Saturday, 05 March 2016 11:51

የሶርያ ድርቅ ካለፉት 500 አመታት ወዲህ የከፋው ሊሆን ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     - ድርቁ በአካባቢው በሚገኙ 7 አገራት ተከስቷል
     በሶርያና በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን አካባቢ በሚገኙት ቆጵሮስ፣ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ፍልስጤምና ቱርክ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተው ድርቅ፣ በአካባቢው ያለፉት 500 አመታት ታሪክ የከፋው ሊሆን እንደሚችል መጠቆሙን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ከአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ፣ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲና ከአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፣ በአካባቢው እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ መምጣቱን ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ ባለፉት 500 አመታት የአካባቢው ታሪክ የከፋው የመሆን ከፍተኛ እድል እንዳለው መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
ጆርናል ኦፍ ጂኦፊዚካል ሪሰርች አትሞስፌርስ በተባለ የህትመት ውጤት ላይ ለንባብ የበቃውና የአካባቢውን አገራት የረጅም ዘመናት የአየር ንብረት ሁኔታ በመዳሰስ የተዘጋጀው የተመራማሪዎቹ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በአካባቢው አገራት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ ለድርቁ በምክንያትነት ለተጠቀሰው የአየር ንብረት ለውጥ የበካይ ጋዞች ልቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና ድርቁ በግጭትና በእርስ በእርስ ግጭት ለሚታመሱት የአካባቢው አገራት ዜጎች ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን መነገሩንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2015 times