Saturday, 20 February 2016 09:48

የመጨረሻው ቃለተውኔት

Written by  ደራሲ፡- ፍ ሬድሪክ ብራውን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ባንኮኒው እርጥብና የተጨማለቀ  ነው። ልኡል  ቻርለስ ሀኖቨር ግሪሻም የታች-ክንዱን ከፍ ያለውና ደረቁ ክፈፍ ላይ አድርጓል። ‘ስቴጅክራፍትን’ እያነበበ ነው ። ያለህ አንድ ሱፍ ከሆነና እሱም የነተበ ከሆነ ፣ ባንኮኒው ላይ ማሳረፍ ያለብህ ክርንህን ሳይሆን ፣ የታች-ክንድህን እንደሆነ ታውቃለህ። ስትቀመጥ አንድ ወይም ሁለት ኢንች ያህል ሱሪህን ከጉልበትህ ላይ ሰብሰብ እንደምታደርገው ማለት ነው። በተለይ ተዋናይ ከሆንክ እኒህን ነገሮች አትረሳም ፤ አስታውሰህ ታደርጋቸዋለህ ። ተዋናይ የነበርክ ፣ የነበርክ ግን መናኛ ተዋናይ የነበርክ ፣ ያልተሳካልህና መቼም የማይሳካልህ ሆነህ እንኳ ፤ ቀሪው ህይወትህን እየገፋህ ያለኸውም በብላክሜይል (**)  ሆኖም እንኳ ፤ ደስ በሚል የበልግ ቀን ፣ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ፤ በዞረ ድምር ፣ አልባሌ መሸታ ቤት ውስጥ ፣ እርካሽ ቢራ እየጠጣህ እንኳ ፤ ከንቱነት እየተሰማህ ፣ የማትረባ መሆንህን ጠንቅቀህ እያወቅህ እንኳ ታስታውሳለህ ።
 (** Blackmail ፦ በመልካም ጊዜ የሰሙትን ፣ በአጋጣሚ ያወቁትን ፣ ወይም የጉዳዩ ባለቤት እራሱ የነገራቸውን ፣ ወይም ከሌሎች የሰሙትን ፣ ወይም አነፍንፈው ያገኙትን የሰዎች ምስጢር አወጣለሁ በማለት ሰዎችን እያስፈራሩ ገንዘብ መቀበል ወይም አግባብ ያልሆነ ነገር እንዲያደርጉ ማስገደድ ነው - ተርጓሚው።)
ሁሌም ‘ስቴጅክራፍትን’ ታነባለህ ። ወግ ነው ።
‘ስቴጅክራፍትን’  እያነበበ ነው። አንድ ፅሁፍ እግረ መንገዱን አየ። አዲስ ስለሚወጣ ተውኔት የተጻፈ ዘገባ ነው። ሁለተኛው አንቀጽ ላይ  የፀሀፌ ተውኔቱን ስም አነበበ ። የአንድ አይኑ ቅንድብ አንድ ሙሉ ሚሊ ሜትር ወደ ላይ ተሰቀለ ። ቀለብ የሚሰፍርለት ዋይን ካምፕቤል አዲስ ተውኔት ፃፈ ። ከሶስት ድፍን አመታት በኋላ መሆኑ ነው ። ቶሎ ቶሎ ፣ ፃፈ አልፃፈ ለዋይን ጉዳዩ አይደለም ። የመጨረሻዎቹ ሁለት ተውኔቶቹ አይደለም ለኪስ ለምላስ በሚከብድ ዋጋ ነው ለሆሊውድ የተሸጡት ። ዋይን ካምፕቤል ፃፈ አልፃፈ ምንም አይጎድልበትም። ካቪየር ይበላል ። ሻምፓኝ ይጠጣል ። አዲስ ተውኔቶች ተፃፉ አልተፃፉ ልኡል ቻርለስ ሀኖቨር ግን ሀምበርገር ሳንድዊች ሲበላ ፣ ቢራ ሲጠጣ ይኖራል ። የሚያበሳጨው ሀምበርገር ሳንድዊች መብላቱና ቢራ መጠጣቱ አይደለም ። ይሁን ግድ የለም ። የሚቀፈው ገንዘቡን የሚያገኝበት መንገድ ነው ። ብላክሜይል ይባላል ። ቀፋፊ ቃል ነው ። ቃሉ የምር ያስጠላዋል ።
አሁን ግን ምናልባት ፣ እንዲያው ምናልባት …
ሌላው ቢቀር ለተፈጠረው እድል ብቻ ዋንጫውን ከፍ ማድረግ ይገባዋል ። ባንኮኒውን ተመለከተ ፤ ሀምሳ ሳንቲም አለ ። የቀረችውን አንድ ዶላር ከኪሱ አወጣና ያለው ደረቅ ቦታ ላይ አኖራት ።
“ማክ !” ተጣራ ።
አስተናጋጁ ፣ ማክ በግድግዳው አሻግሮ ህዋውን እያጤነ ነበረ ። ነቅቶ ወደ ልኡል ቻርለስ ሄደ ።
“እሱኑ ላምጣ ቻርሊ ?”
“እሱኑ አይደለም ማክ ። አሁን ቡናማ ቢጫውን ፈሳሽ ነው ።”
“ውስኪ ማለትህ ነው ?”
“እንዴታ ! እንዲያ ማለቴ ነው እንጂ ። አንድ ለአንተ ፤ አንድ ለእኔ ። አሀ ፣ ከወይኑ ጋር የእኔም እላቂ ህይወት …” (***)
ማክ አንድ አንድ ጉንጭ ውስኪ ፣ ሁለት ብርጭቆዎች ላይ ቀዳ ፤ የልኡል ቻርለስን የቢራ ብርጭቆም ሞላው ። “ቀጣዩ በኔ ነው ።” አለ ማክ ። ካሽ ሪጅስተሩ ላይ ሀምሳ ሳንቲም መታ።
ልኡል ቻርለስ አንድ ጉንጯን የውስኪ መለኪያ አነሳና ክፍ አድርጐ ያዛት ። አሻግሮ ተመለከተ ፤ አስተናጋጁን ማክ አልነበረም የሚመለከተው ታዲያ ፤ ከጀርባ ባለው ቆሻሻ መስታወት የራሱን ምስል አየ ። እጅግ ታዋቂ የሚመስል ሰውዬ መልሶ አየው ። ፈገግታ ተለዋወጡ ። ከዚያ ሁለቱም ማክን አዩት ፤ አንዳቸው ከፊት ለፊት ፣ ሌላቸው ከጀርባ ።
“ለክቡር ጤናህ ፣ ማክ ።” አሉ ሁለቱም ፤ ልኡል ቻርለስ ጮክ ብሎ ፤ የእሱ ነፀብራቅ ደግሞ ድምፅ ሳያሰማ ።
ማክ ቀና ብሎ ፦
“አጭቤ ነገር ነህ ቻርሊ። ደስ ትለኛለህ ግን። አንዳንዴ የምር ልኡል ትመስለኛለህ ። አላውቅም ።”
“ምናልባት ፣ የፀጉር ዘለላ ይሆናል ድንበራቸው ፣ የእውነትና ሀሰት” (****) አለ ልኡል ቻርለስ ፦ “እኔ እምልህ ማክ ፣ እንዲያው ምን አልባት ኦማርን ታውቀው ይሆን ?”
“ኦማር ማ ?”
“ድንኳን ሰራተኛው ። ታላቁን የጥንት ሽማግሌ ነዋ ፣ ማክ ። ይህቺን ስማማ ፦
        … ኋላ አንዱ ጠባሳ
ሸንካፋ መሳዩ ተንጋዶ ተነሳ ።
‘ሁሉ እሚያሾፍብኝ ወጥቶ ውልግድግዴ
እጁ ሲያንጥ ሲቀርጥ ተንቀጠቀጠ‘ንዴ ?’” (*****)
“አልገባኝም ።” አለ ማክ ።
ልኡል ቻርለስ በረጅሙ ተነፈሰ ።
“እንዴት ነው ማክ ውልግድግዴ ወጥቷል ? ከልቤ ነው የምጠይቅህ ። ስልክ ደውዬ ወሳኝ ቀጠሮ ላስይዝ ነው ። አድባሯ ከቀናችኝ ነው እንግዲህ ። ስታየኝ እንዴት ነኝ ? ሰው እመስላለሁ ወይስ ውልግድግዴ ወጥቷል ?”
“ለክፉ አትሰጥም ቻርሊ ።”
ልኡል ቻርለስ በእርጋታ ፈገግ አለ ።
“አንድ መለኪያ የሚያስጠጣ ፈረንካ ያለኝ ይመስለኛል ። ቅዳልኝ ።”
ማክ ቀዳለትና ወደ ሌላ ደንበኛ ሄደ ።
ሞቅታ መጣ ፤ ለሰስ ያለ ሞቅታ ። መስታወቱ ውስጥ ያለው ምስል ፈገግ አለለት ። ሁለቱ ብቻ የሚጋሩት የሆነ ምስጢር ያላቸው ይመስላሉ ። አላቸው ደሞ ። በመጠጡ አጋዥነት ሊረሱት እየሞከሩ ነው። መርሳትም ካልተቻለ እያዋከቡ የሆነ የአእምሮ ስርቻ ውስጥ መወሸቅ ። ደስ በሚለው ሞቅታ ተገፋፍቶ (ስካር አይደለም ሞቅታ ነው) መስታወቱ ውስጥ ያለው ሰው እንደለመደው ፦ “አጭበርባሪና የውድቀት ምሳሌ ነህ ፣ ልኡል ቻርለስ። ህይወትህን የምትገፋውም በብላክሜይል ነው ።” አላለውም ። ይልቁንስ እንዲህ አለው ፦ “ጥሩ ሰው እኮ ነህ ፣ ልኡል ቻርለስ ። ላለፉት ጥቂት አመታት ፣ (ቁጥራቸውን እንርሳው) ፣ እድል ስትጫወትብህ ቆየች እንጂ መልካም ሰው ነህ ። አሁን ነገሮች ሊለወጡ ነው ። መድረኩን ትፈነጭበታለህ ። ተመልካቹን በእጅህ መዳፍ ትይዘዋለህ ። ተዋናይ ነህ ወዳጄ ።”
ሁለተኛውን መለኪያ ውስኪ ጨለጠውና ፣ ቀስ ብሎ ቢራውን እያጣጣመ ፣ የተዋናዮች መፅሀፍ ቅዱስ የሆነው ‘ስቴጅከራፍት’ ላይ ያየውን ዘገባ ዳግም አነበበ ። ብዙ ዝርዝር የለውም ። ያለው ግን በቂ ነው። የሜሎድራማው ርዕስ ፦ “እንከንየለሹ ወንጀል” ፤ ይህ ብዙም አይጠቅምም። ደራሲው ፦ ዋይን ካምፕቤል ፤ ይህ እጅግ ጠቃሚ ነው ። ዋይን ለተዋናይነት ሊመለምለው ይችላል። ዋይን ይህቺን መሞከር አያቅተውም ። በብላክሜይል ዛቻ ምናምን አይደለም ፤ እንዲያውም ከነጭራሹ በተቃራኒው ነው ። በፍላጐት ።
ይህ ብዙ ጠቃሚ ነገር ባይሆንም ፣ ተውኔቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት በኒክ ቆርያኖስ ነው። ቆይ ግን ፣ በእርግጥ የገንዘብ ድጋፉ የሚገኘው ከኒክ ቆርያኖስ መሆኑ ጠቃሚ አይደለምን ? እስኪ በስክነት አስብበት ። … ልክ ነው ። ልክ ነው ። ጥቅም አለው ። ኒክ ቆርያኖስ ፣ ከየት መጣ ሳይባል በአንድ ጀንበር ዲታ ሆኖ ከተፍ ያለ ሰው ነው ። ታዋቂና ገናና ባለሀብት ነው። “እንከን የለሹ ወንጀል” አንድም የገንዘብ እጥረት ብሎ ነገር አይገጥመውም ፤ ድጋፍ አድራጊው ኒክ ከሆነ። ሰውየው የማይነጥፍ ምንጭ ነው ። እንዲህ የምትል ወሬ አለች ፦ ሳይቋረጥ ለአርባ ሰአታት በተደረገ  የካርታ ቁማር ፣ ኒክ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ተበልቷል። ኒክ ምን ቢያደርግ ቆንጆ ነው ? ሳቀ ። ቻዎ ። ሌላም ደስ የማይሉ ብዙ ወሬዎች አሉ ። ፖሊስ ግን በአንዱም ላይ ማስረጃ ሊያገኝ አልቻለም ።
ልኡል ቻርለስ አእምሮው ውሰጥ በተፈጠሩ የሀሳብ ሩካቤዎች ፣ በተወለደው ዲቃላ ሀሳብ ፈገግ አለ። የተውኔቱ ርዕስ ‘እንከን የለሹ ወንጀል’ ነው። የኒክ ቆርያኖስ ወንጀሎችም እንከን የለሾች ናቸው። ይህ ሀሳብ ለቆርያኖስ መጥቶለት ይሆን ብሎ አሰበ ። ምናልባት ይህ ተመሳስሎሽ ማርኮት እንደሆነስ እጁን ተውኔቱ ውስጥ የዶለው። ልኡል ቻርለስ የራሱ ሀሳብ ገረመው። ፈገግ አለ። የህይወት ጥቃቅንና አነስተኛ ደስታዎች የሚገኙት እንደነዚህ ካሉ ሀሳቦች ነው ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማሰብ ጥቃቅንና አነስተኛ ደስታ ታገኛለህ ። ተሸናፊ ፣ መሳቂያ ፣ ተራ አጭበርባሪ እንደሆንክ ጠንቅቀህ እያወቅህ ፤ በአእምሮም ይሁን በሰውነትህ አኳኋን ምንም እንዳልተፈጠረ ታስመስላለህ። በእንደዚህ አይነት ጥቃቅንና አነስተኛ ደስታዎች ህይወትህን ትገፋለህ። ወጉ አይቀርም። ህልምም ይኖርሀል፤ ለዚያውም ታላላቅ ህልሞች። ህይወት እንዲህ ናት።     

Read 2723 times