Saturday, 20 February 2016 09:32

‘ታዋቂነትና አዋቂነት…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ሀሳብ አለን… ‘ታዋቂነት በአቢሲንያ’ የሚል መጽሐፍ ይጻፍልን፡፡ ግራ ገባና! አሀ…አለ አይደል…ታዋቂ ማለት
ሀ. ‘ባያውቅም የሚያውቅ፣’
ለ. ‘ባይጸልይም መባረክ የሚችል፣’
ሐ.‘ባያነብም መፃሕፍት መተቸት የሚችል’’…
ምናምን እየተባለ ይዘርዘርልንና እኛም ግራ ከመጋባት እንትረፍማ፡፡
ስሙኝማ…መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ጠቅላላ ሚዲያው ለምኑም ለምናምኑም ‘አርቲስት’ የሚባሉትን ብቻ የሚጠራው ግርም አይላችሁም! አሀ… አርቲስቶች… “አይ ሀቭ ኤ ድሪም…” ብለው ሚዲያውን ከሰፊው ህዝብ መዳፍ ፈልቅቀው ያወጡት ይመስላላ! ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…በተለይ በበዓላት ቀናት ከምናያቸው የአርቲስቶች ቃለ መጠይቆችና በተለይ ደግሞ  ‘ጨዋታዎች’’… አንዳንዶቹ አሸማቃቂ እየሆኑ ነው፡፡ ያውም ልጆች እንኳን ከዛ በስንት እጥፍ በሚያስቡበት ዘመን!
እናላችሁ…ምን ችግር አለ መሰላችሁ…አርቲስቶች ወይም ‘ታዋቂ ሰዎች’ በየምክንያቱ ለቃለ መጠይቅ ሲቀርቡ… አለ አይደል… ከ‘ኪሎ በላይ’ የሆነ ጥያቄ እየተጠየቁ እኛንም ክው ያደርጉናል፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት የፊልም ሰው በቴሌቪዥን እየተጠየቀች ነበር፡፡ እናላችሁ… በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው የፊልም ኢንደስትሪ ከእኛ የተሻለ ስለመሆኑ አይነት ነገር ትጠየቃለች፡፡ እናላችሁ… እሷዬዋ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው…
“ምን እነሱ የሚያሳዩት ዶሮ ምናምን ነው…”
ምን ታድርግ…ከሁለትና ወይም ሦስት ፊልም ጋር ስለተነካካች ከ‘ኪሎ በላይ’ ስለ አፍሪካ የፊልም ኢንደስትሪ ተጠየቀቻ! ችግሩ ምን መሰላችሁ…የጥያቄ ቅደም ተከተሉ ልክ አይደለማ! መጀመሪያ መጠየቅ የነበረባት…
“አፍሪካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለተመልካቾቻችን ብትገልጪልን?” ተብሎ ነበር፡፡ እናማ…ጋዜጠኛው ዘሎ የፕሬሚየር ሊግ ጥያቄ ሲጠይቃት ምን ታድርግ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ብሔራዊ ዲቪዥን እንኳን ገና ሳይገባ የፕሬሚየር ሊግ ጥያቄ ሲቀርብ… “አይ ስለዚህ እንኳን ብዙም መረጃው የለኝም…”
“ይገርምሀል ይህንን እንኳን እኔም ማወቅ የምፈልገው ነው፣” ምናምን ማለት ማንን ገደለ! ይቅርታ ማንን ከ‘ታዋቂነት ዙፋን’ አወረደ!
እናማ…‘ጋዜጠኞች’… አለ አይደል… ‘ከኪሎ በላይ’ የሆኑ ጥያቄዎች እየጠየቅን ‘ታዋቂዎች’ን ‘ሄደውበት በማያውቁት’ መንገድ አንውሰዳቸውማ፡፡
ከ‘ኪሎ በላይ’ የሆነ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
በነገራችን ላይ ታዋቂ ስለሆኑ ብቻ ‘ሁሉንም ነገር አውቃለሁ’ አይነት ነገር እኛ ዘንድ ብቻ አይደለም፡፡ እነኚህ ምናቸውንም፣ ምናምናቸውንም እየኮረጅን (‘እየነጠቅን’ ማለትም ይቻላል፣) ‘ባዶአቸውን ሊቀሩ’ ጫፍ ላይ ያሉት ‘ፈረንጆች’ ቀላል ይዘባርቃሉ እንዴ!
አሽተን ኩቸር አሪፍ ተዋናይ ነው፡፡ እናላችሁ…. አንድ ጊዜ ምን አለ መሰላችሁ…
“ግንባርህ ላይ ያሉት መስመሮች ብዛት ምን ያህል ህይወቶች እንደኖርክ ይናገራሉ፡፡” አሁን ኩቸርን ፊልም ላይ ስታዩት ዘብረቅ ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን? እናማ…‘ታዋቂ’ መሆን ሌላ፣ ‘አዋቂ’ መሆን ሌላ! (ይቺን መፈክር ለማድረግ የፈለገ ‘ፍሪ ዳውንሎድ’ ፈቅጃለሁ፡፡)
እናላችሁ…እኛ ዘንድ አንዳንድ ጊዜ የግንባር መስመር ቆጠራ ድረስ ባይደርሱም…ከዚህ አይነቱ የማይሻል አስተያየት የሚሰጡ የእኛው ‘ታዋቂዎች’ አሉ፡፡
ሻኪል ኦኔል ምርጥ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ነው፡፡ በዛ ሰውነቱ ቅርጫት ኳስ ሜዳው ላይ ሲነግሥበት ስታዩት…አለ አይደል…አንዲትም የተዛባች ነገር ከአንደበቱ የምትወጣ አይመስላችሁም፡፡  (እውቅናና እውቀት ተቀላቀሉብና!)
ታዲያላችሁ…አንድ ጊዜ ግሪክን ጎብኝቶ አገሩ ይመለሳል፡፡ ግሪክን መጎብኘት ማለት ደግሞ በአብዛኛው እነኛን ጥንታዊ የስነ ህንጻ ጥበቦች ማየት ነው፡፡ እናማ…ጋዜጠኞቹ እነኚህን ጥንታዊ የግንባታ ጥበቦች መቼም ሳያይ አይመጣም ብለው “በጉብኝትህ ወቅት ፓርቴኖንን አይተኸዋል?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…
“እንደ እውነቱ የሄድኩባቸውን የምሽት ክበቦች ሁሉ ስማቸውን ማስታወስ አልችልም፡፡” ቂ…ቂ…ቂ… ይሄኔ ዘመዶቹ ‘ትከሻ ብቻ’ ሳይሉት አይቀሩም፡፡
ከ‘ኪሎ በላይ’ የሆነ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
አሁን፣ አሁንማ…አለ አይደል… ‘አዋቂ አላዋቂውም፣’ ‘አላዋቂ አዋቂውም፣’…ብቻ ምን አለፋችሁ… ሁሉ ነገር እንደ ‘ማህበራዊ ምግብ’ አይነት ሆነና ግራ ተጋብተናል፡፡ እናላችሁ…የቱ “በትክክል ተመልሷል…” የቱ “ለዛሬው አልተሳካልህም…” እንደሚባል ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የምር…አለ አይደል…ኤፍ ኤሞች ላይ የሚሰሙ የ‘መረጃ’ ስህተቶች መአት ናቸው፡ ብዙዎቹ ስሀተቶች ደግሞ ከኢንተርኔት የሚገኙ መረጃዎች ሲተረጉሙ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ እናማ…ብዙ ሰው በሚዲያ የሚሰማቸውን ነገሮች ሁሉ እንደ ‘እውነተኛ መረጃዎች’ ስለሚወስዳቸው አስቸጋሪ ነው፡፡
ዓይኔን ሰው አማረው
ዓይኔን ሰው አማረው
የሰው ያለሀ የሰው
የምትለዋ ስንኝ የምርም ዘመን ተሻጋሪ ነችሳ!
አንድ ጊዜ ደግሞ የሆነ አቀንቃኝ (አይደል የሚባለው!) ስለ ሙዚቃ በቴሌቪዥን እየተጠየቀ ነበር፡፡ እናላችሁ…ስለ ዓለም ሙዚቃ አስተያየቱን ይጠየቃል፡፡ እናማ…ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“ምን ሙዚቃ አለ፣ ራፕ ብቻ ነው፡፡” ቂ…ቂ…ቂ…
ከ‘ኪሎ በላይ’ የሆነ ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…ይሄ ታዋቂነትና አዋቂነትን የመቀላቀል ነገር የት ይደርሳሉ የሚባሉ ልጆችን መንገድ ላይ እንዳያስቀራቸው ፍሩልኝማ፡፡
የካን ፊልም ፌስቲቫል በየዓመቱ ካን ውስጥ ይካሄዳል፡፡ (አራት ነጥብ፡፡) ክሪስቲና አጉሌራ የተባለችው ድምጻዊት ምን ብላ ጠየቀች አሉ መሰላችሁ…
“የዘንድሮ የካን ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት የት ነው የሚካሄደው?”  
“የዘንድሮ የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ የት ነው የሚካሄደው?” ለማለት ያሰባችሁ፣ ድምፃዊቷ ትምህርት ትሁናችሁ፡፡ ቂ…ቂ..ቂ…
አሁን ዴቪድ ቤካም ቀሺም ነገር የሚናገር ይመስላል! አንድ ጊዜ ምን አለ አሉ መሰላችሁ…የልጁን ክርስትና መነሳት እንደሚፈለግ ከተናገረ በኋላ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ግን በየትኛው ኃይማኖት እንደሆነ ገና አላውቅም፡፡” የምር…ቤካም ራሱ ነው እንዲህ ያለው፡፡
ደግሞላችሁ… ነገር የሚገንባት የምትባለው ብሪቲኒ ስፒርስ አንድ ጊዜ ምን አለች አሉ መሰላችሁ…
“እንደ እውነቱ ጃፓን ለመሄድ ፈልጌ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም አሳ መብላት አልወድም፡፡ እዛ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ አሳ በጣም የሚወደድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡”  ቂ…ቂ…ቂ… (ጆርጅ ቡሽ እንኳን አፍሪካ ‘አገር’ አለመሆኗን ያወቁት ዘግይቶ ነው ይባል የለ!)
ብሩክ ሺልድስ በጊዜዋ የታወቀች ተዋናይት ነበረች፡፡ እናላችሁ… በአንድ ወቅት የፀረ—ማጨስ ዘመቻ ቃል አቀባይ ሆና ነበር፤ አንድ ጊዜ መግለጫ ስትሰጥ ምን አለች መሰላችሁ…
“ማጨስ ሊገድልህ ይችላል፡፡ ከሞትክ ደግሞ ከህይወትህ እጅግ ዋና ክፍል አጥተሀል ማለት ነው፡፡” ቂ…ቂ…ቂ… የፀረ—ምናምን ዘመቻ ውስጥ ቃል አቀባይም ሆነ ‘ቃል ተቀባይም’ የምትሆኑ… ይቺን ነገሬ በሉልኝማ፡፡
“ከልክ በላይ ከበላህ ከልክ በላይ ትወፍራለህ፣ ከልክ በላይ ወፈርክ ማለት ደግሞ ክብደትህ ጨመረ ማለት ነው፣” አይነት ነገር… አለ አይደል…ብዙ እርፍና የሚጠይቅ አይመስልም፡፡
ታዋቂዎች አዋቂ የሆኑ ሲመስላቸውና አጉል ሲራቀቁ ምን እንደሚፈጠር ማሪያ ኬሪ በአንድ  ወቅት አለች የተባለችውን ስሙኝማ…
“ቴሌቪዥን ላይ እነኛን ድሀ፣ የተራቡ ህጻናት ባየሁ ቁጥር አለቅሳለሁ፡፡ ማለቴ፣ እንደ እነሱ ብቀጥን ደስ ይለኛል፣ ግን ያለ ዝንቦቹና ሞት ሳይኖር ማለት ነው፡፡” አያስደነግጥም!
እናማ…ታዋቂዎቻችን ከ‘ኪሎ በላይ’ የሆነ ነገር ሲገጥም…አለ አይደል…“አይ ስለዚህ እንኳን የማውቀው ነገር የለም…” ማለት ከ‘ታዋቂነት’ መዝገብ አያስፍቅም፡፡  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5939 times