Saturday, 05 March 2016 11:58

ለማዳ እንስሳት...በእርግዝና ወቅት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

“...ትዝ ይለኛል። አንዲት ጉዋደኛዬ የመጀመሪያ ልጅዋን እርጉዝ ሆና ሳለች በአጠገቡዋ ድመት አትደርስም ነበር። ለምንድነው ? ብዬ ስጠይቃት ድመትም ሆነች ውሻ በአጠገቤ አላስደርስም። ምክንያቱም በሽታ የሚያስይዙኝ ይመስለኛል...ትል ነበር። እኔ ግን ከድመት ጋር በጣም ቅርብ የሆነ አኑዋኑዋር ስለምኖር የምትለኝን ነገር አልሰማም ነበር። በሁዋላ ግን ሰውነ ፎከት በፎከት ብቻ ሆነ። በጣም ያሳክከኝ ጀመር። ለህክምና በቀረብኩበት ጊዜ የተሰጠኝ መልስ ከለማዳ እንስሳት የሚመጣ ነው የሚል ነበር። ታዲያ እኔ ያውም እርጉዝ ሳልሆን እንደዚህ አይነት ችግር ካስከተለብኝ እርጉዝ ሲሆኑማ ምን ችግር ያስከትል ይሆን?” ነኢማ መሐመድ...ከኮልፌ
በኢትዮጵያ በአብዛኛው ድመትና ውሻ የሚፈለጉት ለአገልግሎት ነው። ድመትም አይጥ የተባለውን ቀበኛ እንድታጠፋ ሲሆን ውሻ ደግሞ ግቢ እንዲጠብቅ የሚፈለግ ነው። ውሻ እንዲያውም በአገራችን ብቻም ሳይሆን በመላው አለም ለተለያየ የደህንነት ስራ የሚፈለግ ሲሆን በቅንነት በታማኝነትና ጉዋደኛ ወይንም የዘመድ ያህል ከአስተዳዳሪው ጋር ይኖራል። በመሆኑም ብዙውን ጊዜ ውሾች ችግር እንዳይደርስባቸው ጥንቃቄ ይደረግላቸዋል። ነገር ግን የተፈለገውን ያህል ቅርበትና ፍቅር ቢሰጣቸውም አኑዋኑዋራቸው ዞሮ ዞሮ ከግቢ ውስጥ እንጂ ወደቤት አይገቡም። ድመቶች ደግሞ አኑዋኑዋራቸው ለየት ያለ ነው። ብዙዎች ከሰዎች ጋር የሚተኙበት ለምግቡና መጠጡም ቅርብ የሚሆኑበት በተለይም ከልጆች ጋር አብረው ለመብላት እስኪቃጣቸው ድረስ ከሰዎች የሚቀራረቡበት ሁኔታ ይታያል። እናም ነኢማ እንዳለችው ለመሆኑ እነዚህ ለማዳ እንስሳት ሕመም ያስከትላሉ? ወይንስ? በሚል ጥያቄአችንን በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ለዶ/ር ሙህዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አቅርበናል። እሳቸውም ማብራሪያቸውን የሰጡ ስለሆነ ታነቡ ዘንድ አቅርበናል።
“...ነገሩን ጠለቅ ብለን ሳናስተውለው ሳንጨነቅና ችግር ያስከትል ይሆናል ብለን ሰለማናስብ ችግር የሌለ ይመስለናል እንጂ ለማዳ እንስሳቱ ለሰዎች እንዲወዱዋቸው የሚያስችላቸው ባህርይ ቢኖራቸውም የጤና ችግር ማስከተላቸው ግን አይቀርም። “ አሉ ዶ/ር ሙህዲን።
ጥያቄ፡ ለመሆኑ ለማዳ እንስሳት የሚባሉት የትኞቹ ናቸው?
መልስ፡ ተላማጅ እንስሳት የሚባሉት በአሁኑ ወቅት ዘርፋቸው እየበዛ ነው። በእርግጥ በቀደመው ጊዜ በተለምዶ የሚታወቀው ከሰው ጋር በመላመድ የሚኖሩ ውሻና ድመት ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ግን ከአእዋፍ ዝርያዎችም እንደፓሮት የመሳሰሉት እንዲሁም ከተሳቢ እንስሳቶች እንደኤሊ የመሳሰሉት ሁሉ በለማዳ እንስሳነት ተመድበዋል። በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንደህብረተሰቡ የአኑዋኑዋር ወግና ባህል ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ተላማጅ እንስሳት መኖራቸው እርግጥ ነው። በእኛ አገር ግን ውሻና ድመት እንዲሁም አልፎ አልፎ ፓሮት በለማዳ እንስሳነት ተመድበዋል። በአለም ላይ ውሻና ድመት እንዲሁም ፓሮት 62/ከመቶ በሚሆኑ ቤቶች ከሰዎች ጋር በቅርበት እንደሚኖሩ ይገመታል።
ጥያቄ፡ ለማዳ እንስሳት በሰው ላይ የሚያስከትሉት የጤና ችግር ምንድነው?
መልስ፡ በእርግጥ እኛ አገር ውስጥ የተደረገ ጥናት የለም። በአንድ ወቅት በአሜሪካ አገር ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በአመት ውስጥ ወደ 4/አራት ሚሊየን የሚሆኑ በተላማጅ እንስሳት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎች መመዝገባቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። በቆዳ ላይ ከሚታይ አነስተኛ ሽፍታ ጀምሮ አስከፊ እስከሆነው ማለትም ለሕይወት አስጊ እስከሆነ የበሽታ አይነት ሊያመጡ ይችላሉ። በለማዳ እንስሳት የሚከሰቱ ሕመሞች ምንድናቸው ሲባል ...
በአይን ከማይታዩ ጥቃቅን ማይክሮስኮፒክ ኦርጋኒዝምስ የምንላቸው ጀምሮ ከዋና ዋናዎች ውስጥ እንደ ጭርት ወይንም ቋቁቻ የመሳሰሉ፣
በባክሪያ አማካኝነት የሚመጡ እንደ ተስቦ የመሳሰሉ፣
በቫይረስ አማካኝነት ከሚመጡ እንደ አደገኛው ሬቢስ ወይንም የእብድ ውሻ በሽታ የሚባለው፣
በፕሮቶዞዋ አማካኝነት የሚከሰቱ እንደ እከክ አይነት ሕመሞችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ከላይ ከተጠቀሱት በሽታዎች በተጨማሪ በጣም አደገኛው ቶክሶፕላዝሞሲስ ፕሮቶዞዋ ሲሆን በአይን ከማይታዩ ጥቃቅን ሕዋሳት አንዱ ሆኖ ከእንስሳት ወደሰው ከሚተላለፉት በሽታዎች እጅግ በጣም ግዙፉን ቁጥር የሚይዘው የኢንፌክሽን አይነት ነው። ይሄ ኢንፌክሽን በአብዛኛው ከውሻና ከድመት ወደሰው የሚተላለፍ ነው። ይህ በአይን የማይታይ ጥቃቅን ሕዋሳቶቹ ወደሰው ሊተላለፉ የሚችሉት ፡-
በቀጥታ ግንኙነት በማድረግ የድመቶቹን ሰገራ ወይንም ሽንት በቀጥታ በእጅ በመንካት
የድመቶቹን ሰገራ ወይንም ሽንት ለማጽዳት በምንንቀሳቀስበት ጊዜ በአየር አማካኝነት ወደ መተንፈሻ አካል ሊገባ ሲችል ሌላው የመተላለፊያ መንገድ ነው።
ጥያቄ፡ የዚህ ሕመም ምልክት ምንድነው?
መልስ፡ ምልክቶቹ በጣም አነስ ያሉ ናቸው። አነስተኛ የሆነ የኢንፌክሽን ስሜት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ...ለምሳሌ ጆሮ ከጀርባው ባለው ክፍል ማበጥ፣ የሰውነታቸው አቅም ደከም ያሉ ሰዎች ላይ ደግሞ እራስን እስከመሳት የሚያደርስ ሕመም ሊያስከትል ይችላል።
ጥያቄ፡ እርጉዝ የሆኑ እናቶች ላይ ምን ችግር ያስከትላል?
መልስ፡ እርጉዝ እናቶች ሕዋሱ ወደሰውነታቸው ከገባ በተለይም በመጀመሪያው 3/ሶስት ወር ላይ የእንግዴ ልጅን በቀላሉ ማለፍ የሚችል ስለሆነ ጽንሱ እንዲመረዛ ያደርጋል።
ጽንስ ከተመረዘ የአፈጣጠር ችግር ያለበት ልጅ እንዲወለድ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ጽንሱ ካለጊዜው እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል።
የጽንስን ክብደት በማስተጉዋጎል የተፈለገውን ክብደት እንዳይይዝ ሊያደርግ ይችላል
የጽንሱ የአፈጣጠር ችግር የከፋ ሲሆን ደግሞ ጭንቅላታቸው በጣም ትልቅ መሆን እንዲሁም ነርቭ ሲስተም ውስጥ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
ባጠቃላይም ጽንሱ ጊዜው ሳይደርስ እንዲወለድ ወይንም ደግሞ በእናቱ ማህጸን ውስጥ እንዳለ እንዲሞት ሊያደርግ ይችላል። የተጠቀሰው ከችግሮቹ መካከል ጥቂቱ ነው።
ጥያቄ፡ በሕጻናት ላይ የሚያስከትለው ችግር ምን ይመስላል?
መልስ፡ ሕጻናቱም እንደማንኛውም ሰው በሁሉም ነገሮች ሊጠቁ ይችላል። በተለይም በጣም መተሸሸትና እንስሳቱን መቅረብ ስለሚወዱ የውሻ ወይንም የድመት ጸጉር በሚበንበት ጊዜ የመተንፈሻ አካል ችግርን ሊያስከትልባቸው ይችላል። በእርግጥ ይህ ለሁሉም ሰው የሚደርስ ችግር ነው።
ጥያቄ፡ ጥንቃቄው ምንድነው?
መልስ፡ የመጀመሪያው እጅን መታጠብ ነው።
ለማዳ እንስሳቱን በተለያየ መንገድ ከነካን በሁዋላ ወይንም ብንነካም ባንነካም ምግብ ከመመገባችን በፊት እጅን በሚገባ መታጠብ ተገቢ ነው።
ሁለተኛው ነገር ለማዳ እንስሳት የሚጸዳዱበት ቦታ እና ቆሻሻቸው የሚወገድበት ቦታ በስነስርአቱ መዘጋጀት አለበት።
ለማዳ እንስሳቱ በቂ እና ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለባቸው።
እርጉዝ እናቶች ለማዳ እንስሳቱ የሚያድሩበት የሚውሉበትን ቦታም ሆነ የሚጸዳዱበትን አካባቢ መነካካት የለባቸውም። እርጉዝ እናቶች ለማዳ እንስሳት በቤታቸው ባይኖሩዋቸው ይመከራል።
ለማዳ እንስሳቱ የሚመገቡዋቸው ምግቦች የበሰሉ መሆን ይገባቸዋል። በንክኪም ይሁን ከተጸዳዱ በሁዋላ በሚኖረው ቆሻሻ አማካኝነት የሚተላለፉት ሕመሞች ዋና ምክንያት እንስሳቱ ያልበሰለ ስጋ የመሳሰለውን ስለሚመገቡ እና እነርሱ በበሽታው ተጠቅተው እንደገና ወደሰው የሚያስተላልፉበት መንገድ ሰፊ ስለሆነ ነው።
ሕብረተሰቡ ይሀንን ችግር አስቀድሞ አውቆ እንዲከላከል የሚችልበትን ግንዛቤ መፍጠር ሌላው የመከላከያ መንገድ ነው። ትምህርት መስጠቱ ያስፈልጋል። በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ወይንም በሐኪሞች እንዲሁም በእንስሳት ሐኪሞችም አማካኝነት ትምህርቱ ለህብረተሰቡ ሊሰጥ ይገባል።

Read 4127 times