Saturday, 13 February 2016 11:55

ከ2 ቢ. ብር በላይ በሆነ ወጪ የህፃናት ሆስፒታል ሊገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአህጉሪቱ በትልቅነቱ ሊጠቀስ የሚችል የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ሊገባ ነው፡፡
በአለርት ማዕከል ግቢ ውስጥ ይገነባል የተባለው ይኸው የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተሟላና በሙያው በብቃት በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የተደራጀ እንደሚሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ የግንባታ ሥራ በቀጣዩ አመት እንደሚጀመርም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የአለርት ማዕከል በ1.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የእናቶች ህክምና መስጫና ማዋለጃ ማዕከል ባለፈው ማክሰኞ መርቀው የከፈቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ፤ ማዕከሉ መንግስት የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያደርገው ርብርብ አንዱ አካል የሆነውን የጤና ተቋማትን የማስፋፋት ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው እናቶች በማዕከሉ ተገቢውን ክብካቤና የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ዋንኛ ሥራው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የማዋለጃ ማዕከሉ፤ የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ የማዋለድ አገልግሎት፤ የድህረ ወሊድ ክትትል፣ የማህፀን ቀዶ ህክምና፣ የቤተሰብ ምጣኔና የክትባት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን 22 የመኝታ አልጋዎች፣ 5 የማማጫ አልጋዎች፣ ሁለት የኦፕሬሽን ማድረጊያ ጠረጴዛዎች ያሉትና የሪከቨሪ ስክራብ ሩም የተሟሉለት መሆኑም ታውቋል፡፡

Read 3985 times