Saturday, 20 February 2016 10:07

24ኛው የ ESOG አመታዊ ጉባኤ ተካሄደ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

     እንደውጭው አቆጣጠር ፌብረዋሪ 16 -17/20016 በአዲስ አበባ ሒልተን ሆል የተካሄደው የ ኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG አመታዊ ጉባኤ መሪ ቃል  (From MDG to SDG reinvigorating ) ከምእተ  አመቱ የልማት ግብ ወደ ዘለቄታዊ የልማት ግብ በሚደረገው ሽግግር የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርን ድርሻ አጠናክሮ ማስቀጠል የሚል ነው። በፕሮግራራሙ ላይ የተነሱ ሀሳቦችን በሚቀጥለው ሳምንት እትም እናስነብባችሁዋለን።  ጥር 2008/ የጤናማ እናትነት ወር የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር
በኢትዮጵያ ካሉት የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች 65በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚሰሩ ናቸው።
ቀሪዎቹ 35 በመቶ የሚሆኑትም የሚገኙት በየመስተዳድሩ ትልልቅ ከተሞች እንደ መቀሌ፣ አዋሳ፣ አዳማ በመሳሰሉት ነው።  
በዚህ እትም ጥር 2008/የጤናማ እናትነት ወር በሚል በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የወጣው መመሪያ  (Guide line) ከያዛቸው አንዳንድ ነጥቦች ለአንባቢዎች ብለናል። የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ አኩዋያ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ምን ይመስላል? መሻሻል የሚገባውስ ነገር ምንድነው? የሚለውን በአለምአቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን በካናዳ ቀርቦ ከነበረው እውነታም በመጠኑ እናስነብባችሁዋለን።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ አብዛኞቹ እናቶች በምጥ ሰአትም ሆነ ልጃቸውን ከሕክምና ተቋም ውጭ እቤታቸው ለመውለድ መምረጣቸው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው አይደለም። በተደረገው ግምገማ እንደተደረሰበት ከሆነ በዘርፉ ባለው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ የእናቶችንና የጨቅላ ሕጻናትን ጤንነት በተሻለ መንገድ ለመጠበቅ ከማያስችሉ ምክንያቶች መካከል፡-
በሰለጠነና በዘመናዊ መንገድ ብቁ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እውቀቱንና ልምዱን ያካበቱ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት፣
የሰለጠኑ ባለሙያዎች በየጊዜው ስራ መቀያየር፣
የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት፣
የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ አቅርቦቶች እጥረት፣
ለጨቅላ ሕጻናት ተገቢው አገልግሎት በሁሉም ተቋማት በእኩል አለመገኘቱ፣
በተፋጠነ እና በአስቸኳይ አገልግሎቱ በተፈለገ ጊዜ አለመገኘቱና ወደከፍተኛ የህክምና ተቋም የሚደረገው ሽግግር በሰአቱ አለመፈጸም እንዲሁም የመጉዋጉዋዣ እጥረት...ወዘተ  
ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች እናቶች በቤታቸው አምጠው እንዲወልዱ የሚያስገድዱዋቸው ሲሆን አጋጣሚው ካልፈቀደም ከእናቶች አካልና ሕይወት ባለፈም ጨቅላ ሕጻናቱ እንደሚቀጠፉ በይፋ የሚታይ እውነታ ነው፡። ምንም እንኩዋን ኢትዮጵያ የእናቶችንና የሕጻናቱን ጤንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ መሻሻሎችን በየጊዜው የምታደርግ ቢሆንም ዛሬም ድረስ አገሪቱ የጤና አገልግቱን በብቃት ለእናቶች ጨቅላዎችና ለሕጻናት ለማዳረስ ችግር ማጋጠሙ አልቀረም። እናቶች በየትኛውም የገጠሪቱ አካባቢ ቢሆን በምጥ ሰአት ከሕክምና ተቋም እንዲገኙ ወይንም ልጃቸውን በሰለጠነ ሰው ኃይል ርህራሄና ክብር እየተሰጣቸው እንዲ ወልዱ ማስቻል የግድ አስፈላጊ ነው። ይህንን በማድረጉ ሂደትም በመንግስት፣ በልማት አካላት እንዲሁም በመላው ህብረተሰብ ትብብር ማድረግና የተቀናጀ አሰራርን መተግበር ያስፈልጋል። ይህ ከተደረገ ተገልጋዩን ያረካል። የተጠቃሚዎችን አቅም ያጎለብታል። አገልግሎት ሰጪዎችንም ለተሻለ አሰራር ያነሳሳል።
አለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፊደሬሽን  FIGO በ2015/ካናዳ ባንኮበር በተባለው ከተማ አድርጎት በነበረው ስብሰባ ላይ 140/የሚሆኑ አገራት የተወከሉ ሲሆን ከዚህም አንዱዋ ኢትዮጵያ ነበረች። ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የተወከሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔ ሻሊስትና የማህበሩ የቦርድ አባላት በስብሰባው ላይ የ90/ደቂቃ ጊዜ በማግኘት ኢትዮየጵያ የእናቶችን ጤንነት በመጠበቅ ረገድ ከምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ እና ሌሎች ተያያዥ እውነታ ዎችን አቅርበዋል። በስብሰባው ላይ መረጃውን ካቀረቡት መካከል ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ  እንደገለጡት የቀረቡት ነጥቦች ሶስት ነበሩ።
እስለ 2015/የምእተ አመቱ የልማት ግብ ቁጥር አምስት የእናቶች ጤና በኢትዮጵያ ከምን ደረጃ ላይ ነው?
የቤተሰብ ምጣኔና ውርጃ በኢትዮጵያ በምን ሁኔታ ላይ ነው?
በኢትጵያ የማህጸንና ጽንስ ድህረ ምረቃ ትምህርት ምን ይመስላል? አሁንስ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ምን ይመስላል? የሚሉ ነበሩ። እንደ ዶ/ር ባልካቸው ማብራሪያ፡-
    የምእተ አመቱ የልማት ግብ ከ1990-2015 ባለው ጊዜ የእናቶችን ሞት 75ኀ መቀነስ የሚል ግብ አስቀምጦ መነሳቱ ይታወሳል። በተለያዩ የዳሰሳ ስራዎች እንደሚታወቀው ኢትዮ ጵያ በእናቶችና ሕጻናት ሞት መቀነስ ከፍ ያለ ለውጥ አስመዝግባለች። በተለይም በሕጻናት ላይ ከሁለት አመት ቀድማ ግቡን ያሳካች ሲሆን በእናቶች ላይም ስኬቱ የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ለሚጠበቀው የቀረበ ውጤት ግን ኢትዮጵያ አስመዝግባለች። በሁለተኛ ደረጃ በስብሰባው የቀረበው ነገር ከቤተሰብ ምጣኔና ከጽንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ የሚያሳይ ሲሆን በዚህም በአሁን ሰአት ሁሉም የጤና ተቋማት የቤተሰብ ምጣኔን እንደአንድ የስራ መስካቸው አድርገው እንዲያዩና አገልግሎቱን በተቋማቸው ከመስጠት በተጨማሪ ወደ መስክ እየወጡ እናቶችን በማስተማር የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው። ለዚህም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል የጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ዋነኞቹ ናቸው። ከአምስትና አስር አመታት በፊት እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እየፈለጉ የማያገኙበት ሁኔታ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በጤና ተቋማት ሁሉ በቅርብ አገልግሎቱን ስለሚያገኙ ያ ችግር ተቀርፎአል። ስለዚህም በአሁኑ ሰአት ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አጠቃቀም ደረጃው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን እናቶች ሳይፈልጉ የሚያረግዙበት ሁኔታም እየተወገደ ይገኛል።
    በሶስተኛ ደረጃ በፊጎ ስብሰባ ላይ ኪአትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የቀረበው መረጃ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል ከሚረዱ መካከል የጤና ባለሙያዎች በብቃት መገኘት አንዱ ነው። ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን በማምረት በኩል ከፍተኛ መሻሻሎችን እያሳየች መሆኑ አይካ ድም። በዚህም አሰራር ከዝቅተኛ ደረጃ እስከከፍተኛ ደረጃ የህክምና ባለሙያዎችን በማብቃት በኩል  ብዙ እየተሰራ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ቁጥር በመላው ኢትዮጵያ ወደ 280/ አካባቢ ነው። እነዚህም ሐኪሞች የሚገኙት በአብዛኛው ማለትም 65/ ከመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ውስጥ ነው። አዲስ አበባ ከ3-4/ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያለባት ሲሆን ቀሪው ወደ 90/ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ ጋ የሚደርሱት ባለሙያዎች 35/በመቶ ብቻ ናቸው። እነርሱም ቢሆኑ የሚገኙት ትልልቅ በሚባሉት ከተሞች ማለትም...መቀሌ፣ ባህርዳር፣ አዋሳ፣ ድሬደዋ፣ አዳማ በመሳሰሉት ነው። ስለዚህም ከፍተኛ የሆነ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ችግር እንዳለ የታወቀ ነው።ብለዋል ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ።  
    ዶ/ር ባልካቸው በማስከተልም የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎችን እጥረት ለማስወገድ ከአንድ አመት በፊት የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ከሁሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አሁን ያለውን የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ከግምት ውስጥ ገብቶ ሁሉም ድህረ ምረቃ የሚሰጡ ኢንስቲቱዩሽኖች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር የድህረ ምረቃ ቅበላቸውን በመጨመር ከፍ ያለ ባለሙያዎችን ማግኘት አለብን በሚል ስራው በመሰራት ላይ ነው። ለምሳሌ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከአምቦ፣ ከወራቤ፣ እና ሌሎችም አዲስ አበባ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር በመያያዝ ተጨማሪ የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በመቀበል በማሰልጠን ላይ ነው። ይህም በተለያዩ የህክምና ተቋማት ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ይህ አሰራር ከተወሰኑ አመታት በሁዋላ ጥሩ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ያስገኛል። ያ ማለት ደግሞ ለእናቶችና ጨቅላ ሕጻናቱ የሚሰጠውን የህክምና ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። ብለዋል ዶ/ር ባልንቸው ንጋቱ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት።
ጤናማ እናትነትን እውን ለማድረግ በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር የተዘጋጀው መመሪያ  የሚከተሉትን ነጥቦች አስቀምጦአል።  
የህክምና ባለሙያዎች ለእናቶች ክብርና ርህራሔ የተሞላበት አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
የህክምና ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት የተሟሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
እናቶች መብታቸውን በሚገባ አውቀው ማስከበር ይጠበቅባቸዋል።  
ከዚህም በተጨማሪ የስራው ተባባሪ አካላት፡-
የክኒካል እና የቁሳቁስ እንዲሁም የገንዘብ እገዛ ማድረግ፣
ስራውን የመከታተልና የመገምገም ተግባር ላይ መሳተፍ፣
የምክር አገልግሎት፣ ስልጠና፣ ሴሚናር መስጠት በመሳሰሉት ተግባር ላይ የሕክምና ተቋማትን እንዲያግዙ ይጠበቅባቸዋል። 

Read 1757 times