Saturday, 19 March 2016 11:43

ዋልያዎቹ ያለ በቂ ትኩረት ከበረሃዎቹ ቀበሮዎች ይፋጠጣሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

      የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የሶስተኛ ዙር ግጥሚያ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  ከሜዳቸው ውጭ አልጀርስ ላይ ከአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን የሚያገኙት ያለ በቂ ትኩረት ነው፡፡ ለወሳኙ ግጥሚያ ዋልያዎቹ ዝግጅታቸው ከአንድ ወር ያነሰ፤ የአቋም መፈተሻ ግጥሚያ ያላደረጉ፤ በተሟላ የቡድን ስብስብ ያልተዘጋጁ እንዲሁም በጉዞ ሁኔታዎች ለአድካሚ መጉላላቶች የሚጋለጡ መሆናቸው በቂ ትኩረት አለማግኘታቸውን ያመለክታል፡፡   
ከዋልያዎች ተጨዋቾች በተለይ ግብ አዳኙ ሳላዲን ሰኢድ በብቃት ማነስ አለመካተቱ የቡድኑን ክፍተት የሚያጎላው ሲሆን በተለያዩ አገራት የሚገኙት አንጋፋዎቹ ዋልያዎች ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለ ከቡድኑ ጋር በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸውም ተፅዕኖ ይፈጥራል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋቾች በሚኖርባቸው የጨዋታ እና የጉዞ መደራረብም ቡድኑ ፈተና ውስጥ የገባ ይመስላል፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫው የሶስተኛ ዙር ማጣርያ በፊት አልጄርያ ባለፉት 5 ጨዋታዎች በ3 አሸንፋ፤ በ1 አቻ በውጣት በ1 ብቻ ስትሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ግን በ3 ተሸንፋ፤ በ1 አቻ በምወጣት በ1 ብቻ ድል ቀንቷታል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአልጄርያ አቻው ጋር በታሪክ በ6 ጨዋታዎች ተገናኝቷል፡፡ 1 ድል፤ 2 አቻ ሶስት ሽንፈቶችም አስተናግዷል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2014 እኤአ ላይ  ሲሆን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች አልጄርያ በሜዳዋ 3ለ1 እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ 2ለ1 አሸንፋለች፡፡
ዮሐንስ ሳህሌ የዋሊያዎቹ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመርጠው ስራቸውን ከጀመሩ 11 ወራት ተቆጥረዋል።  ፌዴሬሽኑና አሰልጣኙ በተፈራረሙት የቅጥር ውል መሰረት ቡድኑ እ.ኤ.አ. በ2017 ጋቦን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ በቅጥር ውሎ መሠረት ዋሊያዎቹ ከተደለደሉበት ምድብ 10 ከስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ውስጥ ወደ ዋናው ውድደድር ለማለፍ የሚያስላቸውን ነጥብ በማግኘት የ31ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊነታቸውን ማረጋጋጥ አለባቸው፡፡ ይህን ውጤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሳካት ከቻለ  የውል ስምምነቱ የአሰልጣኝ ዮሐንስ የስራ ዘመን እ.አ.አ እስከ ኤፕሪል 2017 ዓ.ም ድረስ እንደጸና እንደሚቆይ ደንግጓል፡፡ በ2017 እኤአ ጋቦን በምታዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚሳተፍበት የምድብ ማጣርያ በምድብ 10 ከአልጄርያ፤ ከሌሶቶ እና ከሲሸልስ ጋር መደልደሉ ይታወቃል፡፡ ከ2 ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በኋላ አልጄርያ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ ዋልያዎቹ በ4 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ በሁለተኛ ደረጃ እየተከተሉ ናቸው፡፡ ከምድቡ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሰፊ እድል ያላት አልጄርያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀሪዎቹ 4 የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ከአልጄርያ ጋር ከሜዳው ውጭና በሜዳው፤ ከሌሶቶ ጋር ከሜዳው ውጭ እንዲሁም ከሲሸልስ ጋር በሜዳው ይጫወታል፡፡ የምድቡን መሪነት በማግኘት በአፍሪካ ዋንጫው ቀጥታ ተሳትፎ ለማግኘት ዋልያዎቹ በተለይ በአራቱ ጨዋታዎች መሸነፍ የለባቸውም፡፡ በተለይ ከአልጄርያ ጋር በሚያደርጓቸው የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ነጥብ መውሰድ ከቻሉ ተስፋ ይኖራቸዋል፡፡ ምድቡን በመሪነት መጨረስ ካልሆነለት ቡድኑ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የሚችለው በምርጥ ሁለተኛነት ከጨረሰ ነው፡፡ ከ14 ምድቦች በምርጥ ሁለተኛነት ለማለፍ ሁለት አገራት እድል ይኖራቸዋል፡፡ በምድብ ማጣርያው የሁለት ዙር ጨዋታዎች ከተደረጉ በኋላ ባስመዘገቡት ነጥብ መሰረት ከየምድቡ  ምርጥ ሁለተኛ ሁኑት በወጣላቸው ደረጃ መሰረት፤ ከምድብ 6 ሞሮኮ በ6 ነጥብ እና በ4 የግብ ክፍያ አንደኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ከምድብ 7 ናይጄርያ በ4 ነጥብ እና በ2 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ በምድብ 10 የምትገኘው ኢትዮያ በ4 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ከላይቤርያ፤ ዚምባቡዌ እና ዛምቢያ ጋር ሶስተኛ ደረጃን ተጋርተው ፉክክራቸውን ይቀጥላሉ፡፡

Read 2940 times