Print this page
Saturday, 13 February 2016 11:57

አዲሱ ጉንፋን መሰል የኢንፍሌዌንዛ በሽታ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ኤኤችዋን ኤንዋን (AHINI) የተባለው አዲሱ ጉንፋን መሰል ኢንፍሌዌንዛ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተቀስቅሶ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በጥር ወር ብቻ በተደረገ ቅኝት፣ 32 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውንና ከእነዚህ መካከልም አራቱ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ዳዲ ጂማ ተናግረዋል፡፡
ወቅትን ጠብቆ የሚቀሰቀስ ጉንፋን መሰል በሽታ እንደሆነ የተነገረለት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ፤በፍጥነት ከሚዛመቱ በሽታዎች መካከል የሚመደብ ሲሆን ተገቢው ህክምና ካልተደረገለትም ለሞት ሊያጋልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
እንደ ማንኛውም የጉንፋን በሽታ በትንፋሽና ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ የህዝብ ትራንስፖርቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ሰዎች በስፋት የሚሰባሰቡባቸው ሥፍራዎች በሽታውን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ለማስተላለፍ ምቹ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በሽታው በተለይም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትንና ከስልሣ አምስት አመት በላይ የሆናቸውን ሰዎች እንዲሁም ነፍሰ ጡር ሴቶችን በይበልጥ ያጠቃል፡፡ አንድ ሰው ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ እያለ ምንም አይነት የህመም ስሜቶች ሳይኖሩት በሽታውን ሊያስተላልፍ እንደሚችልና ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከ5-7 ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንደሚተላለፍ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
 በስኳር፣ በደም ግፊት፣ በልብና የኩላሊት በሽታዎች መያዝ ለኢንፍሉዌንዛ ይበልጥ ተጋላጭ  የሚያደርግ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ላይ በቀላሉ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡ በጉንፋን መሰሉ ኢንፍሎዌንዛ የተያዘ ሰው ከመደበኛው የጉንፋን በሽታ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ትኩሳት፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መከርከርና የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመሞች፣ የአፍንጫ ፈሳሾችና ማስነጠስ የበሽታው ዋንኛ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በታዩ ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ኤኤችዋን ኤንዋን የተባለው ኢንፍሌዌንዛ፤ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ሲሆን በዓለም በየዓመቱ ከ3-5 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙና ከ500ሺ በላይ የሚሆኑት በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከአለም ጤና ድርጅት የተኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በላብራቶሪ ምርመራ የተገኙት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ ናሙናዎች አሜሪካ አገር ወደሚገኘው “ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል” (CDC) መላካቸውንና ይህም የተደረገው በሽታው በየጊዜው ባህርይውን ስለሚለዋውጥ፣ ለተጨማሪ ምርመራ እንደሆነ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የአለም ጤና ድርጅት፤አለም አቀፍ የጤና ሥጋት እንደሆነ የጠቆመው የዚካ ቫይረስ በአገራችን መከሰቱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እስከ አሁን አለመገኘታቸውንና አገሪቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን የገለፁት የሥራ ኃላፊዎች፤ የቫይረሱን መኖር አለመኖር ለማረጋገጥ የሚያስችል ኬሚካል ከውጪ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ቫይረሱ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ እንደነበር የሚያሳዩ ፍንጮች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡  

Read 8789 times
Administrator

Latest from Administrator