Saturday, 13 February 2016 11:58

ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች፤ ለቲማቲም በሽታ መድሃኒት አገኙ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የቲማቲም ምርቶችን በማጥቃት ከፍተኛ ውድመት ያደርሳሉ ለተባሉ በሽታዎች፣ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች  አዲስ መድሃኒት በምርምር ማግኘታቸውን ገለፁ፡፡
“ኬንት ፓወር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኸው መድሃኒት፤ በቲማቲም ተክል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ባክቴሪያና ፈንገሶችን የሚያጠፋና ምርቱ በቫይረስ እንዳይጠቃ የሚከላከል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ተገኘ ዘለቀና ታደሰ ገ/ኪሮስ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በቲማቲም ምርቶች ላይ በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ በሽታዎች ሳቢያ ምርቱ ስለሚቀንስ በበቂ መጠን ለገበያ ሊቀርብ አለመቻሉን የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፤  በምርቱ ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳና አምራቹም በለፋው መጠን አምርቶ ለተጠቃሚው ምርቱን በበቂ መጠን የሚያቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አስበው ወደ ምርምር መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ተማራማሪዎች፤ ከሁለት ዓመታት እልህ አስጨራሽ የምርምር ጥረትና ትጋት በኋላ ነው የቲማቲም በሽታዎችን ማጥፋትና መከላከል የሚችል መድሃኒት ማግኘታቸውን ይፋ ያደረጉት፡፡
በተመራማሪዎቹ የተገኘው ኬንት ፓወር የተሰኘው ይኸው መድሃኒት፤ ቀደም ሲል ከነበረውና አርሶ አደሩ ከሚጠቀመው ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች በዋጋው በእጅጉ ያነሰና በአገልግሎቱ የተሻለ መሆኑን ታውቋል፡፡ በአንድ የቲማቲም ምርት ዘመን፣ በስድስት ሄክታር መሬት ላይ የተዘራውን የቲማቲም ምርት ከበሽታ ለመከላከል ከውጪ የሚገባውን መድሃኒት የሚጠቀም አርሶ አደር ከ63ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ተማራማሪዎቹ፤ አዲሱን “ኬንት ፓወር” ግን በስድስት ሺህ ብር ብቻ ገዝተው፣ በበሽታ ያልተጠቃና በመድሃኒት ያልተበከለ ንፁህ የቲማቲም ምርት ማግኘት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህንኑ የምርምር ግኝታቸውን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ሰርተፍኬት ያገኙ ሲሆን በምርምር ያገኙትን መድሃኒት ለአርሶ አደሩ በስፋት ለማድረስ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የምርምር ውጤታቸውን በፋብሪካ ደረጃ እያመረቱ ለተጠቃሚው ለማድረስ 23 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ለፋብሪካው ግንባታ የሚሆን የቦታ ጥናት ማድረጋቸውንም ተመራማሪዎቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁመዋል፡፡ 

Read 6268 times