Print this page
Saturday, 18 February 2012 11:50

ጉዞ ወደ ጐንደር - (የጉዞ ማስታወሻ - ክፍል 5)

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(0 votes)

ጐንደር ማለዳ ነቅታለች፡፡ ለጥምቀት ያለችውን የክት ቀሚሷን ለብሳ አደባባይ ወጥታለች፡፡ “እልል” እያለች፣ እያሸበሸበች፣ “ሆ” እያለች፣ እየዘመረች ወደ ጥምቀተ ባህሩ ወርዳለች፡፡ የፋሲል መዋኛ ዙሪያውን በቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ በምዕመናንና በቱሪስቶች ተከቧል፡፡ ከጥምቀተ ባህሩ በስተምዕራብ አቅጣጫ ካህናት፣ ቀሳውስት፣ ጳጳሱና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በልብሰ ተክህኖ አጊጠው ጥምቀተ ባህሩን የመባረክ ስነስርአት ተጀምሯል፡፡ በስተምስራቅ ደግሞ ህዝበ ክርስቲያኑና ቱሪስቶች ይታያሉ፡፡ ሃይማኖታዊው ስርአት ተከናውኖ እንዳበቃ ምዕመናኑ በማራኪ መንፈሳዊ ስርአት ከፀበሉ መቋደስ ጀመሩ፡፡ ህፃናትና ወጣቶች ወደ ጥምቀተ ባህሩ እየዘለሉ በመግባት በደስታ እየተፍለቀለቁ መዋኘት ያዙ፡፡

በዙሪያ ገባው እጅግ ማራኪ መንፈሳዊ ትዕይንት ይከናወናል፡፡ በጥምቀተ ባህሩ ውስጥና ዙሪያውን የተለየ ህብር ሰፍኗል፡፡ የተጠመቁት ከገንዳው እስከሚወጡ ሌላው ህዝብ ዙሪያውን ከብቦ ይጠባበቃል፡፡ ከአፍ እስከ ገደፉ በህዝብ የተጥለቀለቀውን የፋሲል መዋኛ ግቢ የከበበው የካብ አጥር የዘመናት ዕድሜ ቢኖረውም፣ ጊዜ ሊያፈርሰው አልሞከረም፡፡ ዙርያውን የቆሙት ዕድሜ ጠገብ ዛፎች የካብ አጥሩን በስሮቻቸው አቅፈው ደግፈው ይዘው ዛሬም ድረስ ፀንቶ እንዲቆም አድርገውታል፡፡ በግቢው ውስጥና ዙርያውን የሚከናወኑ መንፈሳዊ ስነ ስርአቶች ህዝቡ ለዘመናት ካካበተውና ዛሬም ድረስ ተግባራዊ ከሚያደርገው ባህላዊ ክዋኔዎች ጋር ተዳምረው ሲታዩ በተመልካች ልብ ውስጥ ልዩ ስሜትን ይፈጥራሉ፡፡

ደስ የሚል ማለዳ …

ጐንደር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አምራና ደምቃ የዕለተ ጥምቀትን የጧት ፀሃይ እየሞቀች ትፍለቀለቃለች፡፡ ለዘመናት የዘለቁ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቿን ለእንግዶቿ “እነሆ” ትላለች፡፡

የአለባበስ፣ የአጊያጊያጥ፣ የባህላዊ ሙዚቃ እሴቶቿን የሚያሳዩ ክንዋኔዎች በጥምቀተ ባህሩ ዙሪያ ይከናወናሉ፡፡

ረፋድ ላይ ..

ከፊት ሚካኤልና ከአጣጣሚ ሚካኤል በስተቀር ሌሎች ታቦታት ከማደሪያቸው ተነስተው ወደ የመንበራቸው ጉዞ ጀምረዋል፡፡

ታቦታቱ በካህናትና ምዕመናን ታጅበው በደማቅ ሁኔታ ከግቢው ሲወጡ ማየት እጅግ የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ የጥሩንባው፣ የከበሮው፣ የሀርሞኒካው፣ የእልልታና የሆታው፣ የዝማሬው ድምፅ በአንድ ላይ ተቀይጦ ከጐንደር ሰማይ ስር ያስተጋባል፡፡

የጐንደር ጐዳናዎች ታቦታቱን አጅበው በሚጓዙ ምዕመናንና ቱሪስቶች ተሞልተዋል፡፡ እጅግ ማራኪ የሆነ ሃይማኖታዊ ትዕይንት ታቦታቱን አጅቦ በጐንደር ጐዳናዎች ላይ በቀስታ ይፈስሳል፡፡ በዚህች ዕለት ከዚህች ከተማ ሰማይ ስር መገኘት መታደል ነው፡፡ ከማለዳ አንስቶ በየጐዳናዎቿ የሚከናወነውን አስደማሚ መንፈሳዊ ትዕይንት መታደም መቻል መባረክ ነው፡፡

የባህል መዲናነቷን በአይን አይቶ ማረጋገጥ ነው፡፡ የሃይማኖትና የታሪክ ሃብታምነቷን መመስከር ነው፡፡

የአቀበት መንገድ ተከትሎ ከሚጐርፈው ህዝብ መሀል ነኝ፡፡

ይህቺ ብዙ የተፃፈላት፣ ብዙ የተባለላት፣ ብዙ የተዘፈነላት ጐንደር ናት! የባህል፣ የቅርስ፣ የታሪክና የሃይማኖታዊ እሴት ማዕከል የሆነች ታላቅ ከተማ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡

እዚህች ከተማ ውስጥ ብዙ ነገር አለ፡፡ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ከመያዝ በተጨማሪ የጥበብ፣ የቅርስና የባህል ማዕከል ሆነው የሚገኙ ከ60 በላይ ጥንታዊና ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት አሏት፡፡

18 ያህል ጥንታዊና ታሪካዊ መስጊዶችንም ይዛለች፡፡ ለዚህም ነው ጐንደር አፍሪካ ከሚገኙ ከተሞች በላቀ ሁኔታ በሃይማኖታዊ ቱሪዝም ማዕከልነት ተጠቃሽ ለመሆን የበቃችው፡፡

እንኳን እንዲህ ጥምቀት ደርሶ፣ ለወትሮም በርካታ ቱሪስት ከዓመት አመት ከየአቅጣጫው፣ ውቅያኖስ ተሻግሮ ሊያያት ጐራ የሚልባት ከተማ ናት - ጐንደር፡፡

ጥምቀት እንዲህ ደምቆ ተከብሮ ቢያልፍም ጐንደር ግን ከአመት አመት የጐብኝን ቀልብ የሚያማልሉ ጥንታዊ የቅርስ መስህቦችን ይዛ “እዩኝ” ማለቷን ትቀጥላለች፡፡

ጐንደር ንጋት ላይ የደረበችውን ደማቅ ካባ ሲመሽ አታወልቀውም፡፡ ታቦታቱ ወደ የመንበራቸዉ ከገቡ በኋላም የጐንደር ጐዳናዎች አይቀዘቅዙም፡፡ የጐበዛዝት ሆታና ጭፈራ አመሻሽ ላይም አይደበዘዝም፡፡ ጀምበር ከአዘዞ በስተጀርባ ብትወድቅም፣ ጐንደር ቀሚሷን አታወልቅም፡፡

እንዲህ መሽቶ ለአይን ያዝ ማድረግ ቢጀምርም፣ አመት ጠብቃ የመጣች ጥምቀት ጐንደር ላይ ደምቃ ውላ ወደመጣችበት ልትሄድ ብትዘጋጅም … ጐንደር ውበቷ አይቀንስም፡፡

ጥምቀት ዞራ ለመምጣት ብትሄድም፣ ወደ ጐንደር የዘለቀ ቱሪስት ይጐበኘው አያጣም፡፡ ለዘመናት ያቆየችው ይደመምበት ጥበብ፣ ይደነቅበት ቅርስ፣ ይመሰጥበት ሞልቶ የተረፋት ናት - ጐንደር፡፡

ይሄን በማወቅ ነው ቱሪስት ከአመት አመት ወደ ጐንደር የሚዘልቀው፡፡ በ2003 ዓ.ም ብቻ ከመቶ ሺህ በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች ጐንደርን ጐብኝተዋታል፡፡ ዙርያዋን አይተው አጣጥመዋታል፡፡ እኔም እያየኋት ነው … አይቼ እያጣጣምኳት … በብዕሬ እየከተብኳት … ጐንደር የሚለው ስያሜ … “ጉንደ - ሃገር” … ከሚለው የግዕዝ ሃረግ የመጣ መሆኑንና ትርጉሙም “የሀገር ግንድ”፣ “የሃገር-መሰረት”፣ “ርዕሰ-ሃገር”፣ “የሃገር ራስ” ማለት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እርግጥም ጐንደር “ርዕሰ-ሃገር” ናት፡፡ ለ250 አመታት ያህል የአገሪቱ መናገሻ ከተማ በመሆን አገልግላለች፡፡ ነገስታት በየዘመናቸው እየተፈራረቁ ከጐንደር መንበራቸው ላይ ሆነው አገር ሲመሩ ኖረው አልፈዋል፡፡ እነሱ ቢያልፉም ለዘመናት ተሻግረው እዚህ የደረሱ የነገስታቱ አብያተ-መንግስታት ግን ዛሬም ድረስ ቆመው ታሪክን ይዘክራሉ፡፡ እነዚህ አብያተ መንግስታት የሚገኙበትንና 70 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ይህን አፅድ ዩኔስኮ በአለም ቅርስነት መዝግቦ ይዞታል፡፡

“የአፄ ፋሲል ግቢ” ተብሎ የሚጠራውና የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታትን የሚያስቃኘው ይህ አፅድ በውስጡ ብዙ ነገር ይዟል፡፡ ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ጥበብ፣ ብዙ ቅርስ፣ ብዙ መስህብ፣ ብዙ ትንግርት፣ እና ደግሞ ብዙ ትዝብትና ስጋት፡፡

“በኳሊ በር አልፎ፣ ጃንተከል ዋርካው

ሲደክሙ እሚያርፉበት፣ ናፈቀኝ ጥላው” የሚለውን ዘፈን እያንጐራጐርን በጃንተከል አልፈን ወደ ፋሲል ግቢ እንዝለቅ፡፡ እንዲህ በሰንሰለት ተጠፍረው ሳይከረቸሙ ይህ ግቢ 12 በሮች ነበሩት፡፡

እድሜ የአፈር ሸማ አከናንቧቸው፣ ዝገት ከላይ እስከታች ወርሷቸው ስራ አቁመው የተዘጉት እነዚህ በሮች እንኮዬ በር፣ ዕቃ ግምጃ ቤት በር፣ ፊት በር፣ ወንበር በር፣ ተዝካር በር፣ አዛዥ ጥቁሬ በር፣ አደናግር በር፣ ኳሊ በር፣ እምቢልታ በር፣ፈረስ ባልደራስ በር፣ ቀጭን አሸዋ በር እና ዕርግብ በር ይበላሉ፡፡

ወዲህ ባለውና በጣሊያን ወረራ ዘመን በተከፈተው በር አልፈን ወደ ውስጥ እንዝለቅ፡፡ እዚህ ግቢ ውስጥ ከ17ኛውና ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነገስታት መካከል የስድስቱ አብያተ-መንግስታትና ሌሎች በርካታ የህንፃ ፍርስራሾች ይገኛሉ፡፡

ፋሲለደስ፣ አእላፍ ሰገድ ፃድቁ ዮሃንስ፣ አድያምሰገድ ኢያሱ፣ ዳዊት ሳልሳዊ፣ መሲህ ሰገድ በካፋ፣ ብርሐን ሰገድ ቋረኛ ኢያሱ … ሁሉም አፄዎች ብሎም እቴጌ ምንትዋብ እዚህ ቅፅር ውስጥ ሆነው ነበር የያኔዋን ኢትዮጵያ የሚመሩት፡፡

ወደ አብያተ መንግስታቱ እንሂድ … ወደ ጥንታዊዎቹ ህንፃዎች እናምራ …

እነሱ ጋ ብዙ ነገር አለ፡፡ እነሱ ብዙ ነገር ናቸው፡፡ ዕድሜ በክርኑ ደቁሶ ሊያነኳኩታቸው ያልቻላቸው፣ ዘመን ቀስ በቀስ ሊያፈራርሳቸው ቢሞክርም ፀንተው የቆሙት እነዚህ ጥንታዊ ህንፃዎች ብዙ ነገር ይናገራሉ፡፡

370 አመታትን ወደ ኋላ ወስደው ታሪክን ይዘክራሉ፣ ጥበበን ይመሰክራሉ … ይሄ … ግቢው መሀል ላይ ከነ ሙሉ ግርማ ሞገሱ ቆሞ የሚታየን ግዙፍ ህንፃ የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግስት ነው፡፡ 32 ሜትር ርዝመት ያለው ቤተ-መንግስቱ፣ 25 ሜትር በ25 ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን በኖህ መርከብ ቅርፅ የተሰራ ነው፡፡ 3 ፎቆች ያለው የዚህ ህንፃ አናቶች የግማሽ እንቁላል ቅርፅ ያላቸው ናቸው፡፡

ወደ ውስጥ እንዝለቅ … ረጅሙን መወጣጫ ደረጃ ተከትለን፡፡ በረጅም ወጥ ጣውላ የተሰራውን በር አልፈን “ዙፋን ችሎት” ተብሎ የሚጠራውና አፄ ፋሲል ችሎት ይቀመጡበት የነበረው ሰፊ ክፍል ውስጥ እንገኛለን፡፡ ግድግዳው ላይ የዳዊት ኮከብ ቅርፅ የሚታይበት ይህ ክፍል፣ እንዲህ ኦና ሊሆን ከዘመናት በፊት ግን ከአፍ እስከ ገደፉ በችሎት ታዳሚዎች የሚጥለቀለቅ ትልቅ የፍርድ አደባባይ ነበር፡፡

በህንፃው የውስጥ ደረጃ ሽቅብ ወጥተን የምናገኘው ይህ ሰፊ ክፍል የግብር አዳራሽ ነበር፡፡ አፄው የወንድ መኳንንንቶችን ግብር ጥለው ጮማ ሲያስቆርጡበት፣ ጠጅ ሲያስኮመኮሙበት የነበረውን አዳራሽ አልፈን ግራና ቀኙን እየተዟዟርን ሌሎች የቤተ-መንግስቱ ክፍሎችን እንጐብኝ፡፡

የአፄውን መልበሻ ክፍልና በመፀዳጃነት ያገለግል የነበረውን ጠበብ ያለ ጓዳ አይተን ሁለተኛው ፎቅ ላይ ንጉሱ የ”ስማ በለው” አዋጅ ያሰሙበት የነበረ አነስተኛ በረንዳ ላይ ቆመን ጐንደርን ቁልቁል እናያታለን፡፡

ይሄ በስተምስራቅ በኩል ከህንፃው ጋር ተያይዞ የተሰራው ክፍል፣ ዛሬ እንዲህ የሸበቱ አለቶች ጥርቅም የሆነ ፍርስራሽ መስሎ ቢታይም ያኔ ግን የወይን ጠጅ መጥመቂያ ጓዳ ነበር፡፡ ከፊት ለፊቱ የሚታዩት ሦስት ክፍሎች ደግሞ የጥንታዊው ዘመን “ፍሪጆች” ናቸው፡፡ የወይን ጠጁ በጋን እየተሞላ ይቀዘቅዝ የነበረው እነዚህ ክፍሎች ውስጥ ነው፡፡  ከግዙፉ የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግስት ወጥተን፣ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ አለፍ ብሎ የሚገኘውን 6 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ አይተን ወደ ቀጣዩ መስህብ እናምራ፡፡

ወደ አድያም ሰገድ ኢያሱ ቤተ-መንግስት ህንፃ ነው ጉዟችን፡፡ ከ1674 እስከ 98 የነገሰው አድያም ሰገድ ኢያሱ በንግስና ዘመኑ ለአስራ አንድ ጊዜያት ያህል ከተቀናቃኞቹ ጋር ጦርነት ገጥሞ በሁሉም ድል የተቀዳጀ ጀግና ንጉስ መሆኑ በታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ጀግናው ታሪኩን ሰርቶ አልፏል፡፡ ታሪኩ ግን ይሄው ዘመናትን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል፡፡ የዘመኑ ስልጣኔም የዘመናት ዕድሜን ተሻግሮ እዚህ ህንፃ ላይ ታትሞ ከፊት ለፊታችን ቆሟል፡፡

“በዘመናት መፈራረቅ፣ በትውልዶች መተካካት፣ በብዙ ነገሮች መምጣትና መሄድ … በእነዚህ ሁሉ መሆን ውስጥ ፀንቶ የመቆም ምስጢር ምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ያጭራሉ - እነዚህ ዘመናትን አልፈው ከእነ ሙሉ ግርማ ሞገሳቸው የቆሙ አብያተ - መንግስታት፡፡

ጣራው በፈረስ ኮርቻ ቅርፅ የተሰራውና ሁለት ፎቆች ያሉት የአድያም ሰገድ ኢያሱ ቤተመንግስት ከእነ ሙሉ ውበቱና ጉልበቱ ዘመናትን ቢያሳልፍም የተወሰነው የጣራው ክፍል ግን ከእንግሊዞች የመፍረስ ጥቃት አላመለጠም፡፡ እነዚህ አብያተ-መንግስታት እንዲህ የወራሪ በትር እያረፈባቸው እንኳን ዘመናትን ተሻግረው አሁን ድረስ ፀንተው የቆዩበትን ሚስጥር እያሰላሰሉ ጥቂት እንደተጓዙ አለፍ ብሎ ካለው ፍርስራሽ ህንፃ ውስጥ መልስ ያገኛሉ፡፡

ይህ ፍርስራሽ ህንፃ “ኖራ መፈተኛ” ተብሎ ይጠራል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እዚህ ግቢ ውስጥ የሚገኙት አብያተ-መንግስታት ለዘመናት ጉልበት ኖሯቸው ሳይፈርሱ ሊዘልቁ የቻሉት በጥንታዊ የኪነ-ህንፃ ጥበብ በጥንቃቄ በመሰራታቸው ነው፡፡

ያኔ … በፊት … ድሮ … ድሮ …

አዲስ አበባ ከመብቀሏ አስቀድሞ … “ቫት” ከመምጣቱ ከዘመናት በፊት … ጐንደር የአገሪቱ መናገሻ በነበረችበት ዘመን፣ ያኔ …. ጥንት … ዱሮ … ህዝቡ ለነገስታቱ ይገብር ነበር፡፡

እንደ ዛሬው ተማኝ ኮሚቴ ገምቶ የጣለበትን፣ በ“ቫት ሬጅስተር ማሽን” ተሰልቶ የተወሰነለትን ባይሆንም ህዝቡ ያኔም ለመንግስት ይገብር ዘንድ ግዴታ ነበረበት፡፡ ነገስታቱ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ይጥሉ የነበሩት ግብር ግን እንዳሁኑ “ብር” ሳይሆን “ቆዳ” ነበር፡፡ “እከሌ ይሄን ታህል፣ እከሌ ያንን ታህል” ተብሎ የሚጣልበት ግብር የከብት ቆዳ ነበር፡፡

ያኔ … መቀመጫውን ጐንደር ላይ ያደረገው የአገሪቱ መንግስት ከህዝቡ የሚሰበሰበውን ቆዳ “ኤክስፖርት” አያደርግም ነበር፡፡

የከብቱ ቆዳ በአግባቡ ይሰበሰብና በትላልቅ በርሜሎች ይቀቀላል፡፡ ሙክክ ብሎ ሲበስል መረቅ ይወጣዋል፡፡ መረቁ ከኖራና ከእንቁላል ጋር ተደባልቆ ይበጠበጥና እንደገና እሳት ላይ ተጥዶ ይንተከተካል፡፡ በስተመጨረሻም ጥሩ የሆነ “ጀሶ” ይወጣዋል፡፡

ጀሶው እንደገና ከኖራ ጋር ተደባልቆ ይቦካና ወደዚህ ከፊት ለፊታችን ወደሚታየን “ኖራ መፈተኛ” ተብሎ የሚጠራ ክፍል ገብቶ ጥራቱ ይመረመራል፡፡

“ሸጋ ሆኗል” የተባለው ኖራ በወጉ ከሚደረደሩ የተመረጡ ድንጋዮችና የተለዩ ጣውላዎች መካከል ማጣበቂያ በመሆን እርስበርስ አስተሳስሮ ያቆማቸው ህንፃዎች ናቸው እኒህ በጥንካሬያቸው አጀብ የሚያሰኙን አብያተ መንግስታት፡፡

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3117 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 12:03