Saturday, 19 March 2016 11:35

ለፈጣን አውቶብስ መንገድ ዲዛይን፣ የ64.6 ሚ. ብር ስምምነት ተፈረመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

የ85 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት ተገኝቷል
                                                 
       የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ ለሚያስገነባው የፈጣን አውቶቡስ መንገድ ምህንድስና ጥናቶች፣ ለመጀመሪያ ዲዛይንና ለዝርዝር ዲዛይኖች ስራ ከጥምር ድርጅቶች ጋር የ64.6 ሚ. ብር የኮንትራት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ፈቃደ ኃይሌ ባለፈው ረቡዕ ጥምር ድርጅቶቹን ከሚመራው የፈረንሳዩ “SAFEG SAS”፣ ከተባባሪው “ኢትዮጵያን ሀምዳ ኢንጂነሪንግ ኮንሰልት” እና ከብሪቲሽ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት ፕላኒንግ ሀላፊዎች ጋር በባለስልጣኑ መስሪያ ቤት አዳራሽ ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡
ስምምነቱ የዓለም አቀፍ የግዢ ደንብን መነሻ በማድረግ በተካሄደው የፍላጎት ማቅረቢያ ጨረታ ውጤት መሰረት መከናወኑ የተገለፀ ሲሆን በመጋቢት 2007 ዓ.ም 13 የኢንጂነሪንግ ኩባንያዎች ለዚህ ፕሮጀክት ፍላጎታቸውን አቅርበው ነበር ተብሏል፡፡
አጠቃላይ የስምምነቱ ዋጋ 64 ሚ. 690ሺ597 ብር ሲሆን በተለያዩ የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ስር የሚመለከታቸው ዩኒቶች በተለየ ሁኔታ ከሚያቀርቡት ተጨማሪ ጊዜ ውጭ በ26 ወራት እንደሚፈጸምና በ2010 አጋማሽ ላይ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢ/ር ፈቃደ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከዊንጌት ተራ፣ በመርካቶ አልፎ እስከ ቄራ ድረስ ከቀላል የባቡር አገልግሎቱ ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ በሁለት ቦታዎች እንደሚተላለፍና ይሄም የስምምነቱ ዲዛይን አካል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የግንባታ ስራው እንዲሁም የመገልገያ ቁሳቁስ አቅርቦት በ2009 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ እንደሚጀምርም ተብራርቷል፡፡
ፕሮጀክቱን ለመደገፍና ይበልጥ ለማፋጠን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት የ85 ሚ. ዩሮ ብድር በአነስተኛ ወለድ ማግኘቱም ታውቋል።
ፕሮጀክቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚካሄደው የከተማ መልሶ ማልማት ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል የተባለ ሲሆን በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መሰረት ከ6 ዓመት በኋላ ሰባት የፈጣን አውቶብስ መስመሮች ስራ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡ ፈጣን የአውቶብስ አገልግሎት ሲጀመር ምቹና ክፍያውም ተመጣጣኝ ይሆናል ተብሏል፡፡

Read 1482 times