Saturday, 19 March 2016 11:41

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያውያን ዋናዎቹ ድምቀት ናቸው
      16ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት ምሽት በአሜሪካዋ ፖርትላንድ ከተማ  ሲጀመር  ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉት  12 አትሌቶች የሻምፒዮናው ድምቀት እንደሚሆኑ ተጠብቋል። ኢትዮጵያውያኑ ከ800 ሜ. እስከ 3000 ሜ. ባሉ የውድድር መደቦች በሁለቱም ፆታዎች ይወዳደራሉ፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በፖላንድ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና  በፖላንድ ሲካሄድ ኢትዮጵያ  ሁለት ወርቅ፣2 ብርና 2 ነሀስ በድምሩ ስድስት ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ሊኖር እንደሚችል ተጠብቋል፡፡
በ1985 እኤአ ላይ ዎርልድኢንዶር ጌምስ በሚል ስያሜ በፈረንሳይ ፓሪስ ተጀምሮ ከ1987 እኤአ ጀምሮ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመባል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች በወንዶች ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ የሚጠቀሰው ኃይሌ ገብረስላሴ ነው፡፡ ኃይሌ በሻምፒዮናው 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በሩጫ ዘመኑ ያስመዘገበ ሲሆን በ3ሺ ሜትር 3 እንዲሁም በ1500 1 የወርቅ ሜዳልያዎች ለመጎናፀፉም በላይ፤  በ1500 3፡33.77 በሆነ ጊዜ በ1999 እኤአ እንዲሁም፤ በ3ሺ ሜትር 7፡34.71 በሆነ ጊዜ የሻምፒዮናውን ሪከርዶች በስሙ አስመዝግቦ ይገኛል፡፡  በሴቶች ደግሞ አትሌት መሰረት ደፋር በ3ሺ ሜትር 4 የወርቅ፤ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ይዛለች፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በ1500 ሜትር 3፡59.75 በሆነ ጊዜሪከርድ የየዘችው ገለቴ ቡርቃ ናት፡፡በሻምፒዮናው ታሪክ በአንድ የውድድር መደብ 9  ሜዳልያዎች በመሰብሰብ በከፍተኛ የውጤት ክብረወሰኗ የምትጠቀሰው ሞዛምቢካዊቷማርያ ሞቶላ ስትሆን መሰረት ደፋር ተጨማሪ ሜዳልያዎች ካገኘች በሰባት ሜዳልያ በቅርብ ርቀት ትከተላታለች፡፡
ባለፉት 15 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 74 አገራት የሜዳልያ ድል በማስመዝገብ በምንግዜም የውጤት ደረጃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከ16ኛው ሻምፒዮና በፊት ፡ ኢትዮጵያ 40 ሜዳልያዎችን በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ የሰበሰበች ሲሆን  21 የወርቅ 7 የብርና 12 የነሐስ ሜዳልያዎች በምንግዜም የውጤት ደረጃው በ3ኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡
በ16ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወከሉ  አትሌቶች
800ሜ. ወንዶች
መሐመድ አማን
800ሜ. ሴቶች
ሀብታም አለሙ
ትግስት አሰፋ
1500ሜ. ወንዶች
ዳዊት ወልዴ
አማን ወጤ
1500ሜ. ሴቶች
ዳዊት ስዩም
ጉዳፍ ፀጋዬ
አክሱማዊት እምባዬ
3000ሜ. ወንዶች
የሚፍ ቀጄልቻ
የኔው አላምረው
3000ሜ. ሴቶች
መሰረት ደፋር
ገንዘቤ ዲባባ

Read 1916 times