Saturday, 06 February 2016 11:32

ባለሙያዎችና ተመልካቾች - ስለቴሌቪዥን ድራማዎች ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “ችግራቸው የቅርፅና የይዘት ነው”
(ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
 እኔ በግሌ የቲቪ ድራማዎች በዝተዋል ብዬ አላምንም፡፡ እዚህ ጎረቤት ኬንያ፣ በቀን 4 ተከታታይ ድራማ ይታያል፡፡ በMBC 2 አረብ ሳት፣ ቀንና ሌሊት ፊልም ነው የሚታየው፡፡ በሳምንት አንድ ድራማ ብቻ ይታይ ከነበረበት ጊዜ አንጻር ካየነው ጥሩ ነው፡፡ አዎንታዊ ጎኑ  በዋናነት፣ሰዎች አማራጭ የሚያዩት ነገር እንዲኖራቸው ማድረጉ ነው፡፡ አንድ ድራማ ብቻ በነበረ ወቅት ምርጫ የለም፤ መጥፎም ሆነ ጥሩ ያንኑ ማየት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ለተከታታይ ድራማ እድገት በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ እንግዲህ ብዛት ይቀድማል፤ጥራት የሚመጣው ዘግይቶ ነው፡፡ አሉታዊ ጎኑ ብዙ ሲሆኑ ተመሳሳይነትና ተደጋጋሚነት ይኖራቸዋል፤ በዚህም ተመልካቹን የማሰልቸት ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡  
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
እንግዲህ እንደነገርኩሽ በዙ ሲባል ያስቀኛል፡፡ የሚታየው ነገር ጥራት ቢኖረው እኮ ችግር የለውም፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የቅርፅና የይዘት ነው፡፡ በድራማዎቹ ምንድን ነው እየተላለፈ ያለው መልእክት? ጥልቀትና ብስለት አለው ወይ? ግልብ ነገር መስራት የትም አያደርስም፡፡ እና በይዘትም በቅርፅም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ  የተሻሉ ስራዎች ይኖራሉ፡፡  
በድራማዎቹ መካከል --- ተወዳጅ ለመሆን እርስ በርስ የመፎካከር ነገር ይታያል?
 ገና አልተጀመረም፤ፉክክር የሚጀምረው ጥራት ሲመጣ ነው፡፡ ምናልባትም በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት አሪፍ ስራዎችን ልናይ እንችላለን፡፡ ጥሩ የድራማ አፃፃፍና ምርጥ ፕሮዳክሽኖች ይመጣሉ፡፡   
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
በአሁን ሰዓት የቴሌቪዥን ድራማ ገንዘብ ያስገኛል የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ፕሮዲዩሰሮች ተበራክተዋል። ያለአቅማቸው የማይችሉትን እየጎረሱ ነው፡፡ ለገንዘብ መስራት ሃጢያት አይደለም፡፡ ግን ብቃት ያስፈልጋል። ገንዘብ ላይ ያተኮረ፣ ስምና ዝናን ያማከለ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ብቃት የሌላቸው ዳይሬክተሮችና ፕሮዱዩሰሮች ይገጥሙሻል፡፡ እነዚህ ጥራት እያደገ ሲመጣ ከጨዋታ ውጭ ይሆናሉ፡፡
“አንዳንድ የቲቪ ድራማዎች አይመጥኑም”
(ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
አዎንታዊ ጎኑ ሁልጊዜ ከብዛት ጥራት ይገኛል፡፡ ሰዎች ከጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ከድክመትም ይማራሉ፡፡ ብዙ ጠንካሮች እድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሆነ ነው አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡ የቴሌቪዥን ድራማ ገና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ዘርፍ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለልጆችና አዋቂዎች ተመሳሳይ ነገር ነው የሚቀርብላቸው፡፡ ለሁሉም አንድ ነው፡፡ እንደዚህ ያልጠራና ሁሉን ያላማከለ፣---- አቅጣጫ የሌለው ሲሆን ብዥታ ይፈጥራል፡፡
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
ምናልባት የኢቢሲ ኤዲቶሪያል ፖሊሲን መሰረት ተደርጎ ስለሚሰራ ይሆናል፡፡ የቲቪ ድራማዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና መሰል ጉዳዮችን እንዲፈትሹ ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን  በሳይኮሎጂ ህብረተሰቡን የማከምና ፆታዊ፣ማህበራዊና ሌሎች ጉዳዮችን መዳሰስ ይቻላል።  አንዳንዴ በድራማዎች መካከል መመሳሰል ሊከሰት ይችላል፡፡ ሆኖም አተያያቸውና የትኩረት አቅጣጫቸውም ሊመሳሰል አይችልም፡፡ አንዳንድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ድራማዎች ብቃታቸው ታይቶ ነው አየር ላይ የሚቀርቡት? የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በተለይ የተወሰኑት በህዝብ አይን፣ ጊዜ፣ አእምሮና ባህል ላይ እንደ መቀለድ የሚቆጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በጭራሽ ለቲቪ ድራማ የማይመጥን ሥራ እያየን ነው፡፡ ምስሉ ያብረቀረቀ ሁሉ ያምራል ማለት አይደለም፡፡ አሁን በሚሄድበት ሃዲድ ምን ያህል ይጓዛል የሚለው ያጠያይቃል፡፡
ከብዛታቸው አንፃር የቲቪ ድራማዎች ያለባቸው ተግዳሮት ምንድን ነው?
ሰው ለምሳሌ እያየሁ ያለሁት “መለከት” ነው “ዋዜማ” ሊል ይችላል፡፡ ሎጎውን እስኪመለከት ድረስ ኢቢኤስ ነው ኢቢሲ በሚል መደነጋገርም ይፈጠራል፡፡ ይህን የሚያመጣው የገፀ ባህሪያት መመሳሰል ነው፡፡ ደግነቱ የኛ ተመልካች ቶሎ የሚሰለች አይደለም፡፡ በጊዜ ሂደት ግን አዲስ ነገር መፈለጉ አይቀርም፤ካላገኘ የተሰራውን ባለመመልከት፣ በመዝጋት መቅጣት ይጀምራል። አማራጮች ሲያገኝ ወደ ማወዳደር ይገባል፡፡ ሰው እስኪሰለች ድረስ መጠበቅ ግን አይገባም፡፡ ድራማዎችና በጥራትና በሚመጥን መልኩ መስራት አለባቸው፡፡
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
የፊልሙ አካሄድ ወደ ቲቪ ድራማም እየመጣ ነው። ሰዎች ከፍለው ማፃፍ እየጀመሩ ነው፡፡ መኪናቸውን ሸጠው ወደዚህ ሥራ የሚገቡ አሉ፡፡ ታዲያ የተፃፈ ሁሉ ይታያል ማለት አይደለም፡፡ ገምጋሚው አካል ደረጃቸውን በጥራት ፈትሾ ማሳለፍ አለበት፡፡ ጥሩ ድራማ ከቀረበ እኮ የግዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ነጋዴው በሰልፍ ይመጣል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ግን ትውልዱ ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ልጆቻችን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አገራዊ ጉዳዮችን ለነሱ በሚመጥን መንገድ ተሰርቶ ማየት ካልቻሉ ልንለያይ ነው፡፡ እኔና ልጆቼ በጋራ ተቀምጠን የምናየው ፕሮግራም መሰራት አለበት፡፡ አሁን የእኔ ልጅ ሳይማር አረብኛ ይናገራል፡፡ በአገሩ ቴሌቪዥን ቋንቋና ባህሉን ማሳደግ ሲገባው፣ የአረብ ቻናል በማየት አረብኛ ችሏል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የሚመጥኑና ሁሉንም ያማከሉ፣ የጠሩ ስራዎች ሊቀርቡ ይገባል፡፡   
“ድራማ ለፅድቅ ልስራው የምትይው አይደለም;
(የፊልም ዳይሬክተር፤ ተስፋዬ ማሞ)
የቴሌቪዥን ድራማዎች አልበዙም? መበራከታቸው በጥበቡ ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖ ይኖራል?
መብዛታቸው አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ ተፅእኖ የለውም፡፡ መብዛት ችግር የለውም፡፡ ዋናው የበዙት ምን አይነቶቹ ናቸው የሚለው ነው፡፡ በተረፈ ብዙ መሆናቸው ውድድርና የእርስ በርስ ፉክክርን ያበረታታል፡፡
የቲቪ ድራማዎች አጠቃላይ ይዘታቸው ምን ይመስላል?
 የተጠና ነገር ሳይኖር በጅምላ መፈረጅ ይከብዳል። ግን የሚያስገርመው---- ስንት ዓመት ድራማ ስንሰራ ኖረን፣ገና ጀማሪ ስለሆንን፣ ሁሉም ይሞክር አይነት እየተባለ ነው፡፡ ይሄ “ጀማሪ ነኝ፣ ጀማሪ ነኝ” መቼ እንደሚቆም እግዜር ይወቀው፡፡ ብዙ ጊዜ ከድራማው ይልቅ ዝነኛ ሰዎችን፣ ታዋቂ ፊቶችን ---- ለማካተት ነው ትኩረት የሚሰጠው፡፡
ከብዛታቸው አንፃር የቲቪ ድራማዎች ያለባቸው ተግዳሮት ምንድን ነው?
ለምሳሌ በኢቢሲ እሁድ የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ሁለት ድራማ አይጠፋም፡፡ ድራማ ሲባል ለምን ረቡዕና እሁድ ብቻ እንደሚታሰብ አይገባኝም፡፡ በሌሎች ቀናት ለምን አይበተንም፡፡ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሲሆን ተመልካች ሳይወድ በግድ አንዱን ብቻ መርጦ እንዲመለከት ያደርገዋል፡፡ ወደፊት ቻናል እየበዛ ሲመጣ ደግሞ ውድድሩ በነሱ መካከል ይሆናል፡፡ ያኔ እኛም የተሻለ ነገር እናያለን፡፡
አንዳንድ ድራማዎች በስፖንሰርሺፕ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ታልመው ስለሚሰሩ ደረጃቸው የወረደ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ? …
 እንደሱ ብሎ መነሳት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ ገመናን ብናይ፣ገንዘብ የመሰብሰብ ሳይሆን በሙያ የማትረፍ አላማ ነበረው፡፡ ሰው ለሰውም እሱን ተከትሎ ስለመጣ፣ ከገመና የተሻለ ነገር ለማቅረብ በውድድር ስሜት በመሰራቱ፣ ጥሩ ነገር ለማየት ችለናል፡፡ አሁን አሁን  ሲጀመር ጥሩ ይሆንና በኋላ ጥድፊያ! በእርግጥ ድራማ ከፍተኛ ወጪ ያለው ስራ ነው፡፡ ለፅድቅ ልስራው የምትይው አይደለም፡፡ ግን እንደ ፊልሙ እየሆነ መጥቷል፤ ገንዘብ ስላለ ብቻ የሚገባበት፡፡
ገንዘብ ይዞ መምጣቱ ባልከፋ፤ግን የወጣውን ገንዘብ  ለመመለስ ሥራው ተወዳጅ መሆን አለበት፤ ያለበለዚያ ባለገንዘቡም ተመልካቹም አያተርፉበትም፡፡ እናም በተቻለ አቅም በባለሙያዎችና በጥራት መስራት ያስፈልጋል፡፡
*   *   *
“አማራጭ ከሌለሽ ያለውን ታያለሽ;
 “መብዛታቸው ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው!አሁን አማራጭ ስላለ የምትፈልጊውን ታያለሽ፡፡ `ለምሳሌ ”በቀደሙት ሳእታት ኢቲቪ ላይ Up”ßእሮብና እሁድ ነው ያለው፡፡ አማራጭ ከሌለሽ ያለውን ጠብቀሽ ታያለሽ፡፡ አሁን ላይ በእኩል ሰዓት ለምሳሌ እሮብን ብታይ ኢቢኤስ ላይም አለ፣ ኢቢሲ ላይም አለ፡፡ የመረጥሽውን መከታተል ትችያለሽ፡፡;
(ወጣት ቤተል:ሔም ባህሩ)
“የሚንዛዙ ድራማዎች አሉ”
 “መብዛታቸው መልካም ቢሆንም እየተንዛዙ ያሉ ድራማዎች ደግሞ አሉ፡፡ ለምሳሉ አንድ ሂደት ለማሳየት ረጅም ሰዓት የመውሰድ ነገር አለ፡፡ ያ ደግሞ ጥራቱን ያጓድላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለተመልካችም ያሰለቻል። ሌላው ለምሳሌ ኢቢኤስና ኢቢሲ በተመሳሳይ ሰዓት ድራማ ያሳያሉ፡፡ ይሄ ለማንም ጥሩ አይደለም፤ተናበው ቢሰሩ ይመረጣል”
 (አካሉ ጴጥሮስ)
“መብዛታቸው ምርጫ ሰጥቶኛል”
“የተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተከፍተዋል፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ በነሱ አማካኝነትም በርካታ ድራማዎች ይታያሉ፡፡
ምን ያህል ጥሩ ናቸው፣ አይደሉም የሚለውን ሙያዊ ትንታኔ ለመስጠት ይከብደኛል፡፡ ባለኝ እውቀትና እይታ ግን አብዛኞቹ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ትኩረታቸው ፍቅር ላይ ነው፤ መጨረሻቸውም ፍቅር ነው፡፡ ልክ ፊልም ላይ እንደምናየው /አሁን የተወሰኑ መሻሻሎች ቢኖሩም/ ሁሉም ፍቅር ላይ ነው፡፡ ሌሎች በፊልም፣ በድራማ፣ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ሥራዎች ቨማየት፣ የአገራችንን የድራማ፣ ፊልምና ቲያትር እድገት ራሳችን ማሻሻል መቀየር እንችላለን፡፡ ተመሳሳይ ናቸው፤- የፍቅር ታሪኩ አመጣጡና ድንበሩ ይለያይ እንጂ ከመፋቀር አይዘልም፡፡ መሻሻል አለበት እላለሁ፡፡ ሆኖም መብዛታቸው ምርጫ ሰጥቶኛል፤ በምመርጠው ቴሌቪዝን የፈለግሁትን ለማየት ችያለሁ”
(ሄለን አይችሉም)  
“እኔ መብዛታቸው ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ድሮ ትዝ የሚለኝ ፣ድራማ ሲኖር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ˜አንድ ብቻ ስለሆነ፤ ማታ እኮ እንትን ይታያል እል ነበር፡፡ አሁን ግን የመረጥኩትን ማየት አያለሁ፡፡”
(ትእግስት ወገኔ)

Read 3077 times