Saturday, 05 March 2016 11:00

እኛና ‘ኤክስፓየሪ ዴት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…በቀደም አንድ ቤት ገባሁና ቦምቦሊኖ አዘዝኩ፡፡ እናላችሁ…ቦምቦሊኖውን ቀመስ ሳደርገው ያለማጋነን የልጆች መጫወቻ መኪና ጎማ ነው የመሰለኝ! ሀሳብ አለን….ቦምቦሊኖ ላይ ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ይጻፍልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… እዚሀ አገር ቢያንስ፣ ቢያንስ  በ‘ቶክ’ የማይቻል ነገር የለም ብዬ ነው። (በሁለት ዲጂት ዕድገት ዘመን እንዴት ቦምቦሊኖ ትበላለሀ እንዳትሉኝማ! አንዳንድ ቦታ ዋጋዋን ብታዩ…“ቦምቦሊኖ እንኳን ሳንሳቀቅ መብላት ላንችል ነው!” ትላላችሁ፡፡)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ሳይበላ አይታደርም…” አይነት ነገር ስናወራ አንድ ስትባል ሆድ የምታባባ ግን ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባት አባባል አለች፡
እፍኝ ቆሎዬን ቁርጥም አደርግና፣
አንድ ጣሳ ውሀ ግጥም አደርግና፣
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ተባለና፡፡
የምትለዋ ነገር…ወይ ማሻሻያ አንቀጽ ምናምን ይደረግላት…ወይም የመጠቀሚያዋ ጊዜ ስላበቃ ትቅርልን፡፡ ልክ ነዋ…እፍኝ ቆሎ ስንት እንደሚያወጣ ያየ አይተርታትማ!
ስሙኝማ…ብዙ ‘‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የምር ግን…እዚህ አገር ‘ቦተሊካው’ ራሱ መአት ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው ነገሮች ያሉት አይመስላችሁም! ልክ ነዋ…አሁንም የሀሳብ ክርክር ሳይሆን…“ብቻ አንተን አያድርገኝ…” አይነት ‘ቦተሊካ’ የበዛበት ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ለምሳሌ ይሄ…“ያለፈው ስርአት ጥሎብን የሄደው…” ምናምን የሚሉት ነገር ግራ ይገባችኋል፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ…የሀያ ምናምን ዓመት ወጣቶች ላይ ሁሉ “ያለፈው ስርአተ ጥሎብን የሄደው…” ምናምን አይነት ነገር ሲባል ነገራችን ሁሉ ‘የመጠቀሚያው ጊዜ’ እንዳለፈበት ታያላችሁ፡፡ እናማ…የቀሺም ‘ቡትልክና’ ዘመን እንዳለፈ ማወቅ አሪፍ ነው፡፡ የምር ግን…‘ቦተሊከኞች’ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች…‘ቦተሊከኝነት’ የሞተ ፈረስ ላይ ድንጋይ መወርውር ብቻ አለመሆኑን ቢያውቁ አሪፍ ነው፡፡ አንደኛው ‘ያለፈው ስርአት’ እኮ ካበቃለት ሩብ ምእተ ዓመት ሆኖታል! ካለፈው ስርአት በፊት የነበረው ‘ሌላኛው ያለፈ ስርአት’ ደግሞ አርባ መናምን ዓመት አለፈው! ለጠቅላላ እውቀት ብለን ነው፡፡
ደግሞላችሁ…“አውስትራሊያም እኮ ድርቅ አለ…” አይነት ‘ሰበር ቦተሊካ’ የመጠቀሚያው ጊዜ እንዳለፈበት ልብ ይባልማ! ልክ እኮ “ስድብን ምን አመጣው!” ቢባል…እነ ትረምፕም ይሳደባሉ እንደ ማለት ነው፡፡ ቂ…ቂ..ቂ…
እናላችሁ… ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በዛ ሰሞን አንድ ወዳጄ የሆነ የሠርግ መልስ ይሄዳል፡፡ እናላችሁ… ምን ሲባል ይሰማል…ለካስ የሰርጉ ማግስት የወንድ ሚዜዎች ወይ የዞረ ድምር አልለቀቃቸውም፣ ወይ አሽሙር ፈልገው… “ብር አምባር ሰበረልዎ፣ ሸጋው ልጅዎ…” ሲሉ እንደነበር ይሰማል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ! አሀ…ልክ ነዋ…ስንቴ ነው ‘የሚሰበረው!’ ቂ…ቂ…ቂ…ከአሥራ ሦስት ‘ደምፕ ከተደረገ’ ቦይ ፍሬንድ በኋላ! “ለአሁኑ አልተሳካም” ከተባሉ ‘ፊያንሴዎች’ በኋላ! ነው ወይንስ…“ብር አምባር በድጋሚ የሚሰበርባት የዓለም ብቸኛዋ አገር…” ምናምን የሚል ሜዳሊያ እንዲለጠፍልን ነው፡፡
ደግነቱ ማስረጃ የጠየቀ የለም፡፡ የድሮ ሰዎች እኮ… አለ አይደል… ዝም ብሎ “ብር አምባር ሰበረልዎ!” ስለተባለ ብቻ ማጨብጨብ የለም፡፡ አሀ… “የደሟን ሸማ ቁጭ አድርጓት…” ይላሉዋ!
እናማ… “ብር አምባር ሰበረልዎ…” የሚሏት ‘የድል’ ዘፈን ‘‘ኤስክፓየሪ ዴት’ እየደረሰባት ይመስላል፡፡ ለነገሩ…የቫለንታይን ዴይን “አልጋ በቅናሽ” ማስታወቂያ የሰማ ከዚሀ ሌላ ምን ሊያስብ ኖሯል!
ስሙኝማ…የሠርግ ነገር ካነሳን አይቀር ሠርጎች ላይ አሁን፣ አሁን በብዛት የማይሰሙ ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው ዘፈኖች አሉ፡፡ አሀ…ሰዋችን በትንሽ ትልቁ ሆድ ስለሚብሰው ቅልጥ ያለ ረብሻ ሊፈጠር ይችላላ! ገና ሙሽራው ልብሱን እየለበሰ ጢምቢራው የሚዞር ሚዜ በበዛበት ዘመን… “ኧረ ሚዜው ድሀ ነው፣ ሽቶው ውሀ ነው!” ቢባል ምድር ቀውጢ ባትሆን ነው! “አንቺ ስቱፕድ፣ እኔ ነኝ ድሀ!” ብሎ ከቮልሼቪክ አብዮት ቀጥሎ ከፍተኛ የሚባለውን አብዮት ‘ለማፈንዳት’ የማይመለስ ሚዜ ይኖራላ!
እናማ.. “ሚዜው ድሀ ነው፣ ሽቶው ውሀ ነው…” “የሚዜው ፈዛዛ የለውም ለዛ…” ምናምን ነገሮች ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ እየደረሰባቸው ነው፡፡
ደግሞላችሁ… “ይቺ ናት ወይ ሚዜሽ አየንልሽ…” ቢባሉ ዘንድሮ መአት የሙሽሪት ሚዜዎች አይበሽቁም! ዘፈኑን የምታወርደውን… “በእሷ ቤት እኮ አሽሙር መናገሯ ነው!” ምናምን ሊሏት ይችላሉ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸውን አእምሮዎች ይዘን የምንዞር አልበዛንም! የምር…እስቲ ዙሪያችሁ  ተመልከቱና ከስንቱ ጋር ተደማምጣችሁ ማውራት እንደምትችሉ ልብ በሉማ!
ከወራት በፊት አንድ የምናውቀው ሰው ከአሥራ ምናምን ዓመት ‘ዳያስፖራነት’ በኋላ ለጉብኝት ይመጣል፡፡ እናላችሁ…ምን አለፋችሁ… ከአብሮ አደጎቹ፣ ከዘመዶቹ ምናምን ወሬ ናፍቆታል። እናላችሁ….ጥቂት ቀናት ወዲህ፣ ወዲያ ሲል እንደቆየ…ምን አለፋችሁ….ስሜቱ ሁሉ ሙሽሽ ነው ያለው። ቁም ነገር ሊያወሩት የሚችሉ ሰዎች ማግኘት አስቸገረዋ!
“ሰዉ ሁሉ ከስንት ዓመት በፊት የነበረ ቦታ ላይ እንደተገተረ ነው!” ምናምን ሲል ነበር አሉ፡፡ እንደውም… አለ አይደል… እሱ ነገሬ አላለ እንደሆነ እንጂ ብዙዎቻችን የነበረንን ቦታ እንኳን ማስጠበቅ አቅቶናል! ስንትና ስንት ሜትር እንደተንሸራተትን ቢያይ አይደለም የአገሩን ሰው፣ የአገሩን ካርታ እንኳን ሁለተኛ አያይም ነበር፡፡
የእውነት ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው አእምሮዎች የያዝን መአት ነን፡፡ (‘ቦተሊከኞች’ በሆነ ሰበብ አደባባይ ሲወጡ “ነብር አየኝ በል…” እንላለን እንጂ… የእኛን ማን አየብን! ቂ…ቂ…ቂ…)
ኮሚክ እኮ ነው….ስለ ከተሜነት ሲወራ አሁንም ዘቢብ ኬክ በሠላሳ ሳንቲም፣ ‘ቤድ’ በሦስት ብር የሚገኝ የሚመስለው የተተከልኩባትን ቦታ አልለቅም ያለ መአት አለ፡፡ (እኔ የምለው… የበቀደሙ ‘የአልጋ ቅናሽ’ ላይ…እስከ ሦስት ብር ድረስ የቀነሰ ነበር እንዴ!)
ታዲያላችሁ….የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ አጭቀን…“የንጉሥ ዙፋን ካልተሰጠኝማ!” የምንል መአት ነን፡፡ ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው አእምሮዎችና ሀሳቦች የዚህ አገር ትልቁ ችግር አይመስሏችሁም! በነገራችን ላይ…ለጨዋታው ያህል… ‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈበት አእምሮ ሀያ አምስት ዓመትም፣ ሰማንያ አምስት ዓመትም ሊሆን እንደሚችል ልብ ይባልማ!
በቀደም “አሁንም የመንግሥት ሥራ ላይ ነህ?” ስልህ “እሱማ ኤክስፓየር አደረገ…” ምናምን ያልከኝ ወዳጄ…አስመጪና ላኪ ሆንኩ እንዳትለኝ! ቂ…ቂ…ቂ…የዘንድሮ ‘ለውጥ’ ከሀሊ ኮሜትም የፈጠነ ነው ብዬ ነው፡፡
ስለ ‘ሲቪል ሰርቨንትነት’ ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…አንድ አርብቶ አደር፣ አንድ ገበሬና አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ናቸው፡፡ እናማ ምን ይባላሉ…“እያንዳንዳችሁ ይቺን ጦጣ አንድ የሚያስቅ፣ አንድ የሚያስለቅስና አንድ ብን ብላ እንድትጠፋ የሚያደርጉ ነገሮች ንገሯት…” ይባላሉ፡፡
መጀመሪያው አርብቶ አደሩ የሆነ ነገር አላት። ጦጣዋ ምንም አይነት ስሜት አላሳየችም፡፡ ቀጥሎ አርሶ አደሩ የሆነ ነገር ሹክ አላት፡፡ አሁንም ምንም አይነት ስሜት አላሳየችም፡፡ ከዚያላችሁ…የመንግሥት ሠራተኛው የሆነ ነገር ሹክ ሲላት ፍርስ ብላ ትስቃለች፡፡  
በማስለቀሱም በኩል ሁለቱ የሆነ ነገር ሹክ ሲሏት ምንም አይት ስሜት አታሳይም። የመንግሥት ሠራተኛው የሆነ ነገር ሹክ ሲላት ስቅስቅ ብላ ታለቅሳለች፡፡
እንደገና ብን ብላ እንድትጠፋ በማድረጉ ሁለቱ የሆነ ነገር ሲሏት ምንም አይነት ስሜት አታሳይም። የመንግሥት ሠራተኛው የሆነ ነገር ሲላት ለዓይን በፈጠነ መልኩ ብን በላ ጠፋች፡፡
ይሄን ጊዜ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ግራ ይገባቸዋል።
“እኛ ስናናግራት ምንም ስሜት አላሳየችም። አንተ ስታናገራት ግን በመጀመሪያ ፍርፍር ብላ ሳቀች፣ ቀጥሎ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፣ ከዚያ ብን ብላ ጠፋች፡፡ ምን ብትላት ነው?” ብለው ይጠይቁታል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛውም ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“ፍርፍር ብላ የሳቀችው የመንግሥት ሠራተኛ መሆኔን ስነግራት ነው፡፡ ስቅስቅ ብላ ያለቀሰችው ደሞዜ አምስት መቶ ብር መሆኑን ስነግራት ነው…” አለና ዝም አለ፡
“ብን ብላ የጠፋችውስ ምን ብትላት ነው?” ይሉታል። እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ገንዘብ አበድሪኝ  ስላት፡፡”
እናላችሁ…‘ኤክስፓየሪ ዴት’ ያለፈባቸው ነገሮች፣ ባህሪያት፣ አእምሮዎች፣ አስተሳሰቦች…ጠፍረው ይዘውናል ነው የምላችሁ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5335 times