Saturday, 20 February 2016 10:12

የአውሮፓን ኳስ ጎልማሳ አሰልጣኞች እየተቆጣጠሩት ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በየሊጎቹ አማካይ የስራ ዘመን  ከ18 ወራት አያልፍም
   
      በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በተለይ እድሜያቸው ከ50 በታች የሚሆናቸው ጎልማሳ አሰልጣኞች በትልልቆቹ ክለቦች  ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከ5 የውድድር ዘመናት በፊት ያልነበረ ነው፡፡ እድሜያቸው 55 እና ከዚያም በላይ የሆናቸው አንጋፋ አሰልጣኞችን የመቅጠር ፍላጎቱ እየወረደ መጥቷል፡፡ ታዋቂ የስፖርት ባለሙያዎች የሰሯቸውን የተለያዩ ትንተናዎች በማገናዘብ መረዳት የሚቻለው በአውሮፓ የክለብ እግር ኳስ ያለ ውጤት በዋና አሰልጣኝነት በአማካይ ከ17  ወራት በላይ መቆየት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ አንጋፋዎቹ አሰልጣኞች የውጤት ጫና የሚበዛባቸውን ቅጥሮች መቋቋም አዳግቷቸዋል፡፡ አስቀድሞ ለአንጋፋ አሰልጣኞች በሚሰጠው ክብር በዘላቂነት  ሊሰሩ የሚችሉበት የስራ ደህንነት አሁን የሚሰራበት አካሄድ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ግን ከላይ የቀረቡት የአሰልጣኝ ቅጥሮች አዳዲስ አቅጣጫዎች  ለጎልማሳዎቹ አሰልጣኞች እየተመቹ ናቸው፡፡ ጎልማሳዎቹን አሰልጣኞች በቅጥራቸው ዙርያ የሚቀርብላቸው የስራ ዘመን ኮንትራት ማጠር ሳያሳስባቸው ከፍተኛ ደሞዝ በሚገኝባቸውና በውጥረት በተሞሉ ሃላፊነቶች እየተረከቡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም ዓይነት የእድሜ ደረጃ ለሚገኙ አሰልጣኞች ግን በብዙዎቹ የአውሮፓ ክለቦች ያለምንም አይነት ዋንጫ ከሁለት የውድድር ዘመን በላይ በሃላፊነት መቀጠል የማይታሰብ ሆኗል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚወዳደር ክለብ ዋንጫ የማያገኝ ወይንም የተሻለ የውጤት ደረጃ የሚያስመዘግብ ከሆነ የዋና አሰልጣኝ አማካይ የሃላፊነት ቆይታ  ከ2 ዓመት አይዘልቅም፡፡ በእንግሊዝ በከፍተኛ የክለብ ውድድሮች ከሃላፊነታቸው የሚባረሩ አሰልጣኞች ብዛት ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት እየጨመረ መምጣቱን   የሚጠቅሱ መረጃዎች ባለፉት 2 የውድድር ዘመናት ከሃላፊነታቸው የተነሱ  አሰልጣኞች ብዛት ከ65 በላይ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህም የሊጉን የአሰልጣኞች የስራ ደህንነት የከፋ አድርጎታል፡፡
አሰልጣኞች ከሃላፊነታቸው የሚባረሩባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ በተለይ በ5ቱ  የአውሮፓ ታላላቅ የእግር ኳስ አገራት የሚገኙ ክለቦች ከየሊጎቻቸው ዋንጫ ፉክክር መውጣታቸውና በተደጋጋሚ ሽንፈቶች ሲገጥሟቸው፤  ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ውጭ የሚያደርግ ደረጃ ላይ መቀመጣቸው፤ ከደጋፊዎች፤ ከቁልፍ የክለብ ተጨዋቾች ፣ አመራሮች እና ሌሎች ሰራተኞች ጋር የሚፈጠሩ እሰጥ አገባዎች አሰልጣኞቻቸውን ከሚያባርሩባቸው ሁኔታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በሁሉም የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በስፋት በመንፀባረቅ ላይ የሚገኙት  እነዚህ ሁኔታዎች በሁሉም የእድሜ እርከን ያሉ አሰልጣኞች ቢያንስ ለሁለት የውድድር ዘመናት የሚሰሩበትን እድል አሳጥቷቸዋል፡፡  በአውሮፓ 5ቱ ታላላቅ ሊጎች የዋና አሰልጣኞች ቆይታ በእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ለ24 ወራት፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ለ22 ወራት፤ በጣሊያን ሴሪኤ ለ19 ወራት እንዲሁም በስፔን ላሊጋ ለ11 ወራት በአማካይ ሊቀመጥ እንደሚችል የሚያመለክቱ ትንተናዎች ተሰርተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ባካሄደው ጥናት ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች አሰልጣኞችን የመቅጠር እና የማባረር ሂደት እስከ 3.3 ቢሊዮን ፓውንድ ባለፉት 10 የውድድር ዘመናት እንደተንቀሳቀሰበት አስታውቋል፡፡
አንጋፋዎቹ አሰልጣኞች ተፈላጊነት እያጡና ደሞዛቸው እየቀነሰ ከገበያው ውጭ  እየተደረጉ ሲሆን በአንፃሩ የጎልማሳ አሰልጣኞች ተፈላጊነታቸው እየጨመረ እና ደሞዛቸው እያደገላቸው ነው፡፡ ማንችስተር ሲቲ፤ ማንችስተር ዩናይትድ፤ ፓሪስ ሴንትዠርመን፤ ሪያል ማድሪድ እና ቼልሲ አንጋፋ አሰልጣኞቻቸውን በማባረር ጎልማሳ አሰልጣኞችን በሚቀጥሩበት ስትራቴጂ በማተኮራቸውየሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ገበያው የሚፈልጋቸው ጎልማሳ አሰልጣኞች ብዙዎቹ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች ነው፡፡ እንደውም ሲአኢኤስ የተባለ የእግር ኳስ መረጃ አሰባሳቢ ተቋም ይፋ ባደረገው ሪፖርት በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ እግር ኳስ ዋና አሰልጣኝ አማካይ ዕድሜ  መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የውድድር ዘመኑ ውድ ተከፋይ እና በቅርቡ የእንግሊዙን ማንችስተር ሲቲ ለመረከብ ስምምነት የፈፀመው አሰልጣኝ ፔፔ ጋርዲዮላ 44 ዓመቱ ሲሆን በፊፋ የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ የተሸለመው የባርሴሎናው ሊውስ ኢነርኬ  46 ፤ በአትሌቲኮ ማድሪድ እስከ 2020 እኤአ ለመቆየት የተስማማውና በቼልሲ የሚፈለገው አርጀንቲናዊው ዲያጎ ሲምዮኔ 48 ፤ በሊቨርፑሉ በያዝነው የውድድር ዘመን መስራት የጀመረው የርገን ክሎፕ 48 ፤በሪያል ማሪድ ክለብ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ የተቀጠረው ዚነዲን   ዚዳን 46  ዓመታቸው ነው፡፡
ታዋቂው የስፖርት መፅሄት ፎር.ፎር.2 የአውሮፓ እግር ኳስ 50 ምርጥ አሰልጣኞችን በተለያዩ መስፈርቶች በማወዳደር በ2015 መጨረሻ ይፋ ባደረገው የደረጃ ዝርዝር ከቼልሲ ክለብ ሃላፊነታቸው የተነሱት የ52 ዓመቱ ጆሴ ሞውሪንሆ 1ኛ ደረጃ ነበራቸው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን ክለቡን ከ4 ዓመታት በኋላ መልሰው የሊግ ሻምፒዮን በማድረጋቸው እና በሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ ትኩረት በመሳባቸው ነው ሞውሪንሆ የመፅሄቱን ደረጃ አንደኛ ሊሆኑበት የበቁት፡፡ አሁን የባየር ሙኒክ አሰልጣኝ የሆነው እና በ2016 /17 የውድድር ዘመን በማንችስተር ሲቲ የሚሰራው  ፔፕ ጋርዲዮላ ሁለተኛ ደረጃ ሲወስድ የባርሴሎናው ሊውስ ኢነርኬ 3ኛ ሆኗል፡፡ ከጎልማሳዎቹ መካከል  ዲያጎ ሲሞኔ በአትሌቲኮ ማድሪድ፤ ማሲሚላኖ አሌግሪ በጁቬንቱስ እንዲሁም የርገን ክሎፕ በሊቨርፑል፤ እስከ 6ኛ ደረጃ አከታትለው ሲወስዱ በስራ ላይ የሚገኙት አንጋፋ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር 11ኛ ናቸው፡፡ በደረጃው አሰራር ላይ መፅሄቱ ከተጠቀማቸው መስፈርቶች መካከል የታዋቂ የእግር ኳስ ተንታኞች አስተያየት ፤ ያለፈው  የ2014 /15 የውድድር ዘመን ውጤት፤ በአጠቃላይ በክለቦቻቸው ከተጨዋቾች ጋር ያላቸውን ግንኙነት፤ የአጨዋወት ፍልስፍና እና አቋም የፈጠሩትን ለውጥ ማገናዘቡን መጥቀስ ይቻላል፡፡  በፎር.ፎር. 2 የምርጥ 50 አሰልጣኞች ዝርዝር 6 ስፓንያርዶች እና ፈረንሳውያን፤ 5 ጣሊያናዊያን፤ አርጀንቲናያንና ጀርመናውያን እንዲሁም 4 ሆላንዳያን መካተታቸው ውጤታማዎቹ አሰልጣኞች ያሉበትንም አገራት አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል በፊፋ የ2015 የዓለም ኮከብ አሰልጣኝ ሽልማት በወንዶች የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት የባየር ሙኒኩ ፔፕ ጋርዲዮላ፤ የባርሴሎናው ሊውስ ኢነርኬ እና ቺሊን ለኮፓ አሜሪካ ድል ያበቁት ጆርጌ ሳምፖሊ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡ ሶስቱም አሰልጣኞች እድሜያቸው ከ50 ዓመታት በታች እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ የአንጋፋዎቹ ዘመን እያበቃ የጎልማሳዎቹ ዘመን እየመጣ ይመስላል፡፡ እንደሞውሪንሆ፤ ቤኒቴዝ እና ቫንጋል አይነት አሰልጣኞች በላሊጋው ክለቦች ያን ያህል አይፈለጉም፡፡ የአንጋፋ አሰልጣኞች እጣ ፋንታ በአንዳንድ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቢፈለጉም በሚቀጥሉት የውድድር ዘመናት ወደ ብሄራዊ ቡድኖች ማተኮር እና ወደ ቻይና ሊግ መዘዋወር ሊሆን ይችላል፡፡ ባለፈው1 ዓመት ብቻ በ5ቱ ታላላቅ ሊጎች ከ53 በላይ አሰልጣኞች ተቀያይረዋል፡፡
የጀርመን፤ የጣሊያንና የፈረንሳይ ሊጎች በራሳቸው ዜጎች አሰልጣኞች በአመዛኙ መመራታቸው ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ከ11 የተለያዩ አገራት የመጡ አሰልጣኞች የሚሰሩ ሲሆን በስፔን ላሊጋ ደግሞ ከ2 የተለያዩ አገራት የመጡ አሰልጣኞች ይገኛሉ፡፡ በፈረንሳይ ሊግ 1 ፤ በጣሊያን ሴሪኤ እና በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ከሚወዳደሩ መጤ አሰልጣኝ በእያንዳንዱ የሚገኘው ከ2 በላይ አይደለም፡፡
በአሰልጣኞች ከፍተኛ ደሞዝ ከፋይነት የእንግሊዝ እና የስፔን ሊጎች የተሻሉ ናቸው፡፡ በሴሪኤ ያሉ አሰልጣኞች በከፍተኛ ተከፋይ አሰልጣኞች የደሞዝ ደረጃ እስከ 10ኛ ያልገቡበት ሲሆን በእነፃሩ የስፔን ላሊጋ እስከ 5 አሰልጣኞች በዝርዝር ውስጥ በማስግባት ውክልናው መለየቱ ይስተዋላል፡፡ በከፍተኛ ደሞዝ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሁን በባየር ሙኒክ የሚገኘው እና በቀጣይ የውድድር ዘመን በማንችስተር ሲቲ የሚሰራው ፔፕ ጋርዲዮላ በ24 ሚሊዮን ዶላር በዓመት ስለሚያገኝ ነው፡፡ በቼልሲ ሲሰሩ ቆይተው አሁን ክለብ የሌላቸው ጆሴ ሞውሪንሆ በ17 ሚሊዮን ዶላር፤ አርሴን ቬንገር በ14 ሚሊዮን ዶላር፤ በማን ዩናይትድ ያሉት ሊውስ ቫንጋል በ11.75 ሚሊዮን ዶላር፤ በራሽያ ብሄራዊ ቡድን ያሉት ፋብዮ ካፔሎ በ10 ሚሊዮን ዶላር፤ የሊቨርፑሉ የርገን ክሎፕ በ8.5 ሚሊዮን ዶላር፤ የባርሴሎናው ሊውስ ኢነርኬ በ7.5 ሚሊዮን ዶላር፤ በሰቲ ዘንድሮን ብቻ የሚሰሩት ማኑዌል ፒሌግሪኒ በ7 ሚሊዮን ዶላር፤ የሪያል ማድሪዱ ዚነዲን ዚዳን በ5.8 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የቤነፊካው ጆርጌ ጄሱስ በ5 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ክፍያቸው እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ አከታትለው ያገኛሉ፡፡
በፉትቦል ዳታ ቤዝ የአሰልጣኝነት የስራ ዘመን አጠቃላይ የውጤታማነት ስሌት መሰረት ወቅታዊ ደረጃውን የሚመራው የባርሴሎናው ሊውስ ኢነሪኬ በ20346 ነጥብ ነው፡፡ የሲቪያው ኡናዬ ዩምሪ በ15348 ነጥብ፤ የባየርሙኒኩ ጋርዲዮላ በ13162ነጥብ፤ የጁቬንትሱ ማሲሞ አሌግሪ በ12 353 ነጥብ እንዲሁም የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲያጎ ሲሞኔ በ11775 ነጥብ እስከ 5 ያለውን ደረጃ ያገኛሉ፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ የአንጋፋ አሰልጣኞች ዘመን እየተገባደደ የጎልማሶች ዘመን እየመጣ መሆኑን የሚጎቱቱ አንዳንድ የቅጥር ሁኔታዎችን መመልከት ያስፈልጋል፡፡  በ2015 መጨረሻ ላይ የጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ ጎልማሳውን ፔፕ ጋርዲዮላ በማሰናበት አንጋፋውን ካርሎ አንቸሎቲ መቅጠሩ የመጀመርያ ነው፡፡ በርግጥ ከታላላቆቹ ሊጎች በጣሊያን የሚሰሩ እና የጣሊያን ዜግነት ያላቸው አንጋፋ አሰልጣኞች ተፈላጊነት ያን ያህል እየወረደ አይደለም፡፡ ባየር ሙኒክን ከተረከቡት አንጋፋ አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ባሻገር ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በትንሽ ክለባቸው ከፍተኛ ስኬት ላይ የሚገኙት ክላውድዮ ራንዬሪ ጣሊያናዊ አንጋፋ አሰልጣኝ ናቸው፡፡  በሌላ በኩል የሆላንድ ዜግነት ያላቸውም ሁለት አንጋፋ አሰልጣኞች በእንግሊዝ ይገኛሉ፡፡  ወደ አንጋፋዎቹ ተርታ እየገቡ ያሉትን ጆሴ ሞውሪንሆ ተክተው በሞግዚትነት እየሰሩ ያሉት ጉስ ሂድኒክ እና በኦልድትራፎርዱ ክለብ ማን. ዩናይትድ ሁለተኛ የውድድር ዘመናቸውን በከፍተኛ ጫና እየሰሩ የሚገኙት ሊውስ ቫንጋል ናቸው፡፡  

Read 2475 times