Saturday, 12 March 2016 11:52

በዚካ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የዓለም የጤና ድርጅት በደቡብ አሜሪካ አገራት የተከሰተውና ነፍሰ ጡር ሴቶችን በማጥቃት የሚታወቀው የዚካ ቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና በመጪዎቹ ወራት በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ፡፡
ቫይረሱ ከትንኞች በተጨማሪ በወሲባዊ ግንኙነት እንደሚተላለፍ መረጋገጡን የጠቆሙት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን፣ ቫይረሱ የተሰራጨባቸው አገራት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንና ወቅቱ የዝናብ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ስርጭት ይስፋፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጠዋል፡፡
ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አገራት የሚገኙና ወደ አገራቱ የሚጓዙ ነፍሰጡር ሴቶች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ ቫይረሱን ለመዋጋት እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የአለማቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ተቋም በደቡብ አሜሪካና በካረቢያን አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ተጨማሪ የ2.3 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተነግሯል፡፡

Read 1857 times