Saturday, 12 March 2016 11:21

በቦክስ የኦሎምፒክ ማጣርያ በያውንዴ ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  4 ወጣት የኢትዮጵያ ቦክሰኞች በቀላል ሚዛን ይፋለማሉ
     4 የብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጂኔሮ በምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ  በቦክስ ስፖርት የአፍሪካን ተወካዮች ለመለየት  በካሜሮን ዋና ከተማ ያውንዴ የማጣርያ ግጥሚያዎች ትናንት ተጀምረዋል፡፡ በማጣርያው ኢትዮጵያ ከ52 እስከ  64 ኪሎግራም ባለው የቀላል ሚዛን  መደብ 4 ወጣት ቦክሰኞችን  ታሳትፋለች፡፡  
ባለፈው ማክሰኞ በካፒታል ሆቴል ለቦክሰኞቹ በኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት ፌደሬሽን ሽኝት  ተደርጓል፡፡ የፌደሬሽኑ አመራሮች  ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃና  በባለሙያዎች የተደገፈ ዝግጅት መካሄዱን ገልፀው፤ በተለይ ካፒታል ሆቴል ቦክሰኞቹ በ20 ቀናት ዝግጅታቸው ማረፊያ፤ምግብ ፤ የጂም አገልግሎትና የባለሙያ ድጋፎችን በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው በመጥቀስ አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም የወጣቶቹ የኦሎምፒክ ህልም እውን ከሆነ  ካፒታል ሆቴል ድጋፉን እንደሚያጠናክር የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቦክስ ስፖርት ፌደሬሽን ሃላፊዎች ዓለም አቀፍ ተሳትፎን በሚያመቻቹ ሁኔታዎች ለመስራት በኦሎምፒክ መድረክ መሳተፍ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ይገልፃሉ፡፡
የገቢ አቅም በሚያጠናክሩ፤  እና የክለቦችን ንቁ ተሳትፎ በሚያሳድጉ ውድድሮች በመስራት ላይ እንደሆኑም በማስረዳት፤   ኢቢኤስ የቴሌቭዥን ጣቢያ በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እና ውድድሮችን በማዘጋጀት ለሚያደርገው ድጋፍ እንዲሁም  የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለውድድሮቹ በቂ እና ወቅታዊ ሽፋን በመስጠት ለሚያከናውናቸው ተግባራትም ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
የኦሎምፒክ ማጣርያው በያውንዴ
የአፍሪካ ቦክስ ስፖርት  የኦሎምፒክ ማጣርያ በያውንዴ ከተማ ትናንት ተጀምሮ ለሚቀጥሉት 8 ቀናት የሚካሄድ ነው፡፡ በውድድሩ ታሪክ ሪከርድ ሆኖ በተመዘገበ ብዛት ከ38 አገራት 272 ቦክሰኞች  ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ በ31ኛው ኦሎምፒያድ አፍሪካ በቦክስ ስፖርት  ለ30 ወንድና 6 ሴት ቦክሰኞች የተሳትፎ  ኮታ ተመድቦላታል፡፡ ከማጣርያው በፊት አፍሪካን በመወከል በኦሎምፒክ የመሳተፍ እድላቸውን ያረጋገጡ 5 ቦክሰኞች በመኖራቸው ግን  በማጣርያው በወንዶች ምድብ የሚወሰነው ቀሪው የ25 ቦክሰኞች ኮታ  ነው፡፡  ለሪዩ 2016 ኦሎምፒክ ማለፋቸውን ካረጋገጡት 5ቱ ቦክሰኞች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሚሆነው የመጀመርያው አፍሪካዊ የዓለም ሻምፒዮንና በ2015 የአፍሪካ ምርጥ ቦክሰኛ ሆኖ የተሸለመው የሞሮኮው መሐመድ ራቢ ነው፡፡ ሌሎቹ ቦክሰኞች 1 የሞሮኮ፣ 2 የአልጀሪያ እንዲሁም 1 የግብጽ   ናቸው፡፡ በያውንዴ በሚካሄደው  የቦክስ ስፖርት  የኦሎምፒክ ማጣሪያ ላይ የአዘጋጇ ካሜሮን የናይጀሪያ፣ የቱኒዚያና የግብጽ ቦክሰኞች ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተዘግቧል፡፡     
‹‹በባለሙያዎች ክትትል ፤ በምቹ ማረፊያና ምግብ ፤የጂም አገልግሎት የተጠናከረ ዝግጅት አድርገናል››
ዋና አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ሰለሞን ወልደ ኪዳን
 የቦክስ ብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ሰለሞን ወልደ ኪዳን ነው፡፡  በክለብ ደረጃ በቀድሞ ስሙ ኦሜድላ አሁን ፌዴራል ፖሊስ በሚባለው ክለብ ተወዳዳሪ የነበረው ኢንስፔክተር ሰለሞን ፤ በክለቡ ላለፉት 8 ዓመታት በዋና አሰልጣኝነት ከሠራ በኋላ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ሃላፊነት መጥቷል፡፡ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ ለአፍሪካ ተወካዮች በሚካሄደው ማጣርያ የኢትዮጰያ ቦክሰኞች ባለፈው 1 ዓመት በነበራቸው ልምድ ጥሩ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠብቃል ፡፡
ከዚህ የኦሎምፒክ የመጨረሻ ማጣርያ በፊት በዋና አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ሰለሞን የሚመራው ቡድን ደህና ውጤት ያስመዘገበ ነው፡፡ ቦክሰኞቻችን ገና ወጣቶች ቢሆኑም በአህጉራዊ ውድድሮች ልምዳቸው ጠንካራ ነው የሚለው ዋና አሰልጣኙ ኢንስፔክተር ሰለሞን ወልደሚካኤል፤ ቦትስዋና ላይ በተካሄደ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ  ተሳትፈው የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን እንዳገኙና በኮንጎ ብራዛቪል ተካሂዶ በነበረው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በቀላል ሚዛን 49 ኪሎግራም፤ በመካከለኛ ሚዛን 64 ኪሎግራም እንዲሁም  በከባድ ሚዛን 75 ኪሎግራም ሶስት የነሐስ ሜዳልያዎችን ማግኘታቸውን ይጠቅሳል፡፡   በካሜሮን በሚካሄደው የኦሎምፒክ ማጣርያ ሲሳተፉ ይህ ልምድ ተጠቅመው ነውም ብለዋል፡፡ የኢትዮጰያ ቦክሰኞች በአፍሪካ ደረጃ በተመሳሳይ እና ጥሩ ደረጃ ላይ መሆናቸውን በሙሉ ልብ የሚናገሩት ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ምናልባት በአሜሪካ እና በአውሮፓ በፐሮፌሽናል ደረጃ የሚጫወቱ ቦክሰኞች ያሏቸው የምእራብ አፍሪካ አገራት ሊጠንክሩባቸው ይችላል ሲል ተናግሯል፡፡አራቱ ወጣት ቦክሰኞች ለኦሎምፒክ ማጣርያው ልዩ ዝግጅት ማድረጋቸውንም የገለፀው ኢንስፔክተር ሰለሞን፤ በካፒታል ሆቴል ሙሉ ወጭያቸው ተሸፍኖ፤ በጂምናዚያሙ እና በምግቡ ለ20 ቀናት ያደረጉት ዝግጅት በጣም ጥሩ የሚባል ነው ብሏል፡፡  ኢንስፔክተር ሰለሞን እሱ ከሚሰራው ዋና ስልጠና ባሻገር የተለያዩ ባለሙያዎችን በድጋፍ ሰጭነት በማሳተፍ ዝግጅት መደረጉን ይገልፃል፡፡ በተለይ የአካል ብቃት ዝግጁነቱን ከዶክተር ኤልያስ አቢሻከር ባገኙት ድጋፍ በማከናነወናቸውና ፤ ከካፒታል ሆቴል ጂምናዚዬም እና ስፓ የፊቲነስ ባለሙያም አብረው መስራታቸው ዝግጅታችንን አጠናክሮታል ሲል ይናገራል፡፡
ወጣቶቹ ቦክሰኞች ለረጅም አመት በስፖርቱ  ከኦሎምፒክ የራቀውን የኢትዮጰያ ተሳትፎ በማነቃቃት ይጠቅማል የሚለው ዋና አሰልጣኙ፤ የቦክስ ስፖርት ስልጠናው አድካሚ፤  የስፖርተኛው የብቃት ደረጃ የሚጠይቅ፤ ጥበባዊ የሆነውን ስፖርት አክብሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብሎ፤ በኢኮኖሚ ጠቀሜታውም ላይ ትኩረት አድርገው ሁሉም ክለቦች መስራት ይኖርባቸዋል በሚል መልዕክቱን አሳትፈዋል፡፡
‹‹የአካል ብቃት ልኬት በተቋም ደረጃ ልሰራ ነው››
ዶክተር ኤልያስ አቢሻክራ  
ዶክተር ኤልያስ አቢሻክራ  በፈረንሳይ ለ37 ዓመታት እየኖሩ ፤ የተማሩና የሰሩ ባለሙያ ናቸው፡፡ በጆግራፊ ቢኤ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በስፖርት ሳይንስ ማስትሬት ዲግሪያቸውን  በፈረንሳይ አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪ በካራቴ ስፖርተ አሰልጣኝነት ከፍተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ከፈረንሳይ የካራቴ ፌደሬሽን ከፍተኛ ውድድሮችን በማለፍ 5ኛ ደረጃ ጥቁር ቀበቶ ታጥቀዋል፡፡  
የአካል ብቃት  እንደ ስፖርቱ ብዙ አይነት እና የአሰራር አቅጣጫ እደሚለያይ የሚገልፁት ዶክተር ኤልያስ፤ በቦክስ ትልቁ የብቃት መለኪያ የተወዳዳሪው ፅናት ቢሆንም ጉልበት ጠንካራ ምቶች እንዲሰነዝሩ የሚያስፈልገው ጉልበት፤ በየዙሩ ጫና ካለበት ግጥሚያው በፍጥነት የሚያገግሙበትን ሁኔታ  መለካት ስለሚኖርበት ለወጣቶቹ ቦክሰኞችይህን ተግባር አከናውኛለሁ ብለዋል፡፡ በሰውነታቸው ያለውን የስብ መጠን፤ የፅናታቸውን ደረጃእና ቶሎ የማገገም ሁኔታዎችን በመለካት ጥሩ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ ዶክተር ኤልያስ አቢሻክራ ለኦሎምፒክ ለመብቃት ለማጣርያ ግጥሚያ ወደ ብራዚል ለሚሄዱት አራቱም ወጣት ቦክሰኞች የአካል ብቃት የመለካት ተግባራትን በግል ተነሳሽነት እንዲሁም ከአሰልጣኛቸው ሰለሞን ጋር መልካም ግንኙነት ስላላቸው ዝግጅቱን በሙያቸው ደግፈዋል፡፡ አራቱ ወጣት ቦክሰኞች በጥሩ ዝግጅት መቆየታቸውን  በልኬቴ ለማረጋገጥ ችያለሁ ያሉት ዶክተር ኤልያስ፤ የአካል ብቃትን መለካት አስፋላጊ እንደሆነ ሲያሳስቡ ቦክሰኞቹ ማጣርያውን አልፈው ኦሎምፒክ ከገቡ በከፍተኛ ደረጃ ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ ብሏል፡፡ በመጀመርያው የአሜሪካ የቦክስ ክለብ የሚሰራውና ያስተማርኩት  አሰልጣኝ ፍሯንሷ ሊዤ ከሌላ የዓለም ሻምፒዮን ከሆነ ወጣት ቦክሰኛ ጋር ወደ ኢትዮጰያ መጥተው የልምድ ልውውጥና የባህል ተመክሮ ለመፍጠር ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር እየሰሩ መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡በኢትዮጰያ የአካል ብቃት መለኪያ ፕሮፌሽናል ላብራቶሪ ተቋምን ለመመስረት በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡ በአውሮፓ ደረጃ ለመስራት  ዝግጅቱን እያጠናቀቅን ነው የሚሉት ዶክተር ኤልያስ፤ ለላብራቶሪ የሚያስፈልጉ አብዛኛዎችን መሳርያዎች ወደአገር ውስጥ ማስገባታቸውን ጠቅሰው እሰከ 45ሺ ዶላር የሚያወጣ የስፖርተኛውን ፅናት የሚለካ የኢንዱራንስ መሳርያ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውንም እንዲሁም የጉልበት መለኪያ መሳርያን ለማስመጣት እየተንቀሳቀስኩ ነው ብለዋል፡፡ የተቋማቸውን ይስራ ሃሳብ በፈቃድ ለመተግበር ለንግድ ሚኒስቴር እንዳመለከቱ እና ለወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትርም አስገብተው ከሚያደርጉት ውይይት በኋላ ስራ የሚጀምሩበትን  እድል ሊፈጥር ይችላል እንደሆነ ዶክተር ኤልያስ ሲገልፁም የላብራቶሪው መቋቋም ትልቅ ርምጃ ነው ብለው፤ በአገሪቱ የስፖርት እንቅስቃሴ መስፋፋት ያለበት የሙያ መስክ መሆኑን በምናከናውናቸው ተግባራት እናረጋግጣለን ይላሉ፡፡ ከስቶፕ ዎችና ከልሙጥ ሜትር ወጥተን ደረጃቸውን በጠበቁ የስፖርት ብቃት መለኪያ መሳርያዎች ለመስራት ሁሉም የስፖርት ባለድርሻ አካላት ጉልህ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ስፖርት በሳይንስእና ቴክኖሎጂ፤ እና በከፍተኛ ደረጃ በተማሩ ባለሙያዎች ምርምር፤ ክትትል እና ጥናት ተደግፎ ስልጠናው የሚጠናከር ሊሆን እንደሚገባው ዶክተር ኤልያስ አቢሻክራ ያስገነዝባሉ፡፡
በአገሪቱ የስፖርት እንቅስቃሴ የአካል ብቃት እና የዝግጅት ሁኔታ በቴክኖሎጂ መሳርያዎች አለመለመድ፤ አለመኖር እና ባለሙያዎችን አቅርቦ ባለማሰራት ገሚሱ አስፈላጊውን ግምገማ አያድረጉም ብለውም፤ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ፤ ከአንዳንድ ክለቦች ጋር እንዲሁም አሁን ከቦክስ ፌደሬሽኑ ጋር በጀመሩት ትስስር ሁኔታውን ለማስፋፋት ፍላጎት አላቸው፡፡ የስፖርተኛ ብቃት በረቀቀ ልምምድ፤ ሳይንሳዊ ልኬት እና የተተነተነ መረጃዎች መመራት አለበት የሚሉት ዶክተር አቢሻከር የኢትዮያ ስፖርት በእነዚህ ወሳኝ አቅጣጫዎች መመራት እንዳለበት ሲመክሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ለመሆን ወሳኝ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ከዘመናዊውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ከሚደረገው የስፖርት እንቅስቃሴ ብዙ ርቀን ነው ያለነው የሚሉት ዶክተሩ፤ በተለይ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች ስፔሻላይዝ እየሆኑ መንቀሳቀስ አለባቸው ብለው በክለብ፤ በብሄራዊ ቡድን፤ በተቋማት፤ በማሰልጠኛዎችና በአካዳሚዎች የሚሰሩ የስፖርት ስልጠናዎች በበቂ የባለሙያዎችቡድን መሰራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡

Read 2949 times