Saturday, 27 February 2016 12:24

ቅ/ጊዮርጊስና መከላከያ ከሜዳ ውጭ ወሳኝ የመልስ ጨዋታዎች ያደርጋሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   ጥለው ካለፉ ሁለቱንም የዲ.ሪ ኮንጐ ክለቦች ይጠብቋቸዋል
   በአፍሪካ ክለቦች  ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ካፕ 2ቱ የኢትዮጵያ ተወካይ ክለቦች በቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ በሲሸልስ እና በግብፅ ከተሞች ያደርጋሉ፡፡
ሁለቱ ክለቦች በመልስ ጨዋታቸው ተጋጣሚዎቻቸውን ጥለው ማለፍ ከቻሉ በአንደኛ ዙር  ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚገናኙት  ከሁለት የዲ.ሪ ኮንጎ ክለቦች ጋር ይሆናል፡፡ ከ2 ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ በሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሱን ሴንት ማይክል ዩናይትድን 3ለ0 በማሸነፍ የማለፍ እድሉን ሲያሰፋ፤  በኮንፌደሬሽን ካፕ መከላከያ በግብፁ ክለብ ሚሰር ኤልማክሳ 3ለ1 በመሸነፉ ከሜዳ ውጭ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ20ኛው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ
በ2016 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በውድድሩ አዲስ ታሪክ ለ20ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከቅድመ ማጣሪያ አንስቶ የ43 አገራት 57 ክለቦች ይሳተፉበታል፡፡  በ2007 ዓ.ም የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮንነቱ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ቅ/ጊዮርጊስ ከ2 ሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም ከሲሸልሱ ሴንት ማይክል ዩናይትድ ጋር ባደረገው የቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ  3ለ0 በማሸነፉ  በመልስ ጨዋታው የማለፍ እድሉን ሰፊ አድርጎታል፡፡ ቅ/ጊዮርጊስ ያሸነፈባቸውን 3 ጐሎች ያስመዘገቡት ተጨዋቾች አዳነ ግርማ በ16ኛው ደቂቃ፣ በሃይሉ ግርማ በ43ኛው ደቂቃ እንዲሁም ናይጀሪያዊው ጉድዊን ቺካ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ነበር፡፡  ሁለቱ ክለቦች ከነበራቸው ታሪክ አንፃር በመልሱ ጨዋታ ውጤትን ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀላሉ ሊያስመዘግብ እንደሚችል የተገመተ ሲሆን በ1998 እኤአ በተመሳሳይ ምእራፍ በተገናኙበት ወቅት  8 ለ 1 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስና ከሲሸልሱ ሴንት ማይክል ዩናይትድ ጥሎ ለማለፍ የሚችለው በመጀመሪያ ዙር የደርሶ መልስ ማጣሪያ ከባድ ፈተና የሚጠብቀው ይሆናል፡፡ ካለፈው ዓመት የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የዲ.ሪ ኮንጐው ቲፒ ማዜምቤ ጋር ስለሚገናኝ ነው፡፡
የሲሸልሱ ክለብ ሴንት ማይክል ዩናይትድ በ2014 የአገሪቱ ሊግ ሻምፒዮን የነበረ ሲሆን ለ13 ጊዜያት በሲሸልስ ሊግ እንዲሁም ለ10 ጊዜያት በሲሸልስ ኤፍ ኤካፕ ዋንጫዎችን የሰበሰበ  ስኬታማ ክለብ ነው፡፡  በ1993 እ.ኤ.አ የተመሠረተው ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ኮንድረው ጂን ሊውስ ሲሆኑ በትንሿ ሮቺ ካይመን ከተማ የሚገኘውንና 10ሺ ተመልካች የሚያስተናግደውን ስታድዬም በሜዳነት ይጠቀማል፡፡ ሴንት ማይክል በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከዘንድሮ በፊት በ9 የውድድር ዘመናት በነበረው የተሳትፎ ልምድ ከመጀመሪያ ዙር ማለፍ አልቻለም፡፡
በሌላ በኩል  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ግብ አግቢ ሳላዲን ሰይድ ለቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ከሳምንት በፊት መፈራረሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሳላዲን ለመጀመርያ ጊዜ  በ2002 ዓም ቅዱስ ጊዮርጊስን ከለቀቀ በኋላ ወደ ግብፅ አቅንቶ ለአል አህሊ ሸንዲና ዋዲ ዳግላ  እንዲሁም እንዲሁም ለአልጀሪያው ኤምሲ ክለቦች ሲጫወት ቆይቷል፡፡ የቅዱስ ጊዬርጊስ ክለብን መልሶ ሲቀላቀል ለስድስት ወራት የሚያቆየውን የውል ስምምነት መፈረሙ ሲገልፅ ዘንድሮ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ  ተሰልፎ እንደማይጫወት ተረጋግጧል፡፡

መከላከያ በ13ኛው የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ
በ2016 የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን በውድድሩ ታሪክ ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከቅድ ማጣርያው አንስቶ ከ53 የአገራት የተውጣጡ 51 ክለቦችና ከሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ማጣሪያ ውጭ የሚሆኑትን 8 ክለቦች በመጨመር  በ59 ክለቦች ተሳትፎ የሚከናወን ነው፡፡
መከላከያ  በኮንፌዴሬሽን ካፑ  የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ በግብፁ ክለብ 3ለ1 በመሸነፉ የመልሱ ጨዋታን ያከበደበት ሲሆን ጥሎ ማለፍ የሚችለው 3ለ0 እና ከዚያም በላይ ማሸነፍ ከቻለ ነው፡፡ መከላከያ ከሳምንት በፊት በሜዳው ባደረገው የኮንፈዴሬሽን ካፕ ጨዋታ በባዶ ስታድዬም መጫወቱ  ላይ ጫና የፈጠረበት ሲሆን፣ የግብጽ ክለብ ለጨዋታው ባደረገው ዝግጅት በሞሮኮ ተቀምጦ ከራጃ ካዛብላንካና ከሌላ ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አቋሙ ተጠናክሮ ነበር፡፡
ከ2 ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገው ጨዋታ መከላከያ ክለብ 3ለ1 ሲሸነፍ የግብፁ ክለብ ሁለት ጐሎችን በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሁሴን ራጅስና ኡመር ባራባች ያስቆጠረ ሲሆን በ85ኛው ደቂቃ 3ኛውን ጐል ኤልሳይድ ሃዋዲ የተባለ ተጨዋች አስመዝግቧል፡፡ የመከላከያ  ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ደግሞ መሐመድ ናስር ነበር፡፡ ከመከላከያ እና ከሚስር አልማክሳ በቅድመ ማጣርያው የመልስ ጨዋታ ጥሎ ማለፉን የሚያረጋግጠው ክለብ  በአንደኛ ዙር የደርሶ መልስ ትንቅንቅ ሊገናኝ የሚችለው ከዲ.ሪ ኮንጐ ክለብ ሲ ኤስ ዶን ቦስኮ ጋር እንደሆነ ታውቋል፡፡     የግብፁ ክለብ ሚስር አልማክሳ  እኤአ በ1937 የተመሠረተ ሲሆን 20ሺ አመልካች የሚያስተናግደውን በፋዩም ከተማ የሚገኘውን  ፋዩም ስታድዬም በሜዳነት ይጠቀማል፡፡ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ግብፃዊው ኤሃብ ጋህል ናቸው፡፡

Read 2766 times