Saturday, 19 March 2016 11:10

‘ዳያስፖራው’ና ግራ የገባው በስልክ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
‘ግራ የገባው’ የአገር ልጅን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ አብሮ አደግ ‘ዳያስፖራ’ ስልክ ደውሎ አነጋግሮታል ወይም ሳያነጋግረው አይቀርም ‘ተብሎ ይታሰባል፡፡’
ዳያስፖራ፡— ሄይ ሜን…
ግራ የገባው፡— ሄሎ፣ ማን ልበል?
ዳያስፖራ፡— ዩ’ር ኪዲንግ ሚ! አላወቅኸኝም?
ግራ የገባው፡— ይቅርታ ጌታዬ አላወቅሁህም፡፡ (ዛሬ ደግሞ ምን አይነቱን ነው ያመጣብኝ፡፡ በግድ የሰው ድምጽ ማወቅ አለብኝ እንዴ! ወፌ የተገለበጥኩ ያህል የሚያንገበግበኝ የሚስቴ ድምጽ እንኳን እየጠፋኝ ነው…)
ዳያስፖራ፡— ኦ ዛት’ስ ኤ ትራጄዲ!
ግራ የገባው፡— (እሰይ! የአንተ ድምጽ አልታወቀምና ነው ትራጄዲው!  አገር ቤት ብቅ በልና የእኔን የኪራይ ኮንዶሚኒየም ስታይ ትራጄዲ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ፡፡) ማን ልበል ጌታዬ?
ዳያስፖራ፡— ጄኮብስ ነኝ፡፡
ግራ የገባው፡— ጄ…ጄኮብስ! (ፈረንጅ! ያውም አማርኛ የሚናገር! እኔ እንኳ ከፈረንጅ ጋር ልተዋወቅ ለምን እንደሆነ እንጃ አሁን፣ አሁን በአጠገቤ የሚያልፍ ቱሪስት ፈረንጅ ከስንት አንዴ ነው የሚገጥመኝ፡፡ ቻይኖቹ ‘ካልተቆጠሩ’ ማለት ነው!) ይቅርታ ምንም ሊመጣልኝ አልቻለም።
ዳያስፖራ፡— አይ ዶንት ቢሊቭ ዚስ! ኦኬ ያዕቆብ ነኝ…ዩ ኖው ያዕቆብ ከዲሲ…  አብሮ አደግ….
ግራ የገባው፡— (ታዲያ እንደ እሱ አትልም!) ያዕቆብ ይቅርታ፣ አ… አንተ መሆንህን አላወቅሁም። (ደግሞ በሌላ እንዳይተረጉምብኝ!) ይኸው እመ ብርሀንን…
ዳያስፖራ፡— ኢት’ስ ኦኬ!  ኢት’ስ ኦኬ!
ግራ የገባው፡— እንደምነህ ያዕቆብ!
ዳያስፖራ፡— ፋይን… አይ’ም ዶዪንግ ፋይን፡፡ እናንተ እንዴት ናችሁ?
ግራ የገባው፡— አለን…አለን አይደል የሚባለው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን አለን! (ይሄኔ ሚስቴ ብትሰማ አንተም አለሁ ትላለህ! ሱሪህ የሯጭ ቁምጣ ይመስል ላይህ ላይ ተሸብሽቦ አሁን አለሁ ትላለህ!” እያለች ትነዘንዘኝ ነበር፡፡)
ዳያስፖራ፡— አሁንም ያ ሴንስ ኦፍ ሂየመርህ አለ!
ግራ የገባው፡— (ወይ ሴንስ ኦፍ ሂዩመር!… ሴንስ ኦፍ ሂዩመር ምናምን የሚሉት ትርጉሙ እንኳን እንደጠፋኝ አላወቀ!) አዎ ዘና ማለቱ አይሻልም ብለህ ነው!
ዳያስፖራ፡— ሶ…አገር ቤት ችግር ነው ይላሉ፡፡ ኢት’ስ ሶ ታፍ ኦን ዩ ጋይስ፡፡ ሶሻል ሚዲያ ላይ እያየሁ ነው፡
ግራ የገባው፡— አዎ፣ ችግር ነው፡፡ እሱ ካመጣው እንግዲህ ምን እናደርጋለን፡ (ወይ ሶሻል ሚዲያ! የእኔን ፎቶ ብልክልህ ከአንድ ሺህ የሶሻል ሚዲያ ጽሁፍ በላይ ይገባህ ነበር፡፡)
ዳያስፖራ፡— ዩ ጋይስ ግን…ለምንድነው ብሌም ሺፍት የምታደርጉት!
ግራ የገባው፡— (ሰውየው ጋንጃዋን ምናምን እየሳበ ነው እንዴ!) እንዴት ማለት…
ዳያስፖራ፡— የችግሩ ሶርስ እናንተ ጋ ሊሆን ይችላል…ዩ ጋይስ…
ግራ የገባው፡— (ይቺን ይወዳል!) የምትለኝ አልገባኝም… (በርገርና የዶሮ ቅልጥሙን በሳንቲም እየገሸለጠ ጭራሽ እናንተ ናችሁ ይላል! እማዬን የድስት ጥራጊም ቢሆን ስጪኝ እያለ ሲያስቸግር የነበረ…) እንዴት ነው እኛ ሶርስ ልንሆን የምንችለው!
ዳያስፖራ፡— ኦኬ …ፎርጌት ኢት…ባይ ዘ ዌይ ደብዳቤህ ኢንተረስቲንግ ነው፡፡
ግራ የገባው፡— (ጎሽ አሁን ጨዋታ አመጣህ፡፡ “ወደ ገደለው ማለት ይሄ ነው” ብለው በድንጋጤ ስልኩን ወርውሮ ይሮጥ ነበር፡ ለነገሩ እኔም ራሴ መጀመሪያ ‘ወደ ገደለው’ ሲሉ የሆነ ወንጀል ሊያነካኩኝ ነው ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡)
ዳያስፖራ፡— ስማ… (የተቆራረጠ ሳቅ፣) ይሄ ጤፍ ሰፋ ባለ አሮጌ ድስት ምናምን ያልከው… (ከት ብሎ ይስቃል) ዩ አር ፈኒ ሜን! (በሳቅ…)…ምን ነበር የምትሉት…
ግራ የገባው፡— ልፈነዳ…
ዳያስፖራ፡— በሳቅ ልፈነዳ… (በሳቅ ይንፈቀፈቃል)
ግራ የገባው፡— (ኧረ ትን ብሎህ በዛው በቀረህ! ጭራሽ ዩ አር ፈኒ ይለኛል! ይፈንፍነውና!) ምን ታደርገዋለህ… ጤፉ ተወደደ፡፡
ዳያስፖራ፡— ሉክ እኔ ግራ የሚገባኝ…ዩ ጋይስ ለምን ሺፍት አታደርጉም!
ግራ የገባው፡— (ሰውዬው ዛሬ በሺፍት ተለክፏል እንዴ!) ሺፍት ስትል…
ዳያስፖራ፡— አይ ሚን ጤፉ ሲወደድ…ዳይቨርሲፋይ ሜን! ወደ ሌላ ዲሽ ዙሩ! ኢት ሳምቲንግ ኤልስ!
ግራ የገባው፡— እዚህ አገር የሚበላው ነገር ሁሉ ተወዷል፡፡
ዳያስፖራ፡— ካም ኦን! ዱ ዩር ማትስ…ካሰባችሁበት አይጠፋም፡፡
ግራ የገባው፡— (አንተ ምን ታደርግ…በእግሩ የሚሄደውም፣ በባህር የሚዋኘውም፣ በደረቱ የሚሳበውም ምንም ሳይቀር የሚበላበት አገር ሆነህ!) አልሰሜን ግባ በለው ይባላል፡፡
ዳያስፖራ፡— ኋት ወዝ ዛት?
ግራ የገባው፡— ምኑ?
ዳያስፖራ፡— አሁን…አል…አልሰሜ…ኋት ዲድ ዩ ጀስት ሴይ!
ግራ የገባው፡— አልሰሜን ግባ በለው፡፡
ዳያስፖራ፡— ምን ማለት ነው?
ግራ የገባው፡— ምን ብዬ ላስረዳህ… ለማያውቅ ሰው ሁሉም ነገር ቀላል ይመስለዋል፡፡
ዳያስፖራ፡— ኦ! ሶ ዛት’ስ ኢት! እኔ እኮ ነገርኩህ ሶሻል ሚዲያ አያለሁ፡፡
ግራ የገባው፡— (ሶሻል ሚዲያ የእኔን የቻይኖች ፓስታ ምናምን መብያ የሆነችውን እግር አሳይቶሀል! የሪፍት ቫሊ ቅጣይ የመሰለውን የሚስቴን ሆድ አሳይቶሀል! የባዮሎጂ መማሪያ ሊሆኑ ምንም ያልቀራቸውን ልጆቼን አሳይቶሀል!) ሶሻል ሜዲያው እኮ የጓዳችንን መች አወቀው…ግማሹም አሪፍ ፊክሺን ነው፡፡
ዳያስፖራ፡— ኦ ማይ ጋድ!…አሪፍ ነው ያልከው! ይቺን ቃል ከስንት ጊዜ በኋላ ሰማኋት! ሶ…ሶ…ሎንግ ኤጎ! ኤኒዌይ ዋጋ እንደፈለጉ ሲጭኑባችሁ ለምን ዝም ብላችሁ ታያላችሁ፡፡ ኋይ ዶን’ት ዩ አክት!
ግራ የገባው፡— (እንዴት ነው ነገሩ!) ታዲያ ምን እናድርግ?
ዳያስፖራ፡— ፋይት ሜን! ፋይት!
ግራ የገባው፡— ከማን ጋር…
ዳያስፖራ፡— ፕራይስ ዝም ብለው ከሚጨምሩባችሁ ጋር ነዋ!
ግራ የገባው፡— ጭራሽ መጋዘኑን ቆልፈው በረሀብ ይጨርሱን!  
ዳያስፖራ፡— ሉክ…ኮንሲዩመር ግሩፕስ አይነት የሏችሁም!
ግራ የገባው፡— ቢኖሩንስ…
ዳያስፖራ፡— በእነሱ በኩል የሚያስወድዱባችሁን ሰዎች ፕሮደክትስ ቦይኮት ታደርጋላችኋ!
ግራ የገባው፡— እንደዛ አይነት ነገር እኛ ዘንድ አይሠራም። (በሆዴ ላይ ቦይኮት! ትምህርት ቤት ሲረበሽም ክፍል ቦይኮት አድርጌ አላውቅም፡፡)
ዳያስፖራ፡— ኋይ ኖት?
ግራ የገባው፡— ልጆቻችንስ…አንተ ያልገባህ እኮ ዋጋ ሲጨምሩ አንድ ሁለቱ ሳይሆኑ ሁሉም ናቸው፡፡
ዳያስፖራ፡— ማይ ጋድ! ገቨርመንት ምንድነው የሚሠራው!
ግራ የገባው፡— (እሱን ራስህ ጠይቅ፡፡ ለምተነፍሰው እየተጠነቀቅሁ ጭራሽ በስልክ ሊያስጠልፈኝ ነው እንዴ!) እ…
ዳያስፖራ፡— ኤኒዌይ…ኢት’ስ ኤ ትራጄዲ፡፡ …ባይ ዘ ዌይ ሚስቴ በስልጣኗ እንደፈለገችው አምሽታ ትገባለች ያልከው…
ግራ የገባው፡— አዎ…ይኸውልህ¸... እዚህ ደረጃ ደርሰናል።
ዳያስፖራ፡— ኋት ኢዝ ሮንግ ዊዝ ዛት?
ግራ የገባው፡— ማለት…ምኑ?
ዳያስፖራ፡— አይ ሚን፣ ሚስትህ በራሷ ብታመሽ አይ ሲ ኖ ፕሮብሌም፡፡
ግራ የገባው፡— (አይ ምነው!  አሁን ገና ወጥ ረገጥክ።) ስማኝ ያዕቆብ፣ እያወራን ያለነው ስለ ኢትዮዽያ ነው….
ዳያስፖራ፡— የትም ቢሆን ኢት ዳዝንት ማተር! ኢፍ ሺ ዴትስ አናዘር ጋይ በቃ ትለያያለህ፡፡ ማሬጅ እኮ ኮንትራት እንጂ ፕሪዝን አይደለም።
ግራ የገባው፡— (ይቺን ይወዳል! አጅሬው እንዴት ነው እንዲህ የሆነው!) ያዕቆብ፣ አግብተሀል?
ዳያስፖራ፡— የስ ኤንድ ኖ...
ግራ የገባው፡— እ… አልገባኝም…
ዳያስፖራ፡— አሁን፣ አይ አም ዊዝ ሳም ቺክ…ሉክ ሁለት ጊዜ አግብቼ ፈትቻለሁ፡፡ ዛት’ስ ሀው ኢት ወርክስ! ዋን ጎዝ፣ አናዘር ዋን ካምስ!
ግራ የገባው፡— እሺ፣ ይሁን…. (ምን አጨቃጨቀኝ!)
ዳያስፖራ፡— ባይ ዘ ዌይ ለልጆችህም ነፃነት ስጣቸው…
ግራ የገባው፡— (እውነት! ማልኮም ኤክስ!) ያዕቆብ…ነጻነት የሚያስፈልገኝ እኔ ነኝ፡፡
ዳያስፖራ፡— ዩ ሪሊ አር ፈኒ! ስማ…ለልጆችህ ስማርትፎን ብትገዛላቸው ኋት ኢዝ ሮንግ!
ግራ የገባው፡— (ሳይቸግረኝ ደብዳቤ ጽፌ ሞራሌ ላይ የአሜሪካን ፉትቦል ይጫወትበት!) ያዕቆብ የአንድ ስማርት ፎን ዋጋ እኮ የቤተሰቤ የዓመት ቀለብ ነው!
ዳያስፖራ፡— አይ ኖው…ለምን ባንክ ሄደህ ክሬዲት ምናምን አይሰጡህም! አይ ሚን…
ግራ የገባው፡— ያዕቆብ ስለደወልክኝ…
ዳያስፖራ፡— ዌይት… ካርዴ ገና አላላቀም፡፡ ሉክ… እኔ ምን ላድርግልሀ…
ግራ የገባው፡— ምንም አልፈልግም፡፡
ዳያስፖራ፡— ባይ ዘ ዌይ (ይስቃል) ያቺ ሸሚዝ የመጥረጊያ እንጨት ያልካት…ኢት ወዝ ሶ ሂላረየስ ሜን! ትን እስኪለኝ ነው የሳቅሁት።
ግራ የገባው፡— (እዛው ትን ብሎህ ባስቀረህ ይሻል ነበር።)
ዳያስፖራ፡— ኤኒ ዌይ… አንድ ነገርማ ማድረግ አለብኝ…አር ዩ ዲፕሬስድ!
ግራ የገባው፡— ማለት…
ዳያስፖራ፡— አይ ሚን፣ ሜንታሊ…ደህና ነህ…
ግራ የገባው፡— (ጭርሱን ቀወስክ ሊለኝ ነው…) ደህና ነኝ፡፡
ዳያስፖራ፡— ሉክ አይ’ል ቴለ ዩ ኋት አይ’ል ዱ…አንደ በጣም ፖፑላር የዲፕሬሽን መጽሐፍ አለ፡ እሱን ገዝቼ እልክልሀለሁ…
ግራ የገባው፡— የዲፕሬሽን መፅሐፍ ማለት…
ዳያስፖራ፡— ማለት… ብሬክዳውን እንዳታደርግ… ዩ ኖው…
ግራ የገባው፡— (ኧረ የእናት አባቴ አምላክ ይሰባብርህ!)  ደህና ሁን!
ዳያስፖራ፡— ዌይት ምን መሰ….
ስልኩ ጥርቅም አለ፡፡
እናንተም ደህና ሰንብቱልኝማ!




Read 6657 times