Saturday, 06 February 2016 11:36

ሌሎች የሥነጽሑፋችን አባቶች

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(1 Vote)

 ቢሆን እንዳልነው፣ ጊዜና አጋጣሚው ፈቅዶ ባለፈው ሳምንት ያወሳነውን ጉዳይ እነሆ ዛሬም ልንቀጥልበት ሆነ፡፡ ባለፈው ሳምንት “የአማርኛ ፈጠራ ድርሰት አባቶች” በሚል ርዕስ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የመጀመሪያውን የአማርኛ ልቦለድ ድርሰት “ጦቢያ (ልብ ወለድ ታሪክ)ን” በመጻፍ፣ እንዲሁም ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ የሆነውን ተውኔት “የአውሬዎች ተረት (ፋቡላ)ን” በመጻፍ ለሥነጽሑፉ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ አውግተናል፡፡
እነሆ ዛሬ ደግሞ አዲሱን ዘውግ ከእነዚህ ደራሲያን ተቀብለው አዳዲስ ጉዳዮችን በማከልና ዘውጉን በማዘመን ስላስቀጠሉት ሦስት አንጋፋ ጸሐፍት፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እና ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በጥቂቱ እናወሳለን፡፡ ለዚህም የጸሐፍቱን ማንነትና ለሥነጽሑፉ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ሊያስተዋውቅ በሚችል መንገድ ነገራችንን እንቃኝ፡፡
በሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከተነሱት ቀደምት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል፣ ቁንጮ ተብለው የሚታዩት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ እንደሆኑ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በ2003 ዓ.ም “ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች” በሚል ርዕስ የደራሲውን ሁለት ጥራዞች ይዞ ለታተመው መጽሐፍ በጻፉት መግቢያ ላይ ይገልጻሉ፡፡ ከዛም አልፎ “ነጋድራስ ገብረ ሕይወት… እስከዚያን ጊዜ ገነው የነበሩትን የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች ሚዛናዊ ያልሆነ የታሪክ አዘጋገብ በመተቸት፤ ሳይንሳዊ የሆነ የታሪክ አጻጻፍ ዘይቤ ነድፈዋል” በማለት ፈር ቀዳጅነታቸውን ይመሰክራሉ፡፡
ነጋድረስ ገብረ ሕይወት (በአስገራሚ አጋጣሚ) ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳሉ ነው ወደ ኦስትሪያ በመሄድ ዘመናዊ ትምህርትን የቀሰሙት፡፡ በኋላም ወደ በርሊን (ጀርመን) በመሄድ ህክምናን አጥንተዋል፡፡ ገብረ ሕይወት ከበርካታ ዓመታት በኋላ የአጼ ምኒልክን በጠና መታመም ተከትሎ ምኒልክን ያክሙ ዘንድ ከጀርመን ከተላኩ ሀኪሞች አንዱ ሆነው በጎልማሳነት እድሜ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
ከሀገራቸው የወጡት በልጅነታቸው በመሆኑ አፍ የፈቱበትን የትግርኛ ቋንቋ የረሱ ቢሆንም ከአውሮፓ ከተመለሱ በኋላ በሰባት ወራት ውስጥ ቀን ከሌ’ት በትጋት በማጥናት ትግርኛን ጨምሮ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በዚህም የምኒልክ ልዩ አስተርጓሚና ጸሐፊ እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡ በኋላም በነጋድረስነት ማዕረግ የጉምሩክ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ለውጥ ፈላጊና ለሀገራቸው ቅን አሳቢ የነበሩት ገብረ ሕይወት፣ በሀገሪቱ ኋላ ቀርነትና በዘመኑ በነበረው አስተዳደር ያዝኑና እጅጉን ይቆጩ ነበር። ይህንንም በጽሑፎቻቸው ይሞግቱና ያስረዱ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ገብረ ሕይወት ያጠኑት ህክምናን ቢሆንም፣ ታላላቅ ዋጋ ያላቸውን ረጃጅም ደብዳቤዎችን ጨምሮ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” የተባለውን ድንቅ የታሪክ መጽሐፍና እስካሁንም ድረስ ታላቅ እውቅና፣ አድናቆትና ክብር ያስገኘላቸውን “የመንግስት እና የሕዝብ አስተዳደር” የተባለውን በዛ ዘመን ፍጹም ሊታሰብ የማይችል አስደማሚ መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡
“አጤ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ” የተባለው ሥራ፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ “አጤ ምኒልክ” በሚል ርዕስ ንጉሡን አወድሰው ለጻፉት መጽሐፍ መልስ የሰጡበት ሲሆን ጽሑፉ የደራሲውን ጥልቅ እውቀት፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ሩቅ አሳቢነት የሚያጠይቅ ነው፡፡
በተለይ በ1916 ዓ.ም “የመንግስት እና የሕዝብ አስተዳደር” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ በአጻጻፍ ስልት፣ በመረጃዎች አተናተን እና በይዘት ረገድ በሀገራችን ሥነጽሑፍ ቀድሞ ያልታየ ታላቅ ሥራ ነው፡፡ ይህም መጽሐፉን፣ በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ መጽሐፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የመጽሐፉ ድንቅነት ከዚህም በላይ የገዘፈ ነው፡፡ ገብረ ሕይወት በዚህ መጽሐፍ ያነሱት የ“structural economics” ትወራ (theory) በአውሮፓ ልሂቃን የተደረሰበት ገብረ ሕይወት ከጻፉ ከ40 እና 50 ዓመታት በኋላ መሆኑን ለመጽሐፉ (የቅርብ ጊዜ ሕትመት) ሁለተኛውን መግቢያ የጻፉት ኢኮኖሚስቱ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ይገልጻሉ፡፡ እንግዲህ የገብረ ሕይወትን በዘመናዊ የአጻጻፍ ስልትና ይዘት መራቀቅ ለመገንዘብ ከዚህ በላይ ምስክር ከወዴት ያሻል? ከዓለም ቀድመው የተራቀቁ ድንቅ ሰው!
ያም ሆኖ ብዙዎችን የሚያሳዝነው ገና በወጣትነት ዘመናቸው ታላላቅ አስተሳሰቦችን ያቋቱ ሥራዎችን ያበረከቱልን ነጋድራስ ገብረ ሕይወት፣ ያጣናቸውም ገና በ31 ዓመታቸው መሆኑ ነው፡፡ የእነዚህ አይነት ሰዎች ሞት፣ ወዳጅ ዘመድን አልፎ ሀገርንና ትውልድን ያስተክዛል፡፡ ማጉደሉ ያህላል የለውምና!
በዘመኑ ታላቅ ሥነጽሑፋዊ አሻራቸውን ያሳረፉና በዚህም በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያላቸው ሌላው ጸሐፊ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ የሀያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዳሚ ምዕራፍ ለአማርኛ ሥነጽሑፍ የመሰረት መጣያ ዘመን መሆኑን የሚገልጹት የሥነጽሑፍ መምህሩ ቴዎድሮስ ገብሬ “… በተጠቀሰው ዘመን ተነስተው የአማርኛን ስነ ጽሑፍ መሰረት ከጣሉና ካጠበቁ ደራሲያን መካከል እውቁ የፖለቲካ ሰውና ዲፕሎማት፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልድ ሥላሴ አንዱ ናቸው፡፡” ይላሉ። (“ወዳጄ ልቤ እና ሌሎችም” ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፤ 2000 ዓ.ም)
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ምንም እንኳን በዘመናቸው እንደነበሩት አንዳንድ ምሁራን የዘመናዊ ትምህርትን ባይቀስሙም ቅሉ “የአብነት ትምህርት” አዋቂነታቸው የተመሰከረላቸው ነበሩ፡፡ በእጅ ጽሑፋቸው ማማር ምክንያት በጸሐፊነት የመንግስት ሥራን የተዋወቁት ኅሩይ፣ የራስ ተፈሪን አልጋ ወራሽነት መሾም ተከትሎ (የራስ ተፈሪ ከፍተኛ ደጋፊ እንደነበሩ ይነገራል) በየጊዜው የተለያዩ ሹመቶችን በማግኘት ከአዲስ አበባ ከንቲባነት እስከ የውጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ደርሰዋል፡፡
ኅሩይን በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ የሚያደርጉዋቸው ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ በነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ የተዋወቀውን የልቦለድ ዘውግ አዳዲስ ጉዳዮችን አክለው ማስቀጠላቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከእሳቸው በፊትም ሆነ በሳቸው ዘመን ከነበሩ ደራሲያን በተለየ በርካታ ሥራዎችን (20 የሚደርሱ ሥራዎችን ጽፈዋል) መጻፋቸው ነው፡፡ የኅሩይ መጻሕፍት የብዛታቸውን ያክል የሚያነሷቸውም ጉዳዮች እንዲሁ የበዙ ናቸው፡፡ የአብዛኞቹም ጉዳይ ተግሣጽና ምክር፣ መንፈሳዊ አስተምሮ እንዲሁም የባህል ለውጥን አስፈላጊነት መስበክ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዘመናቸው እንደነበሩት ሌሎች ምሁራን ሁሉ የጃፓንን የስልጣኔና እድገት ጎዳና ያደንቁና ኢትዮጵያ የጃፓንን መንገድ እንድትከተል ይሰብኩ የነበሩት ኅሩይ “ማህደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን” የሚል መጽሐፍ እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለአማርኛ ሥነጽሑፍ በርካታ ጉዳዮችን እንዳበረከቱ የኢትዮጵያን የሥነጽሑፍ ታሪክ ያጠኑት ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “አጭር የኢትዮጵያ ስነ ፅሑፍ ታሪክ፡፡” በተባለው ጽሑፋቸው ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹ ኅሩይ ከአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ቀጥሎ የፈጠራ ድርሰትን በሰፊው መጻፋቸው፤ አማርኛ ቋንቋ ከዘዬ ተላቆ ደረጃውን የጠበቀ የጽሕፈት ቋንቋ እንዲሆን ማስቻላቸው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድን የፈጠራ ሥራ (“ወዳጄ ልቤ”ን) ሙሉ ለሙሉ አሊጎሪያዊ አድርገው መጻፋቸው፤ እንዲሁም ለሥራዎቻቸው መቅድሞችን በመጻፍ፣ ልቦለድ ጽሑፍን በምዕራፎች በመከፋፈል፣ ሥእሎችን የያዙ ሥራዎችን በመጻፍ ብላቴን ጌታ ኅሩይ የመጀመሪያ ሰው መሆናቸው ነው፡፡ ከዋሉበት አይቀር እንዲህ ነው!
አንዳንዶች “ያለጊዜያቸው ቀድመው የተገኙ” እስከማለት ድረስ የሚያደንቋቸው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀውን የተውኔት ዘውግ በማሳደግና በሰፊው በማስተዋወቅ ለሀገራችን ሥነጽሑፍ ሌላው ባለውለታ ናቸው፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ “የአብነት ትምህርት”ን በሚገባ የተማሩ፣ በተለይም በቅኔ አዋቂነታቸው ወደር የማይገኝላቸው ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ዮፍታሔን የደራሲነት ፍቅር እንዲያድርባቸው በዚህም የበርካታ ተውኔቶች ጸሐፊ እንዲሆኑ ምክንያት የሆነው (ያስቻላቸው) በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በመምህርነት መቀጠራቸው ነው፡፡ በወቅቱ ዮፍታሔ በትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩ የውጪ ዜጎች (አብዛኞቹ ግብጻውያን ነበሩ) እያዘጋጁ እንዲታዩ የሚያደርጓቸውን ተውኔቶች በማየት  ተውኔቶችን መጻፍ ጀመሩ፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔን ሕይወትና ሥራዎች በጥልቀት ያጠናው ባለቅኔውና የሥነጽሑፍ መምህሩ ዮሐንስ አድማሱ “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ” በተባለው መጽሐፉ የሚከተለውን ይላል፡፡ “… የዮፍታሔ የቲያትር ኪን ዕውቀት በመማር፣ መጽሐፍ በመመልከት የተገኘ ዕውቀት አልነበረም… በድምጫ፣ በማስተዋል ተመሥርቶ፣ በግል ተውህቦው ተዋቅሮ የታነፀ ኪን ነው፡፡ በተፈጥሮው ለዚህ ዐይነት ሥራ የታደለ፣ “ጊዜው ላመሉ” የጠራው ባለ ቅኔ ነበረ፡፡”
ከዮፍታሔ በርካታ ተውኔቶች መካከል በመድረክ ቀርቦ ከፍተኛ እውቅና እና አድናቆትን ያተረፈው “አፋጀሽን” የሚለው ተውኔታቸው ነው፡፡ ሥራውም የሚያጠነጥነው በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል በነበረው ጦርነት ላይ ነበር፡፡ ዮፍታሔ በዘመኑ በህብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን መልከ ብዙ ችግር በተውኔቶቻቸው የተቹ፣ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ደራሲ፣ በሳል የፖለቲካ ሰው እና ጠንካራ አርበኛም ነበሩ፡፡
ዮፍታሔ ምንም እንኳን በርካታ ተውኔቶችን በመጻፍና በማዘጋጀት ለመድረክ ያበቁ ቢሆንም (“ጎበዝ አየን” (1928) ከሚለው የግጥም ሥራቸው በቀር) አንድም ተውኔታቸው ለመታተም አልታደለም፡፡
ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተጀመረውን አማርኛን ደረጃውን የጠበቀ የጽሕፈት ቋንቋ የማድረግ ጥረትን የቀጠሉበት ከመሆናቸውም በላይ ግእዝና አማርኛ ቋንቋዎችን በማዋሐድም ጉራማይሌ ቋንቋን እስከ መፍጠር ድረስ ይጠበቡ ነበር፡፡ ዮፍታሔ የበርካታ መዝሙሮችም ደራሲ ናቸው፡፡ ከደረሷቸው መዝሙሮች መካከልም ከ1966 ዓ.ም በፊት የነበረው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር” እና እጅጉን ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው “ሙሽራዬ” የተባለው የሠርግ መዝሙር (ዘፈን?) ይጠቀሳሉ፡፡ አበቃሁ፡፡
መልካም ሰንበት!

Read 3973 times