Saturday, 12 March 2016 11:56

አይፎን ለመግዛት ልጁን የሸጠው ቻይናዊ 3 አመት ተፈረደበት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የአይፎን ሞባይል ቀፎ የሚገዛበት ገንዘብ ለማግኘት ሲል፣ ሴት ልጁን በተወለደች በ18ኛው ቀን በድረ-ገጽ አማካይነት ሽጧል በሚል ሰሞኑን በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው አ ዱኣን የተባለ ቻይናዊ፣ የ3 አመት እስር እንደተፈረደበት ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ነዋሪነቱ ፉጂያን በተባለቺው የቻይና ግዛት እንደሆነ የተነገረለት ግለሰቡ፣ ኪውኪው በተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ ልጁን ለመሸጥ ያወጣውን ማስታወቂያ የተመለከተ ግለሰብ ልጅቷን ለመግዛት 2ሺህ 500 ፓውንድ መክፈሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
አባትዬው ልጁን በመሸጥ ያገኘውን ገቢ አይፎንና ሞተር ብስክሌት ለመግዛት ሊያውለው አስቦ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ ልጅቷ የተረገዘቺው ያለ እቅድ እንደነበረና አባትዬውም ሆነ እናትዬው የ19 አመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች እንደሆኑ ዘገባው አስረድቷል፡፡
እናትዬው ዢያኦ ሚ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ገቢ ታገኝ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አባትዬው በበኩሉ አብዛኛውን ጊዜውን በኢንተርኔት ካፌዎች ተጎልቶ የሚያሳልፍ ስራ ፈት እንደነበረና ልጁን ለመሸጥ የወሰነውም ለማሳደጊያ የሚሆን በቂ ገንዘብ የለኝም በሚል ስጋት እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ልጁን የሸጠው ይሄው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው እናትዬው ለፖሊስ በሰጠቺው ጥቆማ መሰረት እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2518 times