Saturday, 12 March 2016 11:42

ተስፋ ልደቱ

Written by  ፍፁም ንጉሴ
Rate this item
(8 votes)

በርካታ እጆች … ጠንካራ ፈርጣማ እጆች! አካላቸው የማን እንደሆኑ የማይታዩ እጆች --- አንስተው ወደ ትልቁ በርሜል ከተቱት፤ በጠጅ ወደ ተሞላው በርሜል … እየቀዘቀዘው … ሽታው አፍንጫውን እየሞላው፣ እየተንሳፈፈ በደስታ ወደ ቢጫው ትንሽዬ ባህር … እያየ … እየዘቀጠ ----- ጫማው ልብሱ …. አንገቱ ድረስ … ሳቅ … ንግግር ---- እየተደራረበ እንደ ጫጫታ ሆኖ …!
“ይውጣልህ”
“በብርሌ ልትጠግብ ስላልቻልክ …”
“ከነጫማና ልብስህ ጭምር …”
“አንተ ከንቱ!”
“ጠጃም!”
ድምፃቸው ----- ሳቃቸው እየራቀው፣ ጆሮዎቹ በጠጅ ሞልተው አላሰማ ሲሉት … በተከፈተ አፉ ጠጁ ሲሞላ … ነፍሱ … እየረካች … ወዲያው ግን ሽቅብ ሊያስመልስ ሲሞክር … ጠንካራ ሃይል ቁልቁል ደፍቆ ሲያስቀረው፣ ደስታው ወደ ጣር … እርካታው ወደ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ፣ በቢጫ ቀለም የተሞላ ዕይታው ወደ ብዥታ … ቀጥሎ ወደ ፅልመት ሲቀየር፣ ቃል ሊያወጣ ----- ሊጮህ ----- “በቃኝ” ለማለት ሲታገል ሲያቅተው …
እ ---- ሪሪሪሪሪ ------ የማለት ያህል እየጮኸ ነቃ፡፡
የናፈቀውን አየር ምጎ ውስጡ ከቀረው የጠጅ አምቡላ ጋር ወደ ውጭ ለቀቀው … በመንቃቱ ተረፈ፡፡
እንደለበሰው የተኛው አሮጌና ቆሻሻ ልብሱ በገላው ሙቀትና ትነት ታፍኗል፤ በመጠጥ ሽታ የታመቀችው ጠባብ ክፍል ደስ በማይለው የሰውነቱ ጠረን ታፍጋለች፡፡ … ከአፍታ በኋላ ግን በመንቃቱ ተፀፀተ … ያንን ሁሉ ጠጅ ማጣቱ አንገበገበው፡፡ “መሞቴ ላይቀር በቢጫው ባህር መሞት ይሻለኝ ነበር” አለ፡፡ ልቡ ሊፈነዳ ደርሷል፡፡
ከግዙፉ አሮጌ ቪላ ጀርባ ካለ ረዥም ሰርቪስ ቤቶች በአንዷ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የመኪና ድምፅ ሰማ፡፡ አባቱ ለምሳ መጥተው ቡናቸውን ጠጥተው ወደ መደብራቸው መመለሳቸው እንደሆነ አወቀ፡፡ ለዓይንም አይፈላለጉምና… ደስ አለው፡፡
እንደ ምንም ተነሳ ----- ስብርብር ብሏል፤ሁሉ ነገሩ መጠጥ መጠጥ ---- ጠጅ ጠጅ ይላል፡፡ ቢጨመቅ አንድ የጠጅ ማንቆርቆሪያ ሳይወጣው አይቀርም፡፡ ከመንጋቱ የብርሌ መለሎ አንገት ባይኑ መጣበት … የጠጅ ቤቱ ድባብ … አረበበበት … ጓጓ ተጣደፈ፡፡
ከፍራሹ ጎን ምግብ በሰሃን ተቀምጧል፡፡ በሩን ሳይዘጋው እንደተኛ አወቀ፡፡ እናቱ መጥተው ነበር፡፡ “አይታኛለች ማለት ነው፤ ደግነቱ ለኔ የምታፈሰው እንባ የላትም፤ገና ድሮ ጨርሳዋለች” አለ … በማጉተምተም፡፡ ከንፈሮቹ እርስ በርስ ይጠባበቃሉ፤ ማሩ ወይም ስኳሩ ይሆናል … ምግቡን አንስቶ አየው፤ ሲሸተው ተናነቀው፤ ሆዱ ባዶ ስለሆነ አስጠላው፤ ምግብ በባዶ ሆዱ አይበላም፡፡ አንድ ወይም ሁለት ብርሌ መጎንጨት አለበት፡፡
ጉዳዩ --- ሱሱ …. ልማዱ … ሃሳቡ …. ደስታው ሃዘኑ … ማግኘቱ ማጣቱ ---- ናፍቆቱ ጠላቱ … ወዳጁ ጠጁ ነው … ጠጁ ብቻ!
ድፍን 6 ዓመታት አልፈዋል፤እልም ብሎ ከዘቀጠበት፡፡ በነዚህ ዓመታት “ተስፋ ልደቱ” ከመባል ወደ ‹ጠጅ›---- ‹ብርሌው›----- ‹አንቡላ›----- ‹ከንቱ› ሌላም ወደ መባል፤ በረዥም ቁመቱ መለሎ፣ ሎጋ ዘንጣፋው … ከመባል የተፈጥሮን ህጋዊ ሂደት ለውጥ ደብል በመምታት ወደ መጉበጥና … ወደ መንገላጀጅ ------ ወደ መጃጃል … ተሸጋግሯል … ሰልካካ የሚባል … ፊቱ … ወደ አስጠሊ ሞላላነት … ቀይ ቀለሙ ወደ ነብራማነት ----- የገፁ ስጋዊ ሙላት ወደ አስፈሪ እብጠት---- የገፁ ፀዳል ወደ ግርጣትና ዳለቻነት ተለውጧል፡፡ አፍንጫው አንድ ወጥ እንዳልነበረ አሁን መሃል ላይ በተጋደሙበት ጠባሳዎች … የተቀጣጠለ መስሏል። ሳቁን የሚያስናፍቁ ጥርሶቹ፣ ስቆ በተነሳቸው ፎቶዎቹ ላይ ብቻ ቀርተዋል፡፡ ያሁኖቹ … ዝገዋል … ወይበዋል … ተሸራርፈዋል … እንደው ባጠቃላይ ከ8 ዓመት በፊት ያየው ዛሬ ቢያየው … ከቤት የተጣለ የታላቁ ታላቅ ወንድሙን ሊመስለው ይችል ይሆናል፡፡ ወይም በእግዜር አሰራር የቀና ሰይጣን አስመስሎ ሊሰራው ሞክሮ፣ ባልተሳካ ሁኔታ ሰርቶ ያልጨረሰው ሊመስለው ይችል ይሆናል፡፡ አንዱን ቀን አጥፎ ሁለት እያረገ ሲኖር የቆየ ይመስል፣ በ35 ዓመቱ የ70 ዓመት አዛውንት መስሏል፡፡
የተንጣለለውን የሃብታም ወላጆቹን ግቢ አቋርጦ ወጣ ----- ጠጅ ቤቱ እየራቀበት … በትኩስ ፍቅር ወዳሳበደችው ሴት እንደሚሄድ እየተዋከበ ገሰገሰ … ከመንገዱ ማዶ ክፍቱ ጠጅ ቤት ሲታየው መብረር ተመኘ፡፡ ግራና ቀኝ ሲያይ ሲያቋርጥ … በመኪኖች የጥሩምባ እሪታ እየታጀበ ነበር፡፡ ደንገጥም አላለ፤ ባለመኪኖቹ ተሳደቡ ተራገሙ … አልሰማም፡፡
አንድ ቀጭን ፍቅረኛው ነች የምትታየው … ጎንበስ ብሎ በተከፈተው በር ዘው ብሎ ገባ፡፡ በድፍርስ ዓይኖቹ የጠጅ ቤቱን ምስራቅና ምዕራብ፣ ሰሜንና  ደቡብ በቅፅበት ቃኘ፡፡ በኪሱ ስባሪ ሳንቲም የለውምና ጋባዦቹን ፈለገ --- የሉም፡፡ በጥፊ የተመታ ያህል ጭው እያለበት አግዳሚው ላይ ዘፍ ብሎ ወደቀበት … ራቅ ብሎ ሽማግሌዎች የተረት አይነት ወሬ ያወራሉ … “ያኔማ” እያሉ በወርቃማ ዘመናቸው ትዝታ ይደሰታሉ፤ የዛሬን ጠጅ እየጠጡ #አዬ ጠጅ ድሮ ቀረ” ይላሉ … ከፊት ለፊቱ ያለው ሰው ላይ ተስፋ ሊጥል ከጅሎ ነበር … ፈጣን ሎተሪ ይፍቃል ይጥላል፤ሌላ ይፍቃል … በንዴት ሳይጠጣ እየሰከረ ታየው፤ “ከንቱ” አለው፡፡
 ጠጅ ቀጂውን፤ “ቅዳልኝ”
“ሂሳብ?”
“በናትህ ተረጋጋ” ባይናገር ደስታው ነው፤ ካልጠጣ ምኑም አያገለግልም፡፡
“እ?” አለ ቀጂው የማንቆርቆሪያውን ቆልማማ አፍ ወደሚያምረው የብርሌዋ ከንፈርና አንገት አነጣጥሮ፡፡
“ቅዳ ይሰጥሃል”
“መቼ?”
“ዛሬ”
“አትቀልድ”
ሊጮህ ሊሳደብ … ነጥቆም ቀድቶ ሊጠጣ ፈለገ፤ በጣም ፈለገ፡፡ አቅም ግን አጣ፤ከፊቱ ወዳለው ሰው አተኮረ፤ ተያዩ-----ሰውየው በሎተሪ ቁማር ቅጥል ብሏል … በጠጁ ሊያበርድ ያንደቀድቀዋል … ማንቁርቱ ወደ ላይ ወደ ታች ስትል … ተስፋ በአፉ ግጥም ብሎ የሚሞላ ምራቁን ይውጣል … ሰውየው በጥያቄ ሲያፈጥበት በለስላሳ እጆቹ የጎፈረ ከርዳዳ ፀጉሩን ቆፈር ቆፈር፣ አንገቱን ወዲህ ሰበር ወዲያ ዘንበል አደረገ … አይኖቹን … ያስከጀለችውን ሸጋ ለማማለል እንደምትጥር ኮረዳ አስለመለመ … በእጆቹም ወደ ጠረጴዛው ጠቆም ለማድረግ ሞከረ።
“ደሞ እንደዚህ ተጀመረ?” አለ ሰውየው እየተደነቀ
“እንዴት አልከኝ?”
“በል አንድ ጠጣ”
“ብለህ ብለህ ምን አመጣህ?”
ተስፋ ከዚያ በኋላ ያለውን አልሰማውም፤ ቀጂውን ባይኑ ፈለገው፡፡
“ና … ቅዳልኝ”
“ነገርኩህ” አለ፤ ቆጣ ብሎ
“ጓደኛዬ ጋብዞኛል”
ቀጂው እየቀለደበት፤ “መጨረሻህ ልመና ሆነ” አለው፡፡ “ብትሞት ይሻልሃል” ሲል አከለበት ከምሩ።
“ለማኝ … ለማኝ” ጆሮው ላይ እየነጠረ … ጠጁን ቁልቁል ----- ዝናብ እንደጠማው አዲስ መሬት--- ጠጁ ሆዱ ውስጥ ሰርጎ ይጠፋል፡፡
“ለማኝ” አለ ለራሱ፤ የምላሱ ካቴና ወለቀ፤ ሰውነቱን እንደ መንዘር እያደረገው በቅፅበት ፈታ ይል ጀመር፤ ያይኖቹ ቆቦች እንደ ሻተር ወደ ላይ ተከፈቱ፤ ጋባዡን እንደ አምላክ አየው፤ በሚያባክነው ብር ግን አዘነ፡፡
“ይገርማል ለማኝ አለኝ ---- ወይኔ … ተስፋ …”
ተስፋ ልደቱ .. ተስፋና ዕድሉ ካለበት ጠጅ ቤት እጅግ የሰፋ ነበር፡፡ ዕድሉ አሁንም አለ፤ ተስፋ የለም እንጂ፡፡ በስርዓቱ አስተማሩት አባቱ አቶ ልደቱ ----- ጠንክረው ሰርተው የከበሩ ሰው ናቸው … የሱ ታናሽ ወንድምና እህት አውሮፓ ናቸው፡፡ አንቱ የተባሉም ሆነዋል … እሱ ግን አንተም በዝቶበት አለ ------ ከዓመታት በፊት … ማለትም 12ኛን ጨርሶ አልሻገር ሲላቸው መደብር እንዲውል አደረጉት ----- እያደር እንደፈለጉ አልሆን ሲላቸው ከ8 ዓመት በፊት ታክሲ ገዝተው ራስህን ቻል … ትዳር ያዝ ብለው ከአደራና ከምርቃት ጋር አስረከቡት ----  ሹፌር ሆነ፤ ከሀብታም ልጅነት ወደ ልጅ ሃብታምነት ተሸጋገረ ተባለ ---- አዲስ ህይወት፣ አዲስ ጓደኞች፣ አዳዲስ ልማዶች ----- ለውጦች አመጣ፣ ገቢውን ይቀንስ ጀመር፤ ለሚስቱም የውሸት ምክንያቶችን መስጠት ለመደ፤ እያመነች ሳታምንም እየቻለች … እሱ ግን ቀጠለ፤ ከምክንያት ወደ ቁጣ .. ወደ ምን አገባሽ ተሸጋገረ … አምሽቶ መግባት፣ አርፍዶ መውጣት ጀመረ …
 ሚስቱ ስታረግዝ እሱ እርግዝናው ያልታየ ሌላ ዓመት ወልዶ ያሳድግ ያዘ ---- ወደ ወላጆቹ ዘንድ ሄደች---- ተጠራ ተጠየቀ ተመከረ ---- ተወገዘ ተሰደበ … ትንሽ መለስ ካለ በኋላ .. ጭራሽ ባሰበት። ሁለት ሶስት ጊዜ ተመከረ ----- ማስጠንቀቂያም ተሰጠው፡፡ የድሮ ተስፋ እንደወጣ ሳይመለስ ቀረ፤ ታክሲውን ተነጠቀ … ቆይታም ሚስቱ ራሷን ነጠቀችው፤ ደረቱን ነፍቶ ከቤት የወጣው ተስፋ፣ አንገቱን ሰብሮ ተስፋውን ጥሎ ወደ ቤቱ ተመለሰ … ለሌላ ስራና ትምህርት ተጋበዘ፤ አልቻለም-----
የናቱን ሆድ እያባባ፣ የወንድምና የእህቱን ልብ እያሳዘነ በሚያገኘው ገንዘብ የበለጠ እየጠፋ እየጠፋ ሄደ ----- ሚስቱን አባቱ ወደ ውጭ ሃገር ሲልኳት ልጇን ተቀብለዋት ነበር፤ በአያቶቹ ቤት የሚያድገው ልጁ አምስት ዓመት ሞልቶታል----ለሱ የተሰጠውን ስም ለልጁ ሰጥተው “ተስፋ ልደት” ይሉታል፡፡ የወላጆቹም ልብ ከሱ ወደ ልጁ ቁልቁል በመውረድ፣ ልጁ ስሙን ብቻ ሳይሆን ልጅነቱን ጭምር እንደነጠቀው ይሰማዋል፡፡
ተስፋ ብርሌዋን አጋብቶ ተቁለጨለጨ… ወዲያው ኪሶቹን በፍጥነት እየበረበረ፣ “ይኸውልህ … ወንድ” እያለ  … ወደ ጋበዘው ሰው እየተሳበ እያፈጠጠ ቆይቶ፣ አንዲት የተጣጠፈች ወረቀት አውጥቶ አሳየው፡-
“ምንድን ነው?” አለው ኮስተር ብሎ
“ትወዳለህ አይደል እስኪ ይሄን ግዛኝ” የሚንቀጠቀጥ እጁን ዘርግቶ አቀበለው፤ሰውየው ተቀብሎ እየገረመው ----- መሳቅም እየቃጣው፤ “ሎተሪ?!”
“አዎ ሎተሪ … ባለ አምስት ብር”
በገዛ ስራው ሃፍረት እየቆነጠጠው፤ “ያባቴ ጓደኛ ብር ከምሰጥህ … ዕድልህን ብሞክርልህ ይሻለኛል ብለው ነው የገዙልኝ”
ወዲያውም ባዶውን ብርሌ ይዞ ጎኑ ሄዶ እየተቀመጠ፤ “ይገርምሃል … ዕድል እኔን ትወደኛለች፤ እኔ ነኝ ለዕድሌ ግድ የሌለኝ …” ተቁለጨለጨ …
“ስንት ልጠጣ?” በሰውየው ገፅ ላይ ሀዘኔታ ተነበበ-----በደንብ አየው፤ ተስፋ አቀረቀረ “ብችል በነጻ ብሰጥህ ደስ ይለኝ ነበር ግን አልቻልኩም፤ እንደምታየኝ ነኝ ሱሴ ዓይኖቼን ደረቅ አርጓቸዋል” የዛጉ ጥርሶቹን ብልጭ አደረገለት፡፡
“እሺ” ጠረጴዛውን ያለ ፋታ ደበደበው። ቀጂው ሲከታተላቸው ስለቆየ፣ “አሁን ያንተ ነገር ከማሳሰብም ያስፈራኝ ጀመር፤ ሎተሪ ሸጠህ ትጠጣለህ፤ ጥሩ ነው ትላለህ ወንድሜ” ብሎ ገዢውን አየው፣ “እንጃ … እሱ ያቃል”
“እሱማ አያቅም … እሺ ብትለው ሚስቱን ሸጧት ይጠጣባታል …”
“ስንት ልክፈልህ?” አለው ሰውየው፤የቀጂውን ንግግር ያልሰማ በመምሰል
“የፈለከውን”
“ጥሩ ጠጣ…”
ቀኑን አየውና፤ “ከነገ ወዲያ ነው የሚወጣው”
“ነው? አላየሁትም”
“ግን ቢወጣስ?”
“ዕድልህ ነው”
“ዕድልህን ገዝቼ ማለት ነው”
“መሆኑ ነው፤ ካሁን ቀደም ያለገንዘብ ብዙ ዕድሎቼን ሸጫለሁ ባክህ”
ደስታ በደስታ ሆኗል፤ ቀና ብሎ ነው የሚጠጣው … በሙሉ ዓይኑ ያያል .. ዘለግ አርጎ ይናገራል፤ በመጨረሻ እንደ ልማዱ እየተደገፈ እየወደቀ እየተነሳ ነበር ወጥቶ ወደ ማደሪያው የሄደው፡፡
ከቀናት በኋላ ተስፋ ከመሰሎቹ ጋር ቀስመው በማያባራ ንብነታቸው ጠጃቸውን መሬት በማይወርድ ወሬ እያወራረዱ፣ በስካር በጫጫታ፣ በልዩ ልዩ ጠረኖች ------ አዳራሹ የጠባብ ቤት ያህል ታፍኗል፡፡ አንድ ሰው “ተስፋ ጠጄ” … ዘለግ አድርጎ ደጋግሞ ተጣራ፤ “ምን ላድርግህ” የጠጁ ዛር ቆሞለታልና ጠሪ አላስፈለገውም፤ ወደ ደጅ ይዞት ሄደ ----- ወደ አንድ አቅጣጫ ጠቆመው፤ ጨለማ ውስጥ የቆመ ሰው ይታየዋል፤ ማንነቱን መለየት አልቻለም፤ ሰውየው በጣም የዘነጠ፣ እራሱን ላለማጋለጥ የሚሞክር ነው፡፡
“እረሳኸኝ?”
“እንጃ”
ሰውየው ቀጭን ፖስታ እጁ ላይ አስቀመጠለት፤ “ሎተሪው ወጥቶልኝ ነው /150 ሺህ ብር/ ይህቺን ያዛት ብዬ ነው፡፡” ጥሎት ሄደ፤ ተስፋ ምድርና ሰማዩ ዞረበት፤ ማመን አልቻለም፤ ምሽቱን የቻለውን ያህል አጥፍቶ ወደ ቤቱ እያመራ ነበር፤ ቤቱ ግን አልደረሰም፤ በቀረው ገንዘብ የቀረ እሱነቱን አፍርሶ ወድቆ ቀረ፡፡  

Read 3424 times