III
ይህን ለምን እንደምጽፍ አላውቅም፡፡
ልጽፈው አልፈለግኩም፡፡
አቅምም ያለኝ አይመስለኝም፡፡
ለጆን ትርጉም አልባ ነገር እንደሚሆንበት አውቃለሁ፡፡ ምን እንደማስብና ምን እንደሚሰማኝ ግን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ መንገር አለብኝ፡፡ አቤት ያኔ የማገኘው እፎይታ!
የማባክነው አቅም ግን ከማገኘው እፎይታ ይልቃል፡፡
አሁን አሁን ለጉድ ሰነፍ ሆኛለሁ፡፡ የማሳልፈው ተጋድሜ ነው፡፡
ጆን ጥንካሬዬን እንዳላጣ ይጨነቃል፡፡ የአሳ ዘይት፣ ቶኒክና ሌሎችም ነገሮች እንድጠጣ ያደርገኛል፡፡ ምን አለፋችሁ የማያጠጣኝና የማያበላኝ ነገር የለም፡፡
ጆን የኔ ውድ! በጣም ነው የሚያፈቅረኝ፡፡ መታመሜን ይጠላል፡፡ ሀቀኛ፣ ቅንና ምክንያታዊ ሆኜ፤ ትናንትና ማታ የአጎቴ ልጅ ሄንሪንና ጁሊያን መጎብኘት እንደምሻ ገልጬ፣ እንዲፈቅድልኝ ጠየኩት፡፡
እሱም አቅም ኖሮኝ እዛ ድረስ መሄድ እንደማልችል፤ ብሄድም እዚያ ብዙ መቆየት እንደማይሆንልኝ አረዳኝ፡፡ ለምን መሄድ እንዳለብኝ አሳማኝ መከራከሪያ አላዘጋጅሁም፡፡ ምንም ነገር ከማለቴ በፊት እንባ ቀደመኝ፡፡
ነገሮችን ጥርት አድርጎ ማሰብ እያቃተኝ ነው፡፡ ያው የፈረደበት የነርቭ በሽታዬ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ውዱ ጆን አፋፍሶ በእቅፉ ይዞኝ፤ ተሸክሞ ደረጃውን አወጣኝ፡፡ አልጋችን ላይ አሳርፎኝ እስኪያንገሸግሸኝ ድረስ መፅሀፍ አነበበልኝ፡፡
እኔ ለእርሱ፡- ብርቅ ነገር፣ የምቾቱ እናት፣ የሀዘኑ መፅናኛ፣ የደስታው ምንጭ፣ በምድር ላይ ያለሁት ብቸኛ ሀብቱ እንደሆንኩ ነገረኝ፡፡ ሌላው ቢቀር ለሱ ብቻ እንኳ ብዬ እራሴን እንድጠብቅና በጤና እንድሆን አሳሰበኝ፡፡
ከእኔ በቀር አሁን ካለሁበት ሁኔታ ማንም ሊታደገኝ እንደማይችልና ያለኝን ሁሉ አእምሮአዊ ሆነ ልባዊ ፈቃድ ተጠቅሜ እንድበረታ ነገረኝ፡፡ ሞኛ-ሞኝ የቀን ቅዠቶቼንም ማስወገድ አለብኝ፡፡ አንድ ብቻ የሚያጽናናኝ ነገር አለ፡፡ ልጄ ደህና እና ደስተኛ ነው፡፡ ይህ አሰቃቂ የግድግዳ ወረቀት ወዳለበት ክፍል አያመጡትም፡፡ እፎይ፡፡
እኛ ቀድመን እዚህ ክፍል ውስጥ ባንገባ ኖሮ ልጄን እዚህ ነበር የሚያኖሩት፡፡ ለጥቂት ነው ያመለጠው! በዙሪያው ያለው ነገር ሁሉ ተፅእኖ የሚያሳድርበት ሚጢጢ ልጅ፣ ለእዚያውም የእኔው፣ የእራሴ ልጅ፣ የፈለገው ነገር ይከሰታል እንጂ እዚህ ክፍል ውስጥ እንዲኖር አልፈቅድም፡፡
ጆን እኔን እዚህ እንድኖር መወሰኑ ለበጎ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከጨቅላው ልጄ ይልቅ እኔ ነገሮችን መቋቋም እችላለኋ፡፡ እንዲያ ነው ነገሩ፡፡ አሁን አሁን ስለ ግድግዳው ወረቀት ለአንዳቸውም ትንፍሽ አልልም፡፡ ቀላል ሰው መሰልኳችሁ? በጣም ብልህ ነኝ፡፡ ወረቀቱን መመርመሬን ግን አጥብቄ ይዣለሁ፡፡
ስለዚህ ወረቀት ከእኔ በቀር አንዳችም ሰው የማያውቃቸው ብዙ ምስጢሮች አሉ፡፡ ማንም ሰው፣ መቼም ሊያውቃቸው አይችልም፡፡ ከአቢይ ንድፉ ጀርባ ያለው ደብዛዛ ምስል በየእለቱ እየጠራ፣ ግልፅ እየሆነ መምጣት ያዘ፡፡
ቅርጹ እንዳለ ሆኖ ቁጥሩ ግን ጨምሯል፡፡
የሆነች ሴት አጎንብሳ፣ ስትድህ ከአቢዩ ንድፍ ጀርባ ትታየኛለች፡፡ እጅግ ያስጠላል፡፡ ምን አለ ግን ጆን ከዚህ ቤት እንድወጣ ቢያደርግ!
Iv
ከጆን ጋር ስለ እኔ ጉዳይ መወያየት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንደኛ፡- ጆን በጣም ብልህ ነው፡፡ ሁለተኛ፡- በጣም ያፈቅረኛል፡፡
ትናንት ማታ ላወራው ሞከርኩ፡፡
የጨረቃ ምሽት ነበር፡፡ ጨረቃዋ አካባቢውን በሙሉ አብርታዋለች፤ ብርሃኗ ከጸሀይ እኩል ነበረ፡፡ አንዳንዴ ጨረቃን ላያት እጠላለሁ፡፡ ቀስ እያለች ነው ሰማዩ ላይ የምትንፏቀቀው፡፡ የምትታየኝም በአንዱ ወይም በሌላው መስኮት ብቻ ነው ፡፡
ጆን እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ እሱን ከእንቅልፉ መቀስቀስ አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ እንደ በድን ሆኜ፣ ሳልንቀሳቀስ ጨረቃዋ አባጣ ጎርባጣው የግድግዳ ወረቀት ላይ እንዴት እንደምትበራ አጠናሁ፡፡ አሁን መዳኽ አማረኝ፡፡ ህልም መሳዩዋ፣ እንደጭስ ሳስታ የምትታየኝና ከንድፉ ጀርባ ያለችው ሴት ንድፉን እያናወጠች ነው፡፡ ለመውጣት የፈለገች ትመስላለች፡፡
ትንፋሼን ውጬ፣ ቀስ ብዬ ተነሳሁ፡፡ ወረቀቱ ይንቀሳቀስ እንደሁ ለማረጋገጥ ሄድኩ፡፡ ስመለስ ጆን ነቅቶ ጠበቀኝ፡፡
“ሚጢጢ ምንድነው ነገሩ?” አለ፡፡ “እንዲህ ምንም ሳትደርቢ አትንቀሳቀሺ፤ ብርድ ያገኝሻል፡፡”
ለመነጋገር ጥሩ ጊዜ እንደሆነ አሰብኩ፡፡ ምንም እየተሻለኝ እንዳልሆነና ከዚህ መሄድ እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡
“ለምን የኔ ውድ!” አለ፡- “ኪራያችን የሚያበቃው ገና ከሶስት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የምንለቅበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡ ቤታችንም ታድሶ አላለቀም፤ ይህም አሁን እንዳንሄድ ያደርገናል፡፡
አንቺን የሚሰጋሽ አንድ ነገር ቢኖር ኖሮ ጨርቄን ማቄን ሳንል እንሄድ ነበር፤ ግን አንድም ችግር የለም፡፡ እንዲያውም አንቺን ባይታወቅሽም እየተሻለሽ መጥቷል፡፡ እያገገምሽ ነው፡፡ ውዴ፣ ዶክተር መሆኔን እንዳትዘነጊ፡፡ የቆዳሽ ቀለም ወደ ድሮው ተመልሷል፤ የምግብ ፍላጎትሽ ተሻሽሏል፤ ክብደትም ጨምረሻል፡፡ ከእነዚህ ሌላ ምን ትፈልጊያለሽ? ይህን ሁላ ሳይ እንዴት ቅልል እንዳለኝ፣ እንዴት ደስ እንደተሰኘሁ አትጠይቂኝ፡፡”
“ክብደት ይህቺን ታህል አልጨመርኩም፡፡” አልኩኝ፡- “እንዲያውም የባሰ ቀንሼያለሁ፡፡ የምግብ ፍላጎትሽ ላልከው፣ ማታ ማታ አንተ እዚህ ስትኖር ይጨምርና ጠዋት አንተ ስትሄድ ለጉድ ይቀንሳል፡፡”
“የዋኋ ልብሽ የተባረከች ትሁን!” ብሎ በሰፊው አቀፈኝ፡- “እነሆ የፈለግሺውን ያህል እንድትታመሚና የታመምሽውንም፣ ያልታመምሽውንም አጋነሽ እንድታወሪ ፈቅጃለሁ! አሁን በዚህ ደስታችን ላይ ደስታ ለመጨመር ብንተኛ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ስለጉዳዩም ጠዋት እንነጋገራለን፡፡”
“ከዚህ አንሄድም፣ እንቆያለን እያልከኝ ነው?” በጨፈገገ ስሜት ጠየቅሁት፡፡
“ለምን ብለን ነው የምንሄደው? እንዴት ብለን ነው የምንሄደው? የቀሩን ሶስት ሳምንታት ብቻ ናቸው! ከዚያ ምርጥ የሽርሽር ጉዞ እናደርጋለን፡፡ በዚሁ ጊዜ ጄኒ ቤታችንን አዘጋጅታ ትጠብቀናለች፡፡ የምሬን ነው የምልሽ፤ እየተሻለሽ ነው፡፡”
“ሰውነቴ ምናልባት ደህና የሆንኩኝ...” ብዬ ስጀምር እመር ብሎ ተነሳና ቀጥ ብሎ ቁጭ አለ፡፡ በከባድ ተኮሳትሮ፣ በሀይለኛ ወቀሳ አየኝ፡፡ አንዲትም ቃል መጨመር አልቻልኩም፡፡ ዝም፡፡
“የኔ ውድ!” አለ፡- “እንደው ለኔ ብለሽ፣ እንደው ለልጃችን ብለሽ፣ በመጨረሻም ለራስሽ ብለሽ… እኒያ ሀሳቦች ወደ አእምሮሽ እንዲመጡ አትፍቀጂላቸው፡፡ አንቺን በቀላሉ ሊማርክሽ የሚችል ግን እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ አጉል፣ ቂላ-ቂል የቀን ህልም ነው፡፡ ቆይ፤ እንደ ሀኪምነቴ የምነግርሽን አታምኚም?”
ያው ግልጽ ነው፤ ከዚያ በኋላ ምንም አልተናገርኩም፡፡ ደግነቱ ብዙም ሳንቆይ ተኛን፡፡ ጆን እንቅልፍ የወሰደኝ መስሎታል፡፡ ተጋድሜ ለሰአታት የውጪውና የውስጠኛው ንድፍ የሚንቀሳቀሱት፣ አንድ ላይ ይሁን ለየብቻ እየተመራመርኩ ነበር፡፡
V
በብርሃን ጊዜ ምን ይሆናል መሰላችሁ፡- ምስሎቹ በየተራ መከሰታቸውን ይተዋሉ፤ ሁሉ ነገር ይዘባረቃል፤ አንድም ስርዓት ያለው ነገር አይሆንም፤ ሁሉም ነገር ህግ ይስታል፡፡ ጤነኛ አእምሮ ደግሞ እንዲህ አይነት ነገር መታገስ አይችልም፡፡ ምን ያህል እንደሚያበሳጭ ልናገር አልችልም፡፡
ቀለሙ ከምትችሉት በላይ አስጠሊታ፣ ከምትቆጥሩበት በላይ ተለዋዋጭና ከምታስቡት በላይ አናዳጅ ነው፡፡ ንድፉ የሚፈጥረውን ስቃይ ማንም አይቋቋመውም፡፡
ልትለምዱት ያላችሁ ይመስላችሁና መስመሮቹን ተከትላችሁ ትሄዱ፣ ትሄዱ፣ ትሄዱ … አሁን ወደ ኋላ ይገለበጥላችሁና ወደ ነበራችሁበት ይመልሳችኋል፡፡ እንደገና ‘ሀ’ ብላችሁ ትጀምራላችሁ፡፡ ከዚያ ምን ይቀራል ትላላችሁ፡- በጥፊ ያጮላችኋል፤ ከመሬት ጋር ያደባያችኋል፤ እዚያው እንዳላችሁ ይረጋግጣችኋል፡፡ ልክ እንደ አስፈሪ ቅዠት ነው፡፡
የውጪው ንድፍ በቀለም ያሸበረቀ ነው፤ የፈንገሶችን ቀለም ይመስላል፡፡ ወረቀቱ የራሱ የሆነ፣ ከእኔ በቀር ሌላ ማንም ያላስተዋለው ልዩ ባህሪ አለው፡፡ የብርሃን ሁኔታ ሲቀያየር አብሮ ይቀያየራል፡፡
ፀሀይዪዋ በምስራቁ መስኮት ዘው ብላ ስትገባ (ይህን ረዥምና ቀጥ ያለ የብርሃን ዘሀ ሁሌ ነው ተከታትዬ የማየው) ወዲያው ይለወጣል፡፡ የለውጡን ፍጥነት ለማመን ሁሌ እንደተቸገርኩ ነው፡፡ ለዚያም ነው ሁሌ የማየው፡፡
በጨረቃ ብርሃን (ጨረቃ ካለች ለሊቱን ሙሉ ነው ብርሃኗ የሚታየው) ያው የቀኑ ወረቀት መሆኑን መለየት ያዳግተኛል፡፡
በምሽት በማንኛውም አይነት ብርሃን፡- ደንገዝገዝ ባለ ብርሀን፣ በሻማ ብርሃን፣ በፋኖስ ብርሃን፣ በተለይ በተለይ በጨረቃ ብርሃን ከውጭ ያለው ንድፍ ወደ ፍርግርግ የብረት በርነት ይቀየራል፡፡ ይኼኔ ከጀርባ ያለችው ሴት በግልጽ ትታያለች፡፡
በፊት ለረዥም ጊዜ ከጀርባ፣ ደብዝዞ ይታየኝ የነበረው ንዑስ-ንድፍ ምን እንደሆነ መለየት አቅቶኝ ነበር፡፡ አሁን አወቅሁኝ፡፡ ሴት ናት፡፡ ቀን ቀን የተገራች፣ ጭምትና ዝምተኛ ናት፡፡ አደብ ያስገዛት ንድፉ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የሚገርመው እኔም በዚህ ሰዓት ዝምተኛ እሆናለሁ፡፡
በጣም እየተኛሁ ነው፡፡ ጆን መተኛት ለኔ ጥሩ እንደሆነና የቻልኩትን ያህል እንዳንቀላፋ ነገረኝ፡፡ እንዲያውም ሁሌ ከምግብ በኋላ ለአንድ ሰዓት እንድተኛ ማድረግ ጀመረ፡፡ መጥፎ ልምድ ነው፡፡ እንቅልፍ አይወስደኝም፡፡
ይህ ደግሞ ውሸታም እንድሆን አደረገኝ፤ እንቅልፍ እንዳልወሰደኝ አልነግራቸውም፡፡ ምን በወጣኝ! እውነቱ ምንድነው መሰላችሁ? ጆንን እየፈራሁት መጥቻለሁ፡፡ አንዳንዴ እንግዳ ፍጡር ሁሉ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ጄኒስ ብትሉ፣ ትርጉሙ የማይታወቅ እይታ አምጥታለች፡፡ እንዲህ የሚያደርጋቸው ወረቀቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህን እንደ ሳይንሳዊ የምርምር መነሻ ሀሳብ (ሀይፓዘሲስ) ልትወስዱት ትችላላችሁ፡፡
ሳይነቃብኝ ጆንን በአይነ ቁራኛ እከታተለው ጀመር፡፡ እንደማየው ሳላስነቃ ነው የማየው፡፡ ማንም በማይጠረጥርበት ሰዓት፣ ምክንያት ፈጥሬ ክፍሉ ውስጥ ዘው ብዬ እገባለሁ፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? በተደጋጋሚ ወረቀቱን እያየ እጅ-ከፍንጅ ያዝኩት፡፡ ጄኒንም ይዣታለሁ፡፡ እንዲያውም ጄኒን ያገኘኋት ወረቀቱን ስትዳብሰው ነው፡፡
አላየችኝም ነበር፡፡ እጅግ በተረጋጋ ድምፅና ስሜቴን የሚቻለኝን ያህል ለጉሜ ምን እያደረገች እንደሆነ ጠየቅኋት፡፡ ሲሰርቅ እንደተያዘ ሰው ለጉድ ደነገጠች፡፡ ለምን እንዲህ አድርገሽ ታስደነግጪኛለሽ ብላ ተቆጣች!
ወረቀቱ የቀረበው ሰው ሁሉ ላይ ይላከካል፡፡ እኔም፣ ጆንም ልብስ ላይ በስሞሽ ጊዜ የከንፈር ቀለም ሲለቅ እንደሚሆነው አይነት ሆኖብናል፡፡ ቢጫ ቀለም ልብሶቻችንን፣ ብዙ ቦታ ስሟቸዋል፡፡ ጄኒ ይህን ነግራኝ፣ እባካችሁ ተጠንቀቁ አይነት ምክር አስተላለፈች፡፡ እንዴት ነው ንግግሯ የዋህ ቢጤ ይመስላል አይደል? አሁን ይህቺ ትጥፋኝ፡፡ ንድፉን እያጠናች እንደነበር አውቄያለሁ፡፡ ይህን ምስጢር ከእኔ ሌላ ማንም ሰው እንዲያውቅ አልፈቅድም፡፡
VI
አሁን አሁን ህይወት ይሏት ነገር ከበፊቱ ይልቅ አስጊ እየሆነች ነው፡፡ በተስፋና በጉጉት የምጠብቀው ነገር አለ፡፡ ምን መሰላችሁ? መመልከት ይባላል፡፡ ወረቀቱን መመልከት፡፡ ምግብ ለጉድ እየበላሁ ነው፡፡ ተረጋግቼያለሁ፤ በእርጋታ ከአለም አንደኛ ሆኛለሁ፡፡ ጆን የጤናዬን መሻሻል አይቶ ደስ ብሎታል፡፡ ከወረቀቱ ጋር አልፋታ ብለሽ አስቸገርሽ እንጂ ጤናሽስ እየተሻሻለ መጥቷል አለኝ፡፡ እየሳቀ ነው ይህን ያለው፡፡
እኔም ስቄ ጨዋታው እዚሁ ላይ እንዲዘጋ አደረግሁ፡፡ ያሻለኝ ወረቀቱ እንደሆነ እንዴት እነግረዋለሁ፡፡ ይህን የመናገር እቅድ አልነበረኝም፡፡ ዝም፡፡ እንዲህ ብዬ ብነግረው ይስቅብኝ ነበር፡፡ ከወረቀቱ ሊያርቀኝ ይሞክር ይሆናል፡፡ ምስጢሩን አጠናቅቄ ሳላውቅ ከዚህ ቤት መሄድ አልፈልግም፡፡ አንድ ሳምንት አለን፡፡ ሁሉን ነገር አብጠርጥሬ ለማወቅ በቂ ጊዜ መሰለኝ፡፡
VII
እንዲህ በደስታ ተጥለቅልቄ አላውቅም! ለሊት አልተኛም፤ ከተኛሁ ብዙ የሚታይ ነገር ያመልጠኛል፡፡ አሁን ደግሞ አዳዲስ ነገሮችም እየታዩኝ ነው፡፡ ለእንቅልፉ ቀን ቀን እደርስበታለሁ፡፡ ቀን እየተኛሁ ነው፡፡ ቀኑ አድካሚና ግራ አጋቢ ነው፡፡
አዳዲስ ፈንገሶች እያበቡ ነው፡፡ ወረቀቱ ቢጫ፣ በቢጫ እየሆነ ነው፡፡ ያለ የሌለ አቅሜንና ትዕግስቴን ብጠቀምም ቆጥሬ ልጨርሳቸው አልቻልኩም፡፡
ይህ የምነግራችሁ የግድግዳ ወረቀት ቀለሙ ቢጫ ነው፡፡ እንግዳ የሆነ፣ የሚገርም ቢጫ! በዘመኔ ሙሉ ያየኋቸውን ቢጫ ነገሮች እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ምርጦቹን ቢጫዎች ለምሳሌ ቢጫ አበባ ምናምን አይደለም የማስታውሰው፡፡ ቀፋፊና አስጠሊታ ቢጫ ነገሮችን ነው አስብ የነበረው፡፡
ስለ ወረቀቱ ሌላም እጅግ የሚገርመኝ ነገር አለ፤ ጠረኑ፡፡ እዚህ እንደመጣን ነበር የታወቀኝ፡፡ በወቅቱ ግን ብርሃንም፣ በቂ አየርም ስለነበር እንዳሁኑ አይከረፋም፡፡ ሰሞኑን ሳምንት ሙሉ ደመና እና ዝናብ ሆኖ ሰነበተ፡፡ አሁን መስኮቶቹ ተዘጉም፣ ተከፈቱም ከጠረኑ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ጠረኑ ክፍሉ ውስጥ በየቦታው ሲድኽ ታገኙታላችሁ፡፡
ምግብ ቤት ውስጥ ያንዣብባል፤ ማረፊያ ቤት ውስጥ ያደፍጣል፤ አዳራሹ መደበቂያው ነው፤ ደረጃው ላይ ያለ ሀሳብ ለጥ ብሎ ይጠብቀኛል፡፡ ፀጉሬ ውስጥ ይገባል፡፡ ፈረስ ላይ ሆኜ እንኳ ድንገት ሳያስበው ዞር እላለሁ፡፡ እሱ እቴ፣ አሁንም እንደተከተለኝ ነው፡፡ ይሸተኛል፡፡ ለየት ያለ መአዛ አለው! ምን፣ ምን እንደሚሸት ለብዙ ሰዓታት ተመራመርኩ፡፡
በመጀመሪያ ጊዜ ጠረኑ መጥፎ አልነበረም፡፡ ለስለስ ያለና ይህ ነው ሊሉት እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በቀላሉ አይጠፋም፡፡ ለብዙ ጊዜ ይቆያል፡፡ አሁን ባለው እርጥብ የአየር ሁኔታ ግን መከርፋት ጀምሯል፡፡ ለሊት ከእንቅልፌ ስነቃ መላ ሰውነቴ ላይ ተለጥፎ አገኘዋለሁ፡፡ መጀመሪያ ሰሞን ለጉድ ይረብሸኝ ነበር፡፡ እንደውም የቱ ጋ እንዳለ ለማወቅ ቤቱን ለማቃጠል ሁሉ አስቤ ነበር፡፡
ለመድኩት፡፡ አንድ ነገር ተከሰተልኝ፡- ሽታው የወረቀቱ ቀለም አይነት ነው፡፡ ቢጫ ሽታ!
የቤቱ ግድግዳ ላይ አንድ የሚያስቅ ምልክት አለ፡፡ ከአካባቢው ለየት ያለ፣ የክፍሉን ዙሪያ የሚሄድ ቀጭን፣ ረዥም መስመር ነው፡፡ ከአልጋው በቀር ከሁሉም የቤት እቃዎች ጀርባ ይታያል፡፡ እንዲያውም በጣም በተደጋጋሚ ጊዜ በመታሸቱ በስሞሽ ጊዜ ልብስ ላይ የከንፈር ቀለም ሲለቅ እንደሚሆነው አይነት መልክ ይዟል፡፡ ማን እንደ አሰመረውና ምን ይሁነኝ ብሎ እንዳሰመረው ሲገርመኝ አለ፡፡ ዘወር - ዘወር - ዘወር፣ ዘወር - ዘወር - ዘወር… እያልኩ አየዋለሁ፡፡ እራሴ ይዞራል፡፡
VIII
በመጨረሻም የሆነ ነገር ተገለጠልኝ፡፡
እንዲህ በብላሽ የመጣ መገለጥ አይደለም፡፡ ለረዥም ቀናት ለሊቱን በሙሉ ወረቀቱን በማየትና ለውጡን በመከታተል ነው የደረስኩበት፡፡
የውጭኛው ንድፍ ይንቀሳቀሳል! ባይንቀሳቀስ ነበር የሚገርመኝ፡፡ ከጀርባ ሆና የምታናውጠው ሴትዬዋ ናት፡፡ አንዳንዴ ከጀርባ ያሉት ሴቶች የትየለሌ ይሆኑብኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ አንዲት ብቻ ትሆናለች፡፡ ዙሪያውን በፍጥነት ትድኻለች፡፡ ያኔም ሀይለኛ መናወጥ ይሆናል፡፡
ብርሃኑ ብሩህ እሚሆንበት ቦታ ስትደርስ ሴትየዋ ትረጋጋለች፡፡ አርፋ ትቀመጣለች፡፡ ከበድ ያለ ጥላ ያጠላበት ቦታ ስትደርስ የብረት ዘንጎቹን ትይዝና በከፍተኛ ሀይል ትነቀንቃቸዋለች፡፡ ሁሌም የብረት ፍርግርጉን አምልጣ ለመውጣት እንደሞከረች ነው፡፡ ይህን እገታ፣ ይህን እስር አምልጦ ለመውጣት እጅግ ይከብዳል፡፡ ምንም መላወሻ የለም፡፡ አንቆ ነው የሚይዘው፡፡ ለዚህም ይሆናል ብዙ ጭንቅላቶች የሚታዩኝ፡፡
ለማምለጥ አንገታቸውን በብረት ዘንጎቹ ክፍተት ያሾልካሉ፤ ይሄኔ አንቆ ይይዛቸውና ከታች ወደ ላይ ይዘቀዝቃቸዋል፡፡ አቤት የአይናቸው ንጣት!
አሁን ምናለ እነዚያን ጭንቅላቶች ቢሸፍኗቸው ወይ ገለል ቢያደርጓቸው፡፡ የሁኔታውን አሰቃቂነት በትንሹም እንኳ ይቀንሰው ነበር፡፡
IX
ሴትየዋ ቀን ቀን የምትወጣ ይመስለኛል፡፡
ለምን እንዲያ እንደመሰለኝ ልንገራችሁ? በአይኔ በብረቱ አይቻታለሁ፡፡ ምስጢር ነው ግን፡፡ በሁሉም የክፍሉ መስኮቶች በኩል ትታየኛለች!
ሁሌም የማያት አንዲት፣ ተመሳሳይ ሴት ናት፡፡ ይህን ደግሞ እንዴት እንዳወቅሁኝ ልንገራችሁ? ሴትዮዋ ሁሌም ትድሃለች፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች ደግሞ ቀን፣ በብርሃን አይድዂም፡፡ ቀጭኑ መንገድ ላይ፣ የአትክልት ስፍራው ውስጥ፣ የወይኑ ጥላ ስር ስትድሃ አያታለሁ፡፡ ዛፎቹ ስር ያለው ሰፊ መንገድ ላይ ትድኸለች፡፡ ሰረገላ ሲመጣ የወይኑ ተክል ስር ትደበቃለች፡፡ ይህቺን ታህል አልወቅሳትም፡፡ በቀን፣ ለዚያውም በብርሃን ሲድኹ መታየት በራሱ ለጉድ ያዋርዳል፡፡ እኔ ቀን፣ ቀን የምድኸው በሬን ቆልፌ ነው፡፡ ጆን ስድኽ ካየኝ የሆነ ነገር ሊጠረጥር ስለሚችል ለሊት አልድኽም፡፡
ጆን ሰሞኑን ፀባዩ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡ እንዳላበሳጨው እጠነቀቃለሁ፡፡ ሌላ ክፍል ውስጥ ቢኖር እንዴት መልካም ነበር! ከእኔ ሌላ ማንም ሰው ሴትየዋ በምሽት ከዚያ እንድትወጣ እንዲያደርግ አልፈልግም፡፡
ሴትዬዋን በሁሉም መስኮቶች በኩል ማየት እችል እንደሁ ሀሳብ ገባኝ፡፡ ሞከርኩ፡፡ አልቻልኩም፡፡ በተቻለኝ ፍጥነት ሁሉ ብዞር በአንዴ ላያት የምችለው በአንድ መስኮት ብቻ ነው፡፡
በሁሉም መስኮቶች በአንዴ የማትታየኝ፣ እሷ የምትድኽበት ፍጥነት እኔ ከምዞርበት ፍጥነት በልጦ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴም እጅግ እርቃ ወደ መሀል ከተማው ለመሄድ ስትድኽ አያታለሁ፡፡ ሀይለኛ ነፋስ እንደሚነዳው ደመና ነው ፍጥነቷ፡፡ በአንዴ ውልብ ትላለች፡፡
X
ምናለ አብዩን ንድፍ ከንዑሱ ንድፍ ላይ ማንሳት ቢቻል ኖሮ! ማለቴ ለማንሳት መሞከሩ እራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ ቀስ እያሉ፤ አንድ በአንድ፡፡
ሌላም አዲስ ነገር ተገለጠልኝ፡፡ አሁን አልናገረውም ግን፡፡ ሰዎችን አብዝቶ ማመን ደግ አይደለም፡፡ ይህን ወረቀት ቀዶ ለመጣል ሁለት ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩኝ፡፡ ጆን ሳይነቃብኝ አይቀርም፡፡ አስተያየቱን አልወደድኩትም፡፡ ጄኒን ስለ እኔ ብዙ ጥያቄዎች ሲጠይቃት ሰምቻለሁ፡፡ እሷም ብዙ የምትመልሰው ነበራት፡፡
ቀኑን ሙሉ ተኝቼ እንደምውል ነገረችው፡፡ ለሊት እንደማልተኛ ጆን ያውቃል፤ አንዲትም ትንፋሽ ስለማላሰማ እንዳላንቀላፋሁ ያውቃል፡፡ እኔንም ብዙ ጥያቄዎች ጠየቀኝ፡፡ አፍቃሪና ሩህሩህ ለመምሰል ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ ዘልቄ እንደማየው አያውቅም እንዴ!
ይህ የግድግዳ ወረቀት ያለበት ክፍል ውስጥ ሶስት ወራት ሙሉ ኖሮ ጸባዩ እንዲህ ባይሆን ነበር የሚገርመኝ፡፡ ወረቀቱ እኔን ይመስጠኛል፡፡ እደመምበታለሁ፡፡ በቃ፡፡ የጆንንና የጄኒን ጤና ግን ሳያቃውሰው አልቀረም፡፡
XI
ብራቮ! ዛሬ የመጨረሻ ቀናችን ነው፡፡ በቂ ነው፡፡ ጆን፣ ከተማ ትንሽ ይቆያል፤ ስለዚህ የዛሬንም ምሽት የምናሳልፈው እዚሁ ነው፡፡ ጄኒ ለሊቱን ከእኔ ጋር ልትሆን፤ እኔ ጋ ልትተኛ ፈልጋለች፡፡ አጭበርባሪ ነገር! ለሊቱን ብቻዬን ብሆን የተሻለ እረፍት እንደማገኝ ነገርኳት፡፡
ጄኒን ሸወድኳት፡፡ ጮሌ ሆኛለሁ፡፡ ብቻዬን አይደለሁማ፡፡ ልክ ጨረቃ ስትወጣ ያቺ ምስኪን መዳኽ ትጀምራለች፤ የብረት ዘንጎቹንም ትነቀንቃለች፡፡ ያኔ ልረዳት እነሳለሁ፡፡
እኔ እጎትታለሁ፤ እሷ ትስባለች፤ እኔ እጎትታለሁ፣ እሷ ትስባለች፡፡ እንዲህ እያደረግን ሳይነጋ በፊት ብዙውን የወረቀቱን ክፍል ቀዳደን ጨረስን፡፡ ወደ ላይ የእኔን ቁመት ያህልና ወደ ጎን ደግሞ የክፍሉን ግማሽ የሚሆን ቦጫጨቅን፡፡ ማለዳ ሲሆን ያ አስቀያሚ ንድፍ እንደለመደው ሳቀብኝ፡፡ ዛሬውኑ ድራሹን ላጠፋው ወሰንኩ!
ነገ ነው ከዚህ ለቀን የምንሄደው እና ክፍሉ ውስጥ ያሉትን እቃዎች ወደ አመጣንባቸው፣ እታች ወዳሉት ክፍሎች እያጓጓዙ ናቸው፡፡
ጄኒ የክፍሉን ግድግዳ በመገረም አየችው፡፡ ሆን ብዬ እንዲያ እንደ አደረግሁት ፈታ ብዬ ነገርኳት፡፡ ሳቀች፡፡ እሷ እራሱ ብትገነጣጥለው ደስ ይላት እንደነበር ነገረችኝ፡፡ በዚህ የማይረባ ነገር ጥላቻና እልህ ተይዤ ግን ይህን ያህል እራሴን ማድከም እንዳልነበረብኝ ነገረቺኝ፡፡
እንዲህ እራሷን አጋልጣ አታውቅም!
አንድም ሰው፣ ከእኔ በቀር አንድም ሰው ወረቀቱን ንክች እንዲያደርግ አልፈቅድም፡፡ እንዲያ አድርጎ በህይወት አይቆያትም፡፡ እገድለዋለሁ፡፡
ክፍሉን መልቀቅ እንዳለብኝ ነገረችኝ፡፡ እንዲያ እንደምትል የሚጠበቅና ግልፅ ነው፡፡ በበኩሌ አሁን ክፍሉ ባዶ፣ ንጹህና ፀጥ ያለ ስለሆነ እዚሁ ቆይቼ ማረፍና የምችለውን ያህል እንቅልፍ ማግኘት እንደምፈልግ ነገርኳት፡፡ በተቻለ መጠን እንዳትቀሰቅሰኝ አስጠነቀቅኋት፡፡ እራት ምናምን ብሎ ነገር የለም፤ መተኛት ነው የምፈልገው፡፡ ስነቃ እኔው እራሴ እጣራለሁ፡፡
ጄኒም ሄዳለች፤ ሰራተኞቹም ሄደዋል፤ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት እቃዎችም ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል፡፡ የቀረው ትልቁና ሰፊው አልጋ ብቻ ነው፤ ድሮ አብሮት የነበረው የሸራ ትራስ አሁንም አብሮት አለ፡፡
እቅዳችን እንዲህ ነው፡- ዛሬ ታች ያሉት ክፍሎች ውስጥ እናድራለን፤ ሲነጋ በጀልባ ወደ ቤታችን፡፡ ክፍሉ ተመልሶ እንደድሮው ኦና ሆኗል፡፡ ተመቸኝ፡፡ ህፃናቱ እንዴት አድርገው ክፍሉን እንዳወደሙት አትጠይቁኝ!
አልጋውም የተረፈው በደንብ ተደርጎ ከመሬቱ ጋር ስለተሰፋ ነው፡፡
አሁን ወደ ስራዬ፡፡
ቤቱን ቆለፍኩኝና ቁልፉን ፊት ለፊት ወዳለው መተላለፊያ ወረወርኩት፡፡ ጆን እስኪመጣ እኔም ካለሁበት አልወጣም፤ ሌሎችንም ወዳለሁበት አላስገባም፡፡ ጆንን ትንሽዬ ላስደንቀው ፈልጌያለሁ፡፡
ገመድ አለኝ፡፡ እንዴት እንደተዘጋጀሁ አያችሁ፡፡ ገመዱን ከጄኒ እንኳን መደበቅ ችያለሁ፡፡ ያቺ ሴትዮ ብትወጣና ለማምለጥ ብትሞክር ጥፍር አድርጌ አስራታለሁ፡፡
አንድ የረሳሁት ነገር አለ፡፡ የሆነ ነገር ላይ ካልቆምኩ ገመዱን ከፍታ ላይ ማሰር አልችልም፡፡ አልጋው ደግሞ ንቅንቅ አይልም!
በድካም ዝዬ፣ ሽባ እስከምሆን ድረስ አልጋውን ጎተትኩት፡፡ ፍንክች አላለም፡፡
ተናደድኩኝና ነከስኩት፡፡ ምንም ያተረፍኩት ነገር የለም፡፡ ጥርሴን አሳመመኝ እንዲያውም፡፡
ወለሉ ላይ ሆኜ የምደርስበትን ርቀት ያህል ወረቀቱን ቀዳደድኩት፡፡ ከግድግዳው ጋር ለጉድ ነው የተጣበቀው፡፡ በዚህ ተደስቷል፡፡ እኒያ ሁሉ የታነቁ እራሶች፣ ፍጥርቅ ያሉ አይኖች፣ በየቦታው ያቆጠቆጡ ፈንገሶች በአንድነት ሆነው በንቀትና በፌዝ አሽካኩብኝ፡፡
የፈለግሁትን አይነት አደገኛ ስራ ለመስራት፣ በቂ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- ከመስኮቱ ላይ ቁልቁል መፈጥፈጥ ማንም ሊያደንቅልኝ የሚችል ምርጥ የሰውነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ? መስኮቱ እንኳንስ ሊገነጥሏቸው፤ ሊነቀንቋቸው በሚከብዱ የብረት ዘንጎች ታጥሯል፡፡
ከመስኮቱ ላይ መፈጥፈጡን አልሞክረውም፡፡ የምሬን ነው፡፡ እንዲያ ማድረግ አንድም ተገቢ አይደለም፤ አንድም ሰዎች ድርጊቴን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ፡፡ በመስኮቱ በኩል መመልከት ያስጠላኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? በዚያ በኩል ስመለከት ብዙ ሴቶች፣ በፍጥነት ሲድኹ ይታየኛል፡፡ እኒህ ሴቶች ልክ እንደ እኔ ከግድግዳው ወረቀት ውስጥ ይሆን እንዴ የወጡት?
እኔን ልክ እንደነዚህ ሴቶች አደባባይ ልታወጡኝ አትችሉም፡፡ በብልሃት፣ ደብቄ ባኖርኩት ገመድ እራሴን አስሬያለሁ፡፡ ምሽት ሲመጣ ወደ ነበርኩበት ንድፍ እመለሳለሁ፡፡ እንዲያ ማድረግ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ይከብዳል፡፡ እዚህ ክፍል ውስጥ እንደፈለግሁት እየዳኹ ነው፡፡ እጅግ ደስ ይላል፡፡ ወደ ውጪ መውጣት አልፈልግም፡፡ ጄኒ እራሷ እንድወጣ ብትጠይቀኝ አልወጣም፡፡
አንድ፡- ውጪ የሚዳኸው መሬቱ ላይ ነው፡፡ ሁለት፡- ውጪ ያለው ቀለም ቢጫ መሆን ሲገባው አረንጓዴ ነው፡፡
እዚህ ክፍል ውስጥ በፈለግሁት ፍጥነት መዳኽ፣ ዝግ ብዬ መዳኽ እችላለሁ፡፡ እያንዳንዱን ጥግ ስለማውቅ መንገዱ አይጠፋኝም፡፡
ጆን መጣ፡፡
መጣ አልመጣ ምን ይረባል? ምንም ረብ የለውም፡፡ ወጣቱ ሆይ በሩን ልትከፍተው አትችልም፡፡
እንዴት ጮኾ እንደሚጣራና እንዴት በሩን እንደሚደበድብ በሰማችሁት!
መጥረቢያ አምጡልኝ ብሎ ጮኸ!
ይህን መሳይ ውብ በር ሊፈልጥ? አሳፋሪ ነው!
“ጆን፣ የኔ ውድ!” አልኩኝ እጅግ ለስላሳ በሆነ ድምጽ፡- “ቁልፉ ያለው የመጀመሪያዎቹን ደረጃዎች እንደወረድክ ያለው ተክል ስር ነው፡፡”
ይህ ለቅጽበት ፀጥ አሰኘው፡፡
እንደጠበኩት እጅግ ረጋ ብሎ፡- “በሩን ክፈቺው የኔ ፍቅር!” አለኝ፡፡
“አልችልም፡፡” አልኩት፡- “ቁልፉ ያለው ታች በሩ ፊት ለፊት ያለው ተክል ስር ነው፡፡”
ያልኩትን ደገምኩለት፡፡ ረጋ፣ ቀስ ብዬ ደገምኩለት፡፡ አሁንም ደገምኩለት፡፡ አሁንም፡፡ ቁልፉ አለ ብዬ ወደ ነገርኩት ቦታ መሄድ እንዳለበት አወቀ፡፡ ሄደ፡፡ አገኘው፡፡ መጣ፡፡ ገባ፡፡ በሩ ጋ ቆሞ ቀረ፡፡
“ምንድነው ነገሩ ?!” ጮኸ፡፡ “የአምላክ ያለህ፤ ምንድነው እያደረግሽ ያለሽው?!”
እኔ እንደሁ መዳኼን ቀጥያለሁ፡፡ መዳኼን ሳላቋርጥ ጠምዘዝ ብዬ በትከሻዬ ላይ አየሁት፡፡
“በመጨረሻም ወጣሁ፡፡” አልኩኝ፡- “የአንተንም የጄኒንም ጥረት ሁሉ ተቋቁሜ፣ አሸንፌ ወጣሁ፡፡ ወረቀቱን ሁሉ ስለቀዳደድኩት መልሳችሁ ልታስገቡኝ አትችሉም!”
አሁን ይህ ሰው ምን ይሁን ብሎ ነው ራሱን የሳተው? የምር ራሱን ስቷል፡፡ ደሞም መንገዴ ላይ ነው የተጋደመው፡፡ ስመላለስ በእሱ ላይ እየዳኽኩ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. 1892 ዓ.ም.
(የእንግሊዝኛው ርዕስ፡- The Yellow Wall-Paper)
ስለ ደራሲዋ፡-
ቻርሎቴ ፐርኪንስ ጊልማን እ.ኤ.አ. ጁላይ 3 ቀን 1860 ዓ.ም. ተወለደች፡፡ ቻርሎቴ ቀንደኛ ፌሚኒስት፣ ሶሲዮሎጂሰት፣ ደራሲና የዪኒቨርስቲ መምህርት ነበረች፡፡ አስተሳሰቧ፣ አስተህምሮዋ፣ አኗኗሯ ሁሉ ‘የተለመደው’ ወይም ‘ከሴቶች የሚጠበቀው’ አይነት አልነበረም፡፡ ስራዎቿም፣ ኑሮዋም የጊዜው ጋዜጣና መፅሄቶች የፊት ገፅ ዜና ነበሩ፡፡
The Yellow Wall-Paper የሚለውንና በእራሷ ህይወት ላይ የተመሰረተውን አጭር ልብ-ወለዷን የፃፈችው በ1892 ዓ.ም. ነበር፡፡ በ 32 ዓመቷ፡፡ የመጀመሪያ ልጇን እንደወለደች postpartum-psychosis የሚባል በሽታ ታማ ነበር፡፡ በሽታው መውለድን ተከትሎ የሚከሰት ነው፡፡ የሚገርመው በሽታው፣ ሚስቶቻቸው ሲወልዱ አንዳንድ ወንዶች ላይም ይከሰታል፡፡ ከበሽታው ስቃይም የሚከተሉት ይገኙበታል፡- በጥልቅ ሀዘን መዋጥ፣ ከፍተኛ ድካም፣ የሌለ ነገር ማየት እና መስማት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የምግብ አወሳሰድ መዛባት፣ ያለ ምክንያት ማልቀስ፣ መጨነቅ፣ እና በትንሽ ትልቁ መናደድ ናቸው፡፡
ቻርሎቴ ኦገስት 17 ቀን1935 ዓ.ም. ሞተች፡፡ እራሷን አጠፋች፡፡ ይገርማል፡፡ የሚገርመው እራሷን ማጥፋቷ አይደለም፤ እራሷን የገደለችው በ 75 ዓመቷ ነበር፡፡ ሞት በእራሱ ጊዜ መምጣቱ ቅርብ ነበር ያላለ አልነበረም፡፡
Saturday, 13 February 2016 11:21
እኔ አውቅልሻለሁ
Written by ደራሲ፡- ቻርሎቴ ፐርኪንስ ጊልማን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Published in
ልብ-ወለድ