Saturday, 13 February 2016 10:45

“እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…ኢንፈሉዌንዛ የሚሉት ነገር ደግሞ መጣብን! “ጠንቀቅ በሉ…” ተባልን አይደል! እስከዛሬ ድረስ የሆነ ሰው… “በቃ በእኛ ላይ የማይበረታ ላይኖር ነው!” ሳይል አልቀረም፡፡ ካላለም ይኸው እኛ አልን!
እናላችሁ…እንደ ዘንድሮ ‘አዲስ አበቤነታችን’ ከሆነ እነኚህ ተላላፊ የሆኑ በሽታ ምናምኖችን በሚገድልበት ይግደል እንጂ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ እነኚህ ባለመስታወቶቹ ሳጥንና ከሳጥን ብዙ ያልራቁ የሚመስሉ ህንጻዎች ሊሸፍኑት በማይችሉት ሁኔታ ይቺ ከተማ ቆሽሻለች፡፡
 እናላችሁ…የእኛም ኑሮ ተባለና ይቺውንም ቆሻሻ የሚያነሳ ጠፍቶ በየሰፈሩ ሰዉ “ኸረ እንዴት ነው ነገሩ!” ሲል አይደል የከረመው!”
የምር ግን ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…የሆነ ተአምር ተፈጥሮ ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡ (ያን ጊዜ ‘የነፍስ አባታቸውን’ አያድርገኝ፡ ቂ..ቂ…ቂ…)
እናማ… በዚህ አይነት አኗኗራችን ተላላፊ የሚባሉ የጤና ችግሮች ሲመጡብን እንቅልፍ የማናጣሳ! ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዱ ሰው ግርም ይላችኋል፡፡ አለባበሱን ስታዩት አስተሳሰቡም እንደዛው ከተሜነት ያደረበት ይመስላችኋል፡፡ ታዲያላችሁ… ታክሲ ውስጥም ሆነ መንገድ ላይ አፉን ላመል እንኳን ሸፈን ሳያደርግ ‘አፋችሁ ስር’ መጥቶ ደጋግሞ ያነጥሳል፡፡
ህዝብ ትራንስፖርት ላይ አጠገባችሁ የተቀመጠው…አለ አይደል… ለ‘አስታራቂነት’ የሚበቃ የሚመስለው ሰውዬ፤ አፉን ተፈጥሮ እስከሚፈቅድለት ጥግ ድረስ ከፍቶ ያዛጋባችኋል፡፡
 ልክ እኮ አንጀሊና ጆሊ… አለ አይደል… ላራ ክሮፍት ሆና ስትዘልበትና ስትፈርጥበት የምትውልበትን ዋሻ ነው የሚመስለው፡፡  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… በዚህ አይነት አኗኗራችን ተላላፊ የሚባሉ የጤና ችግሮች ሲመጡብን እንቅልፍ የማናጣሳ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…እሱዬው ሸራ ጫማውን እንዳደረገ ቀኑን ሙሉ የጉልበት ሥራ ሲሠራ ውሎ ማታ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡
 እናላችሁ…እናቱና ወንድሙ ፊታቸው ቅጭም ብሎ ያያል፡፡ ዓይኖቻቸውን ተከትሎ ሲሄድ ለካስ የሚያዩት እግር፣ እግሩን ኖሯል፡፡ ነገሩ ገባውና ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እግሬ ሞተ እንዴ!”
አሪፍ አባባል አይደለች! የተጨናነቀ ሚኒባስ ውስጥ በጠራራ ፀሐይ የምነገባ ሰዎችም “እግሬ ሞተ እንዴ!” የምትለው አባባል ትገባናለች፡፡
እናማ…ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡
በቀደም ዕለት ረፋድ ላይ ምን አየን መሰላችሁ…ቸርችል መውረጃ ላይ የመጀመሪያውን የትራፊክ መብራት አለፍ ብሎ ነው፡፡ እናማ… ሦስት በአሠራዎቹ መጀመሪያ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች ፊታቸውን ወደ ዋናው መንገድ አዙረው እየተሳሳቁ ሽንታቸውን ‘በጋራ ሲሸኑ’ ነበር፡፡
እናላችሁ…ማንም ሰው አልገሰጻቸውም፣ ማንም ሰው ድርጊታቸው ስህተት መሆኑን አልነገራቸውም…ምነ አለፋችሁ፣ ሁላችንም ፊታችንን እያዞርን ነበር የሄድነው፡፡ በተለይ መኪና ውስጥ የነበሩትማ ... አለ አይደል…የ‘ድራይቭ ኢን’ ሲኒማ ሳይመስላቸው አልቀረም፡፡ የልጆቹ ድርጊት ምናልባት ኑሯቸው ላይ ተስፋ ማጣታቸው የፈጠረው  ብቻ ሳይሆን የሞራል እሴቶቻቻን መሳሳት ምን ያሀል ትውድል እየጎዳ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
ለነገሩ እነሱ ላይ ብቻ ከመፍረድ ኮትና ሱሪውን ግጥም አድርጎ ‘ስማርት ፎን’ የሚመስል ነገር ይዞ…በጠራራ ፀሀይ መሀል አደባባይ የሚያንፎለፉለው መአት አይደል እንዴ! (እንኳንም ‘ሁለት አይነት’ ጾታዎች አድርጎ ፈጠረን ያሰኛል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
እናማ…ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት — አሁንም በርችል ቁለቁለት — አንዲት ሸላይ ቢጤ ‘ከተሜ’ ሙዝ እየበላች ትሄድ ነበር፡፡ ታዲያላችሁ… ልጣጩን እግረኛ መታላለፊያው መሀል መንገድ ላይ ጥላ ጉዞዋን ቀጠለች፡፡ ሌላ በዛው ታልፍ የነበረች ወጣት… “ሰው ይጥላል እኮ! ምናለ ቆሻሻ መጣያው ውስጥ ብትጥዪው!” ተላታለች፡፡ (በነገራችን ላይ… እዛው አጠገብ ቆሻሻ መጣያ ነበር፡፡)
እሷዬዋ ከእግር እሰከ ራሷ ገላምጣት ጉዞዋን ቀጠለች፡፡ በጥቂት ርቀት ላይ የነበረና ከእሱ ቁመት እኩል የሚሆን የመጥረጊያ ስባሪ የሚመስል ነገር የያዘ ‘ደንብ ማስከበር’… “አንሺ!” ይላታል፡፡
 ታዲያላችሁ…ይሄኔ በቃ ልክ ልኩን ነገረችው… “ማን መሰልኩህ! በአንድ የስልክ ጥሪ እንዳላስጠበጥብህ!” ምናምን ትላለች ተበላላ ስትጠበቅ ምን ብታደርግ ጥሩ ነው… ሁሴን ቦልትን እንቅልፍ ሊነሳ በሚችል ፍጥነት አነሳችውና አረፈች፡፡
አዲስ አበባ እንዲህ ነች…የወረቀቱ ህግ ሳይሆን የሰውየው የሚከበርባት፡፡
እግረ መንገዴን… እነኚህ በየመንገዱ ተደንቅረው ግማሽ በግማሽ የወላለቁ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች የሚፈበረኩበት ጥበብ የሚገርም ነው፡፡
በዚሀ ሰሞን እንኳን ሲተክሏቸው ከነበሩ አዳዲስ ከሚመስሉ ማጠራቀሚያዎች በራቸው የተገነጠለና የወላለቁ አይተናል፡፡ ወይ አዲስ አበባ!
እናማ…ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡
ኮሚክ እኮ ነው… እኮ በመሀል አደባባይ እንደ ሰሜን ኮሪያ ሚሳይል በመካከለኛና በረጅም ርቀት እየለካ ምራቁን የሚያስወነጭፍ ከተሜ የበዛባት ከተማ ነች እኮ!
ለአንድ ምግብ ሰባና ሰማንያ ብር እያስከፈሉ የእጅ ፎጣቸው ከ‘መሬት ናዳ’ ውስጥ ተጎትቶ የወጣ የሚመስል የእጅ ፎጣ ምግብ ቤቶች ያሉባት ከተማ ነች እኮ! ወደል፣ ወደል የሆኑ እንደ ታይሰን ትከሻ ያበጡ ዓይጦች እንደልባቸው የሚሯሯጡባቸው የጤና ተቋማት ያሉባት ከተማ ነች እኮ!፡፡
ስሙኝማ…ምግብ ቤቶች ውስጥ በቀደም አመለጠ እንደተባለው የህንድ ነብር ‘ትከሻቸውን እያሳዩ’ የሚንጎማለሉብን ድመቶች… አይጥ የሚገኝበትን ቦታ የሚያሳያቸው ጠፍቶ ነው እንዴ! (“እንግዲህ መጀመሪያው ነገር አይጥ የሚለው ነገር ትርጉም ላይ መግባባቱ ላይ ነው…” የሚሉ ወዳጆቼ እንዳሉ መጠርጠሬ ይታወቅልኝማ!) እናማ…ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… የአዲስ አበባ እንትናዬዎች ዘንድሮ የሚቀቡት ‘ዲኦደራነት’ …እንዴት ነው ነገሩ!  አሀ… ‘ሽታው’ ግራ ገባና! ባንቅባውም እኮ ‘ዲኦደራንት’ ምን አይነት ሽታ ሊኖረው እንደሚችል መገመት አያቅተንም፡፡ የዘንድሮ ሚኒባስ ተሳፋሪ  እንትናዬዎች ግን የሚቀቡት ጠረኑ የ‘ዲኦደራንት’ ሳይሆን…አለ አይደል…የሆነ ‘ጠጅ ሳር’ ነው ምናምን እንደሚሉት አይነት ሆነብን፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ሀሳብ አለን…‘የሞተ እግር’ እንዳይረብሸንም፣ ‘ጠጅ ሳር’ እንዳየሸተንም… አለ አይደል… ሚኒባስ ታከሲዎች ውስጥ ጡንጅትና ሰነደል ይደረግልንማ!
የምር ግን…ያቺው የጥንቷ፣ የጠዋቷ አምስት ቀን ራስ ላይ ስትቆይ የአምስት ዓመት ጠረን የምታመጣው ‘ጭንቅላት ማራሻ’ ቅቤ ትሻላላች፡፡ ልክ ነዋ...“ባይድልሽ ራስ ላይ ተሰቀልሽ እንጂ የዘመዶችሽ ማረፊያ ሆድ ነበር…”  እያልን ሽታዋን እንችለው ነበር፡፡ እናማ…ጣይቱ ብጡል ቢያዩን ኖሮ “እንደው ምን ሰይጣን አሳስቶኝ ነው አዲስ አበባ ያልኳት!” ይሉ ነበር፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6123 times