Saturday, 12 March 2016 12:00

እውን... ጡት ማጥባት እርግዝናን ይከላከላል?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(71 votes)

ከብረት የተሰራ የእርግዝና መከላከያ
 ዶ/ር ኃ/ጊዮርጊስ አውላቸው       
ከላይ የምትመለከቱት ፎቶ ጥንት ሴቶች ተገደው በመደፈር እንዳያረግዙ የሚጠቀሙበት የእርግዝና መከላከያ ነበር፡፡የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያስረዱት ረዘም ካለው ጊዜ ጀምሮ እናቶች እርግዝናን ለመከላከል የተለያዩ መንገዶችን ይሞክሩ ነበር፡፡ ከእንስሳት የሚወገድ ቆሻሻን  (poop) ጨምሮ መርዛማ ነገሮችን እስከመጠጣት ሲትሪክ አሲድ ያላቸውን ፍራፍሬዎች በተለያየ መንገድ መጠቀም እንዲሁም ከእንጨት የሚሰሩ መከላከያዎችን በሰውነት ላይ በማድረግ እስከመጠቀም የደረሰ ያልተለመደ እና ሳይንሳዊ ያልሆነ የመከላከያ ዘዴን ይጠቀሙ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቻይናዎች  Lead  እና  Mercury  የተባሉ ኬሚካሎችን ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ይጠቀሙ እንደነበር መረጃው ያሳል፡፡ በግሪክ አገር አንድ የማህጸን ሐኪም ለአንዲት ሴት የነገራት የወሲብ ግንኙነት ከፈጸመች በሁዋላ ሰባት ጊዜ ወደሁዋላዋ እንድትዘልና ከዚያም የጋለ ብረት የቀዘቀዘበትን ሙቅ ውሀ እንድትጠጣ ነበር፡፡ በሀገራችንም በተለይም በገጠር እና በአን ዳንድ ህብረተሰብ መካከል በመፋቂያ መልክ በአፍ የሚያዙ የመሳሰሉትን የተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንደ እርግዝና መከላከያ ይጠቀሙ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚያም ውጭ የተለያዩ ኪኒኖችን ጠንካራ አቅም አላቸው በሚባሉ የለስላሳ መጠጦችና እንደወይን በመሳሰሉ መጠጦች በመውሰድ ብዙዎች ለህልፈት አንደተዳረጉ ምስክር አያሻም፡፡    
ልማዳዊ ድርጊቶቹ ምን ያህል ያልተፈለገ እርግዝናን ተከላክለዋል? ለሚለው መረጃ የሌለ ሲሆን እናቶች ግን ባልተፈለገ እርግዝና ምክንያት ምን ያህል ሲቸገሩ እንደኖሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡  
ባለንበት ዘመን ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶች በስራ ላይ ስለዋሉ ከላይ የተገለጹት አስከፊ ድርጊቶች ተለውጠው ዛሬ በዘመነ መንገድ መርጦና አማርጦ እንዲሁም በትዳር አጋሮች መካከል ተመካ ክረው ከውሳኔ ላይ የሚደርሱበት ክስተት ተፈጥሮአል፡፡ በዚህ እትም  (Assessment of the contraceptive needs and practice of women in the extended postpartum period in Addis Ababa ,Ethiopia) ሴቶች ከወለዱ በሁዋላ የእርግዝና መከላከያ አጠቃቀማቸውን በሚመለከት በአዲስ አበባ የተደረገ ጥናት ምን እንደሚመስል እናስነብባችሁዋለን፡፡ ጥናቱን ያደረጉት ዶ/ር ኃ/ጊዮርጊስ አውላቸውና ተባባሪ ፕ/ር ሺፈራው ነጋሽ ናቸው፡፡ እንግዳ ያደረግናቸው ዶ/ር ኃ/ጊዮርጊስ የጽንስና ማህጸን ሐኪም ሲሆኑ የሚሰሩትም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ ባጠቃላይም እናቶች ከወለዱ በሁዋላ ባለው የመጀመሪያው አመት ወቅት የእርግዝናን መከላከያ ከግምት ውስጥ ያስገባሉ ወይንስ? ለሚለው ዶ/ር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጥ/ ስለ ጥናቱ አጠቃላይ ሁኔታ ይግለጹልን
መ/ ጥናቱ የተደረገው በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለከተሞች ውስጥ ሲሆን በጥናቱ የተካተቱት 845/ ሴቶች ነበሩ፡፡ጥናቱ የተሰራው በ8/ጤናጣቢያዎች እናቶች ለተለያየ የህክምና አገልግሎት ሲመጡ በመጠባበቅ ነው። ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት እንዲመለስ የተፈለገው ጥያቄ ግለሰቦች ምን ያህል ልጅ መቼ መውለድ እንደሚፈልጉ  ነበር፡፡ ጥናቱ በቤተሰብ እቅድ፣ በስነተዋልዶ፣ በሴቶችና የህጻናት ጤና በተመለከተ ውጤታማ ነበር፡፡ እናቶች በማንኛውም ጤና ተቋም ከወለዱ በሁዋላ ባለው የመጀመሪያ አመት ምን ያህሉ የወሊድ መከላከያ ይጠቀማሉ? የሚለውን እና በዚህ አንድ አመት ውስጥ ምን ያህል የእርግዝና መፈጠር እድል ይኖራል ብለው ይረዳሉ? የሚለውን ከግምት ውስጥ ያስገባ ጥናት ነው። ብዙ ሰዎች ልጅ በተወለደ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ደግመው መውለድ አይፈልጉም፡፡ በዚህ ጥናትም 4/በመቶ የሚሆኑ ብቻ ናቸው ካለምንም መከላከያ ልጅ ለመውለድ ፈቃደኛ ሆነው የተገኙት፡፡ በእርግጥ በህክምናው ዘርፍም የወሊድ ጊዜን ማራራቅ ከተለያዩ የጤና ሁኔታ እና ለሚወለዱትም ልጆች ተገቢውን ትኩረት ከመስጠት አንጻር የሚደገፍ ነው፡፡  
ጥ/ ጡት ማጥባት ያልተፈለገ እርግዝናን ይከላከላልን?
መ/ ጡት ማጥባት እንደእርግዝና መከላከያ እንዲያገለግል ከተፈለገ ሶስት ነገሮች መሟላት አለባቸው።
አንዲት እናት ጡት ማጥባትን እንደእርግዝና መከላከያ ልትቆጥረው የሚገባት ለመጀመሪያው ስድስት ወር ብቻ ነው፡፡
ጡት ማጥባት እርግዝና መከላከል የሚችለው ሕጻኑ ጡት ብቻ የሚጠባ ከሆነ ነው፡፡
ጡት እያጠባች ያለች እናት የወር አበባዋን ካየች አሁንም ማጥባቱ የእርግዝና መከላከያ ሊሆናት አይችልም፡፡ ምናልባትም የወር አበባው ከመምጣቱ 15/ቀን በፊት እንቁላል አመንጭታ የነበረ መሆኑን እና ይህ ደግሞ ለእርግዝና ዝግጁ መሆንዋን የሚያሳይ ነው፡፡ የወር አበባ ከመጣ የወለደችበት ጊዜ ስድስት ወር ባይሞላውም እንኩዋን ሌላ ተጨማሪ የእርግዝና መከላከያ ልትወስድ ይገባል፡፡
45/ከመቶ የሚሆኑት እናቶች ጡት ማጥባት እርግዝናን ይከላከላል የሚል ግንዛቤ ቢኖራቸውም ከእነርሱ ግማሽ ያህሉ ግን ምን ሲሟላ የሚለውን አያውቁም፡፡ ስለዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ከሶስቱ አንዱ ቢጉዋደል ጡት ማጥባት ብቻ እርግዝናን ሊከላከል አይችልም፡፡
ጥ/ የጥናቱ ግኝት ምን ይመስላል?
መ/ በዚህ ጥናት ያገኘነው የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በጥናቱ የተካተቱት ከ800/በላይ የሆኑ እናቶች ሲሆኑ በአብዛኛው በወለዱ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መልሰው ልጅ መውለድ አይፈልጉም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ባለትዳሮች እና ከጉዋደኛ ጋር የሚኖሩም አጋጥመውናል፡፡ በዚህ ጥናት ከተገኙት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል አገልግሎቱን ለመጠቀም እየፈለጉ ግን መከላከያውን ያልተጠቀሙ 11/በመቶ የሚሆኑ እናቶች እንዳሉ በጥናቱ ተረጋግጦአል፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች አገልግሎቱ እንዲደርስ ማድረግ ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ በጥናቱ ደርሰ ናል፡፡ የእርግዝና መከላከያውን ያለመጠቀማቸው ምክንያት ሲታይ፡-
በቂ የምክር አገልግሎት አለማግኘት
ድህረወሊድ ክትትል አለማድረግ
ከባህል ወይም ልማድ ጋር በተያያዘ ...ሊሆን ይችላል።
ሌላው ደግሞ የልጅ ፍላጎን አሟልቻለሁ ብሎ መዘናጋት ወደ 5/በመቶ የሚሆኑት እናቶች ጋ ታይቶአል፡፡ እነዚህ እናቶች ግን ፍላጎት እንጂ ያሰቡትን ለማድረግ ምንም የወሰዱት እርምጃ የለም፡፡ መከላከያውን አይጠቀሙም። ከነዚህ ሰዎች መካከል መከላከያ ባለመውሰዳቸው እርግዝና ሊከሰት እንደሚችል የሚያውቁም የማያውቁም ይገኙበታል፡፡ ለእነዚህም ሰዎች በምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ሲሆኑ አበክረን ማስገንዘብ የምንፈልገው ግን በጤና ተቋማቱ የሚሰጡት የምክር አገልግሎቶች ጠቀስ እያደረጉ ከማለፍ ያለፈ ጠንከር ያለና ግንዛቤን የሚያዳብር አለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በጤና ተቋማቱ ውስጥ ለእናቶቹ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች በደንብ ተዘጋጅተው በድህረ ወሊድ ክትትል ወቅት ምን ያህል በመመሪያው መሰረት የምክር አገልግት ተሰጥቶአል ወይንስ ምን ያህሉ ለድህረወሊድ ክትትል አይመጡም የሚለውንም እንዲታሰብ የሚያደርግ አጋጣሚ ነው በጥናቱ የተገኘው ውጤት ፡፡
ጥ/ ምን ያህል እናቶች ከአንድ አመት በፊት በድጋሚ መውለድ አይፈልጉም?
መ/ ይህ በተለያዩ ሀገራት በተደረገው ጥናት የታየ ተመሳሳይ ውጤት ያለው ነገር ነው፡፡ 95/በመቶ የሚሆኑ እናቶች ከአንድ አመት በፊት በጭራሽ ደግመው መውለድ አይፈልጉም፡፡ በእርግጥም ልጅ ከተወለደ ከ12/ወራት በፊት የሚደረግ እርግዝና ለተለያየ የጤና ችግር እናቶቹን ሊያጋልጥ እንደሚችልም በህክምናው የተረጋገጠ ነው፡፡
ጥ/ የትዳር አጋሮች ምክክር ምን ውጤት ያስገኛል?
መ/ በተገኘው መረጃ መሰረት ባለቤቶቻቸውን ወንዶቹን ያማከሩ እናቶች ወደ ሶስት እጥፍ የተሸለ መከላከያ እንደሚወስዱ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ አሁንም ቢሆን በአብዛኛው ወንዶች የቤተሰቡን አኑዋኑዋር በሚመለከት ብዙ ቦታ በቤተሰባቸው ኃላፊነት የተሰጣቸው በመሆኑ ይህንን በሚመለከትም በሚሰሩ ስራዎች እነርሱን ማካተት ግድ ይሆናል፡፡  
የአገር አቀፍ መረጃው እንደሚጠቁመው ለረጅም ጊዜ መከላከያነት የሚያገለግሉ እንደ ሉፕ/በክንድ ላይ የሚቀበር የመሳሰሉ መከላከያዎች ቢኖሩም የሚጠቀሙት ግን ውስን ሴቶች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች 41.9/ከመቶ የሚጠቀሙት በየሶስት ወሩ የሚወሰድ መርፌ ነው፡፡ ከዛም በመቀጠል በየቀኑ የሚወሰዱ ኪኒኖችን የሚጠቀሙም ከ16/ከመቶ በላይ የሚሆኑ እናቶች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ከወለዱ በሁዋላ በምን መንገድ የሚቀጥለውን እርግዝና እንደ ሚያዘገዩ የማያውቁ ብዙ እናቶች በመሆናቸው በአጠቃላይ ከሕክምና ባለሙያዎች ተገቢው ምክር ለህብረተሰቡ እንዲሰጥ ያስፈልጋል፡፡

Read 102475 times