Saturday, 27 February 2016 12:26

የአልጄርያ ኳስ በዶፒንግ ቅሌት እየታመሰ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 የአልጄርያ እግር ኳስ በዶፒንግ ቅሌት እየታመሰ  መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአገሪቱ ከፍተኛ የክለቦች ውድድር የሚገኙ ትላልቅ ተጨዋቾች አበረታች መድሃኒቶችን እንደሚጠቀሙ የሚገልፁ ክሶች በይፋ እየተነገሩ ናቸው፡፡ ጉዳዩ የአልጄርያን እግር ኳስ የወደፊት ዕጣ ፋንታ  በስጋትና ጥርጣሬ እንዲሞላ ያደረገው ሲሆን፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበርን ትኩረት ሊስብ ከበቃ ለእገዳ እንደሚያጋልጥ እየተወሳ ነው፡፡  የአልጄርያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የሆነው ዮሴፍ ቤላሊና ሌሎች ሦስት የትልልቅ ክለብ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በዶፒንግ ማጭበርበር  ጥፋተኞች ሆነው ከውድድር የታገዱበት ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
የአልጄርያ መገናኛ ብዙሐናት በተፈጠረው ቅሌት የአገሪቱን መንግስትና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በቂ ቁጥጥር አለማድረጋቸው ነው በሚል ትችቶች እያቀረቡ ናቸው፡፡  የዶፒንግ ቅሌቱን በልዩ ምርመራ ያጋለጠው ተቀማጭነቱ  በለንደን የሆነው “አል አረቢ አልጃይድ” የተባለ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሲሆን ከ2013 እ.ኤ.አ ጀምሮ ከ10 በላይ የአልጀሪያ ተጨዋቾች በህገወጥ መድሃኒቶች ተጠቃሚነት ጥፋተኞች ሆነው ተገኝተዋል፡፡  አንዳንድ የአልጄርያ ሚዲያዎች በፃፏቸው ዘገባዎች ደግሞ የዶፒንግ ቅሌቱ የተፈጠረው የአገሪቱ ትልልቅ ክለቦች ብቁ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን በቋሚነት ስለማይመድቡ ነው ብለው ተናግረዋል፡፡  የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች የሆነው ቤላሚ ለ2 ዓመታት ከማናቸውም  የእግር ኳስ ውድድሮች የታገደ ሲሆን   ሌሎች ተጨዋቾች እስከ 4 ዓመታት በሚዘልቅ የዕገዳ ቅጣት ርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሏል፡፡  የአልጀርያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዶፒንግ ዙርያ ክለቦችን የሚቆጣጠርበት ስርዓት ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለፅ ላይ ነው፡፡

Read 2767 times