Saturday, 05 March 2016 11:48

ለናሳ 8 የስራ ቦታዎች 18 ሺህ 300 ሰዎች አመለከቱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ በቅርቡ ላወጣቸው 8 የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታዎች ማስታወቂያ፣ 18 ሺህ 300 ያህል አመልካቾች መመዝገባቸውንና ይህም በተቋሙ ስራ ለማግኘት በርካታ አመልካቾች የቀረቡበት የመጀመሪያው ክስተት ሆኖ መመዝገቡን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ለክፍት የስራ ቦታዎቹ ያመለከቱት ሰዎች በዚህ መጠን ለመብዛታቸው እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከልም ማህበራዊ ድረገጾች የስራ ማስታወቂያዎችንና የቅጥር አገልግሎቶችን ማስፋፋታቸው እንዲሁም በጠፈር ጉዞ ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ይገኙበታል፡፡
በተቋሙ ታሪክ እጅግ ፉክክር የበዛበት ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ የቅጥር ሂደት፣ በመስፈርትነት የተቀመጡትን የዜግነትና የትምህርት ደረጃ ሁኔታዎችን ያላሟሉ አመልካቾች ወዲያውኑ ከውድድር ውጭ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ናሳ ላወጣቸው ክፍት የስራ ቦታዎቹ መቅጠር የሚፈልገው አሜሪካውያንን ብቻ እንደሆነና በምህንድስና፣ በባዮሎጂካል ሳይንስ፣ በፊዚካል ሳይንስና በሂሳብ ወይም በኮምፒውተር የትምህርት መስኮች ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የጠፈር ምርምር ተቋሙ እ.ኤ.አ በ1978 ላወጣቸው ክፍት የስራ ቦታዎች 8 ሺህ አመልካቾች የቀረቡበት አጋጣሚ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች የቀረረቡበት ሆኖ ተመዝግቦ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1800 times