Saturday, 13 February 2016 10:59

ከአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት፤ ጅብ የጮኸ ዕለት ይፈርሳል!

Written by 
Rate this item
(30 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ታዋቂ እሥር ቤት ውስጥ አንድ ታዋቂ ኮንትሮባንዲስት ይታሠራል፡፡ ታሥሮም እንደተለመደው ለምርመራ ይጠራል፡፡
መርማሪ
ለምን እንዳመጣንህ ታውቃለህ?
እሥረኛ
አላውቅም
መርማሪ
ሰሞኑን አንተና ግብረ - አበሮችህ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ ህጋዊ ሽፋን ያለው ብስኩት አላመጣችሁም?
እሥረኛ፤
እሱን አውቃለሁ
መርማሪ፤
አምጥተሃል አላመጣህም?
እሥረኛ፤
አምጥቻለሁ
መርማሪ
ከብስኩቱ ሥር ምን ነበር
እሥረኛ
ምንም
መርማሪ
እንግዲህ በቀላሉ አምነህ ምርመራችንን ብንጨርስ ይሻላል፡፡ አለበለዛ ወደ አስገዳጅ ምርመራ
መሄዳችን     ነው፡፡
እሥረኛ
እኔ የማውቀውን አውቃለሁ፡፡ የማላውቀውን አላውቅም ብያለሁ፡፡
መርማሪ
እኔ ደሞ እንዴት እንደማሳውቅህ አሳይሃለሁ፡፡ …
ይልና ወደ አስገዳጅ ምርመራ ይወስደውና ያስገርፈዋል፡፡ እሥረኛው ግርፉ ሲበዛበት “እናገራለሁ”
ይላል፡፡
መርማሪ
እሺ ከብስኩቱ ሥር ምን ነበር?... ብሎ ይጠይቃል
እሥረኛ
ውስኪ
መርማሪ
ሌላስ?
እሥረኛ
የታተመ ብር
መርማሪ
በጣም ጥሩ፡፡ አሁን ግብረ -አበሮችህ የት እንዳሉ ታሳየናለህ፣ ትመራለህ፡፡ ስለተደረገልህ ምርመራ
አንድ ቃል ትንፍሽ አትልም፡፡
አጃቢዎች ይመደቡለትና ግብረ - አበሮቹ ያሉበትን ይመራል፡፡ ግብረ - አበሮች ተይዘው ይመጣሉ፡፡
መርማሪ
ኮንትሮባንድ ተይዞባችኋል … በህጋዊ ብስኩት ሽፋን፡፡ ይሄን ታውቃላችሁ?
1ኛው ግብረ - አበር
አላውቅም
2ኛው ግብረ - አበር
አላውቅም
መርማሪ
በተያዘና እጃችን ላይ ባለ ጉዳይ ባንጨቃጨቅ ይሻላል!
ሁለቱም ግብረ - አበሮች “አናውቅም”፣ “አናውቅም” ብለው ድርቅ አሉ፡፡
ይሄኔ መርማሪው ወደ መጀመሪያው እሥረኛ ዞሮ፤
“እነዚህ ጓደኞችህ አናውቅም አሉ‘ኮ ምን ይሻላል?” ሲል ጠየቀው፡፡
እሥረኛውም፤
“እንግዲህ ለእኔ ያረጋችሁትን ማረግ ነዋ!”
***
አገር የሚበድል ተግባር በማናቸውም ገፁ እኩይ ነው፡፡ ፍትሕም ፍትሐዊ መንገድ ያሻዋል፡፡ በየኬላው፣ በየአየር ማረፊያው አልፎ ተርፎም በየቢሮው ውስጥ ኮንትሮባንድ ይጧጧፋል ይባላል፡፡ መገደቢያ ግን አልተበጀለትም፡፡ ጉዳዩን ገደብ ይሰጡታል የሚባሉት አካላት ራሳቸው ገብተውበታል የሚባለው ሐሜት ዕውነት ከሆነ አንዱ እንቅፋት እሱ ነው፡፡ ስለሱ መናገር አለመቻሉም የዛኑ ያህል እንቅፋት ነው፡፡ “እንደነፃው አገር ያሰብነውን ጽፈን፣ ተናግረን፣ ተወያይተን፣ በነፃ ምርጫ የመተዳደር ዕድል እግዚአብሔር ሊሰጠን አልፈቀደም የሚል ተስፋ አስቆራጭ ዕምነት አደረብኝ” እንዳሉት ነው ተክለፃድቅ መኩሪያ፡፡ አዋጅ ብናወጣ፣ መመሪያ ብንደረድር፣ ቀላጤ ብንልክ ውስጣችን ሙስና ካለ፤ ንፁህ ሥራ አይሠራም፡፡ ንፁህ ልማት አይገኝም፡፡ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ዓይነት አካሄድም ጊዜያዊ ምላሽ የሚመስል ትርዒት ነው፡፡ ግንዱን መገንደስ እንጂ ቅርንጫፉን መቀንጠብ፤ ሙስናን ከሥሩ ገርስሶ አይገላግለንም፡፡ ይብሱንም ሙሰኞች የሚያፌዙበት፣ ውስኪ የሚራጩበት ፌዝ የሆነ ይመስላል ጉዳዩ፡፡
ከተክለ ፃድቅ መኩሪያ “የህይወቴ ታሪክ” ለአብነት ብንጠቅስ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብልሹነትና የሞራል ዝቅጠትን ሁኔታ ጥሩ ማፀህያ ይሆነናል፡፡
“ወጣቶች ሚኒስትሮች፤ ከንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ባለሟሎች አንዳንድ ወጣት ነጋዴዎች ጋር በየቪላው ውስኪ እንደውሃ እያፈሰሱ፣ ጮማና ክትፎ እየበሉ፣ አዝማሪ እያቆሙ፣ ከየሴቱ ወጣት ጋር ሆነው ዓለማቸውን ያያሉ” የሚባለው ወሬ ከሚነፍሰው ጋር፤ እያንዳንዱ የተቻለው በየቤቱ፣ በየምክንያቱ የሚደግሰው፤ የድግሱ፣ የመብሉና የመጠጡ ዓይነትና ብዛት በውጪ ካለው የሥራ ፈትና የድሃ ኑሮ ጋር ሲመዛዘን ልዩነቱ ዐይን ይመታል”
ይህን ከ50 ዓመታት በፊት የነበረ ዕውነታ፣ በየዘመኑ ብናጤነው፣ የሙስና ገጽታ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ መሆኑን እስከዛሬም ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ የድህነታችንም አዘቅት የዛኑ ያህል ጠሊቅ እየሆነ ይመጣል፡፡
ነብስ ያወቀ ተቋም፣ ጥንካሬ ያለው መዋቅር፣ ፍትሐዊነት ያለው አሠራር፣ ኢ-ወገናዊ የሆነ ሥርዓት፣ ተመልሶ ቀስቱ እኛኑ የማይወጋበት (ቡመራንግ) አካሄድ ካልተፈጠረ፣ “ነገራችን ሁሉ የዕንቧይ ካብ የዕንቧይ ካብ” ይሆናል በአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት፤ ጅብ የጮኸ ዕለት ይፈርሳል - ይሏልና!  



Read 7443 times