዝም ቢሆን በጦርነቱ መጀመሪያ አሳልፎ ሰጥቶን በኋላም ‘ያገዘን’ መጠቃታችን ‘አንገብግቦት’ ሳይሆን በአካባቢው የራሱን ጥቅም ለመጠበቅ እንደነበር የታሪክ ጸሀፍት ይነግሩናል። እንደውም ቅኝ ለማድረግም ዳር፣ ዳር ብሏቸው የተዉት ባይሳካ ነው፡፡ ከሌላ ሌላው አስገራሚ ድርጊቶቻቸው ሌላ (ለምሳሌ ነቅለው ሊወስዱት ያልቻሉትን ፋብሪካ፣ መሣሪያ መሰባበር የመሰለ…)
በብዙ መቶዎች የሚሆኑ የታሪክና ባህላዊ ቅርሶችን ጠራርገው ነው የሄዱት፡፡ መቼም እንዲህ አይነት ወዳጅነት የለም! እናማ…በእነሱ ስም የተሰየሙት መንገዶችም ሆኑ አደባባዮች እንዳሉ ሆነው በቀድሞው ንጉሥ ስም የተሰየሙ ተቋማት ሳይቀሩ ስማቸው መለወጡ የሆነ የማይገጥም ነገር አለው፡፡
ቦብ ማርሊም ምን የመሰለ ሀውልት አለው፡፡ እሱና የሬጌ ወዳጆች የሚያመልኳቸው ንጉሥ ስም ግን በታሪክ ድርሳናት ካልሆነ ጠፍቷል፡፡
እናማ…በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ደረጃ ስለ ‘ፈረንጅ’ ሆነ ስለ ‘ፈረንጅ አፍ’ ያለን አቀራረብ…አለ አይደል…“ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ…” ብለን በምንኮራባት አገር… ‘የቅኝ ተገዥነት እርኩስ መንፈስ’ እየሰፈረብን ይመስላል፡፡ ከዚህ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6515 times