Saturday, 18 February 2012 11:00

የዳያስፖራውን አቅም ያንፀባረቀ ልብወለድ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

በሌሎች ዘንድ የሚገኝ ጥበብን ለማየት፤ በአገር ውስጥ የቀሰሙትን ዕውቀት ሌላ አገር ሄጄ ብሰራበት የበለጠ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብለው በማመን፤ በመኖሪያ አካባቢያቸው በሚፈጠር ግጭ ሰለባ ላለመሆንና በመሳሰሉት ምክንያቶች ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጭ ይሄዳሉ፡፡ በጉብኝት፣ በሥራ፣ በስደት ባሕር ተሻግረው ከሚሄዱት አንዳንዶቹ ለራሳቸው፣ ለአገራቸውና ለሄዱባቸው አገራት ትልቅ ፋይዳ ያለው ነገር አበርክተዋል፡፡ሳይንሳዊ ፍተሻ ሲያደረግባቸው እውነት ስለመሆናቸው ማረጋገጫ  ተገኝቶላቸዋል የሚባሉ፤ ማረጋገጫ ባይገኝላቸውም የአገሪቱ ታሪክ አካል ሆነው በቃልና በጽሑፍ የቀረቡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ጉዞ ጋር በተያያዘ ከሚነገሩ ጥንታዊ ታሪኮች መሐል የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የሰለሞንን ጥበብና ዕውቀት ለማየት ባሕር ተሻግራ የሄደችው የንግሥተ ሰባ ታሪክ አንዱ ነው፡፡

የንግሥቲቱ እስራኤልን መጐብኘት ለኢትዮጵያ አስገኝቷል ተብሎ ከሚነገሩት ጥቅሞች መሐል የታቦተ ጽዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ቀዳሚው ነው፡፡ ንጉሥ ሰለሞን ከንግሥተ ሳባ ቀዳማዊ ምኒልክን መውለዱ ደግሞ የሰለሞንን ዘር እየቆጠሩ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ድረስ በኢትዮጵያ የነገሱ 250 ነገሥታት በአገሪቱ ታሪክ ዋናውን ምዕራፍ እንዲይዝ ማድረጉ ሌላው ነው፡፡

የንግሥት ሕንደኬ “ባለሟልና የገንዘቧ ሁሉ አዛዥ የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ፤ ለሃይማኖታዊ ጉዞ ኢየሩሳሌም በሄደበት አጋጣሚ የነቢዩ ኢሳያስን መጽሐፍ ሲያነብ፤ በእግዚአብሔር የተላከው ፊሊጶስ በመንገድ አግኝቶት “የምታነበው ትርጉሙ ይገባሃልን?” በሚል የጠየቀውና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የመለሰው መልስ፣ ኢትዮጵያዊያን ከ34ኛው ዓ.ም ጀምሮ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ስለመተዋወቃቸው ማሳያ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ንጉስ ኢዛና ክርስትናን የተቀበለው የኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ታሪክ ከተመዘገበ ከ366 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡

የእስልምና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ዋነኛው ባለውለታ ተደርጐ ባይጠቀስም ነቢዩ መሐመድ የእስልምናን ሃይማኖት መሥርተው በሳዑዲ አረቢያ ማስተማር በጀመሩበት ዘመን የመጀመሪያው ሙአዚን (የፀሎት ሰዓት መድረሱን የሚያውጅ ሰው) ሆኖ የተመዘገበው ቢላል ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ለዚህ ታላቅ ክብር ያበቃውና በተዘዋዋሪ አገሩንም ማስጠራት ያስቻለ ውብ ድምጽ የነበረው ቢላል፤ በሳዑዲ አረቢያ የተገኘበት ምክንያት ከባርነት ጋር በተያያዘ የሥርዓተ ማህበር ሰለባ ሆኖ ነበር፡፡

ዛሬ ጃማይካዊያን በመባል የሚታወቁትና በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ትላልቅ ሥራዎች ለዓለም እያበረከቱ ያሉት ሕዝቦች ከ400 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ወረኢሉ አካባቢ በሚገኝ “ጃማ” በሚባል ቦታ የሚኖሩ ነበሩ፡፡ በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ለብዙ እንግልት፣ ሞትና ባርነት የተዳረጉት ጃማይካዊያን፤ ኢትዮጵያን የአያቶቻችን እትብት የተቀበረባት ምድር ናት ያሉት ከ400 ዓመት በፊት የነበረውን የስደት ታሪካቸውን መርምረው ማግኘት ስለቻሉ ነው፡፡

ዛሬም ቢሆን በሳይንስ፣ በስፖርት፣ በሕክምና፣ በትምህርት፣ በንግድ፣ በኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ ታዋቂ የሆኑና በዓለም የተለያዩ አህጉራትና አገራት የሚኖሩ በችሎታቸው ታዋቂ መሆን የቻሉት ኢትዮጵያዊያን ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት መንግሥት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት ሄዶ ሲያነጋግር ይታያል፡፡ ዕውቀታችሁን፣ ገንዘባችሁን፣ መልካም አሳባችሁን መጥታችሁ አገርና ሕዝብ እንዲጠቀምበት አድርጉ እያለ መንግሥት የሚታትረው እንዲሁም የእነዚሁኑ ዜጐች ጉዳይ የሚከታተል ቢሮ ያቋቋመው በዳያስፖራው ውስጥ ያለውን አቅምና ችሎታ ስለተረዳ ይመስላል፡፡

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ቀላል የማይባል ሚና እንዳለው በገሃድ የሚታይ እውነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ያሰቡበት የሚመስሉት ደራሲ መኮንን ከድር፤ “ማስክ” (The secret cover) በሚል ርዕስ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችን ማዕከል ያደረገ ልቦለድ ጽፈው በ2003 ዓ.ም ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ በ246 ገጽ የቀረበው “ማስክ” ረጅም ልቦለድ ታሪክ መጽሐፍ በአገራችን በዘርፉ ያለውን ዕድገት አንድ እርምጃ ማስኬድ ችሏል፡፡

የደራሲያን “ስብከት” ፈጦ የሚታይባቸው የድርሰት ሥራዎች የጅማሬ ዘመንን አመልካች ነበሩ፡፡ ከልደት እስከ ሞት መተረክ ቀጣዩ ዕድገት የታየበት አሰራር ሆኖ ቀረበ፡፡ በዚህ ሂደት ዕድገቱ ቀጥሎ ሕብረተሰቡን ቀድመው እየሄዱ ሕዝብን ማሳወቅና መምራት የቻሉ የድርሰት ሥራዎች መታየት ጀመሩ፡፡ “ማስክ” ረጅም ልቦለድ ታሪክ የዘርፉን ዕድገት በአንድ ጠብታ የሚያሳድግ ውሃ ወደ ባሕሩ ቀላቅሏል፡፡ በምንና እንዴት?

የደራሲ መኮንን ከድር ልቦለድ መጽሐፍ ዳያስፖራው ላይ ትኩረት ማድረጉ አይደለም አዲስነቱ፡፡ በፊልም፣ በመጽሐፍ፣ በድራማ፣ በሙዚቃና በመሳሰሉት የኪነጥበብ ዘርፎች ስለ ዳያስፖራ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ “ማስክ” መቼቱን የተለያዩ አህጉርና አገራት ላይ ማድረጉም ያን ያህል አስገራሚ አይደለም፡፡ በስለላ ሙያ የተካኑ ኢትዮጵያዊያን ገፀ ባሕሪያትን ማቅረብ መቻሉም ጀማሪና አዲስ አያሰኘውም፡፡ የመጽሐፉ ልዩ ነገር በኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ ውስጥ ያለው ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ብቃትና ካፒታል ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን መታደግ የሚችል መሆኑን ሊያሳይ መሞከሩ ነው ልዩ የሚያደርገው፡፡

በቅኝ ግዛት ዘመንና አሁንም የዓለምን ኢኮኖሚ በበላይነት መቆጣጠር በመቻላቸው የሦስተኛው ዓለም አገራትን በተለይ አፍሪካን በብዙ ችግሮች እንድትጠላለፍ አድርገዋታል የሚባሉ መንግሥታትና የስለላ ድርጅቶቻቸውን ግራ ማጋባት የቻሉ ኢትዮጵያዊያን ናቸው የ”ማስክ” መጽሐፍ ዋና ገፀ ባሕሪያት፡፡ የእነሱን ዓላማ ደግፈው ከተለያየ የዓለም አገራት የተቀላቀሏቸው አስተኔ ገፀ ባሕሪያትም አሉ፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ከአገራቸው ወጥተው በውጭ አገራት እንዲኖሩ የተገደዱበት የተለያየ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ ከውጭ ሆነው ወደ ውስጣቸው፣ ወደ ማንነታቸው ሲመለከቱ አገራቸውን መርዳት፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ማገዙ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ስለተረዱ አፍሪካን ማዕከል አድርገው፣ የተቀረው የዓለም ክፍልና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው እቅድ ነድፈው የሚንቀሳቀሱት፡፡

የመጽሐፉ ታሪክና ገፀ ባሕሪያት በኒውዮርክ፣ በፓሪስ፣ በናፖሊ፣ በቴላቪቭ፣ በሲሲሊ፣ በሴራሊዮን፣ በኪንሻሳ፣ በሞኖሮቢያ፣ በሀራሬ ነው በዋነኛነት የሚንቀሳቀሱት፡፡ “ማስክ” የዓላማና የፍላጐታችን ጠላት ሆኖ መጥቷል ብለው የገመቱ የሩሲያ፣ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የእስራኤል መንግሥታት ተጨንቀዋል፡፡ ሊቆጣጠሩትና ሊደርሱበት ያልቻሉት አዳዲስ ተግባራት በዓለም ላይ እያከናወነ ስላለው ተቋም (ድርጅት) መረጃ እንዲያመጡላቸው ባለስልጣኖቻቸውን በየዕለቱ ያስጨንቃሉ፡፡

የሁሉም ጥርጣሬ “ማስክ” የሚል መጠሪያ ባለው ግዙፍና በዓለም ላይ ብዙ ቅርንጫፎች ባሉት የንግድ ተቋም ላይ ቢያርፍም ጥርጣሬው እውነት መሆኑን ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ማግኘት አልቻሉም፡፡ በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ የሚገኝ የ”ማስክ” ድርጅት ትልቅ ሕንፃ በፍንዳታ እንዲወድም ተደርጐ ለ40 ያህል ሰዎች ሞት ምክንያት እስኪሆን የተደረሰው አደጋው ስለ “ማስክ” ማንነት ፍንጭ የሚጠቁም መረጃ ይሰጠናል በሚል ግምት የነበረ ቢሆንም ምንም የሚያመለክተው ነገር ሳይገኝ ቀረ፡፡

በተቃራኒው የኢስታንቡል የሕንፃ ፍንዳታና የሕዝብ እልቂት ሲአይኤ፣ ኬጂቢ፣ ሞሳድ የመሳሰሉ ታላላቅ የስለላ ድርጅቶችን እንቅልፍ የሚያሳጣ ውጥረት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ በዋነኛነት የኢትዮጵያዊያን ንብረት የሆነው “ማስክ” በስውር የሚንቀሳቀሰው “ድሪም ላንድ” የሚል በወታደራዊ ክፍል የተደራጀ ልዩ ኃየል አለው፡፡ የድሪም ላንድ ዋና መሥሪያ ቤት በሞኖሮቢያ በሚገኝ ተራራ ስር በሚገኝ ዋሻ ሲሆን፤ በሌሎች ዘንድ የማይገኙ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት ነው፡፡

“በኢኮኖሚ የዳበረችና በሕዝቦቿ አንድነት የተሳሰረች አፍሪካን” መፍጠር መድረሻ ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱት የ”ድሪም ላንድ” ሰዎች፤ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ያሉ ግጭትና ጦርነቶችን የተለያዩ አካላትን እያነጋገሩ ወደ ሰላም እንዲለወጥ ያደርጋሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ባለው የስልጣንና የጥቅም ግጭት ምክንያት የሞት ሰለባ እንዲሆኑ የተወሰነባቸው ባለስልጣናትና ሰዎችን ሕይወት ይታደጋሉ፡፡ ይህንን ታላላቅ ተግባር የሚያከናውኑት ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያዊያን ባሕር ተሻግሮ መጓዝ ባልተቋረጠበት በዚህ ዘመን በቀረበው የደራሲ መኮንን ከድር መጽሐፍ፤ ወደ ውጭ አገራት የሄዱትና እየሄዱ ያሉት ኢትዮጵያዊያን፤ እንደ ንግሥተ ሳባ፣ እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ እንደ ቢላል ለአገራቸው የሚጠቅም ነገር ማምጣታቸውና ማስገኘታቸው አይቀርም ብለው ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይህንን ተስፋ ለማድረግ ደግሞ ዘመናትን ወደፊት ተሻግረው ማሰብን ጠይቋቸዋል፡፡

 

 

 

Read 2952 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:04