Saturday, 13 February 2016 12:19

“ርህራሔና ክብር...ለጤናማ እናትነት”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ህዝብ ከሚቆጠርባቸው አገራት በ2/ተኛ ደረጃ የምትገኝ አገር ናት። የወሊድ መጠኑ በአንድ ሴት 4.1/ ሲሆን የእናቶች ሞት መጠን ደግሞ በ1000/ በሕይወት ከሚወለዱ ሕጻናት 420/መሆኑን ሰነዶች ያረጋግጣሉ። በተለያዩ ምክንያቶች አብዛኞቹ እናቶች ልጆቻ ቸውን የሚወልዱት በቤታቸው ሲሆን ወደሕክምና ተቋም በመምጣት በሰለጠነ ሰው ኃይል የሚወልዱት 15/በመቶ ብቻ ናቸው። ይህም ከአገልግሎት፣ ከእውቀት ማነስ፣ዝቅተኛ ከሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲሁም ተገቢውን አገልግሎት ከሕክምና ተቋማት ማግኘት አለመቻላቸውን ምክንያት በማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ጥር 2008/ የጤናማ እናትት ወር በሚል ለአመት እንዲታወስ ወይም እንደመሪ ቃል እንዲከበርና ተገቢው ስራ በእናቶች ጤንነት ዙሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራበት እንደውጭው አቆጣጠር ዲሴምበር 30/2008 ዓ/ም ለሚመለከታቸው ሁሉ በኢሜይል አሳውቆአል። ይህ ስያሜ ሲወጣ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም። ላለፉት አምስት አመታት በየአመቱ ጥር የተለያዩ መሪ ቃሎች እየወጡ የእናቶችን ጤና በማስጠበቅ ረገድ በጤና ጥበቃ ሚኒስር አማካኝነት የዘመቻ ስራ ሲሰራ ቆይቶአል። ለማስታወስ ያህልም፡-
በጤና ተቋም ስትወልድ እናት ጤና ልጅም ጤና፣
የእርግዝና ክትትል ማድረግ በጤና ተቋም ለመውለድ ይረዳል፣
ከወሊድ ጋር በተያያዘ ምክንያት ምንም እናት መሞት የለባትም፣
የድህረ ወሊድ ክትትልና ጥራት ያለው አገልግሎት ለእናትና ለልጅ ጤንነት መልካም ናቸው ...የሚሉት ይገኙበታል።
በዚህ አመት የተመረጠው ርእስ ደግሞ ክብርና ርህራሔ የተሞላበት የጤና አገልግሎት ለእናቶች እንዲሁም ለልጆቻቸው የሚል አንደምታ አለው።፡
ይህንኑ መሰረት በማድረግም በጤና ጥበቃ ሚኒስር በተቋቋመው ግብረ ኃይል ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አንድ እንግዳ ጋብዘናል። እንግዳው ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የቦርድ አባል ሲሆኑ በጆንስኖው ኢንኮርፖሬትድ ኢንትግሬትድ ፋሚሊ ኼልዝ ፕሮግራም የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናት ከፍተኛ አማካሪ ናቸው።
የዘንድሮው  የጤናማ እናትነት መሪ ቃል ክብርና ርህራሔ የተሞላበት አገልግሎት መስጠት የሚል ሲሆን ይህ አባባል ግን እንደ መሪ ቃል ከመውጣቱም በፊት እያንዳንዱ ሙያተኛ ወደስራ ሲገባ አስቀድሞ ለሚያገለግለው ህብረተሰብ ቃለ መሃላ የሚፈጽምበት ነው።  እንደ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ ማብራሪያ፡-
“...የህክምና ባለሙያዎቹ ቃለ መሀላ ፈጸሙ ማለት በእርግጥም ወደህብረተሰቡ ሲዘልቁ ምን እንደሚጠበቅባቸው እና ምን መፈጸም እንዳለባቸው ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያደርጋቸው መሆኑ አይካድም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህ ቃል ኪዳን አይጉዋደልም ማለት አይቻልም። እንዲሁም የተቋማቱም ዝግጁነት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በትክክል እንዲሰጡ ላያስችላቸው ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ አልፎ አልፎ እንደተደረጉ ጥናቶች መረጃነትም ከሶስት እናቶች አንድዋ ላይ ወይንም ከሰባት እናቶች በአንድዋ ላይ ክብር የሌለው አገልግሎት ለእናቶች የሚሰጥባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ያሳያሉ። ሰዎችን በተለያዩ መልኮች በመፈረጅ ማለትም...በሀብት፣በመማር፣ባለመማር በአካባቢ በመሳሰሉት በመለየትም የተዛባ የጤና አገልግሎት የሚሰጥባቸው አጋጣሚዎችም መኖራቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። አገልግሎቱን የሚሹ እናቶች ነጻነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊውን መረጃ አግኝተው በምጥ ሰአት የሚፈልጉትን ሰው አጠገባቸው አድርገው ...ወዘተ መስተናገድ አለባቸው። “
“...በኢትዮያ የጤና የአምስት አመት ስትራጂክ ፕላን ቀጣዩ ማለትም ከ2015-2020 ባለው ትኩረት የሚደረግባቸው ተብለው የተቀመጡ አራት ዋና ዋና መሰረታዊ ነገሮች አሉ።
ጥራትና ፍትሀዊነት ያለው የጤና አገልግሎት፣
የወረዳ ለውጥ ማምጣት፣
የመረጃ አብዮት አንዲኖርና መረጃን ውጤት ላለው ነገር ማብቃት፣
ርህራሄና ክብር ያላቸው የጤና ሙያተኞችን ማብቃት የሚል ነው።  
ስለዚህም ጥራት ያለውና ፍትሀዊ የሆነ የጤና አገልግሎትን ለማዳረስ የግድ ክብርና ርህራሔ የተሞላበት ማድረግ እናቶች የእርግዝና ክትትል እንዲያደርጉ፣ በተቋም መውለድ እንዲሁም ከወሊድ በሁዋላም የድህረ ወሊድ ክትትልን እንዲያደርጉ ያግዛል የሚል እምነት አለ። እንደተባለውም ማንኛውም የጤና ሙያተኛ ትምህርቱን አጠናቆ ወደስራ ከመግባቱ በፊት ሙያውን በትክክል ሊተገብር ቃለ መሀላ የሚፈጽም ቢሆንም ሁሉም በቃለ መሀላው መሰረት ስራውን በትክክል ያከናውናል ማለት ግን አይቻልም። አንዳንዴ የማይጠበቁ ምላሾች አይገጥሙም ማለት አይደልም። ስለዚህ በሁሉም ስፍራ በሁሉም ሰአት አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትና ሙያተኞች  ለእናቶች ርህራሄና ክብር በተመላው መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚጠበቅ መሆኑን መመሪያው ያስረዳል።”
ዶ/ር ብርሀኑ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የእናቶች ሞት መቀነስ ታይቶአል። በ1990/ እንደውጭው አቆጣጠር በመቶ ሺህ በሕይወት ከተወለዱ ሕጻናት 1400/አንድ ሺህ አራት መቶ የነበረው የእናቶች ሞት ቁጥር አሁን ያለው ከመቶ ሺህ በሕይወት ከተወለዱ ሕጻናት ወደ 350/ሶስት መቶ ሀምሳ ገደማ ነው። ለዚህ ደግሞ አስተዋጽኦ ያደረጉት የመጀመሪያው መልካም አስተዳደር ሲሆን ሌላው ደግሞ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች መኖራቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የጤና ሙያተኞች በተለያየ የሙያ አይነት መኖር እና የተቋማት መስፋፋት እንዲሁም ለሕክምና የሚያስፈልጉ አቅርቦቶች መሙዋላታቸው የእናቶችን ሞት እንዲቀንስ ከረዱት መካከል ናቸው። የጤና ጥበቃ ሚኒስር የእናቶችን ጤና በመጠበቁ ረገድ ማ/ ምን ማድረግ አለበት ለሚለው እንደመመሪያ የሚያገለግል ሰነድ አዘጋጅቶአል። እንደውጭው አቆጣጠር በ2016/ ይፋ የሚሆነው ሰነድ እናቶችና ሕጻናቶች በጋራ አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር ይገልጻል።በሰነዱ እንደተጠቆመውም የእናቶችን ጤንነት መጠበቅ የሕብረተሰቡን መብት እንደማክበር የሚቆጠር ነው። ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለእናቶች መስጠት ማለት ልክ የሴቶችን የትምህርትና የምግብ መብት እንደመጠበቅ እንዲሁም በጤናማ አካባቢ የመኖር እና በኢኮኖሚውና በውሳኔ ሰጭነቱም እንዲሳተፉ እንደማድረግ ሊቆጠር የሚገባው መብት ነው።
ምንም እንኩዋን የኢትዮጵያ መንግስት የጤና አገልግሎቱ እንዲስፋፋ እና እንዲሻሻል ትልቅ እርምጃ ቢወስድም በተለያዩ ማህበራዊ ባህላዊና በየጤና ተቋማቱ ሊኖሩ በሚችሉ የተጉዋደሉ  የአገልግሎት አሰጣጥ ምክንያቶች እንዲሁም የግለሰብን መብት መጣስ እና ተገቢውን መረጃ ለሚመለከተው ታካሚ አለመስጠትን ጨምሮ ክብርን መጋፋትና ለሰዎች እርህራሄን አለማሳየት የመሳሰሉት ችግሮች ሊታረሙ የሚገባቸው መሆኑ እሙን ነው። አንድ ጥናት እንደሚያመለ ክተው በኢትጵያ አንዳንድ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታሎች ውስጥ እናቶች በምጥ ሰአት የሚኖ ራቸውን ሕመም በትእግስት አለማስተናገድ የግለሰብ ክብርና መብት መጣስ እና ለታካሚዎች ግልጽ የሆነ መረጃ አለመስጠት የመሳሰሉት በሕክምናው ረገድ እርካታን የሚያጉዋድሉ መሆኑ ተጠቁሞአል። በእንደዚህ ያለ መስተንግዶ የተከፋች እናት በድጋሚ ወደ ጤና ተቋም ለእርግዝና ክትትል ሆነ ወይንም ለመውለድእና ከወሊድ በሁዋላም ቢሆን በቤትዋ መገልገልን እንደምት መርጥ አያጠራጥርም። የሰው ልጅ በማንኛውም መስፈርት ተፈጥሮአዊ የሆነ የሞራል ጥያቄ እንደሚኖረው አያጠራጥርምና።
ምንም እንኩዋን የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናትን ጤንነት በሚመለከት የተለያዩ መመሪያዎች እና ፖሊሲዎች ቢኖሩም በሀገር ደረጃ በየሆስፒታሎቹ ወይንም የህክምና ተቋማቱ የሚሰራ ባቸው እናቶችንና ጨቅላ ሕጻናቱን በአንድነት በፍቅር እርህራሔና ክብር ለማስተናገድ አስፈላጊውን ሁሉ የሚጠቁም ወጥ የሆነ እና  በግልጽ የተቀመጠ  አሰራር እስከአሁን የለም። የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች የህክምና ተቋማቱ እንዲሁም የባለሙያዎች ዝግጁነት በበርካታ ቦታዎች እናቶች በሚፈልጉት መንገድ እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ አይደሉም።
ስለሆነም ይህ እንደውጭው አቆጣጠር በ2016 የሚወጣው መመሪያ ጨቅላ ሕጻናቱንና እናቶችን በተለየ ክብር እና እርህራሔ ለማስተናገድ አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦችን የሚጠቁም ሲሆን ይህንን መሰረት በማድረግም ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያሟሉ ይጠበቃል።
አንድ የህክምና ተቋም፡-  
ወላዶችን የሚቀበሉበት ንጹህና ሞቃታማ ክፍል ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።
ምቹ የሆነ የመጸዳጃ ቤት እና የመታጠቢያ ቦታ ለእናቶችም ሆነ ለአስታማሚዎች ሊያዘጋጅ ይገባል።
የእራስን ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለታካሚውም ሆነ ሕክምናውን ለሚሰጠው ባለሙያ የስፈልጋል።
በሕክምና ተቋሙ ተኝተው የሚታከሙ እናቶች እያንዳንዳቸው የራሳቸውን አልጋ የሚከልልላቸው መከፋፈያ ተንቀሳቃሽ ግድግዳ ያስፈልጋቸዋል።  
መመሪያው አንደሚገልጸው ማንኛዋም ወላድ በማንነትዋ ማለትም በእምነት፣በባህል ልዩነት፣በእድሜ፣ በሃይማኖት፣በጎሳ፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምዋ፣ በአካል ጉዳት በመሳሰለው ሁሉ ሳትለይ እና ሳትናቅ አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ የማግኘት መብት አላት። አንዲት ወላድ ልጅ ለመውለድ በነጻነት የት መታከም እንዳለባት፣ በማን መታከም እንዳለባት መምረጥ ትችላለች።   

Read 2184 times