Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 18 February 2012 11:13

አዘለም፣ አንጠለጠለም… ያው ተሸከመ ነው!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሰው እህል ሊሸምት ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ አንድ የበቀቀን (ፓሮት) ነጋዴ ያገኛል፡፡ ያ ነጋዴ የያዘው የሚሸጥ ወፍ መልኩ በጣም ያምራል፡፡ ስለዚህ ይሄንን ወፍ ለምን አልገዛውም በጣም ውብ መልክ አለው፤ ሲል ያስባል፡፡

ገዢው ሰው ወደ ነጋዴው ጠጋ ብሎ፤

“ይህ ወፍ ዋጋው ስንት ነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡

ሻጩም፤ “አንድ ሺ ብር ነው” ይለዋል፡፡

ገዢ፤ “ለአንድ ወፍ? አንድ ሺህ ብር?” ሲል በመገረም ይጠይቃል፡፡

ሻጩ፤ “ወዳጄ፤ ወፉ ዝም ብሎ ወፍ አይምሰልህ፡፡ በቀቀን (ፓሮት) የሚባለው ወፍ ነው”

ገዢ፤ “በቀቀን? በቀቀን ምንድን ነው? እንደ ዶሮ ወይም እንደ ጅግራ የሚበላ ነው እንዴ?”

ሻጩ፤ “የለም፡፡ አይበላም”

ገዢ፤ “ታዲያ ካልተበላ ለምን ተወደደ?”

ሻጩ፤ “ይሄውልህ ወዳጄ፤ በቀቀን በዓለም ካሉት ወፎች ሁሉ የተለየ ባህሪ ያለው ነው:-

1ኛ) የትኛውም ቦታ ወይም ቤት ብትወስደው ወዲያውኑ ኑሮውን የመልመድና የመዋሃድ ችሎታ አለው፡፡ ለማዳ ነው፡፡

2ኛ) ዋንኛውና የሚደነቅበት ጥበቡ የተነገረውን ነገር፣ ደግሞ የመናገር ወይም የመቅዳት ችሎታ የተካነ መሆኑ ነው፡፡

እናም ስታስበው ታዲያ፤ ለዚህ አይነት ወፍ አንድ ሺ ብር መክፈል፤ ያውም በዛሬ ጊዜ፣ ያንሰዋል እንጂ ይበዛበታል ትላለህ?

ገዢ፤ “እሺ ጫጩቷን እንኳን መርቅልኝ”

ሻጭ፤ “ወዳጄ የንግግር ጫጩት የለውም፡፡ ትልቁም በቀቀን ትንሹም በቀቀን አፋቸው ያው ነው፡፡ እንደውም፤ ትንሹ በቀቀን ልጅ ስለሆነ በልጅ አንጐሉ የበለጠ የሰማውን ማስተጋባት ይችላል!” አለው፡፡

ገዢው ሰውዬ ነገሩ አሳመነውና የተጠየቀውን ከፍሎ ያን በቀቀን ገዝቶ ወደ ቤቱ ይወስደዋል፡፡

ቤት ውስጥ፤ እውነትም በቀቀን ሆዬ በአንዴ ለመደ፡፡ አንዴ ሳሎን፣ አንዴ ጓዳ፣ አንዴ መኝታ ቤት፣ አንዴ በረንዳ… እየተቀመጠ፤ የቤቱን አባወራ፣ የሚስቲቱን፣ የልጆቹን ወሬና ንግግር ሁሉ ማስተጋባቱን ቀጠለ፡፡ ጩኸቱ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ የሚያባራ አይደለም፡፡

ይህንን ጩኸት የሰማው የቤት ውስጥ ድመት በጣም ተበሳጨና፤

“አንተ ወፍ እንደዚህ ለመጮህ ማነው መብት የሰጠህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡

በቀቀኑም፤ “የቤቱ ጌቶች፤ ያው ያንተም ጌቶች ናቸዋ!”

ድመት፤ “እኔ እድሜ ልኬን እዚህ ቤት ውስጥ ስኖር፤ ያውም አይጥ እያደንኩላቸው፣ እህልና ልብስ እንዳይበላባቸው እየተከላከልኩላቸው፤ ትንሽ ጮክ ብዬ ‘ሚያው’ ያልኩኝ እንደሆን እንኳ፤ “ክፍ! ክፍ! ውጣ! ውጣ!’” እያሉ ያባርሩኛል፡፡ አንተ ግን እንደዚህ ከጣራ በላይ እየጮህክ የሚነካህ የለም!” ሲል በምሬት ተናገረ፡፡

ይሄኔ በቀቀን፤

“አይ ወዳጄ ድመት! ጩኸት ቢሉህ እንዲያው ጩኸት መሰለህ ወይ? ሰዎቹ የሚፈልጉት የነሱን ድምፅ የሚያስተጋባላቸውን ነው፡፡ የራስህ ድምፅና የራስህ ጩኸት ያለህ ከሆንክማ አትፈለግም፡፡ እኔን በደንብ አስተውለኸኝና አዳምጠኸኝ ከሆነ የነሱን ንግግር ልቅም አድርጌ ቀድቼ፤ አንዳንዴም ከእነሱ በላይ ጮኬ፤ አስተጋባለሁ፡፡ ስለዚህም እኔን መቃወም እራሳቸውን እንደመቃወም ይሆንባቸዋል፡፡ ለዚህ ሲሉ እንደ ልቤ የመጮህ ነፃነት ሰጥተውኛል!” ሲል በጥሞና አስረዳው፡፡

ድመት ነገሩ ቢያሳዝነውም እውነትነቱ ስለገባው፤

“ወዳጄ በቀቀን! በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንዳንተ እውነቷን የሚናገር አይገኝም፡፡ እኔም ለነውሻ፤ ለነዶሮ፣ ለነላም፣ ለነበግ ሁሉ ይሄንኑ አስረዳቸዋለሁ!” ብሎ ድመት ወደ አይጥ አደኑ ሄደ!

***

የሚጮህላቸውን፣ የሚከላከልላቸውን፣ ከሚገፉ ያድነን!

ከራሳችን ኦርጅናሌ ድምፅ፣ የቅጂ ድምፅ የበለጠ ከሚሰማበት ዘመን ይሰውረን፡፡ ኦርጅናሌ ድምፅ ከሌለ፣ ኦርጅናሌ እውቀት ይጠፋል፡፡ ኦርጅናሌ እውቀት ሲጠፋ፤ ኦርጅናሌ ሰው ይጠፋል፡፡ ኦርጅናሌ ሰው ሲጠፋ፣ ሁሉም ነገር ልሙጥ ይሆናል፡፡ የተለወጠ ሃሳብ፣ የተለየ አስተያየት፣ የተለየ አመለካከት ይጠፋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለውጥ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ “ጌቶች እንዳሉት…” “ጓዱ ባለው ላይ የማክለው”… “ሌሎቹ ጨርሰውታል፤ ግን ለመጨመር ያህል”… “የቀደመው ተናጋሪ ያለው እንደተጠበቀ ሆኖ”… የሚሉ የደጀ-ጠኚ ንግግሮች የውይይት ሁሉ መግቢያ እየተደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ “የሁሉን እሺ”፤ “የሁሉም ልክ ነው”… አይነት እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ ሃሳብ ማንሸራሸር ሳይሆን ሃሳብ ማቀባበል ይዘወተራል፡፡

በአለፈው ዘመን አንድ የንቃት ውይይት ላይ፤ አንዱ ካድሬ… “ሌኒን እንዳለው… ሌኒን ደህና አድርጐ እንዳብራራው… ሌኒን በትክክል እንዳስቀመጠው…” እያለ ትምህርት ሲሰጥ ቆይቶ ስብሰባው ሲበተን፤ አንድ፤ ነገር አዋቂና ተጨዋች ናቸው የሚባሉ አዛውንት ያገኛል፡፡ ስለተካሄደው ውይይት አስተያየት እንዲሰጡት ፈልጐ “እህስ ስብሰባው እንዴት ነበር? ጥሩ አድርጌ አላስረዳሁም ወይ?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ አዛውንቱም ጢማቸውን እየደባበሱና በትእዝብት ዐይን እያዩት… “አዎ በደንብ አዳምጬሃለሁ… ጥሩ ተናግረሃል… እንደሰማሁት ‘ሌኒን በትክክል እንዳስቀመጠው’ ስትል ነበር?” አሉት፡፡ “አዎ ብያለሁ” አላቸው፡፡ እሳቸውም፤ “ታዲያ ሌኒን በትክክል ካስቀመጠው ምን መነካካት ያስፈልጋል? የራስህ ካለህ አትናገርም ኖሯል?!” አሉት ይባላል፡፡ እንደበቀቀን ሁላችንም አንዱ ያለውን መደጋገም፤ በአንድ አሸንዳ ውስጥ እንድንፈስስ ያደርገናል፡፡ ሌላው ቀርቶ የቃላት ለውጥ ለማምጣት እንኳ ይሳነናል፡፡ የየራሳችንን ሃሳብ የምንገልፅበት መንገድና ነፃነት ሊኖረን ይገባል፡፡ የየራሳችን ቀለም ሲኖር፤ ህብረ-ቀለሙ መጣጣሙ ወይም አለመጣጣሙ በቀላሉ ይታየናል፡፡ ለመለወጥ ወይ ለማረም የሚያስችለንን ድምፅ እስከምናገኝ ብዙ ልንሟገት፣ ብዙ ልንወያይ፤ አንድ ልንሆን ወይም ልንለያይ ይቻለናል፡፡ ወደ ጋራ ምት (common rhythm) የምንደርሰው ከብዙ ቅኝት በኋላ መሆን አለበት፡፡ የጋራ አገራዊ አመለካከት ማፍራት ብዙ ድካም አለበት፡፡ በሀገራችን ባየናቸውም ሆነ በምናያቸው የፖለቲካ ሙግቶች (political debates) (እነሱም ካሉ) ወደ ህብረ-ዝማሬ (chorus) የሚያደሉ የውዳሴ ንግግሮች፣ የድግግም ዲስኩሮች አሊያም የበቀቀን መፈክሮችን እንጂ፤ ከመንጋው ወጣ ያሉ ወይም ፍፁም የተለዩ የራስ እሳቤዎችን አንሰማም፡፡ አንዳንዴ የተለዩ የሚመስሉ - ከቃናው ውጪ ብቻ የሆኑ፤ ወይም “ለማለት ብቻ ማለት” የሚባሉትን አይነት ሆይ-ሆይታዎች፤ የጨረባ-ተዝካር (discord or dissonance) ሲፈጥሩ ይሰማሉ፡፡ በመሰረቱ ግን የሃሳብ ልዩነት የለም ነው ጉዳዩ፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡ “አዘለም አንጠለጠለም ያው ተሸከመ ነው” ነው ፖለቲካው! መለስ ብለን ንግግሮቻችንን እንመርምር፡፡ ለውጥ ያለው ከዚያ ባሻገር ነውና!!

 

 

Read 4500 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:17