Saturday, 19 March 2016 11:31

የጎዳና ተዳዳሪዎችን በሙያ መካን!

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 የጎዳና ሕይወት አሰቃቂ ነው፡፡ የክረምት ዝናብና ብርድ፣ የበጋው ሙቀትና ንዳድ ይወርድባቸዋል። የሚበሉት ምግብ የላቸውም፡፡ ለምነው ባገኙት ሳንቲም ፍርፋሪ ይገዛሉ፡፡ ረሃብና ብርዱን ለማስታገስ የተለያዩ ሱሶች ይጀምራሉ፡፡ ጫት፣ ሲጋራ፣ ቤንዚንና ማስቲሽ መሳብ፣ መጠጥ፣ በለጋ ዕድሜያቸው መደፈር፣ የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት፣ ሐሺሽ፣ … የጐዳና ተዳዳሪዎች እጣ ፈንታ ነው፡፡ ሰብአዊ ፍጡር መሆናቸው ይዘነጋል። ለአገር ልማትና ዕድገት  አስተዋጽኦ የላቸውም፡፡ ለአገር ኩራትና ተስፋ ከመሆን ይልቅ የአገር ሸክም፣ የማኅበራዊ ኑሮ ቀውስ … ይሆናሉ፡፡
መንግሥትና ኅብረተሰቡ እነዚህን ዜጎች የመንከባከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ የድህነት ጉዳይ ነው እንጂ መንግሥት ከጎዳና አንስቶ መጠለያ መስጠት፣ አሰልጥኖ ስራ ማስያዝ፣ በአገሪቷ ልማትና ዕድገት በማሳተፍ ወደ ማህበራዊ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ኃላፊነት ግን የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የባለሀብቶችና ድርጅቶችም ጭምር ነው።  
በዚህ ረገድ “ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ደቬሎፕመንት አሶሴሽን” የተባለ አገር በቀል ድርጅት፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን ቀዬአቸውን ትተው አዲስ አበባ በመምጣት በልመናና በጎዳና ተዳዳሪነት ተሰማርተው የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን መቋቋሚያ ሰጥቶ ወደ ቀዬአቸው መመለሱ ይታወሳል፡፡ ጥረቱ ሸጋ ቢሆንም ግን አልሰመረም፡፡ ተሸኚዎቹ ተመልሰው መጡ፡፡
ይኸው ግብረሰናይ ድርጅት ከቅርብ ዓመት ወዲህ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን አዲስ ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የጎዳና ሕይወት የመረራቸውን፣ የልመና ኑሮ የሰለቻቸውን… ተለውጠውና በአገሪቷ ልማት ተሳትፈው አዲስ ህይወት መምራት የሚፈልጉትን የጎዳና ተዳዳሪዎች በማስታወቂያ ጠርቶ፣ አሰልጥኖ በማስመረቅ በየኢንዱስትሪው እያስቀጠረ ነው፡፡
በአፋር ክልል በአሚባራ ወረዳ የተቋቋመው አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል፤ ከመላ አገሪቱ በጎዳና ተዳዳሪነት ተሰማርተው የነበሩትን ዜጎች በ7 የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (ሲኦሲ) አስፈትኖ በሚገባ ያለፉትን 10,411 ሰልጣኞች ለ3ኛ ጊዜ በሰርተፊኬት አስመርቋል፡፡ ወጣቶቹም ተለውጠውና ከጎዳና ሕይወት ተላቀው የሙያ ባለቤትና ደሞዝተኛ በመሆናቸው በጣም ደስተኞች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ሰሜን ጎንደር የተወለደው የ27 ዓመቱ ወጣት፤ በ2005 በ1ኛው ዙር ወደ ማሰልጠኛው ከመግባቱ በፊት ሕይወቱ የተበላሸና በተለያዩ ሱሶች የተጠመደ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ወደ ጎዳና ባይወጣም ሕይወቱ አስቀያሚ ነበር፤ ጫት ይቅማል፣ ሲጋራ ያጨሳል፣ መጠጥ ይጠጣል … የሱስ አጠቃቀሙ ደግሞ ገደብ አልነበረውም፡፡ “ሥራ የሌላችሁና በሱስ ውስጥ ያላችሁ መንግሥት የሥልጠና ፕሮግራም አዘጋጅቷልና ተመዝገቡ” የሚል ማስታወቂያ በቀበሌው ይለጠፋል። ማስታወቂያውን ሲያይ የነበረበት ህይወት በጣም አስጠልቶት ስለነበር፣ ስልጠናውን ወስጄ መለወጥ አለብኝ በማለት ተመዝግቦ፣ አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል በመግባት፣ በዶዘር ኦፕሬተርነት ሰልጥኖ በ1ኛው ዙር በ2005 ዓ.ም ተመረቀ፡፡ ስልጠናውን እንዳጠናቀቀ ደብረብርሃን መከላከያ ኮንስትራክሽን ተመደበ፡፡ እዚያ አንድ ዓመት ከሠራ በኋላ በአዲስ ራዕይ ሥልጠና ማዕከል፣በዶዘር ኦፕሬተርነት እንዲያሰለጥን ተጠርቶ የ3ኛ ዙር ሰልጣኞችን አሰልጥኗል፡፡
ወጣቱ፣ ከዚያ አስከፊ ሕይወት ወጥቶ፣ አሰልጣኝ በመሆን ሌሎችን መለወጥ በመቻሉ በጣም ደስተኛ ነው፡፡ “ሥራ ያልነበረኝና በሱስ ተተብትቤ የነበርኩ ሰው፣ ከሱስ ተገላግዬ፣ ተለውጬና  ባለሙያ ሆኜ ደሞዝ እንድበላ ስላደረገኝ መንግሥትን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኔ የነበርኩበት ሕይወት ውስጥ ያሉ ሰዎችም ሰልጥነውና ተለውጠው ወደ መደበኛ ኑሮ እንዲገቡ እመክራለሁ” ብሏል፤ ወጣቱ፡፡
የ15 ዓመቱ ታዳጊ ዳኛቸው የወላይታ ተወላጅ ነው፡፡ ወደ ማዕከሉ ከመምጣቱ በፊት በአዲስ አበባ ለ4 ዓመታት የጎዳና ህይወትን አሳልፏል፡፡ ዳኛቸው በጎዳና ሕይወት በቆየባቸው ጊዜያት የተለያዩ ሱሶች ተጠቃሚ ነበር፡፡ እሱና ጓደኞቹ ማስቲሽ ወይም ቤንዚን ይስባሉ፣ ሲጋራ ያጨሳሉ፣ ጫት ይቅማሉ፣ … ለሱሳቸው መግዣ የሚሆነውን ገንዘብ የሚያገኙት አንዳንድ ዕቃዎች በመሸከም ነበር፡፡ 50 ብር ካገኙ 30 ብሩን ለምግብና ለአልጋ አስቀርተው 20 ብሩን ለሱሳቸው ያውላሉ፡፡
10 ጓደኛሞች ሆነው ነበር ወደ ማሰልጠኛ ማዕከሉ የገቡት፡፡ አምስቱ የማዕከሉን ሙቀትና አስቸጋሪነት መቋቋም አልቻሉም፡፡ ታመው ተሸኙ። አምስቱ ግን ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ተመረቁ። ዳኛቸው የተመረቀው በፓወር ኢንጂነሪንግ (ኤሌክትሪክ መዘርጋትና ጀነሬተር መሥራት) ነው የሰለጠነው። ዳኛቸው፣ ከጎዳና ህይወት ተላቆ በመለወጡና ባለሙያ በመሆኑ መንግስትን አመሰግኗል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ ህይወት ውስጥ ያሉ ዕድሉን ተጠቅመው እንዲለወጡ መክሯል፡፡
ወለጋ ነቀምት የተወለደው የ29 ዓመቱ ወጣት፣ በኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሠራዊቱ አባል ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም የ7 ዓመት ግዳጁን ፈፅሞ ወደ ትውልድ አካባቢው ተመለሰ፡፡ ሲሸኝ የተሰጠው ገንዘብ በቂ ነበር፡፡ ልጅነት አታሎት አባከነውና ወደ ጐዳና ሕይወት ገባ፡፡ የጎዳና ሕይወት እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡ ሲብስበት ቢሻል ብሎ አዲስ አበባ መጣ፡፡  ወጣቱ፣ የጐዳና ሕይወት ቢያሳልፍም ከመጠጥ በስተቀር ሌሎች ሱሶች አልነበረብኝም ይላል።  ሥልጠናውን የሰማው በ1ኛው ዙር ነበር፡፡ ጓደኞቹ ወደ ማዕከሉ መጥተው ሲሰለጥኑ እሱ ንቆ ቀረ፡፡ ጓደኞቹ ሰልጠነው ባለ ሥራ ሆነው ሲያይ ቆጨው። በ2ኛው ዙር ለመግባት ወስኖ ሳለ አመመውና ቀረ። በ3ኛው ዙር ወደ ማዕከሉ ገብቶ በኦቶሞቲቭ (ከባድ መኪና) ሰልጥኖ ተመርቋል፡፡ “በዚህ ማዕከል የሰለጠንን ከ10, ሺህ በላይ ሰዎች በተለያየ ቦታ ከባድ ወንጀል የሠራን ነን፡፡ በየወረዳውና በየቀበሌው ማጣራት ቢደረግ ከ1000 ሰዎች በላይ ንፁህ ሰው አይገኝም። መንግሥት ምህረት አድርጐልን ይህን ሥልጠና እንድናገኝ በማድረጉ በጣም አመሰግናለሁ። ‹ጐዳና ለመኪና እንጂ ለሰው ልጅ አይሆንም› በማለት ዕድሉን ሲያዘጋጅ በዕድሉ መጠቀም ብልህነት ነው።” ብሏል - ወጣቱ፡፡   
በእምነት ተስፋዬ የ18 ዓመት ወጣት ናት፡፡ የጐንደር ጋይንት ተወላጅ ስትሆን የተማረችውም እዚያው ነው፡፡ የ2ኛ ዙር ተመራቂና የ3ኛ ዙር አስተማሪ ናት፡፡ በ2004 ከወላጆቿ ጋር ያለመግባባት ስለተፈጠረ ከቤት ወጥታ አክስቷ ጋ አዲስ አበባ መጣች፡፡ የአክስቷ ቤትም አልተመቻትም፡፡ ቤት ውስጥ ብትኖርም ኑሮዋ ከጐዳና የተሻለ እንዳልነበር ትናገራለች፡፡ ብዙ ችግር ነበረባት፡፡ የምትፈልገውን ነገር በወቅቱ አታገኝም፤ ጓደኞቿ የሚጠቀሙበት ነገር ሁሉ ይቸግራት ነበር፤…፡፡
ጓደኞቿ፤ ኤልሻዳይ የሚባል ድርጅት ማስታወቂያ አውጥቷል፤ራሱ አሠልጥኖ ራሱ ሥራ ያስይዛል አሏት። እንደዚያማ ከሆነ እሄዳለሁ ብላ ተመዘገበች፡፡ ወደ ማዕከሉም ገብታ በጋርመንት ሰለጠነች፡፡ በእምነት በትምህርት አቀባበል ጐበዝ ስለነበረች ማሰልጠኛ ስትገባም አላስቸገራትም፤ ጥሩ አቀባበልና ተሳትፎ ነበራት፡፡ በዚህም የተነሳ በማዕከሉ ውስጥ 40 ሴቶችን ታሰለጥን ነበር፡፡ በመጨረሻም ስትመረቅ ከ146 የ2ኛ ዙር ሰልጣኖች ውስጥ እዚያው እንድታሰለጥን እሷ ብቻ ስለቀረች የ3ኛው ዙር አስተማሪ ሆነች፡፡   
“አሁን ደስ ብሎኝ ነው የምኖረው፡፡ ብር አገኛለሁ፤ ግን ብር አገኘሁ ብዬ አላጠፋም፣ ተቀማጭ አደርጋለሁ።” ያለችው በእምነት፤ በምታስተምርበት ወቅት ተማሪዎቹ ሙቀቱንና አንዳንድ ችግሮችን መቋቋም አቅቷቸው ሲበሳጩና ለመሄድ ሲያስቡ፤ እኔም እንደ እናንተ ነበርኩ፡፡ ግን ዓላማ ይዤ ስለመጣሁ ተቋቁሜ ለዚህ በቃሁ፡፡ እኔን አታዩም እንዴ? ስትላቸው፣ እውነቷን’ኮ ነው በማለት ለመመለስ አቆብቁበው የነበሩት እንደሚረጋጉ ገልጻለች። በእምነት አሁን ከቤተሰቦቿ ታርቃለች፡፡ ሄዳም አይታቸዋለች፤ ስልክም ይደዋወላሉ፡፡ 

Read 2528 times