Saturday, 05 March 2016 11:53

የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   - ቢል ጌትስ በ75 ቢ. ዶላር፣ ዘንድሮም አንደኛ ነው
                 - የፌስቡኩ ዙክበርግ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ አግኝቷል
                 - ቻይና ዘንድሮ 70 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
    በየአመቱ የዓለማችንን ባለጸጎች የሃብት መጠን በመገምገም ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው 1ሺህ 810 ባለጸጎች የተካተቱበትን የ2016 የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ አድርጓል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ የሃብት መጠናቸው ከአምናው የ4.2 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ቢልም፣ ዘንድሮም የፎርብስ የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር በአንደኛነት ከመምራት የሚያግዳቸው አልተገኘም፡፡ እኒሁ ስመጥር ባለጸጋ በሃብታቸው መጠን አለምን ሲመሩ የአሁኑ ለ17ኛ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡
ዛራ ፋሽን የተባለው አለማቀፍ የአልባሳት አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ስፔናዊው አማኒኮ ኦርቴጋ፤ በ67 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ 60.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላቸው አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም በ50 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ የአማዞን ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ፣ በ45.2 ቢሊዮን ዶላር አምስተኛው የዓለማችን ቢሊየነር ሆነዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 190 ሴት ቢሊየነሮች መካተታቸውና የወንዶች የበላይነት መግነኑ የታወቀ ሲሆን በ11ኛነት የተቀመጠችውና ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው፣ 36.1 ቢሊዮን ዶላር ያፈራችው የታዋቂው የፋሽንና የመዋቢያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ ሎሪል መስራችና ባለቤት ፈረንሳዊቷ ሊሊያን ቤተንኮርት ናት፡፡
በአመቱ ዝርዝር ውስጥ 540 ዜጎቿ የተካተቱላት አሜሪካ በርካታ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ቻይና በ251፣ ጀርመን በ120፣ ህንድ በ84 እና ሩስያ በ77 ቢሊየነሮች ከሁለት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2016 በርካታ አዳዲስ ቢሊየነሮችን በማፍራት ቀዳሚነቱን የያዘቺው ቻይና ስትሆን፣ 70 ባለጸጎቿን በአመቱ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አካትታለች። በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር በዕድሜ ለጋዎቹ ባለጸጎች ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ፣ የ19 አመቷ የኖርዌይ ተወላጅ አሌክስንድራ አንደርሰንና አንድ አመት የምትበልጣት ታላቅ እህቷ ካትሪና አንደርሰን ናቸው፡፡
ባለፈው አመት 1826 የነበረው የአለማችን ቢሊየነሮች ቁጥር፣ ዘንድሮ ወደ 1810 ዝቅ ብሏል ያለው ፎርብስ፣ ባለፈው አመት ከነበራቸው ሃብት 20.1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳዩት ሜክሲኳዊው ቢሊየነር ካርሎስ ስሊም ከፍተኛ ኪሳራ የገጠማቸው ባለጸጋ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአንጻሩ ከአምናው ሃብቱ የ11.2 ቢሊዮን ዶላር የሃብት መጠን ጭማሪ በማስመዝገብ 44.6 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰውና በዓለማችን የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ደረጃውን ወደ ስድስተኛነት ከፍ ያደረገው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ በአመቱ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ ያስተናገደ ባለጸጋ ተብሏል፡፡

Read 5227 times