Saturday, 06 February 2016 11:16

የመጀመርያው ኢትዮ- ትሪአትሎን በላንጋኖ ተካሄደ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የኦሎምፒክ ርቀት እንዲያሟላ ታቅዷል
   የመጀመሪያ ኢትዮጵያ “የእስፕሪንት ትሪአትሎን” ውድድር ኢትዮ- ትሪአትሎን በሚል ስያሜ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ላንጋኖ ሳቫና የሀይቅ ዳርቻ ሪዞርት አካባቢ በተሳካ መልኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማካሄዱን አስታወቀ፡፡
ሪያ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት የተራራ ላይ ሩጫ በሚል ስያሜ በአይነቱ ልዩና አዝናኝ ውድድር እያዘጋጀ ነው፡፡  የስፖርት ቱሪዝምን ከአካባቢ ጥበቃ ስራ በማስተሳሰር የማስተዋወቅ እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን የማፍራት አላማ በማንገብም ይንቀሳቀሳል።
በአትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም የቦርድ ሰብሳቢነት የተመሠረተው ሪያ ኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝምን የማስፋፋት አላማውን ለማሳካት ጥረቱንም እንደሚቀጥል እየገለፀ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጐችና የሀገራችን ብርቅዬ አትሌቶች የተሳተፉበት ሁለት አመታዊ የተራራ ላይ ሩጫዎችን አካሂዷል ። የቱሪስት መስህብና መዳረሻ በሆኑት አብያታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርቲ እንዲሁም ወንጪ ሀይቅ ላይ ስኬታማ በሆኑ መልኩ ማስተዋወቅም ችሏል፡፡
‹‹እስፕሪንት- ትሪአትሎን›› ሶስት የውድድር አይነቶችን ዋና፣ ብስክሌት እና ሩጫን በአንድ ላይ በማጣመር የሚካሄድ ሲሆን አለምአቀፍ ይዘት ያለው ውድድር ለማዘጋጀት መቻሉን ሪያ ኢትዮጵያ  አስታውቋል፡፡ የሸፈኑት የውድድር ርቀትም 750 ሜ. የሀይቅ ላይ ዋና፣ 20 ኪ.ሜ፣ ብስክሌት እና 5ኪሜ ሩጫ ነው፡፡ የውድድሩ አንድ አካል በነበሩት የህጻናት ምድብም በሁለት የእድሜ እርከን ከ7-10 እና ከ11-14 ተከፍሎ በድምሩ 33 ህጻናት የተገኙበት ነው፡፡ /13 በቡድን 13 በነጠላ/ በመሆን ውድድራቸውን ያካሄዱ ሲሆን የውድድሮቹ ርቀትም በእድሜ እርከን ልዩነት ከ7-10 ላሉት 100 ሜ የሀይቅ ላይ ዋና፣ 1.5 ኪ.ሜ ብስክሌት እና 750 ሜ. ሩጫ ሲሆን ከ11-14 ለሆኑት ደግሞ 200 ሜ የሀይቅ ላይ ዋና፣ 6 ኪ.ሜ ብስክሌት እና 3 ኪ.ሜ ሩጫ ነበር፡፡
ሪያ ኢትዮጵያ ባካሄደው በዚህ ውድድር ላይ 130 ተሳታፊዎች በተለያየ የእድሜ እርከን በሁለቱም ጾታ የተካፈሉ ሲሆን 90 ፐርሰንት የሚሆኑት የውጪ ሀገር ዜጐች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡
ሪያ ኢትዮጵያ በቀጣይም ይህ በሀገራችን ልዩ የሆነውን የትሪአትሎን ውድድር አጠናክሮ በመቀጠል በቋሚነት በአመት አንድ ጊዜ በተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችና ለውድድሩ አመቺ በሆኑ ቦታዎች ላይ ለማካድ እንደሚሠራ አመልክቷል፡፡ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመስራት የኦሎምፒክ ርቀትንና ደረጃ ለማሟላትም ታቅዷል፡፡

Read 1933 times