Saturday, 12 March 2016 10:31

‘ግራ የገባው’ ለ‘ዳያስፖራው’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሚቀጥለው ደብዳቤ አገር ቤት ያለ ‘ግራ የገባው’ የአገር ልጅ ለ‘ዳያስፖራው’ አብሮ አደጉ ጽፎት ሊሆን ይችላል ተብሎ ‘ቢታሰብም’ ችግር የለውም፡፡
ለውድ አብሮ አደጌ፣ እንደምን ከረምክልኝ፡፡ እኛ እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነን፡፡
እውነት፣ እውነት እልሀለሁ በሰው የላክኸው የቃል መልእክት ሲደርሰኝ ገረመኝም፣ ግራ ገባኝም። ከአንተ ለመጨረሻ ጊዜ ሰላምታ ሲደርሰኝ አንድ ስምንት ዘጠኝ ዓመት አይሆንም! ለነገሩ አሁን፣ አሁን የምትሰማው ሁሉ አሳስቦህ የት ጉደባ ነው ያለው ብለህ በማጠያያቅህ አመሰግናለሁ። የላክህልኝ ጉርድ ሸሚዝና ጂንስ ሱሪ ደርሶኛል፡፡ አመሰግናለሁ።
ምን ያህል እንድተለያየን ያወቅሁት ጉርድ ሸሚዝ ስትልክልኝ ነው፡፡ ጉርድ ሸሚዝ ለብሼ አደባባይ ብወጣ ሰዉ “ብሎ፣ ብሎ ሸሚዙ ውስጥ የመጥረጊያ እንጨት ሰክቶ መሄድ ጀመረ!” ብሎ መዘባባቻ ያደርገኛል፡፡ የድሮው እንዳልመስልህ፡፡ ኑሮና ነገር ተብባረው ቦምብ ያፈራረሰው የደማስቆ ጎጆ አስመስለውኛል። እንኳን ጉርድ ሸሚዝ ላደርግ የማደርጋቸው ካናቴራዎች እንኳን እጀ ሙሉ ናቸው፡፡ የሰው አፍ እንዴት እንደሚያንገበግብ አታወቀውም፡፡
አብሮ አደጌ፣ ጻፍልኝ ባልከው መሰረት ይኸው ይቺን ሞነጫጭሬያለሁ፡፡ ደግሞ ደብዳቤው መጨረሻ ላይ ላፕቶፐ ላክልኝ፣ ብሉቤሪ ላክልኝ ምናምን ይለኛል ብለህ አታስብ፡፡
ከቻልክ፣ እንደው የሆነ ቴከኖሎጂ ካለ…. የትርፍ ኪሎውንም ከፍለህ ቢሆን በየሻንጣው የ‘አእምሮ ሰላም’ ላክልኝማ፡፡
ስም ጠቅሰህ አብሮ አደጎቻችን እንዴት ናቸው ላልከው ምን ልበልህ… መቼም በስም አልጠቅስልህም እንጂ ሁለቱ መንገድ ላይ ብቻቸውን እያወሩ መሄድ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡ ሲወራጩ ብታያቸው ሀምሌት እንኳን ብቻውን ሲለፈልፍ እንደ እነሱ አይወራጭም፡፡ ሀምሌትን የጠቀስኩት ወይ አንብቤው፣ ወይ በፊልም ወይ በትያትር አይቼው እንዳይመስልህ! ልመሳሰል ብዬ ነው፡፡ ካልተመሳሰልክ መኖር አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ከቴሌና ከመብራት ሀይል ቢል ሌላ አንብቤ የማላውቀው ሰው ለመምስል ብዬ አነበብኳቸው የምላቸውን መጽሐፍት ብዛት ብታይ…መለስተኛ ቤተ መጽሐፍ ሞልተው ይተርፋሉ፡፡ ይኸውልህ የማስመሰል ደዌ አገሬን እያመሳት ነው፡፡ የንጉሥ አነጋገር መሰለብኝ እንዴ!
ሌሎቹ አብሮ አደጎቻችን ደግሞ በድሮ ቋንቋችን ልንገርህና ድክርት ብለዋል፡፡ አንደኛው ያው ውሀ እንደሚወድ ድሮም ቢሆን ታውቀዋለህ… ብራንዲ የሚጠጣ ሳይሆን ራሱ የብራንዲ ጠርሙሷን መስሎልሀል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ኃይማኖተኛ ይሁን፣ ፈላስፋ ይሁን፣ መድኃኒት አዋቂ ይሁን ግራ አጋብቶናል፡፡
ይኸውልህ አብሮ አደጎችህ እንዲህ ነን፡፡ ደህና የምንባለው እኛ ደግሞ የጓዳችንንን በጓዳ ደብቀን በአደባባይ ሰው ለመምሰል ስንሞክር… “አጅሬው ሁሌ እንደተስማማህ ነው…” እየተባልን እንኖራለን፡፡
ለነገሩ ጓዳ የሚባል ነገር ድሮ ቀርቷል፡፡ ይኸውልህ ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ተከራይቼልሀለሁ። ቤት ውስጥ ወዲህ፣ ወዲያ ስንተላለፍ ስለሚጠበን ‘‘አንተ እለፍ” “አንቺ እለፊ” እየተባባልን ነው፡፡
መቼም የኑሮ መወደድን ነገር ሳትሰማው አትቀርም፡፡ እኔ ቤት እንኳን ጤፍ በጆንያ ማስቀመጥ ከተውን ስንት ጊዜያችን፡፡ አሁን ያለችንን የጤፍ ዱቄት ሰፋ ባለ አሮጌ ድስት ውስጥ ነው የምናስቀምጠው፡፡ ያልተወደደ ነገር የለም፡፡
በዚህ ላይ ቤት ውስጥ ሰላም ቢኖር መልካም። ለዘመድ አዝማድ ነግሬ የሰው መዘባበቻ አልሆንም ብዬ እንጂ ሚስቴ ዮዲት ጉዲት ሆናብኛለች፡፡ እኔ ነኝ እንዴ የበርበሬውን ዋጋ በርበሬ ያደረግሁት! ቢቸግረኝ… “በርበሬ መግዛት ካልቻልን አልጫ እንበላለን” አልኳት። ምነው አፌን በዘጋው ነው ያልኩት! “ድሮስ አልጫ ወንድ ከአልጫ ሌላ ምን ያውቃል አለችኝ፡፡” ምን ታድርግ… እንደ መቶ ብራችን አቅሜ መመናመኑን አየቻ! ይባስ ብላ በራሷ ፈቃድ እንደፈለገችው እያመሸች መምጣት ጀምራለች፡፡ ብቻ መጨረሻችንን ያሳምረው። “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች ሲባል ሰምተሀል! የእኔ ሚስት እንኳን ለልጆቿ ብላ ልትወጋ ራሷ ጎሽ ሆና እኔኑ እየወጋችኝ ነው፡፡
ልጆችህ ላልከው መቼም ይመስገን ነው የሚባለው፡፡ ሴቷ ዘንድሮ ስድስተኛ ክፍል ትፈተናለች፡፡ ወንዱ ደግሞ ስምንተኛ ተፈታኝ ነው። እነሱን ለማስተማር እየለፋሁ ያለሁትን ብነግርህ ትደነግጣለህ፡፡
ከሰው አላንስም፣ ልጆቼን አላሳቅቅም ብዬ ጉዴን በጉያዬ ሸጉጬ የግል ትምህርት ቤት አስገባኋቸው፡፡ ስለገንዘቡ አትጠይቀኝ፣ ስለ ደሞዜም አትጠይቀኝ፡፡ ብነግርህ አማኝ ሆንክም አልሆንክ ተአምር የሚባል ነገር እውነት እንደሆነ ታውቃለህ፡፡
ይኽውልህ ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚያደርጋቸው ትምህርት ይቀሰማሉ ብዬ… ለካስ የግል ትምህርት ቤትም ብዙ ጉድ አለ፡፡ እሱ ብቻ ይጠብቅልኝ፡፡
አሁን አሁንማ መጽሐፍ ግዛ፣ ደብተር ግዛ ማለት ትተውልሀል፡፡ አሁን ግዛ የሚሉኝ ስማርትፎንና ላፕቶፕ! በቀደም እንደውም ወንዱ ልጅ መጣና ምን ቢለኝ ጥሩ ነው…
“አባዬ፣ ሰማህ?” አለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ትምህርት ቤቱ ምን ተፈጠረበት ብዬ…
“አልሰማሁም፣ ምን ተፈጠረ?” አልኩት። ነገ የት ይደርስልኛል ያልኩት ልጄ ምን አለኝ መሰለህ… “አባዬ ሳምሰንግ እኮ ጋላክሲ ኤስ 7 አወጣ!” አለኝልህ፡፡ ነገሩ እኮ በተዘዋዋሪ ማመልከቻ ማስገባቱ ነው፡፡ የእኔ የአባታቸውን የእጅ ስልክ ብታያት ድሮ በአምስት ብር የምንገዛትን ዲስኮ ሰዓት ትመስላለች። ብቻ… ያንን ያለኝ ዕለት ከአሁን አሁን “ግዛ!” ይለኛል ብዬ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ነው ያደረው፡፡
ከየት ላምጣ! ከየት ላምጣ! ድርጅቱም፣ ግለሰቡም፣፡ ማህበሩም፣ ምኑም ምናምኑም ኪሳችንን ነው የሚያየው! “ኧረ ኪሳችን ባዶ ነው!” ስንል የሚያምነን እያጣን ነው፡፡
ሚዲያውንማ ተወው፡፡ ‘ፍሪ ፎር ኦል’ የምትሉትን ሆኖልሀል፡፡ ደግሞልህ ዕጣ አልደርስህ ብሎኝ በገዛኋት ዕቁብ የሸመትኳትን ቲቪ በሰላም እንዳላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ “ከእኔ በላይ ላሳር፣” የሚል ፎካሪ በዛባት። የፈረደባቸውን ያለፉትን ሰዎች መቃብር እየቆፈሩ ድንጋይ መወርወር የእውቀት ጥግ የሚመስላቸውን ሰዎች ሲያዩ ከማውቃቸው ስኳር፣ ደም ብዛትና ሌሎች በሽታዎቼ  በተጨማሪ ስሙን የማላውቀው በሽታም ይይዘኛል፡፡ አብሮ አደጌ ስማኝ፣ በአንድ ጊዜ ደም ብዛትም፣ ደም ማነስም የያዘው ብቸኛው ሰው እኔ ሳልሆን አልቀርም! ልቀልድ እንጂ፣ ምን ላድርግ! የእኔዪቷ አገር ውስጥ የማይሆን ነገር የለም፡፡
ይኸውልህ ዘላለማችንን ትናንትን ስንኮንን፣ ትናንትን ስናብጠለጥል የምንኖር እኛ ብቻ ሳንሆን አንቀርም፡፡ በዚህ፣ በዚህ እንኳን ጊነስ ቡክ ወስጥ ሁሉ መግባት እንችላለን። ነገ የምንለው ነገር እያጣን ነው፡፡ አብሮ አደጌ አሳዝኜህ ከሆነ ይቅርታ። ምን ላድርግ…ባትጠይቀኝ ባልፈለፍኩ። የትኛውን የኃይማኖት አባት እንደምትሰማ እንኳን ግራ የገባ ጊዜ ነው። አገር ሲተራመስ “ኧረ ተዉ፣ በፈጣሪ ስም ይዘናችኋል...” የሚል ማግኘቱ ብርቅ ሆኖብናል።
ስማኝ አብሮ አደጌ፣ ለመሆኑ አንተስ እንዴት ነህ? እኔ አንዳንዴ ነጩ ፖሊስ አንድን ምስኪን ጥቁር በአሥራ ምናምን ጥይት ደብድቦ ገደለው ሲባል… ምን ስታደርግ እንዲህ አሰብክ አትበለኝና አንተ ትዝ ትለኛለህ፡፡ እንደ ድሮ ሞገደኛነትህ “ምን ታየኛለህ…” ሲልህ “ምናባክ እንዳትሆን!” ብሎት ጥይት ቆጥሮበት እንዳይሆን እላላሁ፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን!
ይልቅ ልንገርህ የኳስ ፍቅራችን የት ደርሷል መሰለህ! የኳስ ፍቅር ልበልህ እንጂ! ይኸው የእንግሊዝ ኳስ ቤቴ ገብቶልህ ህጻናቱ ቤቱን እየናጡት ነው። ልጅቷ የአርሴናል ደጋፊ ስትሆን ወንድሟ ደግሞ ማንቼስተር ዩናይትድ ነው፡፡ በቀደም ማንቼስተር አሸነፈ መሰለኝ ሲጯጯሁ ጎን ኮንዶሚኒየም ያሉ ሰዎች መጥተው በራችንን አንኳኩተው “ምን ሆናችሁ፣ ሰው ታመመባችሁ እንዴ!” አሉን፡፡ እኔ ቤት እኮ ያለው ይሄ ነጻው የዓረቡ ዲሽ ነው፡፡ የት ሄደው እንደሚያዩ ግርም ይለኛል፡፡
ይግረምህና አንድ ሰሞን ሚስቴ አንኳን ኳሱን የት እንደምታይ አላውቅም… “እንደው ይሄ ሞሪንሆ የሚሉትን ሰውዬ ስወደው!” ብላኝ ሌሊቱን ቁልጭ ብዬ ነው ያደርኩት፡፡
“አሁን ሞሪንሆን የምታነሳው እኔን ለማስቀናት እንጂ ምኑን አውቃው ነው!” እያልኩ ጨጓራዬን ስልጥ አደርኩልህ፡፡ አትታዘበኝና ከመጠርጠሬ የተነሳ ጠዋት መልኬን በመስታወት ሁሉ አይቻለሁ። ጉድ እኮ ነው ሰዎች… የፈለገውን ያህል ፉንጋ ብሆንስ! ባህር ተሻግራ በሞሪንሆ ትፈትነኛለች፡፡
ይኸውልህ አገር የቤቱ እያረረበት የእንግሊዝን ኳስ ያማስላል፡፡ ድሮም እንግሊዝ የሚገባው ሰርስሮ ነው፡፡ የማዝነው ለልጆቼ፡፡
አብሮ አደጌ ድፍን ወር ባወራልህ የእኛ ነገር አያልቅም፡፡ ሌላ ጊዜ አወራልሀለሁ፡፡ ደህና ሁን ጓዴ፣ በዓይነ ስጋ ለመገናኘት ያብቃን፡፡
እናንተም ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5577 times