Saturday, 06 February 2016 11:34

ስምና ማንነት

Written by 
Rate this item
(27 votes)

 ከብዙ መነፋፈቅ በኋላ ካባቴ ታናሽ ወንድም፤ ካቶ አማረ በዳዳ ጋር ተገናኝተን አራት ኪሎ በሚገኘው ሮሚና ምግብ ቤት ምሳ በላን፡፡
አማረ ቢሏችሁ ቀላል ሰው እንዳይመስላችሁ፤ ከስድሳ ስድስት አብዮት ትንሽ ቀደም ብሎ በዩንቨርሲቲ ኮሌጅ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ በአብዮት ማግስት ዓመት በኢህአፓ አባልነት ተመልምሎ፣ በዚሁ ጦስ ተይዞ ዓለምበቃኝ አምስት ዓመት ታስሯል፡፡ እነ ማርታ ኩምሳ፣ ጌታቸው ኩምሳና ገነት ዘውዴ አብሮ ታሳሪዎቹ ነበሩ። ደራሲ ግርማይ አብርሃ በእሥር ቤት ማስታወሻው ላይ እንደጠቀሰው፤ አማረ በእሥር ቤት ቆይታው እሥረኞችን በነጻ የማስተማር አገልግሎት ከሚሰጡ ታራሚዎች አንዱ ነበር፡፡
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምርያ ያዲሳባ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አዲሳባ ዩኒቨርሲቲ በምማርበት ወቅት የሻይ መጠጫ የሚቆርጥልኝ አማረ ነበር፡፡
አባቴና አማረ ያንድ አባት ያንድ እናት ቢሆኑም በመልክና በእጣ ፈንታ የተለያዩ ነበሩ፡፡ አባቴ የቀይ ዳማ ሲሆን አማረ ክስል ያለ ጥቁር ነው፡፡ ወንድማማቾቹ የሚጋሩት አንድ ምልክት ቢኖር፣ ከጥቁር ጸጉራቸው ማኽል እንደባትሪ ቦግ ብሎ የሚታየው ሽበታቸው ነበር፡፡ ከአማረ በተቃራኒ አባቴ ለፖለቲካ ያለው ስሜት በጣም የቀዘቀዘ ነው፡፡ አማረ የቢሮ ሰው ሲሆን፣ አባቴ የተፈጥሮ ሰው ነው። ከትምህርት ቤት ውጭ ያለውን ጊዜውን ያሳለፈው ከልጆቹ የማያንስ ፍቅርና ጊዜ ለሚሰጣቸው የጓሮ አትክልቱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በድህረ ምሳ ጨዋታ ላይ የዘመዳ-ዝማድ ጉዳይ ስናነሳ ስንጥል ቆይተን ልንሰነባት ስንል፣
“እስቲ ያባቴን የትውልድ ሐረግ ጻፍና ስጠኝ” አልኩት፡፡
“ምን አሳሰበህ” አለኝ በዋዛ፡፡
“እንዴት አያሳስበኝ፤ አባታዊነትን የሚያጋንን ማኅበረሰብ አባል ነኝ፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩን ለመግለጽ “እንዲያው ምናባቴ ላርግህ” በሚልበት፤ ጠላቱ ክፉ እንደገጠመው ሲሰማ፣ “የታባቱ” ብሎ፣ በሚፈነጥዝበት ግራ ሲገባው፤ “ምናባቱ” እያለ በሚያጉተመትምበት ሀገር ውስጥ የምኖር ነኝ። አባት የነገሮች ሁሉ መስፈርያ ሆኖ የሚቀርብበት ማኅበረሰብ ውስጥ ስለአባቴ ማንነት ለማወቅ ብጥር ምን ይገርማል?”
በግርምት ለጥቂት ጊዜ አተኩሮ ሲያየኝ ከቆየ በኋላ ወደ መኪናው ውስጥ ይዞኝ ገባ፡፡ ከዚያ ከመኪና እረኛዋ (ከፓርኪንግ ሠራተኛዋ) እስክርቢቶ ተውሶ፣ በቢጫ ማስታወሻ ደብተሩ ውስጥ አንድ ቅጠል ገንጥሎ የሚከተለውን ጻፈልኝ፤
በዕውቀቱ ሥዩም - በዳዳ - ደስታ - ወየሳ
“ይሄው ነው?”
“እኔ የማውቀው እስከዚህ ድረስ ያለውን ነው፤ ሌላውን ደሞ የሁላችን ታላቅ የሆነችውን አበራሽን ጠይቃት”
ትንሽ አሰብ አድርጌ፤
“አባታችን አባቱ በዳዳ ተብሎ እንደሚጠራ ነፍስ ስናውቅ ጀምሮ ይነግረን ነበር፡፡ ግን በመሰለ ለምን እንደሚጠራ ጠይቀነው አናውቅም፡፡ ለምንድነው አባታችን በመሰለ የሚጠራው?  
አማረ ማብራራት ጀመረ፡፡
ምንጭ፡- (ከበዕውቀቱ ሥዩም
“ከአሜን ባሻገር”
አዲስ መፅሐፍ የተቀነጨበ፤ 2008 ዓ.ም)

Read 8400 times