Saturday, 12 March 2016 11:49

በዱከምና በሰበታ 3 የሳሙና ፋብሪካዎች እየተገነቡ ነው

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(2 votes)

       ዩኒሊቨር ኢትዮጵያ፣ ረጲ-ዊልማርና ፒስ ሰክሰስ የተባሉ ሶስት የሳሙና አምራች ድርጀቶች በግንባታ ላይ ሲሆኑ ተጠናቀው ወደ ምርት ሲገቡ የአገሪቷን የሳሙና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፍኑ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በዓመት ከ35 ሺህ ቶን በላይ ሳሙና ከ692 ሚ. ብር በላይ በማውጣት ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባ ለአዲስ አድማስ የገለጹት የኢንስቲቲዩቱ የሳሙና፣ የቀለምና ተዛማጅ ውጤቶች ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ብርሃኑ፤ ፋብሪካዎቹ ግንባታቸው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምሩ የአገሪቱን የሳሙና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይሸፍናሉ ብለዋል፡፡  
በ13 ሚ. ዩሮ በዱከም የተገነባው ዩኒሊቨር ኢትዮጵያ፤ የደረቅ ሳሙና የሙከራ ምርቱን  የጀመረ ሲሆን በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ላይፍ ቦይ፣ ክኖር፣ ዶቭ፣ ቫዝሊንና ኦሞን ጨምሮ ዘጠኝ ብራንዶቹን ማምረት እንደሚጀምር ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡  መቀመጫውን በእንግሊዝ ለንደን ያደረገውና በመላው ዓለም ቅርንጫፎች ያሉት ዩኒሊቨር፣ በኢትዮጵያ 90ኛውን ፋብሪካ እንደከፈተ የገለጹት አቶ አንተነህ፤ በኢትዮጵያ ለ100 ሰራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ ከ500 በላይ የሚሆኑ አከፋፋዮችም በማከፋፈል ሂደቱ ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ የታዋቂው ቫይኪንግ ዘይት አምራች የሲንጋፖሩ ዊልማርና አገር በቀሉ ረጲ የሳሙና ፋብሪካ በመጣመር የመሰረቱት የረጲ- ዊልማር ፋብሪካም ባለፈው ሀምሌ ወር በሰበታ ዲማ በ7 ቢ. ብር ግንባታው መጀመሩንና የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ በአንድ አመት ተኩል ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡    
ምርቶቹን ከአገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ወደ ውጪ የመላክ ዕቅድ እንዳለው የተነገረለት ረጲ ዊልማር፤ ከሳሙና ሌላ ለፓልም ዘይት ግብአት የሆነውንና በብዛት በእስያ የሚገኘውን የፓልም ዛፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በመትክል የፓልም ዘይትን ለማምረት ማቀዱም ተገልጿል፡፡
 እስከ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የዘይት አምራች ባለመኖሩ መንግስት ዘይቱን ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ በማድረግ ላይ ነው ያሉት አቶ አንተነህ፤ድርጅቱ የምግብ ዘይቱን በአገር ውስጥ ማምረቱ የሚኖረው ጠቀሜታ አያጠያይቅም ብለዋል፡፡ ረጲ ዊልማር ከዘይቱ ተረፈ ምርት በከፊል ያለቀለት ሳሙናን /ሶፕ ኑድል/ የሚያመርት ሲሆን ይህም አገሪቱ በየዓመቱ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባውን ሶፕ ኑድል የሚያስቀር እንደሚሆን ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፋብሪካው ዱቄት ሳሙና፣ ፈሳሽ ሳሙና፣ የልብስ ሳሙና እና የገላ ሳሙናን ጨምሮ በርካታ የሳሙና አይነቶችን ያመርታል ተብሏል፡፡
የረጲ- ዊልማር ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም አቶ አንተነህ አክለው ገልፀዋል፡፡
በ45 ሚ. ብር የተገነባው “ፒስ ስክሰስ” የተባለው የህንድ ሳሙና አምራች ኩባንያ ደግሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት እንደሚገባ ታውቋል። ከዚህ ቀደም B-29 ሳሙናን ያመርት የነበረው ኩባንያው፤አብሮት ይሰራ ከነበረው ድርጅት ጋር አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ምርቱን አቁሞ እንደነበር ያወሱት አቶ አንተነህ፤አሁን እራሱን ችሎ ዱከም አካባቢ በገነባው ፋብሪካ ዱቄት ሳሙናን ጨምሮ ሌሎች የሳሙና አይነቶች ማምረት ይጀምራል ብለዋል፡፡ ፒስ ሰክሰስ ለ100 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩም ታውቋል፡፡   

Read 3062 times