Saturday, 05 March 2016 11:47

የኬንያው መሪ 10 ሺህ ፖሊሶች እንዲቀጠሩ አዘዙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በአገሪቱ የህዝብ ቁጥርና በፖሊስ ሃይሏ መካከል መመጣጠን ለመፍጠር በማቀድ ተጨማሪ 10 ሺህ አዳዲስ የፖሊስ መኮንኖች እንዲቀጠሩ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ ኢምባካሲ በተባለቺዋ የኬንያ ከተማ ባደረጉት ንግግር፣ የፖሊስ ሃይልን ማጠናከር አገሪቱን ከወንጀል ድርጊቶችና ከወንጀለኞች የጸዳች ለማድረግ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ የፖሊስ መኮንኖችን ለመቅጠርና ወደ ስራ ለማሰማራት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ የፖሊስ መኮንኖች አገራቸውን ከወንጀል ድርጊቶች ለመከላከል በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ኡሁሩ ኬንያታ፣ መንግስታቸው ከዚህ በፊት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ የፖሊስ አባላትን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል መስራቱን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የኬንያ ብሄራዊ የፖሊስ አገልግሎት ኮሚሽን የፕሬዚዳንቱን የፖሊስ ሃይል የማጠናከር አገር አቀፍ እቅድ ለማስፈጸም እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የሚመለመሉት 10 ሺህ የፖሊስ መኮንኖችን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡

Read 1459 times