Saturday, 19 March 2016 11:07

መንግስት፤ ምሁራንን ታስፈልጉኛላችሁ ያለበት መድረክ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

· ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላቦራቶሪ ሳይኖራቸው ስታዲየምና አዳራሽ ይገነባሉ
· በአገራችን ውስጥ የሰረቀ ነጋዴ ሁሉ እንሰር ቢባል አንድ ሰው አይተርፍም
· ጠ/ሚኒስትሩ፤የምሁራን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመሰረት ሃሳብ አቀረቡ
    የኢትዮጵያን ሕዳሴ በማፋጠን ዙሪያ ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከምሁራን ጋር የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም በርካታ ነጥቦች ተነስተው ተነጋግረውባቸዋል፡፡ ከተነሱት ነጥቦች መካከል የትምህርት ጥራት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንደርደርያ ሀሳብ ሲያቀርቡ፤ “አሁን ያለው የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው፤ የማስፋፋትና የተደራሽነት ሥራ ላይ ብቻ ማቆም ሳይሆን ዋናው ትኩረት ጥራት ላይ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ማነቆ የሆነው የሰው ኃይል ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ስናስብ፣ ከመምህራን ጥራት ውጭ ሊታሰብ አይችልም። የትምህርት ጥራት ዋናው አስኳል የመምህራን ጥራት ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ይህ እንዴት ይመጣል? ለሚለው፣ ብዙ ሐሳብ ሊኖራችሁ ስለሚችል ከእናንተ ጋር መወያየት ይበጃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥራት ሲጀመር ከአናት ሳይሆን ከሥር ነው፡፡ ስለዚህ ጥራት ያለው መምህር ሊያፈራና ሊመግብ የሚችል ሥርዓት እንዴት ነው መፍጠር የሚቻለው? መመለስ ያለበት ትልቅ ጉዳይና ልታግዙን ይገባል ብዬ የማምነው ነው፡፡ የአሁን ጊዜ መምህራን፣ ክፍል የማይገቡ፣ የራሳቸውን ሥራ የሚያሳድዱ፣ አንዳንድ ጊዜ ገጾቹ የተሳሳቱ የቆየ ኖት (ማስታወሻ) የሚያቀርቡ፣ ናቸው፡፡ የድሮ መምህራን ትላልቆቹ ጭምር ክፍል ገብተው ለማስተማር ፍላጐትና ቁርጠኝነት ያላቸው (ኮሚትድ) ናቸው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ያስተዳድሩ ሲባል የተሟላ ላቦራቶሪ ሳይኖራቸው ስታዲየምና 5ሺ ሕዝብ የሚይዝ አዳራሽ ግንባታ ምን ይባላል? መንግሥት ከአገሪቷ ዓመታዊ በጀት 25 በመቶ ወይም ሩቡን የሚመድበው ለትምህርት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛው የሚሄደው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው፡፡ አፈጻጸሙ ሲታይ ብክነቱ አፍንጫ የሚያስይዝ ነው፤ በጣም ብዙ ብክነት አለ፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ምንድነው ተብሎ ሳይታይ በጀቱ የሚውለው ሕንፃ መጠፍጠፍና ግንባታ ላይ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት እናምጣ ከተባለ ስታ
ዲየምና አዳራሽ መገንባት ወይስ ላቦራቶሪዎች ናቸው ጥራት የሚያመጡት?
እኔ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ መምህራን፣ ግቢ ውስጥ ምን እንዳለ የማያውቁ፣ ዝም ብለው ገብተው የሚወጡ፣ራሳቸውን የትምህርት ሂደቱ አካል ያላደረጉ፣ ውጭ የቆሙ ባይተዋር ሰዎች ነው የሚመስሉኝ፡፡ ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ወጪ ያለ አግባብ ሲከሰከስ እንዴት ዝም ተባለ? በማለት ጠይቀዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ያነሱት ሌላው ጉዳይ ዜጐች መብታቸው ሳይሸራረፍ የሚከበርበት፣እነሱም የሚያከብሩት፤መንግሥትና ሌሎች የፖለቲካ አካላትም የሚያከብሩት  ሥርዓት መኖር ነው፡፡ የዴሞክራቲክ ኅብረተሰብና የዴሞክራቲክ ባህል መገንባት ለእኛ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ዴሞክራቲክ ሥርዓት የሚገነባ ባህል በአገራችን መዳበር አለበት፡፡
እዚህ ላይ ብዙ ጉድለቶች አሉበት፡፡ በጉድለቶቹ ላይ ሕዝቡ የሚያነጣጥረው መንግሥት ላይ ብቻ ነው፡፡ እንዴ! እኔ ጉድለቶቹ የኅብረተሰቡም ጭምር ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሥት የመሪነት ሚና መጫወቱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ጉድለቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ እዚህ አካባቢ ኅብረተሰባዊ ለውጦችን ማምጣት ይጠይቃል፡፡ በዚህ አኳያ ዴሞክራቲክ ባህል እንዴት ነው የምንገነባው? በመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው ቦታዎች ጭምር የዴሞክራሲያዊነት አስተሳሰብ ባህል የሚጐለብትበት ሁኔታ ቀርቦ፣ አንድ አገራዊ መግባባት የሚፈጠርበት ጉዳይ ተደርጐ መወሰድ አለበት፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ስር የሰደደ አገራዊ መግባባት አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ የተጀመሩና ጥሩ መሻሻል ያሳዩ ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል አገራዊ መግባባት ተፈጥሮ የዲሞክራሲ ባህል በአገራችን እንዲገነባ፣ እንዲጐለብት የማድረግ ጉዳይ በአንክሮ መታየት አለበት፡፡ ፓርቲዎች ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በውስጣቸው ዴሞክራሲ ከሌለ፣ ውጭ ወጥቶ ዴሞክራሲ እሠራለሁ ማለት ውሸት ነው፤ስለዚህ ፓርቲዎችና የኅብረተሰብ ቡድኖች ጭምር ዴሞክራቲክ የሚሆኑበትን ባህል ማመቻቸት ይጠይቀናል፡፡ አገራችን ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ባህልና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ወሳኝ ነው፡፡ የተጀመሩና ጥሩ ውጤት ያሳዩ ነገሮች አሉ፡፡ ሆኖም ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መሄድ የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት (ናሽናል ኮንሰንስስ) መኖር አለበት፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሲባል በሁሉም ነገር መስማማት ማለት አይደለም፤ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሳይኖረን ልንሄድ የምንችልበት አገራዊ መግባባት እንዴት ነው የምንፈጥረው በሚል መወያየት ይገባናል፡፡
እዚህ ላይ ምሁራን ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምሁራን፣ ከመሸሽና እኛ ፓርቲ የመሠረትነውን ከመተቸት ባለፈ፣ራሳቸውም በሆነ ሐሳብ የሚስማሙ አካላት የምሁራን ፓርቲ ቢመሠርቱ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም እዚህ አገር ውስጥ በአንድ ትውልድ የተጣመመ ተሳትፎ ነበር፡፡ ያ የተጣመመ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደቀጠለ ነው ያለው፡፡ አሁን  የፖለቲካ ድርጅት የመሰረቱ ሰዎች፣ አብዛኛው በአንድ ወቅት የግራ ፖለቲካ አራማጅ ነበሩ፡፡ የያኔው ቁርሾ መቀጠል አለበት ወይ? ለአዲሱ ትውልድ ምንድነው የምናስተላልፈው? አዲሱን ትውልድ እንዴት ነው የዚያ ቁርሾ ተሸካሚ የማናደርግበት ስልት የምንቀይሰው? እንዴት ነው በራሳቸው አስተሳሰብ የሚቀጥል ትውልድ የምንፈጥረው? እንዴት ነው ዴሞክራሲያዊ ባህል እየጐለበተ የሚሄድበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚቻለው ---- የሚል ጥያቄ አንስተን መወያየት ያለብን ይመስለኛል። ስለዚህ በእኛ እቅድ ውስጥ ምሁራን የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው የሚል አመለካከት ይዘናል፡፡
የሙያ ማኅበራት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ማኅበራት ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ዙሪያ የራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ፅንፈኝነትን አቁመው መቻቻል የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም ጥግ ጥግ ይዞ የሚታኮስ ሳይሆን ተቀራርቦ የሚወያይበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ የመንደርደርያ ሐሳብ እንዳበቃ፣ ምሁራኑ አስተያየት ሰጥተዋል፤ ጥያቄዎችም አቅርበዋል። ሁሉም ተሳታፊዎች ማለት ይቻላል የተመረጠው ርዕስ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥርና ኮርኳሪ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ፕሮግራም አዘጋጅተው በአገር ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ በመጋበዛቸው አመስግነዋል፡፡
ርዕሱ የተመረጠው የኢትዮጵያን ሕዳሴ ለማንቀሳቀስና ለማቀጣጠል ታስቦ ነው ያሉት አንድ ምሁር፤ ይህ መነሳሳት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሊቸልሱ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ ብለዋል፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ነገር ይዘን ተነስተን በሌላ በኩል ደግሞ ልዩነት የሚፈጥሩ፣ የተለያዩ አመለካከቶች የማያስተናገዱ እንዲያውም የሚያሸማቅቁ አሠራሮች ይመጡና ይህን አገራዊና አንድነታዊ መነሳሳት ቀዝቃዛ ውሃ ሲቸልሱበት ይታያል፡፡ የኢሕአዴግን ሐሳብ የማይቀበሉ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ የምትለማው ወይም የምታድገው በዚህ በተያዘው አቅጣጫ ሳይሆን በተለየ መንገድ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን በማስተናገድ በኩል ብዙ መሰናክሎች ነው የሚታዩት፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል ይላሉ፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ የፖለቲካ ምህዳር ብቻ አይደለም የጠበበው፡፡ የጋዜጠኝነት ምህዳርም ይጠባል፣ የበጐ አድራጐት ሥራ ምህዳርም ይጠባል፣ የነጋዴነት ሥራም ይጠባል..፡፡ ስለዚህ አመቺ ያልሆነ ሁኔታ (ሳፎኬትድ አትሞስፊየር) አለ፡፡
ለዚህ ደግሞ አንዳንድ አስፈሪ ሕጐች አሉ፡፡ የፀረ ሽብር ሕግ፣ የፀረ - ሙስና ሕግ፣ የግብር ሕግ፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ሕግ አሉ። ሕጐቹ መኖራቸው ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን ሕጐቹን ለታለመላቸው ዓላማም እየተጠቀምን ነው ወይ? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ጋዜጠኞች ወይም ፖለቲከኞች በፀረ - ሽብር ሕግ ጠልፈው ይጥሉኛል ብለው ይፈራሉ፤ ነፃነት ያጣሉ፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ወይም ሠራተኞች በፀረ - ሙስና ሕግ ሸብበው ይጥሉናል ብለው ይፈራሉ፤ነፃነት ያጣሉ፡፡ ለአገር ዕድገትና ልማት የሚሠሩ ነጋዴዎችና ኢንቬስተሮችም፣ በግብር ሕግ አንድ ነገር አምጥተው ከርቸሌ ይጥሉኛል ብለው ይሰጋሉ። በበጐ አድራጐ የተሰማሩትም በዚያ ሕግ ምክንያት ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ አየሩ ሳፎኬትድ (የተጨናነቀ) ነው፡፡ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልስ ነው፡፡ ስጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡ በእነዚህ ሕጐች የተከሰሱ ሰዎች፤ ፍ/ቤት ከአራትና አምስት ዓመት ክርክር በኋላ ነፃ ሲለቃቸው ነው የምናየው፡፡ ስለዚህ ሕጐቹን ለመበቀያ መሳሪያ እየተጠቀምንባቸው እንዳልሆነ የእርስዎ መ/ቤት ይከታተላል ወይ?
ከፓርቲ ትግል ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ ላይ አተኩራለሁ፡፡ መስከረም አካባቢ ኢሕአዴግ ግምገማ ሲያካሂድ፤ “ከፍተኛ ችግር ነበረብን፣ ችግራችንም በበታች አመራር ላይ ሳይሆን በከፍተኛ አመራር ላይ ነው፤ ስለዚህ እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን” ተባለ። እርስዎ ጥቅምት ላይ ለካቢኔ ሹመኞችን ሲያቀርቡ ግን ያው የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን ነው ያየነው። የሚኒስትርነት ቦታ ላይ ያላስቀመጧቸውን ሰዎችም “አማካሪ” ብለው ወደራስዎ ወሰዷቸው፤ ስለዚህ ለውጥ የለም፡፡ አሁን በመጋቢትም ለውጥ አልታየም፤ እንዳለ ነው ያለው፡፡ ለውጥ አለ ቢባል ታች ወርዶ ነው ቅርንጫፍ እየተጨፈጨፈ ያለው፤ ችግር አለ ብለውን የተቀበልነው የበላይ አመራር ላይ ነው፡፡ እነሱ ላይ እርምጃ ሲወሰድ ግን አናይም ብለዋል፤ምሁሩ በሰጡት አስተያየት፡፡
ከጐንደር የመጡ አንድ ምሁር፤ጫት የወጣቱን አዕምሮ እያደነዘዘ፤ የከተሞችን ውበት እያቆሸሸ መሆኑን ጠቅሶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጫት ላይ ያላቸውን አቋም ጠይቋል፡፡ እሳቸውም   ሲመልሱ፤እኔ ስለ ጫት የመደገፍም የመቃወምም አቋም የለኝም፡፡ ጫት ይጠቅማል አይጠቅምም የሚሉ ወገኖች፣ ምርምር አድርገው ይጠቅማል አይጠቅምም ብለው ተከራክረው ያሳምኑን፡፡ ያኔ በማስረጃ ጐጂ ነው ከተባለ እናስቆማለን። እስከዚያው ድረስ ግን የሚያስገኘውን ዶላር እየበላን እንቆያለን በማለት መልሰዋል፡፡ መጀመሪያ ለተነሳው ጥያቄም የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል፡፡
“መርካቶ ላይ ቦንብ ሊፈነዳ ነው፤ ቦንቡን የሚያፈነዳው እገሌ ነው፡፡ ከዚህ ቦንብ አፈንጂ ጋር እገሌ የተባለ ጋዜጠኛ አለ የሚል መረጃ ሰምቼ እንዴት ነው ዝም የምለው? እኔ የማስበው ያንን ጋዜጠኛ ሳይሆን መርካቶ ላይ የሚያልቀውን ሕዝቤን ነው፡፡ ስለዚህ በማንኛውም መንገድ ድርጊቱ እንዳይፈፀም ማስቆም አለብኝ፡፡ ሽብርተኛ በአካባቢያችን እየተተራመሰ እናንተ በሰላም የምትገቡትና የምትወጡት ለምንድነው? ኬንያ ናይሮቢ ያለ ምሁር መቼ እሞት ይሆን ብሎ ሲጨነቅ፤ እናንተ እዚህ ደረታችሁን ነፍታችሁ የምትዘዋወሩበት ምክንያት ምንድነው? ይህንን ኃላፊነት የማይወጣ መንግሥት ካለ ደግሞ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ዜጐቹን ከጥቃት የማይከላከል መንግሥት መንግሥት አይደለም። ይህን ማድረግ ካልቻልኩ የአገራችሁ ጠቅላይ ማኒስትር ሆኜ እዚህ መቀመጤ ምን ትርጉም አለው? ሕዝቤ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎብኛል፡፡ አርባምንጭ ብሆን ኖሮ ይህ ኃላፊነት የለብኝም፤ እንደፈለኩ ተናግሬ ወጥቼ እገባለሁ፡፡”
በቂ ማስረጃ ባለማቅረባችን ፍ/ቤት ለቆ ከሆነ ደስ ይለኛል፣ ምክንያቱም የመንግሥትን ክስ ፍ/ቤት ነፃ ለቋል ማለት ትልቅ እርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ፍ/ቤት ነፃ ነው፤ የመንግሥት ተፅዕኖ የለበትም ማለት ነው፡፡ ነገሩ መደረጉን እያወኩ፣ ማስረጃ ባለማቅረቤ ፍ/ቤት ለቆብኝ ከሆነ ለወደፊቱ ማስረጃ ሳይኖረኝ አልከስም፤ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
የጋዜጠኝነት ምህዳር ጠቧልና እፈራለሁ፤ የነጋዴነት ምህዳር ጠቧልና እፈራለሁ ማለት ልክ አይደለም፡፡ እውነት እንናገር ከተባለ በአገራችን ውስጥ የሰረቀ ነጋዴ ሁሉ እንሰር ቢባል አንድ ሰው አይተርፍም፡፡ ቢያንስ ደረሰኝ ሳይቆርጥ የሚሸጥ ሰው መዓት ነው፡፡ እኛ’ኮ የምናስረው ጫፍ ላይ ያለውን በጣም ጥቂት ሰው ነው። ሕግ ይከበር ተብሎ ይታሰር ከተባለ ማን ይተርፋል? አንድ ነገር ልንገራችሁ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነጋዴ እቤቱ ውስጥ እስር ቤት አለው ብትባሉ ታምናላችሁ? ከሠራተኞቹ መካከል እሱን ለማጋለጥ ትንሽ የሚንቀሳቀስ ካለ ወስዶ የሚያስርበት? እኛ የምናስረው የዚህ ዓይነቶችን ነው፡፡ አንድ ምሁር ያነሱት ጥያቄ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አመራር አመዳደብን የተመለከተ ነው፡፡ የእነዚህ አመራሮች አመዳደብ መንግሥት ታሳቢ አድርጐ እየሠራበት ያለው ዩኒቨርሲቲዎች ደሴቶች አይደሉም፤ የአካባቢውንና የማኅበረሰቡን ቋንቋና ባህል የሚያውቅ ሰው ቢቀመጥ ጥሩ ነው ከሚል እሳቤ እንደሆነ ይገባኛል፡፡
ነገር ግን በእነዚህ እሳቤዎች እየተፈፀመ ነው ወይ? የፌዴራል ተቋማት የምንላቸው ዛሬ ከክልልም አልፈው የቀበሌ አልሆኑም ወይ? ጠባብነት፣ ጐሰኝነት በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ አይንፀባረቁም ወይ? መንግሥት ይህን እስከመቼ ነው ዝም ብሎ የሚያየው። ክቡር የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ጉዳዩ እንደሚስተካከል ቃል ገብተውልን ነበር፤ መች ነው የሚስተካከለው? እኛ የየትኛውም ብሔረሰብ አባል የአመራር ብቃት ካለው በቦታው እንዳይቀመጥ አይደለም ጥያቄያችን። ለምንድነው ደቡብ ያለው ሰሜን ላይ የማይሠራው? በአማራ ክልል እንኳ ያለን ጐጃሜ፣ ጐንደሬ፣ ሰሜን ወሎ እየተባለ እየተከፋፈለ ነው፡፡ እኛ ብቁና ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎች ማፍራት ሲገባን፣ራሳችን ተመልሰን በጥበት ታጥረናል፡፡ ይህን ነገር መንግሥት በአግባቡ ሊያየው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሌላው ደግሞ መምህራንን የማቆየት ጉዳይ ነው። ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ከሌላው የተሻለ የደሞዝ እርከን እንዲያገኙ ተደርጓል ይባላል፡፡ ነገር ግን ከሕንድ የሚመጡ መምህራንን ደሞዝ አንድ አራተኛ ወይም አንድ አምስተኛ ነው የሚያገኙት፡፡
የሕንድ መምህራን አቀጣጠር ምንድነው የሚመስለው? ምንም ችሎታ፣ እውቀት፣ የትምህርት ማስረጃ የሌላቸውን እየቀጠርን አይደለም ወይ? (በዚህ ጉዳይ ላይ እርስዎ አይደሉም ተጠያቂው፤ሊቀጥሩ የሚሄዱ የዩኒቨርሲቲ አካላት እንደሆኑ ይገባኛል) ተቀጥረው መጥተው በሌላቸው ፕሮፌሽን አገራችን ውስጥ እያስተማሩ አይደለም ወይ? ለዚያውም 40 እና 45 ሺህ ብር እየበሉን፡፡ የእኛ ፕሮፌሰሮች ስንት ነው የሚከፈላቸው? የኢትዮጵያውያኑና የሕንዶቹ ደሞዝ ቢያንስ ሊቀራረብ ይገባል፡፡ ይኼ የሕንድ መምህራን ቅጥር ወይ መቆም አለበት ወይ ለልጆቻችን ብቻ ማስተማር ሳይሆን ለእኛም የእውቀት ሽግግር ማድረግ አለባቸው፡፡
“ሌላው መስተካከል ያለበት ነገር አንድ ዜጋ ግብርና ታክስ መክፈል እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ነገር ግን የዚህች አገር ዜጋ የመንግሥት ሠራተኛ ብቻ ነው ወይ? 35 በመቶ ታክስ እንከፍላለን፣ ዕቃ ለመግዛት ወደ ውጭ ስንወጣ ደግሞ 15 በመቶ እንከፍላለን፡፡
በአጠቃላይ 50 በመቶ ማለት ነው፡፡ የአገራችን ነጋዴዎች ይህን ያህል ይከፍላሉ ወይ? እኔ በበኩሌ ጥያቄዬ የደሞዝ ጭማሪ አይደለም፣ገበያው ሊረጋጋ ይገባል፡፡ ሁለተኛ የምንከፍለው ክፍያ ከሌሎች ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡” ሲሉ ምሁሩ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡     

Read 4978 times