Saturday, 06 February 2016 11:35

እኔ አውቅልሻለሁ

Written by  ደራሲ፡- ቻርሎቴ ፐርኪንስ ጊልማን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

 እንደ እኔና እንደ ጆን ያሉ ተራ ሰዎች የክረምት፣ የበጋ፣ የምናምን የሚባል ቤት የሚኖራቸው፣ እንዲህ አይነት ቅንጦት የሚጎበኛቸው እጅግ አልፎ አልፎ ነው፡፡ እኔና ጆን ለበጋው፣ ከትውልድ፣ ትውልድ ሲወራረስ በኖረ፣ የጥንት ቤት ውስጥ ልንኖርበት ሆነ፡፡
ቤቱ እጅግ የተንጣለለ ነው፡፡ እራሱን የቻለ ግዛት ነው፡፡ ትውልዶች ሲቀባበሉት የኖረ ነው፡፡ ሳስበው፣ ሳስበው በመናፍስት የሚጎበኝ ይመስለኛል። እንዲያም ሆኖ በጣም የሚወዱት አይነት ቤት ነው። ከዚህ በላይ መጠበቅ ወይም መጠየቅ የእድልን ወጪት እንደ መስበር ነው፡፡
ቤቱ እጅግ እንግዳ ነገር ነው፡፡
እንዲያ ካልሆነ ታዲያ ለምን እንዲህ በዘቀጠ ዋጋ ይከራያል? የኪራዩ ዋጋ እንዲህ ዝቅተኛ ሆኖም፣ ለምን ለረዥም ጊዜ የሚከራየው አጥቶ ባዶውን ተቀመጠ? እንዲህ ብዬ ባለቤቴ ጆንን ስጠይቀው ሳቀብኝ፡፡ ትዳር ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር ያለ እና የሚጠበቅ ይመስለኛል፡፡
ጆን እልም ያለ የተግባር ሰው ነው፡፡ ሥራ ላይ ሊውል፣  ወደ ድርጊት ሊመነዘር የሚችል ነገር ብቻ ነው የሚቀበለው፡፡ እምነት ለሚባል ነገር ይህቺን ታህል ቦታ የለውም፡፡ አጉል አምልኮ ለጉድ ይዘገንነዋል፡፡ ስለምንም ነገር ይወራ ብቻ፣ ነገርየው የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ የማይጨበጥና በአንድም ይሁን በሌላ መለኪያ የማይሰፈር፣ በቁጥር የማይገለፅ ከሆነ ያላግጣል፡፡ በግልጽ ያጣጥለዋል፡፡ የሹፈት ሳቁን ይስቃል፡፡
ጆን የህክምና ዶክተር ነው፤ (ይህቺን ለአንዲትም ሰው አልተነፍሳትም፤ ይህ ግን ወረቀት ነው፤ ሚስጢሬን ለማንም አይነግርም፤ በዚያም ላይ ሀሳቤን ገልጬ እፎይ እላለሁ፡፡) ምናልባትም ለዚያ ይሆናል ከህመሜ ቶሎ ያልዳንኩት፡፡
ታማለች ብሎ አያስብም፡፡
ምን ማድረግ ይቻላል?
እጅግ ጎበዝ የሆነ ዶክተር፣ ለዚያውም የእኔው፣ የእራሴው ባለቤት፣ ጓደኞቼንና ቤተ-ዘመዶቼን ሁላ ከጊዜያዊና አልፎ-ሂያጅ መደበትና ከእለታት አንድ ቀን ብቅ ከሚል መረበሽ ሌላ ምንም እንዳልሆንኩ፣ ምንም እንዳላመመኝ ካሳመናቸው ምን ማድረግ እችላለሁ?
ወንድሜም የህክምና ዶክተር ነው፤ ጎበዝ ለዚያውም፡፡ እሱም መታመሜን አይቀበልም፡፡
ፎስፌት ይሁን ፎስፋይት የሚሉትን ነገርና ቶኒክ እወስዳለሁ፡፡ የእግር ጉዞ አደርጋለሁ፡፡ አየርም ‘ታዞልኛል’፤ አየር እቀበላለሁ፡፡ እንቅስቃሴም አለ፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ፡፡ እስኪሻለኝ ድረስ ግን አንዳችም ‘ሥራ’ የሚባል ነገር እንዳልሰራ ተከልክያለሁ፡፡
በበኩሌ፣ ከአንዱም ሀሳባቸው ጋር አልስማማም። የምወደውን፣ የሚስማማኝን፣ የሚያነቃቃኝንና የማያሰለች ስራ ብሰራ ጤናዬ እንደሚሻሻል አምናለሁ፡፡ ግና ምን ማድረግ እችላለሁ? እነሱን ችላ ብዬ እፅፋለሁ፤ ይህም ስራ ሆኖ ለጉድ ያደክመኛል። ለምን ቢባል፣ ስፅፍ እነሱ እንዳያዩኝ አጉል ብልጥ መሆን ነበረብኝ፡፡ ካዩኝማ ቀውጢ ይፈጥራሉ፤ ለጉድ ይጻረሩኛል፡፡
ከሰዎች ጋር ብቀላቀል፣ ሥራ አትስሪ እያሉ መነዝነዛቸውን ቢተውኝና አንዳንድ አነቃቂ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ ጤናዬ እንደሚሻሻል እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንዲህ ማሰቡ ግን መቀናጣት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጆን እንዲያውም እንደ ሀጢአት ይቆጥረዋል፡፡ አሁን ባለሽበት ሁኔታ ልትፈፅሚ የምትችይው ከባዱ ስህተት ስላለሽበት ሁኔታ ማሰብ ነው ይላል፡፡ እንዲያ ሲል የበለጠ ያመኛል፡፡
ይህን ወዲያ ትቼ ስለ ቤቱ ማውጋት ይሻለኛል፡፡
እጅግ ውብ ስፍራ! ከአለም የተነጠለ ቦታ ነው። ከመኖሪያ መንደሮቹ ወደ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል፡፡ መፅሀፍት ላይ የምታነቧቸው የእንግሊዞችን ቤት ቁጭ ነው፡-ከውጪም ከውስጥም ብዙ ዛፎች አሉት፤ በረዣዥም አጥሮች ተቀጥሯል፤ በትልልቅ ቁልፎች የሚከረቸሙ ግዙፍ በሮች አሉት፤ ለአትክልተኛና ለሌሎችም ሰዎች ተነጣጥለው የተሰሩ ብዙ ትንንሽ ቤቶች አሉ፡፡
ወብ የአትክልት ስፍራ አለው! እንዲህ አይነት የአትክልት ስፍራ አይቼ አላውቅም፡፡ የተንጣለለ ነው፡፡ በጥላዎች ተሸፍኗል፡፡ ውስጥ ለውስጥ፣ ጠርዛቸው በቀጭን፣ በረዣዥም የሬክታንግል ጡቦች የተሰራ መንገዶች አሉት፡፡ የጡቦቹን መስመር ተከትለው፣ የተተከሉ የወይን ተክሎች አሉ፤ በእነሱም ጥላ ስር ወንበሮች ተቀምጠዋል፡፡ እጽዋት ማሳደጊያ የመስታወት ቤቶችም አሉ፡፡ ግን ሁሉም ተሰባብረዋል፡፡
በወራሾች መሀል የይገባኛል ክርክር የነበር ይመስለኛል፡፡ ለዚያም ሳይሆን አይቀርም ለብዙ አመታት ባዶውን የተተወው፡፡ እኔ፣ እራሴ መንፈስ ነው የምመስለው፤ ቤቱ ይህን ሳይሻማኝ አልቀረም። የሆነ እንግዳ ነገር አለው፡፡ እንዲሁ ይታወቀኛል፡፡
አንድ ምሽት፣ ለጆን፡- “ቤቱ አንዳች እንግዳ ነገር እንዳለው ይሰማኛል፡፡” ብዬ ነገርኩት፡፡ ጨረቃ ነበረች፡፡ የሚሰማሽ ብርድ ነው ብሎ መስኮቱን ዘጋው፡፡ አንዳንድ እለት በጆን እርር ድብን እላለሁ። የሚያናድድ ነገር ሳይኖር እኮ ነው፡፡ እንዲህ ቆዳዬ የሳሳ አልነበርኩም፡፡ ህመሙ ሳይሆን አይቀርም እንዲያ የሚያደርገኝ፡፡
ጆን እንዲያ ሲሰማሽ ስሜትሽን አትታገይው ይለኛል፡፡ ልቀቂው፡፡ እኔ ግን እንዲያ ሲሰማኝ ስሜቴን በጣም እታገለዋለሁ፤ በተለይ ጆን ካለ። ከስሜቴ ጋር የማደርገው ግብ ግብ ደግሞ ለጉድ ያደክመኛል፡፡ ያለንበት ክፍል ያስጠላኛል፡፡ እኔ መኖር የምፈልገው ልክ እኛ ካለንበት በታች ያለው ክፍል ውስጥ ነው። መስኮቱ በፅጌረዳዎች የተከበበ ሆኖ፣ የግቢውን መተላለፊያ መንገዶች ያሳያል፡፡ ግድግዳዎቹ ላይ የተሰቀሉት የድሮ ጊዜ ባለ ቀለምና በልዩ ልዩ ነገሮች የተጌጡ መጋረጃዎች እጅግ ያምራሉ!
ጆን ስለዚህ ሲወራ መስማት አይፈልግም፡፡  
ሲጀመር ገና አንድ መስኮት ብቻ ነው ያለው። እንደገናም ሁለት አልጋ አይችልም፡፡ በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ እሱ እንኳ ሌላ ክፍል ውስጥ ልሁን ቢል በቅርበት አንድም ክፍል የለም ይላል፡፡ በጣም ይጠነቀቅልኛል፡፡ በጣም ያፈቅረኛል፡፡ ያለ እሱ ልዩ ምክር ውልፍት እንድል አይፈልግም፡፡ በየእለቱ እያንዳንዷን ሰዓት እንዴት ማሳለፍ እንዳለብኝ እቅድ ነድፎ ሰጥቶኛል፡፡ እንደ እኔ ሆኖ እኔን ሊንከባከበኝ ሀላፊነቱን ከእኔ ወስዶ ተሸክሟል፡፡ የእኔ ‘እንደ-እራሴ’ ሆኗል፡፡ ይህን ያህል እየተጠነቀቀልኝ ምስጋና-አልባና ውለታ-ቢስ መሆኔ ዘልቆ ይሰማኛል፡፡
እዚህ የመጣነው ለእኔ ብቻ ተብሎ እንደሆነ ያስታውሰኛል፡፡ በቂ እረፍት ማድረግና  የተገኘውን ያህል አየር መውሰድ እንዳለብኝ ይነግረኛል። “የምታደርጊው እንቅስቃሴ ባለሽ ጥንካሬ ላይ ይወሰናል፤ የኔ ውድ፡፡” ይላል፡- “የምትወስጂው ምግብ ደግሞ ባለሽ የምግብ ፍላጎት ይወሰናል፤ ከሁሉ በላይ ግን የተገኘውን ያህል አየር፣ በሁሉም ሰዓት መውሰድ አለብሽ፡፡” በዚህ ስሌት የቤቱ የላይኛው ክፍል ውስጥ መኖር ያዝን፡፡
ክፍሉ ሰፊና ነፋሻማ ነው፡፡ በሁሉም በኩል መስኮቶች አሉት፡፡ አየርና የፀሀይ ብርሃን በሽ-በሽ ነው፡፡ በመጀመሪያ፡- የህፃናት መንከባከቢያ ክፍል ነበረ፡፡ ቀጥሎ፡- የህፃናት መጫወቻ ክፍል ተደረገ፡፡ ቀጥሎ፣ ቀጥሎ ደግሞ፡- ጂምናዚየም ሆነ። እንዲያ ይመስለኛል፡፡ መስኮቶቹ በሙሉ በብረት ዘንግ የታጠሩ ናቸው፡፡ ይህ የተደረገው ህጻናቶቹ እንዳይሾልኩና አደጋ እንዳይደርስባቸው መሆን አለበት፡፡
ክፍሉ ውስጥ ግድግዳው ላይ ያለው ስዕልና የተሳለበት ወረቀት ተማሪዎቹ ህጻናት ወንዶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ ከአልጋዬ በላይ፣ እኔ እስከምደርስበት እርቀት ወረቀቱ ተቦተራርፎአል። ከዚህ አንጻር ባለው ግድግዳም ላይ ታች ያለው የወረቀቱ ክፍል በትልቁ ተቀዷል፡፡ በዘመኔ እንዲህ አይነት አስጠሊታ ወረቀት አይቼ አላውቅም። መስመሮቹ ድምቅ ያሉ እና አይነ-ግቡ ናቸው፡፡ አይነ-ግቡ የሆኑት በጥንቃቄ ስለተሳሉ አይደለም፡፡ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አውቃችሁ እንኳ እንዲህ አይነት ስህተት ልሰራ ብትሉ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምስሎቹ በአርት ላይ ሊሰራ የሚችለው ግፍ ሁሉ ተሰርቶባቸዋል፡፡
ከመደብዘዙ የተነሳ በወጉ በአይን ለመከተል ያደናግራል፡፡ ስትመለከቷቸው ያበሳጯችሁ እና ለጥናት ይጋብዟችኋል፡፡ አንዱን ልፍስፍስ፣ ወዴት እንደሚሄድ እርግጠኛ ያልሆነ   የመስመር እጥፋት በአይናችሁ ተከትላችሁ ጥቂት እርቀት ስትሄዱ ድንገት መስመሩ ቁርጥ ይላል፡፡ እራሱን እንደገደለ አይነት ስሜት ይሰማችኋል፡፡ እራሳቸውን ያላጠፉ መስመሮች ደግሞ እማይጠበቅ ቦታ ተገጣጥመው፣ የሚያናድድ አንግል ይፈጥራሉ፡፡ እንዲህ ታይቶም፣ ተሰምቶም በማይታወቅ ተቃርኖ መስመሮቹ ተያይዘው ይጠፋሉ፡፡
የወረቀቱ ቀለም አስጠሊታ ነው፡፡ ለጉድ ይዘገንናል፡፡ ቢጫ ነው፡፡ ቢጫነቱ ነበልባል የሌለው፣ ትርክክ ያለ የእሳት ፍም አይነት ነው፡፡ ቆሽሾዋል። የፀሀይ ብርሃን የሚጎበኘው አካባቢ እንደ መደብዘዝ ብሏል፡፡ አንዳንድ ቦታዎቹ ጋ ደሞ ደብዝዝ ያለ፣ አስፈሪ ብርቱካናማ ቀለም አለው፡፡ ሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ በድኝ ተጨማልቋል፡፡ ይህም የበለጠ ቀፋፊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ህጻናቱ ቢጠሉት አይገርምም! እኔም እዚህ ክፍል ውስጥ ብዙ የምቆይ ከሆነ ጥያቄ የለውም፤ እጠላዋለሁ፡፡
ጆን እየመጣ ነው፡፡ የፅሁፍ እቃዎቼን ልደብቅ፡፡ አንዲት ቃል እንድጽፍ አይፈልግም፡፡
እዚህ መጥተን መኖር ከጀመርን ሁለት ሳምንታት ሆነን፡፡ ከመጣን እለት ጀምሮ የመፃፍ ፍላጎት ብዙም አልነበረኝም፡፡ አሁን እዚህ አሰቃቂ ክፍል ውስጥ መስኮቱ ጋ ተቀምጫለሁ፡፡ የአቅም ማጣት እንጂ የጽሁፍ ስራዬን የሚገድብ አንዳችም ነገር የለም፡፡ የፈለግሁትን ያህል መፃፍ እችላለሁ፡፡
ጆን ቀኑን ሙሉ እቤት አይኖርም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ቀናት ጠና ያለ ጉዳይ ሲኖረው እዚያው ያድራል፡፡ የእኔ ጉዳይ ጠና ያለ ሳላይደለ ደስ ብሎኛል። ያለብኝ ህመም ሀይለኛ ድባቴ ጎትቶ ያመጣብኛል። ጆን ምን ያህል እየተሰቃየሁ እንደሆነ አያውቅም፡፡ የምሰቃይበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ እራሱን አሳምኗል፡፡
ህመሜ ጭንቀት ነው፡፡ በጭንቀት ምክንያት አንዱንም ሀላፊነቴን መወጣት አለመቻሌ  መልሶ ያስጨንቀኛል፡፡ ለጆን አጋዥ፣ ተንከባካቢው መሆን ይገባኝ ነበር፡፡ ሸክሙን አቅልዬለት፣ እረፍት ማግኘት ሲገባው እኔው እራሴ ተጨማሪ ሸክም ሆኜበታለሁ፡፡
የእኔ የስራ ድርሻዎች፡- ልብሶቼን መልበስ፣ እራሴን ዘና ማድረግና የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንዲያቀርቡልኝ ማዘዝ ብቻ ናቸው፡፡ እኒህን ጥቃቅን ነገሮች ማድረጉ ብዙ እንደሚያዳክመኝ ብናገር ማን ሰው ያምነኛል?
ደግነቱ ልጄን ለመጠበቅ ማርያም አለች፡፡ እንዴት አይነት ብርቅ ልጅ መሰላችሁ!
አብሬው ልሆን አልችልም፡፡ አብሬው ልሆን ስሞክር የበለጠ እጨነቃለሁ፡፡ ጆን የጭንቀት በሽታ አሞት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ለዚያም ይሆናል ስለ ግድግዳው ወረቀት ስነግረው የሚስቅብኝ! የነገርኩት ሰሞን ግድግዳውን በሌላ ወረቀት ሊያስለጥፈው አስቦ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ችግሩ የግድግዳው ወረቀት ሳይሆን የኔው እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ህመሜ እንዳይባባስ ከእንዲህ አይነት ቅዥቶች እንድጠነቀቅ ነገረኝ፡፡
የግድግዳው ወረቀት ቢቀየር፡- ቀጥሎ ለማንቀሳቀስ የሚከብደውን አልጋ፣ ከዚያ በፍርግርግ የታጠረውን መስኮት፣ ከዚያ ደረጃዎቹን ወርዶ ያለውን በር፣ ከዚያ ወዘተርፈን ቀይሩ ማለቴ እንደሚቀጥል ነገረኝ፡፡
“ታወቂያለሽ፤ እዚህ ከመጣን ጤናሽ እየተሻሻለ ነው፡፡” አለ፡፡ “እውነቴን ነው የኔ ውድ፡፡ ታዲያ ምን ይጠበስ ብዬ ነው ለሶስት ወር ብቻ የተከራየነውን ቤት የማድሰው፡፡” “እንዲያ ከሆነ ታች ያሉት ክፍሎች ውስጥ እንኑር፡፡” አልኩት፡- “እዚያ የሚያማምሩ ክፍሎች አሉ፡፡”  እቅፍ አድርጎኝ የማምር ዝይ እንደሆንኩ ነገረኝ፡፡ እኔ የግድ ከፈለግሁኝና ግድግዳውን ቀለም የማስቀባት ሀላፊነት የምወስድ ከሆነ፣ ታች ያለው ክፍል ውስጥ መኖር እንደምንችል ነገረኝ፡፡ ታች ስላለው ክፍል መስኮት፣ አልጋና ስለሌላም ነገሩ ከዚህ በፊት የነገረኝ ነገር ልክ ነበር፡፡ እኔ እንድንኖርበት የፈለግሁት ክፍል አንድ መስኮት ብቻ እንዳለው፣ ሁለት አልጋ እንደማይችል፣ እሱ እንኳ ሌላ ክፍል ውስጥ ልኑር ቢል ከአጠገቡ ሌላ ክፍል እንደሌለ ነገሮኝ ነበር፡፡ አሁን ያለንበት ክፍል አየር እንደ ልብ የሚገኝበትና ምቾት ያለው ስለሆነ ማንም ሊኖርበት የሚመኘው አይነት ነው። ታዲያ ምን ይሁን ብዬ ነው ለእኔ አጉል ቅንጦት ብቻ ብዬ፣ እሱን ምቾት የምነሳው? ይህ መጃጃል ይሆናል፡፡ በበኩሌ ያለንበትን ሰፊ ክፍል ልወደው ጀምሬያለሁ፡፡ ያን ቀፋፊ የግድግዳ ወረቀት ግን ምን ላድርገው!
በአንደኛው የክፍሉ መስኮት በኩል አሻግሬ የአትክልት ስፍራውን ማየት እችላለሁ፡፡ የሌለው ነገር የለም፡- አይመረመሬ ጥላውና ድባቡ አለ፡፡ በድሮው ጊዜ እንደሚደረገው ተዘባርቀው የተተከሉት አበቦች አሉ፡፡ ችምችም ያሉት ቁጥቋጦዎች አሉ፡፡ ባለብዙ አይና፣ ጉጣምና የተጣመሙ ዛፎቹም ይታዩኛል፡፡
በሌላ መስኮት በኩል ስመለከት ደግሞ የሚያምረው የባህር ዳርቻና በመንግስት ይዞታ ስር ያለው የወደቡ መድረክ ይታየኛል፡፡ ከአለንበት ቤት ወዲያ የሚወስድ በዛፎች የተከበበ፣ ጥላ የማይለየው ጠባብ መንገድ አለ፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ሰዎች ሲመላለሱ በውኔ አልማለሁ፡፡ ጆን፣ አእምሮዬ ምናብ በማነብ፣ እና ታሪኮች በመፍጠር የሰለጠነ ስለሆነ፣ አሁን ያለብኝ ህመም ተደምሮ ለብዙ አይነት የእውን-ህልሞች ሊያጋልጠኝ ስለሚችል እንድጠነቀቅ ይነግረኛል፡፡ ለመጠንቀቅ እሞክራለሁ፡፡
ሳስበው፣ ሳስበው አቅም ኖሮኝ መፃፍ ብችል፣ የሀሳቦች ጫና እንደሚረግብና እረፍት እንደማገኝ ይሰማኛል፡፡ ለመፃፍ ስሞክር ግን ለጉድ ይደክመኛል፡፡ ስለ ጽሁፍ ስራዬ የማወራውና ምክር ሊለግሰኝ የሚችል አንድም ሰው አጠገቤ አለመኖሩ ደግሞ የበለጠ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ይህን ለማቃለል፣ ለምሳሌ የአጎቴን ልጅ ሄንሪን እና ጁሊያን መጎብኘት እችል ነበር፡፡ ጆን ግን ያን ማድረግ የሚፈቀድልኝ ሲሻለኝ ብቻ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እንዲህ አሞሽ እንደእነሱ አይነት ነፃ የሆኑና ፈታ ያሉ ሰዎች ጋ መሄድ የበለጠ ህመምሽን የሚያባብስ ይሆናል አለ፡፡ ቶሎ እንዲሻለኝ ተመኘሁ፡፡
አሁን ስለዚያ ማሰብ የለብኝም፡፡ እኔ ላይ የሚያሳድረውን ክፉ ተጽእኖ የግድግዳው ወረቀት እራሱ የሚያውቅ ይመስለኝ ጀምሯል፡፡ ወረቀቱ ላይ አንዲት ለየት ያለች ቦታ አለች፡፡ እዚህች ቦታ ላይ አንገቱ ተሰብሮ የሚንዘላዘል እራስ ይታየኛል፡፡ ይህ እራስ አምፖል በሚያካክሉ ሁለት አይኖች ከታች ወደ ላይ ያፈጥብኛል፡፡ አስተያየቱ ውስጥ ያለው ስድነትና የማያባራ ፈጣጣነቱ ያናድደኛል፡፡ እኒህ ትርጉም አልባ፣ የማይከደኑ አይኖች በየቦታው ወደ ላይ ወደ ታች፣ ወደ ግራ ወደ ቀኝ  ይንከባለላሉ፡፡ የወረቀቱ ስፋት እኩል ያልሆነበት፣ አንደኛው እሚያጥር ሌላኛው የሚረዝመት ቦታ አለ፡፡ አይኖቹ እየተንከባለሉ እዚያ ጋ ሲደርሱ፣ አንደኛው አይን ከላይ፣ ሌላኛው አይን ከታች ይሆናሉ፡፡
በዘመኔ ሙሉ አሁን የማየውን ያህል ገለፃና ምስል ግዑዝ ነገሮች ላይ አይቼ አላውቅም፡፡ ሆነ ብላችሁ ግዑዝ ነገሮችን ካያችኋቸው ያላቸው ገለፃም ሆነ ምስል ብዛቱ! ልጅ ሆኜ ለሊት እንቅልፍ እንቢ ብሎኝ ግድግዳዎቹ ላይ እና የቤት ቁሳቁሶቹ ላይ ሳፈጥ የሚያስቁና የሚያስደስቱ ምስሎች ይታዩኝ ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለጉድ የሚያስፈሩ ምስሎች ግድግዳዎቹ ላይ ይታዩኛል፡፡
የቤት ውስጥ እቃዎቹም ቀስ እያሉ ወደ አስፈሪነት እየተቀየሩ ይመጣሉ፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች ከእድሜ እኩዬቼ የበለጠ እመለከት ነበር፡፡ የእኔ የበዛ ነበረ። ለምሳሌ የቢሮአችን የበር መክፈቻ እጀታ ምን አይነት ጥቅሻ እንደነበረው አሁንም አስታውሳለሁ፡፡ ጥቅሻው የዋህና የሚያባባ ነበር፡፡ እዚያው ቢሮ ውስጥ የነበረ ወንበር ደግሞ የሚያስመካ ጓደኛ ነገር ነበር፡፡ የህይወት ግሳንግሶች ሲጫኑኝ ዘልዬ እዚያ ወንበር ላይ እቀመጣለሁ፤ ያኔ ሰላምና ደህንነት ይሰማኛል፡፡
ክፍሉ ውስጥ ያሉትን የቤት እቃዎችን ከተለያየ ክፍል ውስጥ ለቅመን ያመጣናቸው ስለሆኑ አይጣመዱም፡፡ ክፍሉ ዝብርቅርቅ ያለ ነው፡፡ ክፍሉን ከጨቅላዎች መንከባከቢያነት ወደ ህጻናት መጫወቻነት ሲቀይሩት የነበሩትን እቃዎች ሁሉ ያወጡዋቸው ይመስለኛል፡፡ ህጻናቱ በደንብ አድርገው ወጉን አሳጥተውታል፡፡ ያላጠፉት፣ ያላበላሹት፣ ያላመሳቀሉት ነገር የለም፡፡
ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት የግድግዳው ወረቀት በየቦታው ተሸርክቷል፡፡ እዚህ ክፍል ውስጥ ከምንም ነገር የቅርባችሁ ሆኖ የሚሰማችሁ የግድግዳው ወረቀት ነው፡፡ ህጻናቱ ምን ያህል ቢጠሉት ነው እንዲህ የቀዳደዱት! ይህን ሁሉ ውድመት ለማድረስ ፅናት ያስፈልጋል፡፡ ህጻናቱ ፅኑአን ነበሩ ማለት ነው፡፡
የመሬቱ ወለል በየቦታው ጎድጉዷል፣ ተፋፍቋል፣ ተሰነጣጥሯል፣ ተሰነጣጥቋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይም ሆን ብለው ንጣፉን ገፈውታል፡፡ ክፍሉ ውስጥ ያገኘነው ብቸኛውና ትልቁ አልጋ እንኳ በብዙ አደገኛ ጦርነቶች ውስጥ ያለፈ ይመስላል፡፡
ይህ ሁሉ ይህቺን ታህል ጉዳዬ አይደለም፡፡ ብቸኛው ጉዳዬ የግድግዳው ወረቀት ነው። የጆን እህት መጣች፡፡ እንዴት ያለች የተባረከች ልጅ መሰለቻችሁ። በጣም ነው የምትጠነቀቅልኝ! እየጻፍኩ ልትይዘኝ አይገባም፡፡ እንከን-የለሽና ትጉህ የቤት ሰራተኛ ናት። የቤት ሰራተኝነቷን እጅግ ስለምትወድ ሌላ ስራ አትፈልግም፡፡ እኔን የሚያሳምመኝ የጽሁፍ ሥራዬ ነው ብላ ታስባለች! ችግር የለም፤ እሷ ስትሄድልኝ መፃፍ እችላለሁ፡፡ ምን ያህል እርቃ እንደሄደች በአንዱ መስኮት በኩል አያታለሁ፡፡
ሙሉውን የግድግዳ ወረቀት እንደ አቢይ-ንድፍ ብትወስዱት ውስጡ ንዑስ-ንድፍ አለው፡፡ ይህ ንዑስ-ንድፍ ለጉድ ነው የሚያናድደኝ፡፡ ለምን መሰላችሁ፡- የሚከሰተው በተወሰኑ የብርሃን ሁነቶች ነው፤ ያኔም ደግሞ በደንብ አይታየኝም፡፡
ያልደበዘዘና ፀሀዩዋ ብሩህ የሆነችበት ቦታ አለ። እዚሁ ቦታ ላይ እንግዳ፤ የሚያናድድና ደርዝ የለሽ ምስል፤ ጉልህ ከሆነው አብይ ንድፍ ጀርባ፣ አድብቶ ይታየኛል፡፡ እህታችን ደረጃውን ስትወጣ እየተሰማኝ ነው፡፡ ኡፎይ ጁላይ 4 አለፈ፡፡ እንግዶቻችን በሙሉ ሄደዋል፡፡ ለጉድ ነው የደከመኝ፡፡ ጆን ከሰዎች ጋር ብትቀላቀዪ ለጤናሽ ጥሩ ነው ብሎ፣ እናቴ፣ ኔሊ እና የቤታችን ልጆች መጥተው ለአንድ ሳምንት እኛ ጋ ሰነበቱ፡፡ አንዲትም ነገር አልሰራሁም፡፡ ጄኒ ነበረች ኃላፊነቱን ሁሉ ወስዳ የነበረው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሲደክመኝ ነበር፡፡
ጆን፣ በልግ ሲመጣ ቬር ሚሼል ጋ ሄጄ መታከም እንደሚኖርብኝ ተናገረ፡፡
(ሲላስ ቬር ሚሼል ፈላደልፊያ ውስጥ እ.ኤ.አ. ከ1829 እስከ 1914 ዓ.ም. የኖረ የነርቭ እና የስነ - ልቦና ሀኪም ነበር፡፡ በእረፍት-መፈወስ፣ Rest-Cure የሚለውን የነርቭ ህመም የህክምና ዘዴ የጀመረው ወይም ያስተዋወቀው እርሱ ነበር፡፡ የነርቭ ስርዓት ህመሞች፤ በተለይ የሴቶች - Diseases of the Nervous System, Especially of Women የሚል የህክምና መጽሀፍ በ1887 ዓ.ም. ፅፏል-ተርጓሚው፡፡)
በጭራሽ መሄድ አልፈልግም፡፡
እሱ ጋ ትታከም የነበረች አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ፡፡ ቁጭ እንደባልሽ ጆንና እንደ ወንድምሽ አይነት ሀኪም ነው፤ እንደውም ከእነሱ የባሰ ነው ብላኛለች፡፡ እሱ ያለበት ድረስ ለመሄድም አቅም የለኝም፡፡
ለአንዲትም ነገር የማውለው ይህችን ታህል አቅም የለኝም፡፡ ያለችውንም ለምንም ነገር ማዋል አልፈልግም፡፡ ወስፌ ሲለግም ቅቤ አይወጋም አይደል የሚባለው? ደግ አደረገ፡፡ በሚያስፈራ ሁኔታ ብስጩ ሆኛለሁ፡፡ ምንም ምክንያት ሳይኖር አለቅሳለሁ፡፡ አንዴ፣ ሁለቴ፣ ምናምን እኮ አይደለም የማለቅሰው፡፡ ብዙ ጊዜ ነው፡፡ ጆንም ይሁን ሌሎች ሰዎች ባሉበት አላለቅስም፡፡ ብቻዬን ስሆን አስነካዋለሁ፡፡
ብዙውን ጊዜ ደግሞ ብቻዬን ነኝ፡፡ ጆን የታካሚዎቹ ህመም ጠና ያለ ይሆንና እዚያው ውሎ፣ እዚያው ያድራል፡፡ የተባረከችው ጄኒ፣ ሰው እንደማልፈልግ ስነግራት ብቻዬን ትተወኛለች፡፡ አትክልቶቹ ውስጥ እንሸራሸራለሁ፣ ወይም የሚያምረው ቀጭን መንገድ ላይ አዘግማለሁ፡፡ ሲደክመኝ የጽጌረዳዎቹ ጥላ ስር አርፋለሁ፣ ወይም እንቅልፌን እለጥጣለሁ፡፡
የግድግዳው ወረቀት ቢኖርም፣ ክፍሉን እየወደድኩት መጥቻለሁ፡፡ እንዲያውም የግድግዳው ወረቀት ስላለ ይሆናል የወደድኩት፡፡ ከአእምሮዬ ለጉድ አልጠፋ ብሏል! ግዙፉና የማይላወሰው አልጋ ላይ (አልጋው ከመሬቱ ጋር በምስማር የተሰፋ ይመስለኛል) ጋደም ብዬ የግድግዳው ወረቀት ላይ በየሰዓቱ በብርሃን መቀያየር የሚከሰተውን ለውጥ እከታተላለሁ። ጅምናስቲክ እንደ መስራት ነው። እንበልና እዚያ አንድም ቀን ተነክቶ፣ እጅ አርፎበት ከማያውቀው ጥግ፣ ከሥር ጀምሬ ይህን እልባት አልባ ነገር እስከመጨረሻው ለመከተል እሞክራለሁ፡፡ ሺህ፣ ምንተሺ ጊዜ ሞክሬያለሁ፡፡
ስለ ንድፍ ስራ ህግጋት ብዙ አላውቀም፡፡ ይህም ነገር የተነደፈው፣ የብርሃን አሰላለፍንና  አስተራረፍ ህግ፣ የቅይይሮሽ ህግ፣ የድግግሞሽን ህግ፣ የቅርጽ ምጣኔ ህግ፣ ወይም ሌሎች ሰምቼ የማላውቃቸውን ህጎች ተከትሎ አይደለም፡፡ ድግግሞሾቹ የሚከሰቱት ግን ስፋቶቹን ተከትለው እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከአንድ ወገን ሲታይ እያንዳንዱ ስፋት በግሉ፣ ብቻውን ተነጥሎ ይታያል፡፡ አንዳንዴ ሁሉም ነገር አግድም ይሄዳል፡፡ ወይም እንዲያ የሚሄድ ይመስላል፡፡ አካሄዱ እንዲያ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ስሞክር አቅሜን አባክናለሁ፡፡
ሁሉን ነገር ለመከተል መሞከሬ ሳያደክመኝ አልቀረም፡፡ ባሸልብ ይሻለኛል፡፡
(ይቀጥላል)

Read 3179 times