Saturday, 19 March 2016 11:40

4ኛው “ኮንስትራክሽን ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤግዚቢሽን” እየተጎበኘ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     የኢትዮጵያ ደረጃ አንድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር “ኮንስትራክሽን ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ኤግዚቢሽን” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው 4ኛው የኮንስትራክሽን አውደ ርዕይ ባለፈው ረቡዕ በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ፡፡
140 ያህል የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች የተሳተፉበትን 4ኛውን የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን መርቀው የከፈቱት የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ሲሆኑ ኤግዚቢሽኑ እስከ ነገ ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ በአገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ዘርፍ ነው ያሉት ዶ/ር አምባቸው፣ ወደ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እየገቡ ያሉ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎችና ባለሙያዎች በየጊዜው ቁጥራቸው መጨመር፣ የኮንስትራክሽን ግብአት አምራቾችና አቅራቢዎች ቁጥር መብዛትና የኮንስትራክሽን ማቴሪያልና ማሽነሪ አቅራቢዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት የዘርፉን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መምጣት ያመለክታል ብለዋል፡፡
ከውጭ አገር ማሽነሪዎችን ጭነው አጓጉዘው፣ ሸጠውና አትርፈው መመለሳቸው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም አድጎ የኮንስትራክሽን ማቴሪያሎችና ግብአቶች ቢያመርቱ የአገር ውስጥ ገበያ መኖሩን ያመለክታል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአገራችን ፋብሪካዎችን ከፍተው ማሽነሪዎቹንና ግብአቶቹን ቢያመርቱ ዘርፉ ትርፋማና እያደገ የሚሄድ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ኤግዚቢሽኖች መከፈት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሱት ዶ/ር አምባቸው፣ መረጃ መለዋወጥ ይፈጥራል፣ ዓለም የደረሰበትን የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ ማቴሪያዎችና ቴክኖሎጂ ደረጃ ያሳያል፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተዋንያን እውቀቱ እንዲኖራቸው፣ ገበያ እንዲፈጠርላቸውና እርስ በርስ ትስስር እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

Read 1265 times