Saturday, 18 February 2012 12:01

አሁንም እንግሊዝ ይምጣልኝ!

Written by  ስብሃት ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(0 votes)

ለመሆኑ አንድ ህዝብና መንግስት ከዚያች ከትንሽ ደሴት ተነስቶ፣ ሩብ አለምን ለመግዛት ያስቻለው የአማካዩ ግለሰብ መሰረታዊ እና ዘላቂ ጠባይ ምን ይመስል ይሆን?

መልስ፡- እንደ ብረት የጠነከረ፣ ምንም ይሁን ማንም የማይበግረው discipline ወይም ስነ ስርአት፡፡ የዚህ ባህሪ ገፅታ “Empire Builder” የሆነ ነብስ ያለው፣ እና በዚህ ላይ በጥንቃቄ የተማረ እንግሊዛዊ ለእራት Tuxedo (ጥቁር ሀር ወይም ሱፍ ሙሉ ልብስ ከነድራታም ኮቱ) መልበስ አለበት፡፡ እራት የሚበላው ብቻውን ቢሆን እንኳ! (ይኸው! እጃችሁን አምጡ ልምታው!) የእንግሊዝ ኤምፓየርን ያፈረሰው Mohandas Gandhi እንኳን ጠበንጃ ቀርቶ ዱላ በቁጣ ሳያነሳ “peaceful Resistance” በሚለው የሰላም መንገድ ነበር፡፡ የእንግሊዝ ዘላቂ ባህሪ ከዲሲፕሊን ሌላ ጨዋነት ነው፡፡ ብልግናን አሳዳጊ ለበደላቸው ወንበዴዎች ይተውላቸዋል፡፡ እነሱም በሚገባ ያውቁታል፡፡ ለምሳሌ በአስራ ዘጠኝ መቶ  ስድሳዎቹ አመተ ምህረት ላይ የተደረሰውና እስከ ዛሬም በመድረክ የሚቀርበው ተውኔት “No sex Please, We are British” የሚባል ኮመዲ ነው፡፡

በህይወቱ እያለ ሰፊው ህዝብ ቅዱስ ጋንድሂ ብሎ የሾመው ሰው የጀመረውን የብሪቲሽ ኤምፓየር አወዳደቅ፣ የሳጥናኤል ታናሽ ወንድም የሆነው አዶልፍ ሂትለር በተፍፃሚተ ኤምፓየት አከተመው፡፡

ከሂትለር ወዲህ ያበቃለት ኮሎኒያሊዝም፣ በወዳጅነት ሽፋን Neo-imperialism የሚካሄድ መሆኑን ኮሎኒያሊስት የነበረውም ኮሎኒ የነበረውም እኩል ያውቁታል፡፡

የዲፕሎማሲ ካህን የሆነው የታላቅዋ ብሪታንያ መንግስት ግን The Bristish Common wealth of Nations በሚል ስም ቅኝ ግዛት የነበሩት አገሮች “ወዳጅ አገር” ሆኑ፡፡ ባንዲራቸው ላይኛው ማእዘን ላይ ትንሽዬ union Jack ትታያለች (ዩንየን ጃክ የእንግሊዝ ባንዲራ ሌላ ስም ነው) Masterly public relations!

እስካሁን ድረስ እንግሊዝ ስንል፣ ባጠቃላይ ህዝቡንና መንግስቱን ከዘመናቱ መለዋወጥ ጋር እያመለከትን ነበር፡፡ ልንዘነጋው የማይገባንን መሰረታዊ ቁም ነገር ለአንባቢ ላስገንዝብ፡፡ ይህን ሁሉ ገድል የፈፀሙት የተፀውኦ ስም ያላቸው ግለሰቦች ናቸው እንጂ፣ Great Brirain ወይም British Empire የሚባሉ ነገሮች በተጨባጭ የሉም፣ ስጋ ያልለበሱ የምናባችን ፍጡራን ናቸው፡፡ ስለዚህ ለኔ እንግሊዝነትን የሚገልፁልኝና የሚወክሉልኝን ሁለት ግለሰቦች “አቀርብላችሁ ዘንድ መንፈስ መራኝ”

(አንድ) Francis Drake

እድሜ ለእንግሊዝ Parliament እና እድሜ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት፣ ለተወሰኑ አመታት ታላቅዋ ብሪታንያ ራሷን የሾመች የአለም ፖሊስ ሆና ነበር፡፡ በውሀ እንፋሎት ሀይል እየተነዱ በፍጥነት የማንንም አገር መርከብ የሚያስከነዱ የጦር መርከቦች ነበሩዋት፡፡ እና የአገሮች ጉልቤ ሆና፣ ባርነት በመላው አለም የተከለከለ መሆኑን አወጀች፡፡

በዚህን ወቅት ፍራንሲስ ድሬክ ጃዊሳ (Pirate) ነበረ፡፡ ለዚህ ተልእኮ ሲነሳ አንዲት መርከብ ብቻ ነበረችው፡፡ በውጊያ መሳርያና በሰለጠነ ሰው ብዛት አቅም ከታላቅዋ ብሪታንያ የጦር መርከቦች ጋር ትስተካከላለች፡፡ ፍራንሲስ ድሬክ ያን ያህል ሀብት ከየት አምጥቶ እንደገዛት እንጃለት! ያገሩ ልጆች The Source of great wealth is always a great Crime ይሉ ነበር ያን ጊዜ፡፡

ፍራንሲስ ድሬክ የማንንም አገር የንግድ መርከብ ይዘርፋል፡፡ በተለይ ደግሞ የታላቅዋ ብሪታንያ ዋና ተቀናቃኝ የሆነችውን የእስፓኝን መርከቦች መዝረፍ የበለጠ ደስታና ኩራት ይሰጠዋል፡፡ (በኛ ዘመን አሜሪካና ራሽያ ይፋጠጡ እንደ ነበሩት አይነት ማለት ነው፡፡)

የእንግሊዝ መርከብ ከሆነች ግን፣ ገና ለአይናቸው ብቅ ስትል፣ እነ ፍራንሲስ ድሬክ አስደንጋጩን የጃዊሳ ባንዲራ አውርደው የእንግሊዝ ባንዲራ ያውለበልባሉ፡፡ እና ያችን መርከብ ወይ የእንግሊዝ የጦር መርከብ እስኪያገኙ ወይም የእንግሊዝ ወደብ እስኪደርሱ ያጅቡዋታል፣ ሌላ ጃዊሳ መርከብ ቢያጋጥም ሊከላከሉላት፡፡

እንዲህ እያለ ፍራንሲስ ድሬክ ከስፓኝ በዘረፈው ወርቅ ሀይል የሶስት መርከብ ባለቤት ሆነ፡፡ ይህን ሁሉ ጀብዱ ስትከታተል የቆየችው Queen Elizabeth the first (የሼክስፒር ንግስት ማለት ነው) አስጠራችውና “በያዝከው የመርከበኛነት ሙያ ቀጥልበት፣ ተገቢውን ሽልማት በይፋ ልንሰጥህ እስክንችል ድረስ ግን ጃዊሳ ነህና እኛ አናውቅህም”

ጃዊሳው ፍራንሲስ ድሬክ ውቅያኖሶቹ ላይ የነገሰ ይመስል እስፓኝን “እንደ ወገቡ ቅማል ጠመዳት አንድ ቀን በማለዳ (ለእስፓኝ “በአሳቻ ሰአት”) ሶስት መርከቦቹ ወደ ወደብ በፍጥነት ገብተው፣ አምስት አዳዲስ የሆኑ፣ armada የተባሉ ትላልቅ የጦር መርከቦችን አቃጥለው አስጥመው ወደ ውቅያኖሳቸው ተመለሱ፡፡

ንግስት ኤልሳቤጥ አሁንም አስጠራችውና ለሰራው ጀብዱ አመሰገነችው፡፡

ፍራንሲስ ድሬክም “ያን ያህልም ጀብዱ አይባልም፣ ንግስት ሆይ” አላት “የስፓኝ ንጉስን ፂም ነው ለብልቤለት የተመለስኩት”

ጊዜውን ጠብቆ ፍራንሲስ ድሬክ በአዋጅ የታላቅዋ ብሪታንያ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ Admiral ሆኖ ተሾመ…

…እስፓኝ ታላቅዋ ብሪታንያን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” የምታወድምባቸው፣ በዘመኑ ከማንም አገር የጦር መርከቦች በግዙፍነት እጅግ በጣም የሚበልጡ መርከቦች እየሰራች ነበር፡፡ The Great Armada ይባላሉ፡፡

አርማዳ ስራው ተጠናቀቀ፣ መርከቦቹ ወደ እንግሊዝ ዘመቱ፡፡

Dover ከተባለው፣ ለንደን አጠገብ ካለው ወደብ ላይ ብቅ ከማለታቸው፣ ወሬው ዘመኑ በሚፈቅደው ፍጥነት Sir Francis ዘንድ ሲደርስ፣ እሳቸው ድንኳናቸው ውስጥ ከጓደኛቸው ጋር Chess ጨዋታ ይዘው ነበር፡፡

ጓደኝየው ለውጊያ ነጥሮ ሲነሳ፣ ሰር ፍራንሲስ “ቁጭ በል” አሉት “ጨዋታችንን ስንጨርስ እንደርሰባቸዋለን፡፡”

ጨዋታቸውን ጨረሱ፣ ለውጊያው ደረሱ፡፡ ለታላቅዋ ብሪታንያ የሚዋጋላት Saint George የቀሰቀሰው ሳይሆን አይቀርም፣ ሀይለኛ ማእበል ተነሳ! የስፓኝን ታላላቅ መርከቦች አንገላታቸው፣ ከመርከበኞቹ ቁጥጥር ውጪ እስኪሆኑ ድረስ!!

አነስተኞቹ የእንግሊዝ መርከቦች ግን በለመዱት አይነት ማእበል እንደ ልብ እየተንቀሳቀሱ (ውር ውር እያሉ) ከማእበሉ ጋር አብረው አርማዳውን “ድባቅ መቱት” ታላቅዋ ብሪታንያ ብቸኛ የአለም ጉልቤ ሆነች…

(ሁለት) Horatio Nelson

ይሄ ደሞ በንግስት ቪክቶሪያ ዘመን Admiral የነበረ ሰውዬ ነው፡፡ ገና አስር አለቃ እንደሆነ በጨበጣ ውጊያ ብቻ ስንት ቦታ እንደቆሰለ አይታወቅም፡፡ በማእረግ እያደገ ሲሄድ ባንዱ ውጊያ በጥይት ሲቆስል፣ በሌላው በግራ በኩል የእግሩ ይሁን ወይስ የክንዱ አንድ ቅልጥም ሲቆረጥ፣ አሁንም በሌላ ውጊያ የቀኝ ይሁን ወይስ የግራ ክንዱ ቅልጥም በቦምብ ሲበታተን፣ እንዲህ እያለ ሲቀናነስ፣ አንድ አይና፣ አንድ እግር በዚህ በኩል፣ ሌላ ቅልጥም በዚያ በኩል የጐደለው የጀግኖች ጀግና ሆኖ፣ Lord Horatio Nelson ተብሎ ሊመለክ ምንም ያህል አልቀረው፡፡

በዚህ ከሞት ጋር ትንቅንቅ እንደገጠመ በኖረው ድንቅዬ ህይወት ውስጥ፣ የሰውየውን አንጡራ “እንግሊዝነት” አብርታ የምታሳይ ደቂቃ አለች፡፡ አሁን ገና በጦረኛ ታሪኩ አጋማሽ ላይ ደርሷል፣ ሶስት የጦር መርከብ እያዘዘ ነው (Francis Drake የስፓኝን ንጉስ ፂም ለብልቦለት ሲመለስ ይታወሰናል)

Captain Nelson በሶስት መርከቦቹ አንዱን የናፖሊዮን ቦናፓርት ወደብ ሊማርክ ጥቂት ሲቀረው “ተኩስ አቁም” የሚል የበላይ ትእዛዝ ደረሰው (በዚያን ዘመን ከመርከብ ወደ መርከብ የሚላላኩት፣ ከሩቅ በቴሌ ስኮፕ እንዲታዩ ደማቅ ቀለም ባላቸው፣ ቁመታቸው የወጥ ማማሰያ እንጨት የሚያህል ዱላዎች እያውለበለቡ ነው፣ ለሃያ ስድስቱ ፊደላት ሃያ ስድስት የተለያየ ምልክት እየተለዋወጡ፡፡)

መልእክት ተቀባዩ በወረቀት ያሰፈረውን መልእክት ለካፒቴን ኔልሰን አሳየው፡፡ ኔልሰን አንብቦ “ፊደላት አሳስተህ እንዳይሆን” ሲል ጠየቀው፡፡ አልተሳሳትኩም አለ፡፡

ኔልሰን ዋሽንት የሚያክለውን ቴሌስኮፕ ነጠቀውና፣ ባለፈ ውጊያ በጠፋው አይኑ ላይ ጀግኖ ወደ አዛዡ መርከብ በኩል “አነጣጥሮ እየተመለከተ”

“ይኸዋ! ልክ እንዳልኩህ ነው፣ መልእክቱ ተኩስ አቁም አይልም” ብሎ ውጊያውን ቀጠለ፣ ድል አደረገ፣ ለሰራው ጀብዱ የማእረግ እድገት ተሰጠው!

ትእዛዝም አልጣሰ፣ ድሉንም ተቀዳጀ፡፡ አይ እንግሊዝ! አሁንም እንግሊዝ ይምጣልኝ!

እስከሚቀጥለው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

ምርቃት

እንግሊዝ በራሱ ሲስቅ ይኸውላችሁ በግጥም፡-

He is an English man

For he himself has said it

And it is greatly to his Credit

That he is an Englishman!

For he could have been a pru-ssian

A Roosian, or even an I-talian!

Yet in spite of all temptation

To belong to other nations

He remains an Englishman!

Gilbert and Sullivan

 

 

Read 2673 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 13:04